የዓድዋ እና የማይፀብሪዉ የአዉሮፕላን ጥቃት | ኢትዮጵያ | DW | 25.10.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የዓድዋ እና የማይፀብሪዉ የአዉሮፕላን ጥቃት

በዓድዋ እና ማይፀብሪ በተፈፀሙ የአውሮፕላን ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች መጎዳታቸውን በህወሓት የሚመራው የትግራይ ክልል መንግስት ገለፀ። የትግራይ ኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊያ ካሳ  የጉዳቱ መጠን እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:32

የትግራይ ኃይሎች ዛሬ ተቆጣጠርነዉ ስላሉት ቦታ በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም

እሁድ ጥቅምት 14፤ 2014 ዓ.ም በዓድዋ እና ማይፀብሪ በተፈፀሙ የአውሮፕላን ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች መጎዳታቸውን በህወሓት የሚመራው የትግራይ ክልል መንግስት ገለፀ። የትግራይ ኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊያ ካሳ  የጉዳቱ መጠን እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል። በአድዋ ህወሓት "ወታደራዊ ትጥቅ እና ወታደራዊ አልባሳትን አመሳስሎ የሚያመርትበት  ማዕከል" እንዲሁም በማይጠብሪ "ማሠልጠኛ እና የሰው ኃይል ማደራጃ" ትናንት እሁድ ጥቅምት 14 ቀን መደብደባቸውን የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት አረጋግጦ ነበር። 
በአየር ድብደባዎቹ የደረሰው ጉዳት በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም። በትግራይ እየተፈፀሙ ያሉትን የአውሮፕላን ጥቃቶች ያወገዘው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የመቐለ ሀገረስብከት፥ ቅዱስ ሲኖዶስ 'ዘር የማጥፋት' ባለው ጦርነት ተሳትፎ ያላቸው የቤተክርስቲያንዋ ሃይማኖት መሪዎች ካላወገዘ ሲኖዶሱ አይወክለንም ብሏል።
ይኽ በእንዲህ እንዳለ በዋናነት በትግራይ ሀይሎች እና የኢትዮጵያ መንግስት የሚደረገው ጦርነት ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፥ የትግራይ ሀይሎች ደሴ አቅራብያ የምትገኘው ኩታበር ከተማ መቆጣጠራቸው አስታውቀዋል። የትግራይ ሀይሎች በዛሬው መግለጫቸው ከኮምቦልቻ አውሮፕላን ማረፍያ በቅርብ ርቀት ላይ መሆናቸው በመግለፅ የሚደረግ ማንኛውም የአውሮፕላን እንቅስቃሴም አግደዋል። የትግራይ ኃይሎች የተባሉትን ቦታዎች ስለ መቆጣጠራቸው በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም። የአማራ ክልል መስተዳድርም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ እስካሁን መግለጫ አልሰጡም። 


ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 
አዜብ ታደሰ 
እሸቴ በቀለ 
 

Audios and videos on the topic