የዓመዓቱ የልማት ግቦች ይዞታ | ዓለም | DW | 30.09.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የዓመዓቱ የልማት ግቦች ይዞታ

የተመድ ያስቀመጠው የዓመዓቱ የልማት ግቦች ዕቅድ የጊዜ ገደብ ሊገባደድ ሁለት ዓመታት ብቻ ነው የሚቀሩት። ሁለቱ ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት ግቦቹ ምን ያህል ለውጥ አሳይተዋል? የተመድ ምክትል ዋና ፀሀፊ ዴቪድ ማሎኔ።

ዶ/ር ዴቪድ ማሎኔ

ዶ/ር ዴቪድ ማሎኔ

ተመድ የነደፈው የዓመዓቱ የልማት ግቦች ዕቅድ ይሳካል ተብሎ የተያዘለት ጊዜ ሊጠናቀቅ የቀሩት ሁለት ዓመታት ብቻ ናቸው ። አሁን ዋነኛው ጥያቄ ይህ የተመድ የልማት ግብ በእርግጥም በተያዘለት የጊዜ ገደብ ስኬታማ ይሆናል ወይ የሚለው ነው። የተመድ ምክትል ዋና ፀሀፊ ዴቪድ ማሎኔ በተለይ ለዶቼቨለ በሰጡት ምላሽ ጥያቄውን በዘወርዋራ እንዲህ መልሰዋል።

«ከግቦቹ አንዳንዶቹ ተሳክተዋል። ለአብነት ያህል ድህነትን በግማሽ የመቀነሱ ሀሳብ ተሳክቷል። በእርግጥ አንዳንዶቹን ለማሳካት እጅግ ይከብዳል።»

ምክትል ዋና ፀሀፊው ከግቦቹ አንዳንዶቹ ከመነሻው ተግዳሮት ቢገጥማቸውም ሊሳኩ ችለዋል ሲሉ አክለዋል። ለአብነት ያህልም አንዳንድ በሽታዎችን በተለይ ደግሞ ኤድስን አስመልክቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄደው ዘመቻ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል ሲሉ ጠቅሰዋል። በእዚያው መጠን አንዳንድ የዓመዓቱ የልማት ግቦች ለውጥ እንደታየባቸውና በጊዜ ሂደትም መልካቸውን እንደቀየሩ ጠቅሰዋል። በተለይ ይላሉ ምክትል ዋና ፀሀፊው፤ በተለይ በዓለማችን ወደ 60 ሚሊዮን የሚጠጉ ህፃናት ትምህርት ያለማግኘታቸው ነገር እጅግ አሳሳቢ ነው።

«ለታዳጊ ሃገራት አንገብጋቢው ነገር የትምህርት ጥራት ጉዳይ ነው። ምናልባትም በእዚህ ዓመት መግቢያ ላይ በሚሊኒየሙ የልማት ግቦች የከፍተኛ አመራር ውይይት ወቅት ቀደም ሲል እንደተጠቆመው ትምህርትን በሚመለከት ወደፊት የሚቀመጠው ግብ በተቻለ መጠን ከቁጥር ይልቅ ጥራት ላይ ሊያተኩር ያስፈልጋል።»

ዓለማችንን በከፍተኛ ሁኔታ በመታት የፋይናንስ ቀውስ የተነሳ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሃገራት ለታዳጊ ሃገራት የሚያደርጉት ርዳታ ተፅዕኖ እንዲያድርበት አድርጓል። ለአብነት ያህል አንዳንድ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት በተለይ በደቡብ የሚገኙት በቀውሱ እጅግ በመመታታቸው የተነሳ ለታዳጊ ሃገራት የሚደረገው ርዳታ መቀነሱ አልቀረም። ይህ ድርጊት ሁለት ዓመታት ብቻ በቀሩት የዓመዓቱ የልማት ግቦች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድር ይሆን? የተመድ ምክትል ዋና ፀሀፊ ዴቪድ ማሎኔ።

«ርዳታ ጠቃሚ ነው፤ ግን ወሳኝ ነገር አይደለም። ወሳኙ ነገር ለእነዚህ ግቦች ሃገራዊ ቁርጠኝነት ነው። እንደውም አንዳንድ እጅግ ደሀ የሆኑ ሃገራት በጠንካራ ሀገራዊ ቁርጠኝነት ጉልህ ለውጥ እያሳዩ ነው። »

ምክትል ዋና ፀሀፊው አንዳንድ ታዳጊ ሃገራት የልማት ዕቅዳቸውን ብሩህ በሆነ መልኩ እንዲቀርፁ ለማስቻል በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሃገራት የሚያደርጉት ርዳታ በእርግጥ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁንና ርዳታ የዓመዓቱ የልማት ግቦችን ለማሳካት ዋነኛው ነገር ተደርጎ መወሰድ ያለበት ስለመሆኑ የሚሰማቸውን ጥርጣሬ ገልፀዋል። ለእዚያ ደግሞ ይላሉ ዋና ፀሀፊው፤ ቻይና ያለምንም ርዳታ በዓለማችን ግዙፍ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች። ይልቁንስ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሃገራት ከታዳጊ ሃገራት ጋር በሚያደርጉት የልማት ትብብር ምዕራባውያኑ የገንዘብ ምንጮች ታዳጊ ሃገራት ደግሞ ልማት አስፈፃሚዎች ብቻ እንደሆኑ አድርጎ ማሰብ በሁለቱም ላይ እንደማሾፍ ይቆጠራል ይላሉ። ምክትል ዋና ፀሀፊው በማጠቃለያቸውም ታዳጊ ሃገራት ያለ ርዳታ ምንም ነገር ማከናወን አይችሉም ወደሚለው የተሳሳተ ድምዳሜ መድረስ ትክክል እንዳልሆነ ገልፀዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሂሩት መለሰ