የዓሊ አብደላሕ ሳሌሕ አገዛዝ 33ኛ ዓመት | ዓለም | DW | 18.07.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የዓሊ አብደላሕ ሳሌሕ አገዛዝ 33ኛ ዓመት

ሰዉዬዉ በርግጥ ቀልጣፋ፥ ጮሌ፥ ብልጣብጥም ነበሩ።አንደኛ ደረጃ ትምሕርታቸዉን ባያጠናቀቁም የየመንን ጦር መቀየጡ አልከበዳቸዉም።ከጦር ትምሕርት ቤት በአስር-አለቅነት ማዕረግ በተመረቁ በሰወስተኛዉ አመት የምክትል መቶ እልቅና ኮኮብ ጫኑ

default

ሳሌሕ

18 07 11

ሐምሌ አስራ-ሰባት 1978።ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ። ንቁ፥ ቀልጣፋዉ፥ የጠንካራዉ የሐሺይዲ ጎሳ ድጋፍ ያልተለያቸዉ ወጣት የጦር መኮንን እና ፖለቲከኛ የየመን አረብ ሊፐብሊክን የፕሬዝዳትነት ሥልጣን ተቆጣጠሩ።ዓሊ አብደላሕ ሳሌሕ።ትናንት ሰላሳ-ሰወስት ዓመቱ።ዛሬ ግን ለሳሌሕ ትናንት አይደለም። የፕሬዝዳት ዓሊ አብደላ ሳሌሕ አገዛዝ፥ የገጠመቻዉ ተቃዉሞና ምክንያቱ የዝግጅታችን ትኩረት ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ጥቅምት 1977 የየመን አረብ ሪፐብሊክን የፕሬዝዳት ሥልጣን የያዙት አሕመድ ቢን ሁሴይን አል-ጋሺኒ ምኞት፥ ሙከራ፥ጥረታቸዉም የፖለቲካ አዋቂዎች እንደሚሉት ለሁለት የተገመሠችዉ የመንን አንድ ማድረግ ነበር።ጋሺኒ ሥልጣን በያዙ ማግሥት የጀመሩት ጥረት በስምተኛ ወሩ ፈር ያዘና የየመን ሕዝባዊት ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ (ደቡብ የመን) መሪ ሳሊም አሊ ሩባኒን ልዩ መልዕክተኛ ያነጋግሩ ጀመር።ሰኔ 1978።በዉይይቱ መሐል ፕሬዝዳንቱ የሰነድ ቦርሳ (ብሪፍ ኬዛቸዉን) ከፈቱ።ያ ቦርሳ በሰነዱ ምትክ ቦምብ ነበር የታጨቀበት።ፈነዳ።

ፕሬዝዳንቱ ብዙ የተመኙ፥ የሞከሩ፥ የጣሩለት ዉሕደት መጥፊያቸዉ ሆነ።ለወጣቱ የጦር መኮንንና ለአዲሱ ፖለቲከኛ ባንፃሩ የሥልጣን መሰላሉን ዘረጋላቸዉ።ሰዉዬዉ በርግጥ ቀልጣፋ፥ ጮሌ፥ ብልጣብጥም ነበሩ።አንደኛ ደረጃ ትምሕርታቸዉን ባያጠናቀቁም የየመንን ጦር መቀየጡ አልከበዳቸዉም።ከጦር ትምሕርት ቤት በአስር-አለቅነት ማዕረግ በተመረቁ በሰወስተኛዉ አመት የምክትል መቶ እልቅና ኮኮብ ጫኑ።1964።

የዚያኑ ያክል ግራ አጋቢ ብጤም ናቸዉ።አል-አሕመር ከተማ ከአል-አሕመር ቤተ-ሰብ (ጎሳ) ነዉ የተወለዱት።ከአንድ ወር በፊት ቤተ-መንግሥታቸዉ ዉስጥ በቦምብ ሊያጠፏቸዉ የሞከሩት ሰዎች ማንነት በዉል አለየም።የሳሌሕን አገዛዝ የሚቃወሙት ሳሌሕን ያቆሰለዉን ያን አደጋ በሙስና የተነከሩ የሁለት ቤተ-ሠቦች (ጎሳዎች) ጠብ ይሉታል።

«ይሕ በሙስና የተዘፈቁ የሁለት ቤተ-ሰቦች ግጭት ነዉ።ከኛ አብዮት ጋር ምንም ግንኙነት የለዉም።ሳሌሕ እኛን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ለመክተት እየሞከሩ ነዉ።ይሕ እንዲሆን ግን አንፈቅድም።»

Jemen Stammesmitglieder in einer friedlichen Demonstration

የጎሳ ተጠሪዎች

ብዙዎቹ አደጋዉን የጣሉት የአል-አሕመር ጎሳ ታጣቂዎች ናቸዉ ብለዉ ያምናሉ።ሰዉዬዉ ከዚያ አደጋ ቢያንስ ላሁኑ ተርፈዋል።ከሚታከሙበት ስዑዲ አረቢያ ወደ ሐገራቸዉ መመለስ፥ ሥልጣን የያዙበትን ሠላሳ-ሰወስተኛ ዓመት ማክበር ግን አልቻሉም።ያም ሆኖ የጂዳዉ ወኪላችን ነብዩ ሲራክ እንደሚለዉ ከደረሰባቸዉ አደጋ ሙሉ በሙሉ ያገገሙ መስለዋል።

በ1964 የምክትል መቶ ዕልቅናዉን ኮኮብ እንደጫኑ ፖለቲካዉን ቀረብ፥ ፖለቲከኞችን ጠጋ ማለት ጀመሩ።የየመንን ፖለቲካ የሚጫጫኑት የጎሳ መሪዎችን አቅምና ችሎታም አልዘነጉት።አሕመድ ቢን ሁሴይን አል-ጋሽኒ በሰዉ እጅ የተገደሉትን ኢብራሒም አል-ሐሚድን ተክተዉ የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን ሲይዙ ዓሊ አብደላ ሳሌሕ የጠንካራዉን የሐሺዲ ጎሳ መሪዎች ከጀርባቸዉ አሠልፈዉ ነበር።
አዲሱ ፖለቲከኛ ያዲሱን ፕሬዝዳትን ቀልብ ለመሳብ ከጀርባቸዉ ያሠለፉት የጎሳ ሐይል በቂያቸዉ ነበር። ፕሬዝዳቱ ሥልጣን በያዙ በወራት ዕድሜ ዓሊ አብደላሕ ሳሌሕን የታዒዝ ግዛት ወታደራዊ አገረ-ገዢ አድርገዉ ሾሟቸዉ።ሩቅ አሳቢዉ ፕሬዝዳት ባጭር ሲቀጩ፥ ላጭር ጊዜ ታዒዝን የገዙት ወጣቱ የጦር መኮንን ረጅም ጉዟቸዉን አንድ አሉ።የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን በጊዚያዊነት ከያዙት አራት ፖለቲከኞች አንዱ ሆኑ።


ጊዜ አላጠፉም።በወሩ የጎሳ መሪዎች ጫና፥ የጦር መኮንኖች ግፊት፥ የአጎራባች መንግሥታት ተፅኖ የሚዘዉረዉ ምክር ቤት ለፕሬዝዳትነት ተመረጡ።ዓሊ አብደላ ሳሌሕ።የየመን አረብ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳት፥ የጦር ሐይሎች ጠቅላይ አዛዥ፥ እና የጠቅላይ ኤታማዦር ሹምነቱን ሥልጣን ጠቅልለዉ ያዙ።ሐምሌ አስራ-ሰባት 1978።

የስዑድ አረቢያ ነገሥታት፥ ከግብፅ አብዮታዊ የጦር መኮንኖች ጋር የተፋለሙባት፥ የሶቬት ሕብረት፥ የኩባ፥ የኢትዮጵያ ሶሻሊስቶች፥ ከብሪታንያ፥ ከዩናይትድ ስቴትስና ከተከታዮቻቸዉ ካፒታሊስቶች ጋር የተሸኮቱባት ሥልታዊት አረባዊት ደሐ ሐገርን መምራት በርግጥ ከባድ ነበር።ዓሊ አብደላ ሳሌሕ ግን የሐይል ሚዛኑን አማክለዉ በቀጨኑ ገመድ መረማዱ አልገደዳቸዉም።

እርግጥ ነዉ አሜሪካ መራሹ ጦር በ1991 ኢራቅን ሲወጋ ዓሊ አብደላሕ ሳሌሕ ዩናይትድ ስቴትስን በጣሙን ሥልጣነ-እድሜያቸዉን በቅርብ-ርቀት የምትቆጣጠረዉ ስዑዲ አረቢያን ተጋፍተዉ ከኢራቅ ጎን መሠለፋቸዉ በቀላሉ የማይገመት ዉድ ዋጋ አስከፍሏቸዋል።ሠልፋቸዉን ፈጥነዉ በማስተካከላቸዉ ግን ከከፈሉት በላይ ዋጋ ምናልባትም ሥልጣናቸዉን መስዋዕት ከማድረግ አምልጠዋል።

ሶቬት ሕብረት ሕብረት መፍረክረክ ስትጀምር በሰሜንና ደቡብ የመኖች ዉሕደት ስም የሶቬትዋን የየመን ሕዝባዊት ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክን ጠቅልለዉ መግዛቱ ተሳክቶላቸዋል።ቀዝቃዛዉን ጦርነት ድል ካደረገዉ ከምዕራቡ ጎራ በመለጠፋቸዉ የዉጪዉን ግፊት በቀላሉ ማስወገድ ችለዋል።ከሐገር ዉስጥ የሚነሳባቸዉን ቅሬታና ተቃዉሞ ለማፈን ደግሞ የአንዱን ጎሳ መሪ ከሌላዉ ጋር ማናከስ፥ አንዱን አቅርቦ ሌላዉን ማራቅ፥ ወይም ሁሉንም ያቀረቡ መስሎ ሁሉንም በማራቁ ሥልት እርስ በርስ አቆላልፈዉታል።

በጀርመኑ የዓለም አቀፍና አካባቢያዊ ጥናት ተቋም የየመን ጉዳይ ባለሙያ አኔተ ቡሽ እንደሚሉት ሳሌሕ የዘረጉት ጠንካራ መረብ አገዛዛቸዉን የሚቃወሙትን ሁሉ በቀላሉ እየጠለፈ ይጥላል።

«ለሳሌሕ ሁል ጊዜም ቢሆን የጎሳ መሪዎቹን መያዝ ከአገዛዝ ሥልታቸዉ አንዱ ነዉ።አገዛዛቸዉን የሚያጠናክሩበት ጠንካራና የተወሳሰበ መረብ ዘርግተዋል።ይሕ ማለት የሐገሪቱን የተለያዩ ክፍሎች በቀጥታ ይገዛሉ ወይም በየሥፍራዉ የሚነሱ ግጭቶችን በበላይነት ይቆጣጠራሉ ማለት አይደለም። የሁሉም ልጓም ግን በእጃቸዉ ነዉ።»

የቱኒዝያና የግብፅ ሕዝብ በየገዢዎቹ ላይ የተቀዳጀዉ ድል ያጃገነዉ የየመን ሕዝብ የሳሌሕን ጠንካራ የአገዛዝ መረብ እየበጣጠሰዉ መሆኑ ብዙ አላነጋገረም።እስካሁን ግን ቱኒስ ወይም ካይሮ ላይ የታየዉ ድል ሰነዓ ላይ አልተደገገመም።ሕዝባዊ አመፅ ከተጀመረበት ካለፈዉ ጥር ጀምሮ በተቆጠረዉ ስድስት ወር በተቃዋሚ ሠልፈኞችና በፀጥታ አስከባሪዎች፥ በሳሌሕ ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎች፥መካከል በተደረጉ ግጭቶች በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሠላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።በሺ የሚቆጠሩ ቆስለዋል። ታስረዋልም።

ሳሌሕ ግን ለሰብአዊ መብት መከበር ቆሚያለሁ ከሚለዉ ዓለም የሙዓመር ቃዛፊ ወይም የበሽር አል-አሰድ አይነት ድብደባ፥ ዉግዘት፥ማዕቀብ አልተሰነዘረባቸዉም።ምክንያቱ ግልፅ ነዉ።የሳሌሕ ከሥልጣን መወገድ የሁቲ ሸማቂዎችን ካጠናከረ ሺዓዊቷ ኢራን አደን ባሕረ-ሠላጤ ጥግ እግሯን ማሰረፊያ አገኘች ማለት ነዉ። ሐገሪቱ ከርስ በርስ ጦርነት ከገባች ደግሞ አል-ቃኢዳ የመን ላይ ጠንካራ ምሽግ አገኘ ማለት ነዉ።

NO FLASH Jemen Freude über die Abreise von Saleh 5. Juni 2011

ተቃዋሚዎች

የኢራንም ሆነ የአል-ቃኢዳ መጠናከር የአካባቢዉን ሐያል-ሐብታም ሐገር ስዑዲ አረቢያንም ከምዕራባዉያን እኩል የሚያሰጋ ነዉ።ለወትሮዉ የሰነዓን ፖለቲካዊ ሥርዓት ባሻቸዉ የሚዘዉሩት የሪያድ ነገስታት የጂዳዉ ወኪላችን ነብዩ ሲራክ እንደሚለዉ ነገሩን አለሳልሰዉ መያዙን ሳይመርጡት አልቀረም።

የሕዝባዊዉ አመፅ መጠናከር ለሪያዶች ከሁቲ አማፂያን፥ ከአል-ቃኢዳ አሸባሪዎች መጠናከር እኩል አስጊ፥ አስደንጋጭም ነዉ።ሪያዶች የባሕሬኑን ሕዝባዊ አመፅ በጦር ሐይል ደፍልቀዉታል።ትናንት ቱኒስ እና ካይሮ የሆነዉ ዛሬ ወይም ነገ ሰነዓ ላይ ከተደገመ ተመሳሳዩ አመፅ ዉሎ አድሮ የቢን ስዑድ ቤተ-ሰበብ ለብቻዉ የተቆጣጠረዉን ዙፋን የማይገለባብጥበት ይሕ ቢቀር የማይነቀንቅበት ምክንያት ሊኖር አይችልም።በዚሕም ሰበብ የሪያድ ነገስታት ሳሌሕን ቢጠሏቸዉ እንኳን እንደ ቤን ዓሊ እንደ ሙባረክ በሕዝባዊ ሠልፍ ከስልጣን መወገዳቸዉን አይደግፉትም።

የሳሌሕ የአገዛዝ ዘመን ሰላሳ-ሰወስተኛ አመት ሲለካ፥ አገዛዛቸዉን የሚቃወመዉ ሕዝብ የአደባባይ አመፅ-ተቃዉሞ ሰባተኛ ወሩን ቆጠረ።የጥንቱ ብልጥ፥ ቀልጣፋ፥ ጮሌ ፖለቲከኛ ዛሬም መፍጨራጨራቸዉ አልቀረም።ሐያሉ ዓለም ባይደግፋቸዉ እንኳን አልተቃወማቸዉም።ግን እስከ መቼ? ነጋሽ መሐመድ ሲሆን ለማየት ያብቃን።
ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላAudios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች