የዓለም ጦርነት ፍፃሜ እና የምዕራብ ምሥራቆች ልዩነት | ዓለም | DW | 11.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የዓለም ጦርነት ፍፃሜ እና የምዕራብ ምሥራቆች ልዩነት

የጦርነቱ ዘግናኝ ዉጤት ከሰዉ ሕይወት በላይ መለኪያ ሊኖረዉ በርግጥ አይችልም።በጦርነቱ ካለቀዉ ሥልሳ ሚሊዮን ከሚገመት ሕዝብ ግማሽ ያሕሉ የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ዜጋ ነዉ።ከ26 ሚሊዮን በላይ።በርሊንን ቀድሞ የተቆጣጠረዉም የሶቭየት ሕብረት ጦር ነበር።ሚያዚያ 21 1945።

የናትሴ ጀርመን ጦር ፖላድን ከወረረበት ከመስከረም 1939 ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የሞስኮ-ለንደን፤ የዋሽግተን ፓሪስ መንግሥታት አንድ ሆነዉ ተዋጉ።ሁለተኛዉ እና የዓለም ተብሎ የሚጠራዉ ጦርነት በአዉሮጳ ግንባር ግንቦት 1945 በተባባሪዎቹ ሐገራት ጦር ድል አድራጊነት ከተጠናቀቀ በኋላም ድል አድራጊዎች ከብዙ ልዩነታቸዉ ጋር የጋራ ድላቸዉን በጋራ ሲያከብሩ ዓመታት አስቆጠሩ።የድሉ 70ኛ ዓመት ባለፈዉ ሳምንት ሲከበር ግን ያሁን ጠብ ቁርቁሳቸዉ የጥንቱን አንድነታቸዉን ማፈረሱ ገሐድ ወጣ።

ጦርነቱ አዉሮጳ ላይ የቆመበትን 70ኛ ዓመት ለማክበር በዋሽግተኑ የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት መታሰቢያ ሥፍራ በተዘጋጀዉ ድግስ ላይ የተለያዩ ሐገራት ተወካዮች ተገኝተዉ፤ በተሰብሳቢዎቹ መሐል በክብር አልፈዉ ነበር።

የተወካዮቹ ዝርዝር ቀጠለ።የዛሬ ሰባ ዓመት በርሊንን የተቆጣጠረዉን ጦር ያዘመተችዉ የሶቬት ሕብረት ወይም የፈረሰችዉን ሶቬት ሕብረት ከሞላ ጎደል የምትወክለዉ የሩሲያ ሥም ግን አልተጠራም።በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማን አስተዳደር ወክለዉ ንግግር ያደረጉት የፕሬዝደንቱ የፀጥታ አማካሪ ሱዛን ራይስ ግን የሶቬት ሕብረትን ሥምና አስተዋፅኦ መዘንጋት አይችሉም ነበር።

«በምሥራቅ ግንባር ደግሞ የሩሲያ፤ የዩክሬን፤ የቤሎ ሩስ፤ እና የቀድሞዋ ሶቬት ሪፐብሊኮች በሙሉ ሕዝብ የጦርነቱን ከባድ ጥፋት አስተናግደዋል።»

የጦርነቱ ዘግናኝ ዉጤት ከሰዉ ሕይወት በላይ መለኪያ ሊኖረዉ በርግጥ አይችልም።በጦርነቱ ካለቀዉ ሥልሳ ሚሊዮን ከሚገመት ሕዝብ ግማሽ ያሕሉ የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ዜጋ ነዉ።ከ26 ሚሊዮን በላይ።በርሊንን ቀድሞ የተቆጣጠረዉም የሶቭየት ሕብረት ጦር ነበር።ሚያዚያ 21 1945

የጦርነቱ ጫሪ-አዶልፍ ሒትለር እራሱን ያጠፋዉ፤የሒትለር ጦር እጅ የሰጠዉም የቀዩ ጦር የናትሴዎችን አናት በፈጠረቀ በሳምንቱ ነበር።ግንቦት 81945።ራይምዝ-ፈረንሳይ፤ የጀርመን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አልፍሬድ ዮድል

«እኛ ከዚሕ በታች የፈርምነዉ የጀርመን ጦር የበላይ አዛዦች፤-የምድር፤የባሕር፤ የአየር ጦራችን እና ባሁኑ ወቅት በዕዝ ጠገጋችን ሥር ከቀዩ ጦር ጋር የሚዋጋዉ ሌላዉ ሐይላችን በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እጅ መስጠቱን እናስታዉቃለን።»

የዶቸ ቬለዉ ጋዜጠኛ ባለፈዉ ሳምንት ለፃፈዉ ሐተታዉ ጦርነቱ የቆሞዉ መቼ ነዉ? የሚል ጠያቂ-ርዕስ ነበር የሰጠዉ።ምናልባት በድል ማግሥት የጎላዉ የምሥራቅ ምዕራቦች ልዩነት የተጀመረዉ በድሉ ዕለት ሳይሆን አልቀረም።

በምዕራቡ ግንባር የተዋጋዉ የተባባሪዎቹ ሐገራት ጦር አዛዥ አሜሪካዊዉ ጄኔራል ድዋይት አይዘንሐዉር በተገኙበት ራይምዝ-ፈረንሳይ ላይ የጀርመን ጦር አዛዦች የፈረሙና ያወጁትን ሞስኮዎች አልተቀበሉትም።

የሶቭየት ሕብረቱ መሪ ጆሴፍ ስታሊን አዋጁን ላለመቀበላቸዉ ሁለት ምክንያት ነበራቸዉ።የጀርመን ጦር ጠቅላይ አዛዥ ያለወጁና ያልፈረሙት ሠነድ የጀርመንን ጦር ሽንፈት አይወክልም-የሚለዉ ቀዳሚዉ ነዉ።ሁለተኛዉ ምናልባትም ዋነኛዉ ርዕሠ-ከተማ በርሊንን የሚቆጣጠረዉ የሶቬት ሕብረት ጦር አዛዦች በሌሉበት የተፈረመዉ አዋጅ የድል አድራጊዉን ማንነት በትትክል አይገልፅም የሚለዉ ነዉ።

ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራቸዉ ምዕራብ ተባባሪ መንግሥታት የሞስኮዎችን መከራከሪያ ሐሳብ ለማፍረስ-አሳማኝ ምክንያት ሥላልነበራቸዉ ተቀበሉት።ጀርመን ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ እጅ መስጠትዋ ከፈረንሳይ የተሰማ ዕለት ማታ የጀርመን ጦር ሐይሎች ጠቅላይ አዛዥ ማርሻል ቪልሔልም ካይተል አዋጁን በፊርማቸዉ እንዲያረጋግጡ አደረጉ።

ማርሻል ካይተል የጀርመን ጦር ሙሉ በሙሉ እጅ መስጠቱን የሚያረጋግጠዉን ትክለኛ ሠነድ ደግመዉ የፈረሙት ግን ግንቦት ዘጠኝ ነበር።

ጀርመንን ጨምሮ ምዕራባዉን እና የእስካሁን ተባባሪዎቻቸዉ ግንቦት ስምንትን እንደ ድል ቀን ሲዘክሩት የቀድሞዋ ሶቬት ሕብረት ሪፕብሊኮችና ወዳጆችዋ እስከ ዘንድሮ ድረስ ግንቦት ዘጠኝን ያከብሩ ነበር።

የምዕራብ፤ ምሥራቅ ተባባሪዎች የድሉ ዕለት የፈጠረዉን ልዩነት ለማጥበብ በሞስኮና በበርሊን መካካል ባለዉ የሠዓት ልየነት ማሳበቡን ሁነኛ መፍትሔ አድርገዉት ነበር።በመሠረቱ የሠዓቱ ልዩነት-ከሰበብ አልፎ ትክክለኛ ምክንያት ቢሆን ኖሮ-ከሞስኮ ይልቅ በዋሽግተንና በአብዛኞቹ የአዉሮጳ ሐገራት መካከል ያለዉ የሠዓት ልዩነት በሠፋ ነበር።

ዩናይትድ ስቴትስ ግን እንደ ምዕራብ አዉሮጳዉያን ተባብሪዎችዋ ሁሉ ግንቦት 8ን እንደ ድል ቀን ስታከብረዉ፤ ሩሲያ እንዳለፉት 69ኝ ዓመታት ሁሉ ዘንድሮም ያከበረችዉ ግንቦት ዘጠኝ ነዉ።ባለፈዉ ቅዳሜ።

በዋሽግተኑ-ዝክር ከሩሲያ አምባሳደር ሌላ-ሌላ ባለሥልጣን እንዳልተወከለ ሁሉ በሞስኮዉም በዓል ከምዕራብ ሐገራት አንድም መሪ አልተገኘም።በዋሽግተኑ ድግስ አምባሳደር ራይስ የአሜሪካንን ጦር አዝማች፤ አዛዥ፤ አዋጊዎች በስም ሲጠቅሱ የሩሲያ ወይም የሶቬት ሕብረትን ሕዝብ እንጂ ጦር አዝማች፤ አዋጊዎችን አልጠሩም ነበር።የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መልዕክትም ተመሳሳይ ነዉ።

«ለድል እንድንበቃ የታላቅዋ ብሪታንያ፤የፈረንሳይ፤ እና የዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ ላደረጉት አስተዋፅኦ እናመሰግናለን።የጀርመንን ጨምሮ የተለያዩ ሐገራት ፀረ-ፋሽስት ሐይላት በሕብዑ ላደረጉት ከፍተኛ ትግል እናመሰግናለን።»

በዩክሬኑ ጦርነት ሰበብ ሞስኮን የሚወቅሱ፤የሚያወግዙ፤ በማዕቀብ የሚቀጡት መንግሥታት መሪዎች በሞስኮዉ በዓል አይገኙ እንጂ የሌሎች መንግሥታት መሪዎች ተካፋዮች ነበሩ።

ትልቁ እንግዳ የቻይናዉ ፕሬዝዳንት ሺ ጂፒንግ ናቸዉ።ከቻይና ሌላ የደቡብ አፍሪቃ፤የግብፅ፤ የቬኑዙዌላ እና የኩባን ጨምሮ ሐያ መሪዎች ተግኝተዋል።የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ግን ያሁኑን-ጠብ ከታሪካዊዉ እዉነታ ለመለየት ታሪካዊ ግዴታ ነበረባቸዉ።

እንደ ሁሉም የምዕራብ አዉሮጳ መሪዎች ቅዳሜ ሞስኮ በተከበረዉ የድል በዓል ላይ አልተገኙም።የጀርመንን ታሪካዊ ግዴታ ለመወጣት ግን ዕሁድ ወደ ሞስኮ ተጉዞዉ በጦርነቱ ለተገደሉ ወታደሮች መታሰቢያ በቆመዉ ሐዉልት ሥር የአበባ ጉንጉን አኖሩ።አሉም።

«የሩሲያ እና የጀርመን ግንኙነት አስቸጋሪ ምዕራፍ ላይ በደረሰበት በዚሕ ወቅት፤ ወደ ሞስኮ የመጣሁት ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ያበቃበትን ሰባኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ሆኜ በጦርነቱ የተገደሉትን ለማሰብና አክብሮቴን ለመግለፅ ነዉ።»

ጦርነቱን በጋራ ተዋግተዉ ያሸነፉት የምሥራቅ-ምዕራብ ሐያላን በድል ማግሥት የገጠሙት ዓለምን በበላይነት የመግዛት ሽሚያ ከሶቬት ሕብረት መፈረካከስ ጋር አብቅቶ ወይም ያበቃ መስሎ ነበር።መጀመሪያ፤ የሶሪያ፤ ቀጥሎ የዩክሬን ፖለቲካዊ ቀዉስ አከታትሎም የርስ በርስ ጦርነት ሲፋፋም ግን ድፍን ሃያ-ዐመት ዉስጥ ዉስጡን ሲብላላ የነበረዉ ፍትጊያ አደባባይ ወጥቷል።

የዓልም ጦርነት በተባባሪዎቹ ሐገራት ድል የተጠናቀቀበት ሰባኛ ዓመት በዓል አርብ ቅዳሜ-በየርዕሰ ከተሞቹ ሲከበር ደግሞ ከጦርነቱ ወቅት አንድነት፤ ከከኮሚንስት ካፒታሊስቱ ሥርዓት ሽኩቻ ይልቅ ባሁኑ ጠብ-ቁርቁስ ስሜት እንደተጫጫነዉ ግልፅ ሆኗል።

ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ከመራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጋር ሆነዉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በዓሉ-ከጠቡ ጋር ግንኙነት እንደሌለዉ፤ የጠቡንም መነሻ አቃለዉ ለማቅረብ ሞክረዉ ነበር።

«የሩሲያና የጀርመን ግንኙነት መጥፎ ደረጃ ላይ መድረሱ ሚስጥር አይደለም።ምክንያቱ የዩክሬን ሁኔታ የፈጠረዉ የግንዛቤ ልዩነት ነዉ።የንግድ ግኙነታችን በአምስት ዓመት ዉስጥ በጣም አሽቆልቁሎ በ2014 6,5 ከመቶ ቀንሷል።»

ፑቲን ቅዳሜ ቀዩ አደባባይ ላይ «ያሰጡት» ወታደራዊ ትርዒት ግን ሩሲያ ጀርመንን ጨምሮ ከምዕራባዉያን ሐገራት ጋር የገጠመችዉን እሰጥ አገባ መስካሪ ነበር።ትርዒቱ ከ16 ሺሕ በላይ የሩሲያ ምርጥ ወታደሮች የተሠለፉበት ነበር።

የሩሲያ ምርጥ አዕምሮ ያመረተዉ ከዘመናይ ጄት-እስከ ተምዘግዛጊ ሚሳዬል፤ ከፈጣን ታንክ፤ ቦምብ እስከማይደፍረዉ ተሽከርካሪ የታየበት ነበር።የፑቲኗ ሩሲያ ጦር ሐይል ከስታሊኗ ሶቬየት ሕብረት ቢበልጥ እንጂ እንደማያንስ ለወዳጆችዋም-ለጠላቶችዋም ለማሳየት ያለመ-ታላቅ ትርዒት።

የሞስኮ-ዋሽግተን ብራስልሶች ልዩነት ላለፉት 69ኝ ዓመታት በዓሉን ከሶቬት ሕብረትና ከሶቬየት ሕብረት ሪፐብሊኮች ጋር አንድ ቀን ሲያከብሩ የነበሩትን ዩክሬን እና ፖላንድን የመሳሰሉ የምሥራቅ አዉሮጳ ሐገራትን ታሪክም ያስቀየረ ነበር።ፖለቲካዊ ሰልፋቸዉን ከምዕራባዉያኑ ጋር ያደረጉት ኪየቭና ዋርሶ የዘንድሮዉን በዓል ያከበሩት ቅዳሜ ግንቦት ዘጠኝ ሳይሆን እንደ ምዕራቦቹ አርብ ግንቦት ስምንት ነበር።

በዓሉ የተለያዩ ሥፍራዎች በተለያዩ ቀኖች መከበሩ ምናልባት ዲፕሎማሲያዊ ሚዛንን ለመጠበቅ-ግራ ቀኝ ለሚረግጡት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ለፓን ጊ ሙን ሳይጠቅም አልቀረም።ፓን አርብ ጠዋት በፖላንዱ በዓል ተገኝተዉ-ዩክሬን በሚከበረዉ ተመሳሳይ በዓል ለመካፈል ማርፈጃዉን ኪየቭ ገቡ።ከፕሬዝደንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ ጋር አከበሩም።

«የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከዩክሬን ሕዝብ ጎን ይቆማል።እዚሕ የመጣሁት ግጭቱ የዩክሬንን ልዓላዊነት፤የግዛት አንድነትና ነፃነትን በሚያስከብር መልኩ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኝ ያለኝን ጠንካራ ድጋፍ በድጋሚ ለመግለፅ ነዉ።»

ኪየቭ ላይ ይሕን አሉና በማግስቱ ትልቁ ዲፕሎማት ያ ትልቅ ወታደራዊ ትርዒት በቀረበበት በዓል ላይ ተገኙ።ታሪክ የተለወጠበት ታሪካዊ ዕለትን በሁለት ቀን ሰወስት ሥፍራ በአካል ተግኝተዉ አዩ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic