1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ገንዘብ ድርጅት አዲስ ሐላፊ

ረቡዕ፣ ሰኔ 22 2003

የሃያ-ስድስት አመቷ የሕግ ምሩቅ ወጣት በ1981 ቤከር እና ማክ ኬንዚይ የተሰኘዉን የዩናይትድ ስቴትስን ዓለም አቀፍ የጠበቆች ድርጅትን ስትቀየጥ የዕድሜ-ትምሕርት ብቻ ሳይሆን የሙያ፥ ብስለት፥ አዋቂነቱንም መሠላል ትወጣጣዉ ያዘች።ከአንግዲሕ አንቱ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/RWVT
IMF-አርማምስል picture-alliance/dpa

29 06 11

የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ፈረንሳዊቱን የምጣኔ ሐብትና የገንዘብ ሚንስትር ክሪስቲን ላጋርድን የድርጅቱ የበላይ ሐላፊ አድርጎ መረጠ።ላጋርድ በወሲብ ቅሌት ሥልጣን የለቀቁትን ፈረንሳዊዉን የቀድሞ የድርጅቱን ሐላፊ የዶመኒክ ሽትራዉስ ካሕንን ሥልጣን ካንድ ሳምንት በሕዋላ በይፋ ይረከባሉ።BRICS በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠሩት አዳዲሱቹ የዓለም ሐብታም ሐገራት ሽትራዉስ ካሕንን የሚተካዉ ሰዉ ከነሱ እንዲመረጥ ቢጠይቁም በአቋማቸዉ አልገፉበትም።ላጋርድ ተወዳደሪያቸዉን የሜክሲኮዉ የባንክ ገዢ አጉስቲን ካረስተንስንም በቀላሉ ነዉ የበለጧቸዉ።

«ለዓለም ገንዘብ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅነት ለመወዳደር ወስኛለሁ።ሥለ ጉዳዩ በቅጡ አስቤበታለሁ፥የፕሬዝዳንቱንም፥ የጠቅላይ ሚንስትሩንም ድጋፍ በማግኘቴ እወዳደራለሁ።»

ክርስቲን ማንደሊን ኦዳት ላጋርድ።የፈረንሳይ የምጣኔ ሐብት፥ የገንዘብና የኢንዱስትሪ ጉዳይ ሚንስትር።ግንቦት አጋማሽ።ከያኔ ጀምሮ እሳቸዉና አለቆቻቸዉ ብዙ እንደፈለጉ-እንደጣሩለት፥ ፈረንሳዮች በጣም እንደ ጓጉ-እንደተመኙት አገኙት።ትናንት።«የዓለም ገንዘብ ድርጅት ክርስቲን ላጋርድ ከሚቀጥለዉ ሐምሌ አምስት ጀምሮ ለሚቀጥለዉ አምስት ዓመት የድርጅቱ የበላይ ሐላፊ እንዲሆኑ መርጧቸዋል።»

NO FLASH Christine Lagarde kandidiert für IWF Posten
ላጋርድምስል dapd

ፈረንሳዊቷ-ፈረንሳዊዉን ተካች።ለሐምሳ አምስት አመቷ ፖለቲከኛ እፎይታ፥ለፈረንሳዮች ደስታ። ለፕሬዝዳንታቸዉ ደግሞ ኩራት።«ክሪስቲን ላጋርድ ጠንክራ ሴት መሆናቸዉን መላዉ ዓለም ይስማማል።ጥሩ ሐላፊ ይሆናሉ።»

ፕሬዝዳንት ኒኮላይ ሳርኮዚ።ዛሬ።

እርግጥ ነዉ ዶሞኒክ ሽትራዉስ ካሕን በዚያች ጎዶሎ ቀን፥ በዚያች መጥፎ አጋጣሚ ከትልቁ ሰገነት በቅፅበት እስከተንከባለሉበት ጊዜ ድረስ ጠንካራ ሠራተኛ፥ በሳል ፕሮፌሰር፥ ብልሕ አስተዳዳሪ፥ ብልጥ ፖለቲከኛ ነበሩ።አሁን ግን ፕሬዝዳት ሳርኮዚ እንዳሉት ያዉ ወይዘሮ ላጋርድ ናቸዉ።

IMF በሚል የእንግሊዝኛ ምፃረ ቃል የሚጠራዉ አለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት የተመሠረተበትን አምስተኛ አመት ሲያከብር የክንግዲሕ መሪዉ ተወለዱ።ጥር 1956(ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ)።የገንዘብ ተቋሙ በጦር የደቀቀችዉን አዉሮጳን እየረዳ፥ ከትንሽነት ወደ ትልቅነት ሲመነደግ፥ አዉሮጳም አዋራዋን እያራገፈች በፖለቲካ-ምጣኔ ሐብቱ የትልቅነቷን ቦታ ያዘች። ትንሺቱ ክርቲንም ፈረንሳይ፥አሜሪካ እያለች የዩኒቨርቲ ጥናት ትምሕርቷን አጠናቀቀች።

የሃያ-ስድስት አመቷ የሕግ ምሩቅ ወጣት በ1981 ቤከር እና ማክ ኬንዚይ የተሰኘዉን የዩናይትድ ስቴትስን ዓለም አቀፍ የጠበቆች ድርጅትን ስትቀየጥ የዕድሜ-ትምሕርት ብቻ ሳይሆን የሙያ፥ ብስለት፥ አዋቂነቱንም መሠላል ትወጣጣዉ ያዘች።ከአንግዲሕ አንቱ ናቸዉ።

ቺካጎ፥ ሆንግ ኮንግ እና ለንደን እያሉ ከሠሩ በሕዋላ በ1999 የግዙፉ የጠበቆች ድርጅት የመጀመሪያዋ ሴት አስተዳዳሪ ሆኑ።ዶመኒክ ሽትራዉስ ካሕን በሁለት ሺሕ አምስት የፈረንሳዩን ሶሻሊስት ፓርቲ የመሪነት ሥልጣን ለመያዝ ሲታገሉ፥በሥልጣን ላይ የነበረዉን ወግ አጥባቂ ፓርቲ የተቀየጡት ማዳም ላጋርድ የፈረንሳይ የንግድ ሚንስትርነትን ሥልጣን ተሾሙ።

ሽትራዉስ ካሕን የዓለም ገንዘብ ድርጅት መሪነትን በሁለት ሺሕ ሰባት ሲሾሙ ደግሞ ላጋርት ከአመታት በፊት ሽትራዉስ ካሕን ይዘዉት የነበረዉን የገንዘብ ሚንስትርነት ሥልጣን ያዙ።«እንደ ቀድሞ ሥራ አስኪያጅ፥ አሁን ደግሞ እንደ ሚንስትር በምመራዉ ቡድን ዉስጥ ከሌሎቹ ለየት ያለ ቢያንስ አንድ ሰዉ፥ የሆነ ሰዉ ለየት ያለ ሥልጠና፥ሥለ ሥራዉ ሒደት ለየት ያለ አመለካከት ያለ አመለካከት ያለዉ ሰዉ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ።አለበለዚያ ሁል ጊዜ ሁሉም አንድ አቋም የሚይዝ ከሆነ ወደ ፊት መራመድ አይቻልም።እንዲያ ነዉ።»

Dominique Strauss-Kahn Gericht IWF 19.05. Flash-Galerie
ሽትራዉስ ካሕንምስል AP

ትናንት የሚሽቱን አገኙ።አንድ አይደለም የሥብጥሪቱ ዓለም ሥብጥር አስተሳሰብ የሚንፀባረቅበት ግዙፍ ድርጅት የመጀመሪያዋ ሴት ሐላፊ ሆኑ።ማዳም ላጋርድ።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ