የዓለም ዲፕሎማቶች መዲና አዲስ አበባ ለምግብ ቤቶት አስተናጋጆች ደንብ አወጣች
ሐሙስ፣ ኅዳር 19 2017የዓለም የዲፕሎማሲ መዲና አዲስ አበባ ለምግብ ቤቶች ደንብ አወጣች
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሆቴሎች ዓለም አቀፍ ደረጃን እንዲይዙ፤ ብሎም የኢትዮጵያን ባህል እሴት ለመጠበቅ የሆቴል አስተናጋጆች በሥራ ወቅት የሚያደርጉት ልብስ ደንብ ይፋ ሆንዋል። «ደንቡ ፤ ሴቶችን ካላስፈላጊ ትንኮሳ ይከላከላል፤ ከዚህም በላይ የዓለም ዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችዉ የአዲስ አበባን ደረጃም ያስጠብቃል» ሲሉ፤ የአዲስ አበባ ቱሪዝም ባህልና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሳዉ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
ባለፈዉ ሰሞን የአዲስ አበባ ከተማ ፍትህ ቢሮ እንዳስታወቀዉ፤ የሆቴል ባለሙያዎች የደረት ክፍላቸውን ወይም ከአንገታቸው በታች ያለውን የሰውነት ክፍል ያልሸፈነ ሸሚዝ ቢለብሱ ፤የሚቀጡበት ደንብ ማውጣቱን አስታውቋል። ቢሮው ከጥቂት ቀናት በፊት እንዳለው ”የሴቶች ጉርድ ቀሚስ ቁመቱ እና ቅዱ ከጉልበት በላይ ከሆነ፤ እንዲሁም ከጋብቻ ቀለበት ውጪ ጌጣጌጦች በሚታዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ከተደረገ" በደንቡ መሠረት ያስቀጣል።
” የሆቴል ባለሙያዎችን አለባበስ እና የመዋቢያ ጌጣጌጥ አጠቃቀም ሥርዓትን“ ለመወሰን የወጣ ደንብ እንደሆነ የተገለጸው “ሙያተኞች ሊደርስባቸው ከሚችለው አካላዊ፤ ሥነ-ልቦናዊ ጫና እና አላስፈላጊ ጥቃቶች ለመከላከል” እንደሆነ ነዉ የተገለፀዉ።
ደንቡ “በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ወጥ የሆነ የአለባበስ፤ የጌጣጌጥ እና የመዋቢያ አጠቃቀም ሥርዓት በመዘርጋት የሀገር ባህልና እሴት እንዲጠበቅ ለማድረግ” ጭምር ያቀደ ነው ተብሏል። ለዝግጅት ክፍላችን በጉዳዩ ላይ ቃለ ምልልስ የሰጡን የአዲስ አበባ ቱሪዝም ባህልና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሳዉ፤ እንደነገሩን ደንቡ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ያቀደ ነዉ።
ደንቡ የአስተናጋጆችንም ሆነ የደንበኞችን መብት የሚጠብቅ ነዉ
ዓለም አቀፉ የሆቴል አስተናጋጆች የአለባበስ ደንብ ፤ ከኢትዮጵያዉያን ባህል ጋር የተስማማ ነዉ ያሉት፤ የአዲስ አበባ ቱሪዝም ባህልና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሳዉ ፤ ደንቡ በሁለተኛ ደረጃ የአስተናጋጆቹን እንዲሁም የምግብ ቤት ተቋማቱን እንግዶች መብትን የሚጠብቅ ነዉ።
የዓለም አቀፍ ቱሪዝም እና ሆቴል አስተዳደር ባለሞያ የሆኑት አቶ ልዑል ሰገድ መሰለ ፤በኬኒያ ብሎም በብሪታንያ ከፍተኛ ትምህርታቸዉን ተከታትለዉ በሁለቱም ሃገራት በዓለም አቀፍ ቱሪዝም እና ሆቴል አስተዳደር ከፍተኛ የሞያ ልምድ አላቸዉ። በኢትዮጵያም በሆቴሎች እና ቱሪዝም ዘርፍ ወደ 10 ዓመታት አገልግለዋል። በኢትዮጵያ የአለባበስ ደንብ ያላቸዉ ደረጃ ለተሰጣቸዉ ሆቴሎች እንደሆን ተናግረዋል።
«በዚህ ጉዳይ ላይ በዶቼ ቬለ የፌስቡክ ድረገፅ አስተያየታቸዉን ያስቀመጡት፤ ያዕቆብ ገብሬ እንደሚሉት፤ የወጣዉ ህግ በጣም ጥሩ ጅማሬ ነው። ይህ ውሳኔ የሆቴል ሴቶችን ህይወት ብቻ ሳይሆን፤ የባለትዳሮችንም ህይወት ይታደጋል። ደረታቸውን፤ ጭናቸውን፤ ዳሌያቸውን ክፍት አድርገው የሚሰሩ እህቶች ፤እግዚአብሔር ይቅር ይበለን እንጂ የስንቱን ህይወት እና ትዳር ቀጥፏል? ከዚህም አልፎ ተርፎ ኢኮኖሚያቸው በዚህ ሰበብ የተበላሸባቸዉ ስንት ናቸው? ጤንነታቸው የተዛባባቸዉስ? ትዳራቸዉ የተቃወሰባቸዉስ ስንቱ ናቸዉ? በወጣዉ የአለባበስ ደንብ ማይስማማ ሰይጣን ብቻ እንጂ፤ ሁሉም ሰው ይቀበለዋል፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።»
በስጋ ቤቶች ላይ ቁጥጥር ያስፈልጋል
የዓለም አቀፍ ቱሪዝም እና ሆቴል አስተዳደር ባለሞያዉ አቶ ልዑል ሰገድ መሰለ፤ በተለይ ጉዳዩ አዲስ አበባ ዉስጥ በሚገኙ ስጋ ቤቶች እንደሚስተዋል ተናግረዋል። ጃራ ቦሩ የተባሉ በዶቼ ቬለ ፌስቡክ ላይ ባስቀመጡት አስተያየት፤ « የሚያስፈልገው ሴቶችን በቁሙ መገነዝ ሳይሆን፤ ስሜቱን መቆጣጠር በማይችል ሙት ላይ ከበድ ያለ ቅጣት ማሳለፍ ብቻ ነው። ሁልጊዜም ሴቶችን ተጠያቂ ለማድረግ ነው የምንሮጠው። ሴቶች አማራጮች ሊቀርቡላቸው ይገባል። የሚያስደስታቸውን አለባበስ መርጠው መልበስ እንዲችሉ እና የሆቴል ባለንብረቶች ደግሞ ምርጫዎቻቸውን እንዲጠብቁላቸው ማመቻቸት ነው አማራጩ ።» ብለዋል። ይህ የወጣዉ ደንብ የሴቶችን መብት የሚጋፋ አይሆንም? የአዲስ አበባ ቱሪዝም ባህልና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሳዉ ደንቡ መብታቸዉን የሚያስከብር ነዉ ሲሉ ተናግረዋል።
ጽኑ ዳግም የተባሉ የዶቼ ቬለ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ፤ «ድሮ ድሮ ወጣ ብዬ ከነ ልጆቼ መዝናናት እወድ ነገር። በአስተናጋጆቹ አለባበስ ምክንያት ፍላጎቴ ጠፍቷል። የሚያሳዝነው ግን እነዚህ አስተናጋጆች ይህን የተራቆተ ልብስ ፈልገው ሳይሆን፤ ተገደው መልበሳቸው ነው። የሚገርመው ደግሞ፤ ይሄን የሚያለብሱ ሴቶች ላይ ወረፋ መብዛቱ ነው። እረ እንደውም ደሞዛቸው እራሱ ትንሽ የሆነው፤ ከቲፕ ታገኙታላችሁ ተብለው ነው የሚቀጠሩት። እረ እንደውም የሰውነት ቅርፅ ታይቶ ነው የሚቀጠሩት፤ አሉ ። ተገደው ሰውነታቸውን እየቸረቸሩ ነው። ህግ መውጣቱ ጥሩ ነው። አስፈፃሚ ቶሎ ይመደብለት።» ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።
የዓለም አቀፍ ቱሪዝም እና ሆቴል አስተዳደር ባለሞያዉ አቶ ልዑል ሰገድ መሰለ፤እንደሚሉት ደንቡ ቀጣይነት ሊኖረዉ በሌሎች ከተሞች ሁሉ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል። አቶ ልዑል ሰገድ እንደሚሉት አብዛኞቹ ትልልቅ ሆቴሎች በፈረንጅ ባለሞያዎች የተያዙ ናቸዉ፤ እንደ ኢትዮጵያን አየር መንገድ ሁሉ ሆቴሎቻችን በኢትዮጵያዉያን መመራት ይኖርባቸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን እና የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ጋር በቅንጅት ደንቡን የማስፈጸም ሥልጣን እንደተሰጣቸዉ ተመልክቷል። አድማጮች የአዲስ አበባ ቱሪዝም ባህልና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሳዉን እና የዓለም አቀፍ ቱሪዝም እና ሆቴል አስተዳደር ባለሞያዉ አቶ ልዑል ሰገድ መሰለ ለሰጡን ቃለ ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም በማመስገን፤ ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ