የዓለም የጡት ማጥባት ሳምንት | ጤና እና አካባቢ | DW | 08.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የዓለም የጡት ማጥባት ሳምንት

የእናት ጡት ወተት ለልጅ ተወዳዳሪ የሌለዉ አስተማማኝ ጤናማ ምግብ መሆኑ በተደጋጋሚ ይመከራል። ጡት የማጥባት ልማድ እየጨመረ በሄደ መጠን የሚታመሙ ልጆች ቁጥር እንደሚቀንስ በቅርቡ የወጣ የተመድ ዘገባ አመልክቷል። ምን ያህል እናቶች ይህን ተገንዝበዉ ልጆቻቸዉን ጡት ያጠባሉ?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:34

ልጆች እስከ 6 ወር የእናት ጡት ብቻ መመገብ አለባቸዉ፤

 

በዓለም አቀፍ ደረጃ የጡት ማጥባት ሳምንት ዘንድሮ ለ25ኛ ጊዜ ነዉ የታሰበዉ፤ ካለፈዉ ሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 1 2009ዓ,ም ድረስ። እናቶች ለጨቅላ ልጆቻቸዉ ጡት እንዲያጠቡ ቢመከርም፤ ሠራተኛ የሆነች እናት ለልጇ ይህን ለማድረግ በቂ ዕድል እንዳልተመቻቸላት የሚናገሩም አልጠፉም።

«ለእናቶች ልጆቻቸዉን ቢሯቸዉ ዉስጥ ይዘዉ ለመገኘት በጣም አዳጋች ነዉ። በዚያም ላይ ይህም ቢሆን እናቲቱ በምትሠራዉ የሥራ አይነት ላይም የተመረኮዘ ነዉ የሚሆነዉ። የቢሮ ሠራተኛ ላትሆን ትችላለች፤ ሜዳ ላይ የተለያየ ሥራ የምትሠራ ከሆነ ሌላ ሰዉ ልጇ መጥባት ሲኖርበት ሊያመጣላት ያስፈልግ ይሆናል። እንግዲህ እነዚህ ከእንቅፋቶቹ ጥቂቶቹ ናቸዉ።»

ፓትሪሺያ ኬርኒዩ በካሜሮን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቤተሰብ ደህንነት ዘርፍ ክፍል ባልደረባ ናት። እሷ የምትሠራበት ክፍል በተለይ እናቶች ልጆቻቸዉን እስከ ስድስት ወራት ጡት እንዲያጠቡ አዘዉትሮ ያበረታታል። በዚህ ምክንያትም ፓትሪሺያ ኬርኒዩ አንዲት እናት ስድስት ወር የወሊድ ፈቃድ ሊሰጣት ይገባል ስትል ትሞግታለች። ካሜሮን ዉስጥ የወለዱ እናቶች ልጆቻቸዉን ጡት ማጥባት እንዲችሉ የሁለት ወር ፈቃድ ይሰጣል። ሁለቱ ወር ሲያበቃም፤ ለአራት ወራት በየቀኑ ወደቤት ሄደዉ ልጆቻቸዉን ጡት የሚያጠቡበት የሁለት ሰዓት ፈቃድ አላቸዉ።

ምንም እንኳን ጥቂት የማይባሉ የአፍሪቃ ሃገራት እናቶች ልጆቻቸዉን ጡት እንዲያጠቡ ለማበረታታት እየሞከሩ ቢሆንም እስካሁን ግን ከስድስት ወር በታች ላሉ ሕጻናት የእናት ጡት ወተትን ብቻ መመገብ የሚለዉን ምክር ያሳካ ሀገር የለም። በዚህም ምክንያት የአፍሪቃ ሃገራት እናቶች ሕጻናት ልጆቻቸዉን ጡት ማጥባትን እንዲያዘወትሩ ድጋፍ በማድረግ እንዲያመቻቹላቸዉ እየተጠየቁ ነዉ።

Australien Senatorin Larissa Waters von der Partei der Grünen spricht im Parlament

ልጃቸዉን እያጠቡ የሚታዩት የአዉስትራሊያ ምክር ቤት የአረንጓዴ ፓርቲ እንደራሴ ላሪሳ ዋልተርስ፤ ለትምህርት ቤቶች መደረግ ስለሚገባዉ የገንዘብ ድጋፍ ሃሳባቸዉን ሲሰጡ፤

የዓለም የጤና ድርጅት አራስ ልጆች ከተወለዱበት ጊዜ አንስቶ እስከ ስድስት ወር ድረስ የእናት ጡት ብቻ ቢመገቡ ሰዉነታቸዉ በሽታን መቋቋም ይችላል ሲል ይመክራል። በአሁኑ ጊዜ ብዙ ወጣት እናቶች ይህን ሲያደርጉ አይታይም። ለምሳሌ የ21ዓመቷ ካሜሮናዊት ጊዚሌ ናጎኖ ከተወለደ ገና ስድስት ሳምንት የሆነዉን ጨቅላ ልጇን ለማጥባት በቂ ጊዜ አላገኘሁም ትላለች።

«ሠራተኛ ነኝ። ይህን ሕጻን ጡት ብቻ ማጥባቱ ይከብደኛል። ወጣ ብዬ ገንዘብ ፈላልጌ እሱን መመገብ ይኖርብኛል፤ እሱን ለማጥባት እቤት ዉስጥ ልቀመጥ ነዉ? እንዴት ሊሆን ይችላል? ለዚህም ሆነ ለዚያ መክፈል የሚያስፈልገኝ ሁሉ እንዴት ይሆናል?እኮ እንዴት?»

እርግጥ ነዉ ቤተሰብን ለማስተዳደር ሲባል በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጥቂት የማይባሉ እናቶች ልጆቻቸዉን ጡት ብቻ ለማጥባት ይከብዳቸዉ ይሆናል። የአራት ልጆች እናት ለሆነችዉ ወ/ሮ ሮዝ መስቲካ ግን ልጆችን ጡት ማጥባቱ በምንም አይተካም። የእናት ጡት ወተትን በአግባቡ አግኝተዉ የሚያድጉ ልጆችም ካልጠቡት ይልቅ በቀላሉ ለበሽታ እንደማይጋለጡ በግል ተሞክሮዋ ማስተዋሏን ትገልጻለች።

«እኔ የመጀመሪያ ልጄን አላጠባሁም። እንደተወለደ ለአራት ሰዓት ያህል ቆይቶ ነዉ የተሰጠኝ። ብርድ ነዉ በሚል ዱቄት ወተት በጡጦ አጥብተዉ ነዉ የሰጡኝ። እኔም ብዙ እዉቀቱም ልምዱም ስላልነበረኝ፤ የመጀመሪያ ልጅ ያስቸግራል ጡት ማጥባት። እንደገና እኛ ሀገር ስለ ጡት ማጥባት ትምህርትም አይሰጥም እንዴት አድርጋ አዲስ እናት ጡቷን ማስለመድ እንዳለበት። እናም በዚህ ምክንያት የመጀመሪያ ልጄን አላጠባሁትም። ግን ሞክሬያለሁ አልፎ አልፎ ለመስጠት ግን ጠባ የሚባል አይደለም። ሁለተኛ፣ ሦስተኛ አሁን አራተኛ ልጄን ሦስት ወር አካባቢ ይሆናታል፤ ሁሉንም አጥብቼያቸዋለሁ። ጉንፋን ወይም ደግሞ ተቅማጥ፣ ትኩሳት ቶሎ ቶሎ የሚይዛቸዉ አይደሉም ሦስቱ ልጆቼ። በደንብ አቅም አላቸዉ ሌላ ምግብ ተጨማሪ ባይበሉ እንኳን የሰዉነት አቅማቸዉ፤ የበሽታ መከላከል አቅማቸዉ በጣም ጠንካራ ነዉ። ጥርሳቸዉ ራሱ ስታይዉ ልዩነት አለዉ፤ ጡት የጠባዉ ልጅ እና ያልጠባዉን ልጅ ስታስተያይ በእኔ ቤት ዉስጥ ልዩነት አላቸዉ።»

Dänemark Stillen in der Öffentlichkeit

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2013 ሐምሌ 10 ቀን ዴንማርክ ዉስጥ በአንዳንድ ቦታዎች ማጥባት የተከለከሉ እናቶች ኮፐንሃገን ምክር ቤት ፊትለፊት ልጆቻቸዉን ጡት ሲያጠቡ ዉለዋል፤

የሕጻናት ሃኪም የሆኑት አባንጎሞ ሱዛንም የእናት ጡት ወተትን ጥቅም አስመልክተዉ የሚሰጡት ምክር የወ/ሮ ሮዝን ተሞክሮ የሚያጠናክር ነዉ።

«ሁሉንም የምግብ ንጥረ ነገሮች የያዘ ነዉ። ዉድ ዋጋ የማያስከፍል እና ልጁ መመገብ በፈለገ ወቅት ሁልጊዜም ተገቢዉን የሙቀት መጠን ጠብቆ የሚገኝ ነዉ። ከእናት ወደ ልጅ ሊኖር የሚገባዉን ግንኙነት የሚፈጥር በመሆኑም ለእናቲቱ ምቾትን ያመጣል። ልጇን ጡት ማጥባት የማትችል እናት፤ ሕጻኑ ልጇ ሰዉነቱን ከበሽታዎች የሚከላከልለትን የተፈጥሮ አቅም የማግኘት ዕድል ላይኖረዉ ይችላል ተብሎ ይታመናል። ለተለያዩ በሽታዎችም ሕጻኑ የተጋለጠ ነዉ።»

የዓለም የጤና ድርጅት የእናት ጡት ጨቅላ ሕጻናትን ለሞት ከሚያደርስ በሽታ ሊያድን የሚችል የመጀመሪያዉ ክትባት ማለት እንደሆነ ነዉ የሚናገረዉ። እስከ ጎርጎሪዮሳዊዉ 2025ዓ,ም ድረስ በዓለም ከሚገኙ ሕጻናት 50 በመቶዉ የእናት ጡት ወተት ብቻ ከተመገቡ ለቀጣይ 10 ዓመታት የ520 ሺህ ልጆች ሕይወት ከሞት እንደሚተርፍ፤ በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸዉ ሃገራትም በኤኮኖሚዉ ዘርፍ እስከ 300 ቢሊየን ዶላር ማፍራት እንደሚቻል የዓለም ባንክ በበኩሉ ግምቱን አስቀምጧል።  

በነገራችን ላይ ባሳለፍነዉ የሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ ዕለት ማለት ነዉ ሁለት ሺህ የሚሆኑ የፊሊፒንስ እናቶች የሕጻናትን ሞት መቀነስ እንደሚያስችል ለማሳየት እና በአደባባይ ጡት ማጥባት ነዉር ነዉ የሚለዉን ልማድ እንደሚቃወሙ ለማሳየት ሕዝብ በሚሰበሰብበት ስፍራ ልጆቻቸዉን ሲያጠቡ ዉለዋል።

Mütter protestieren in London

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2014 ታኅሳስ 6፤ የለንደን እናቶች በካላርጅ ሆቴል ደጃፍ ልጆቻቸዉን በአደባባይ ማጥባት እንዳይከለከሉ በተቃዉሞ ልጆቻቸዉን ሲያጠቡ፤

ይህን ያስተባበሩት ወገኖች እንደተናገሩት ዋና ዓላማቸዉ ፊሊፒኖ እናት ልጇን እስከ ስድስት ወራት የጡቷን ወተት ብቻ እንድትመግብ ማበረታታት እና በሀገሪቱ ያለዉን የሕጻናት ልጆች ሞት መቀነስ ነዉ። ፊሊፒኖዎች ይህን ሲያደርጉ እዚህ ጀርመን በርሊን ከተማ ደግሞ አንዲት እናት ልጇን ሻይ ቡና ልትል በገባችበት ምግብ ቤት ዉስጥ ማጥባት አትችይም በመባሏ ምክንያት እናቶች ልጆቻቸዉን ሕዝብ በሚሰበሰብባቸዉ ስፍራ ጭምር ማጥባት እንዲችሉ በሕግ እንዲደነገግ ዘመቻ ጀምራለች። የሦስት ወር ሕጻን ይዛ ከባለቤቷ ጋር ከገባችበት ካፌ እንዳታጠባ ስለተነገራት ጥላ የወጣችዉ ዮሀና ሽፓንከ በኢንተርኔት በጀመረችዉ የማስተባበር ዘመቻ እስካሁን የ17ሺህ ሰዎችን ፊርማ ለድጋፍ አሰባስባለች። የእናት ጡት ወተትን በተመለከተ ሌላዉ የተሰማዉ መረጃ ደግሞ በኢንተርኔት አማካኝነት ትኩስ የእናት ጡት ወተት ሽያጭን መጧጧፉን ይገልጻል። ጀርመን ዉስጥ አዲስ የተጀመረዉ ይህ ንግድ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ረብጣ ዶላር የሚያስዝቅ ገበያ እንዳለዉ መረጃዉ ይጠቁማል። ለዚህ ንግድ የጀርመኑ ገበያ ያወጣዉ ማስታወቂ ደግሞ «ጫማ፣ መጻሕፍትን በኢንተርኔት መግዛት ተችሏል፤ የእናት ጡት ወተትም ለሽያጭ ቀርቧል» ይላል። የእናት ጡት ወተት ሽያጭ፤ ልጆቻቸዉን ራሳቸዉ መንከባከብ ለማይችሉ እናቶች መልካም አማራጭ መሆኑን የሚናገሩለት ቢኖሩም፤ ለሕጻናቱ አደገኛ ነዉ በማለት አጥብቀዉ የተቹትም አልጠፉም። አድማጮች 25ኛዉን የጡት ማጥባት ሳምንት በተመለከተ ለዕለቱ ያልነዉን በዚሁ አጠናቀቅን። ጡት ማጥባት እንዲችሉ ለእናቶች ረዥም የወሊድ ፈቃድ እንዲሰጥ የምትቀሰቅሰዉ ወ/ሮ ሮዝ መስቲካን ለሰጠችን አስተያየት እናመሰግናለን። እናንተን አስተያየት ጥቆማችሁን አካፍሉን።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic