የዓለም የገንዘብ ተቋሟት ዓመታዊ ጉባዔ | ኤኮኖሚ | DW | 13.10.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም የገንዘብ ተቋሟት ዓመታዊ ጉባዔ

የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም አይ.ኤም.ኤፍ የዘንድሮ ዓመታዊ ጉባዔያቸውን ባለፈው ሰንበት ዋሺንግተን ላይ አካሂደዋል።

default

የምንዛሪው ተቋም በዋዜማው ባለፈው ሣምንት ረቡዕ አቅርቦት በነበረው ዘገባ እንዳመለከተው የዓለም ኤኮኖሚ ከቀውሱ ያገገመው ከአካባቢ አካባቢ በተለያየ ፍጥነትና ሁኔታ ነው። በሌላ አነጋገር በሽተኛው በተወሰነ ደረጃ አገገመ እንጂ ገና በሚገባ አልዳነም። ሶሥት ቀናት የፈጀው ጉባዔ ከዚሁ የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት ይዞታ ባሻገር የፊናንስ ገበዮችን ፍቱን በሆነ መልክ መቆጣጠሩን፣ የበጀት ኪሣራ ቅነሣንና የዓለም ንግድን ሚዛናዊ መሆን አስፈላጊነት ማተኮሪያው እንዲያደርግ የተወጠነ ነበር። ይሁንና በመጨረሻ ድንገት ሳይጠበቅ በምንዛሪ ጦርነት ስጋት መጋረዱ አልቀረም።

ባለፈው ሣምንት ዋሺንግተን ላይ የቀረበው የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ዘገባ በዓለም ኤኮኖሚ ላይ መልሶ የተጣጣመ ሚዛን እንዲሰፍን ጥሪ የተደረገበት ነበር። በምንዛሪው ተቋም ዘገባ መሠረት የዓለም ኤኮኖሚ የማገገም ሂደት እስካሁን በተለያየ ፍጥነት ሲጓዝ ነው የመጣው። በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት ምዕራባውያን ሃገራት ዕድገቱ መለስተኛ ሲሆን እንደገና ቀውስ ላይ የመውደቁ አደጋ ደግሞ አሁንም ከፍተኛ ነው። በአንጻሩ እንደ ቻይና ያሉት በተፋጠነ ሁኔታ በመራመድ ላይ የሚገኙ መንግሥታት እንደገና ከፍተኛ ዕድገት ሊያስመዘግቡ ችለዋል። ሃቁ ይህ በመሆኑም የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ዋና የምጣኔ-ሐብት ባለሙያ ኦሊቨር ብላንቻርድ እንደሚሉት ይህን የሚዛን ዝቤት ማስወገዱ የዓለም መንግሥታት ቀደምት ተግባር ነው።

“ወደተጣጣመ ሚዛን መመለስ! የዘገባችን ዋና ነጥብ ይህ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥታት ውስጣዊ ማዛናቸውን ማስተካከል ይኖርባቸዋል። በቀውሱ ወቅት የግሉ ፍላጎት ወይም ፍጆት ባቆለቆለበት ጊዜ የከፋ ውድቀትን ለማስወገድ የረዳው የኤኮኖሚ ማነቃቂያ ዕቅድ ማስፈኑ ነበር። ይህ አስፈላጊና ትክክለኛ ዕርምጃም ነበር። አሁን ግን የግሉ ፍላጎት በተራው የፈውሱ አንቀሳቃሽ መንኮራኩር ሊሆን ይገባዋል። ምክንያቱም አብዛኞቹ ማነቃቂያ ዕቅዶች ማብቂያቸው ላይ በመዳረሳቸው”

IWF Chefökonom Olivier Blanchard

ኦሊቨር ብላንቻርድ

እንግዲህ ብላንቻርድ እንደሚያሳስቡት ቀጣዩ አስፈላጊ ተግባር የግሉን ፍጆታና መዋዕለ-ነዋይን ማጠናከር ነው። ይህ ደግሞ የብሄራዊ ኤኮኖሚን ውስጣዊ ሚዛን ለመጠበቅ ብቻ የሚረዳ አይደለም። በመንግሥታት መካከል የተፈጠረውን ለዓለም ኤኮኖሚ ይዞታ አደገኛ የሆነ የሚዛን ዝቤት ለማስተካከል ጭምር የሚበጅ ነው። ዝቤቱን ለማለዘብ የበጀት ኪሣራ ያለባቸው ዩ.ኤስ. አሜሪካን የመሳሰሉ አገሮችም የውጭ ንግዳቸውን ለማጠናከር መጣር አለባቸው።
የውጭ ንግዱ ማየል በአገር ውስጥ ፍላጎትን በማጠናከር መንግሥታት የበጀት ኪሣራቸውን እንዲቀንሱ መተንፈሻ ቀዳዳን የሚከፍት ነው የሚሆነው። በሌላ በኩል የተትረፈረፈ የውጭ ንግድ ላላቸው በተለይ የእሢያ አገሮችም ቢሆን በውጩ ንግድ ዕድገት ላይ ጥገኛ እንዳይሆኑ ከፈለጉ የአገር ውስጡን ፍጆታ ማሳደጉ የሚበጅ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም። የዕድገቱ ሚዛን ዝቤት በተለያዩት የዓለም አካባቢዎች የተለያየ ዕድገትንም እያንጸባረቀ ሲሆን የምንዛሪው ተቋም እንደሚተነብየው የበለጸገው ዓለም ዕርምጃ ከታዳጊው ሲነጻጸር አዝጋሚ እንደሆነ ነው የሚቀጥለው።

“ሁኔታው በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት ሃገራት ደካማ የኤኮኖሚ ዕድገት እንድንተነብይ የሚያደርግ ነው። 2,7 በመቶ በዚህ ዓመትና 2,2 በመቶ በሚከተለው”

በአንጻሩ በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ በሚገኙት አዳጊ አገሮች ዕድገቱ የተለየ ነው። ዓአምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም በነዚህ አገሮች በያዝነው ዓመት 7,1 በመቶና በቀጣዩም ዓመት 6,4 ከመቶ ዕድገት እንደሚኖር ይገምታል። የምንዛሪው ተቋም የበለጸገውን ዓለም በተመለከተ ደግሞ የሃገራት ታዛቢው ዮርግ ዴክሬሢን እንደሚሉት ቢቀር የጀርመን የዕድገት ትንበያውን ወደ ላይ ማረሙም አልቀረም።

“የጀርመን የዕድገት ትንበያችንን ወደ ላይ ከፍ አድርገን አርመናል። እናም በዚህ ዓመት የ 3,3 በመቶ ዕድገት ነው የምንጠብቀው። ይህ ደግሞ ቀደም ሲል ከታሰበው በ 1,9 ከመቶ የበለጠ ሲሆን በመጪው 2011 ዓ.ም. ደግሞ ሁለት ከመቶ ዕድገት እንጠብቃለን። ይህም ቢሆን ቢቀር ቀደም ሲል ከታለመው 0.5 በመቶ የላቀ መሆኑ ነው”

Logo der Herbsttagung von IWF und Weltbank

ይህ የምንዛሪው ተቋም በተናጠል አንድ አገርን አስመልክቶ ያደረገው ብችኛ እርማት ሲሆን በአንጻሩ የአሜሪካን ኤኮኖሚ አስመልክቶ የቀረበው ትንበያ ጨርሶ የተለየ ነው። በያዝነው ዓመት 2,6 እና በሚቀጥለው ደግሞ 2,3 በመቶ ዕድገት! ከዚሁ ጋር የአሜሪካ የሥራ አጥ ብዛት ከፍተኛ እንደሆነ ይቀጥላል። ከዚህ አንጻር ትልቁም አቤቱታ ከዚያው ከአሜሪካ መመንጨቱ ብዙም አያስደንቅም። ዋሺንግተን በውጭ ንግዷ ሃያል የሆነችው ቻይና የምንዛሪዋን ዋጋ ያላግባብ ዝቅ አድርጋ በመያዝ ፍትሃዊ የገበያ ፉክክር እንዳይኖር ታደርጋለች ባይ ናት። የምንዛሪው ተቋም የኤኮኖሚ ጠቢብ ኦሊቭር ብላንቻርድ ይሁንና በጉዳዩ ሲናገሩ ለዘብ ያሉ ቃላትን ነው የመረጡት።

“አንድ አገር የምንዛሪውን ዋጋ በተወሰነ መጠን ለማስቀመጥ ወይም ከተቀሩት ላለማጣጣም መፈለጉ ሌሎች አገሮች የበኩላቸውን ማስተካከያ እንዳያደርጉ ሁኔታውን የሚያከብድ ነው የሚሆነው። ስለዚህም በተፋጠነ ዕድገት ላይ ላሉት አገሮች ትብብርና ቅንጅት መኖሩ ጠቃሚ ይሆናል። እነዚህ አገሮች አሁን የምንዛሪ ጦርነት እየተባለ ከሚወራለት ችግር ላይ ሳይወድቁ በጥሩ ሁኔታ ማደግ የሚችሉትም ይህ ሲሆን ብቻ ነው”

በዕውነት የዓለም ኤኮኖሚን እንደገና ቀውስ ላይ ሊጥል የሚችል የገንዘብ ዋጋን ዝቅ የማድረግ ፉክክር፤ ሰሞኑን ሲባል እንደነበረው የምንዛሪ ጦርነት እያስከተለ ነወይ? ለስጋት መንስዔ የሆነው በአሜሪካና በቻይና መካከል መካረር የያዘው ውዝግብ ነው። አሜሪካ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ቻይና የምንዛሪዋን የዩዋንን ዋጋ ባልሆነ መንገድ ዝቅ አድርጋ በመገደብ አግባብ ባሌለው መንገድ የንግድ ተጠቃሚ ሆናለች ስትል ትወቅሳለች። ቻይና በፊናዋ እንደምታስገነዝበው የምንዛሪዋን ዋጋ መጠን መወሰን ያለበት ነጻው የገበያ ሁኔታ ነው።
በመሠረቱ የልማት ዕርዳታ ፕሮዤዎች ገንዘብ አቅራቢው የዓለም ባንክም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት የፊናንስ ጉዳይ እሣት አደጋ መከላከያ የሆነው ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም የምንዛሪ ልውውጥ ችግር የሚፈቱባቸው ተስማሚዎቹ መድረኮች አይደሉም። ግን ችግሩ ገና ከጉባዔው በፊት ሲያነጋግር የምንዛሪው ተቋም አስተዳዳሪ ዶሚኒክ-ሽትራውስ-ካህንም አደጋውን ካነሱት አንዱ ናቸው።

“ስለ ምንዛሪ ጦርነት የሚያወሩት ብዙዎች ናቸው። እኔም ጥቂት ወታደራዊ ቢመስልም ቅሉ ይህንኑ አባባል ተጠቅሜያለሁ። ሃቁ ግን ብዙዎች ምንዛሪያቸውን እንደ ጦር መሣሪያ አድርገው መመልከታቸው ነው። ታዲያ ይሄ ደግሞ ለዓለም ኤኮኖሚ ፍጹም ጥሩ ነገር አይደለም። እና ሁላችንም በጉዳዩ ላይ አዲስ የተጣጣመ ሚዛን እንዲሰፍን ነው የምንፈልገው። ይህ እርግጥ የምንዛሪዎችን ዋጋ ነጻ ሂደት በመግታት ሊሆን አይችልም። ግን ከረጅም ጊዜ አንጻር በዓለም ኤኮኖሚ ላይ የተጣጣመ ሚዛንን ለማስፈን የሚረዳም አይሆንም”

የምንዛሪው ዋጋ ጥያቄ ሲነሣ እርግጥ ይበልጡን አስታራቂ ዕርምጃ የሚጠበቀው ከቻይና በኩል ነው። የጋራ ውሣኔ ማስፈኑና በጋራ ገቢር ማድረጉ ደግሞ ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ላሰባሰባቸው ለቡድን-ሃያ መንግሥታት የሚተው ይሆናል። እነዚሁ በቅርቡ ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ይሰበሰባሉ። ታዲያ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት የሃብታሞቹ ሰባት መንግሥት ሚና እየቀዘቀዘና የሌሎች ድምጽ እየጎላ ሲሄድ ሁኔታው ቀላል እንዳልሆነም የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ሮበርት ዞሊክ ጭምር የተገነዘቡት ነገር ነው።

“ከቀድሞው ይልቅ ዛሬ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ብዙ ተፎካካሪዎች አሉን። ከኤኮኖሚ አንጻርም ጊዜው በጣሙን ከባድ ሲሆን ውጥረትንም ያስከትላል። እኔ የማቀርበው ሃሣብ በመጀመሪያ ይህን ውጥረት እንቋቋም የሚል ነው። ችግሩ ወደ አንድ ጭብጥ ወደሆነ ውዝግብ ወይም የራስን የኤኮኖሚ ጥቅም የመገደብ ደረጃ ከተለወጠ ያለፈውን ምዕተ-ዓመት የ 30 ኛዎቹን ዓመታት ስህተት ከመድገም አደጋ ላይ እንዳንወድቅ የሚያሰጋ ነው”

ስህተቱ እንደሚታወቀው የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስን የሚቀሰቅስ መሆኑ ነው። ይህን ደግሞ የቻይና ማዕከላዊ ባንክ ምክትል አስተዳዳሪ ዪ ጋንግ እንደሚያስረግጡት ቤይጂንግን ጨምሮ ማንም የሚፈልገው ነገር አይደለም።

“እኛ ጦርነት እያካሄድን አይደለንም። የምንዛሪ ዋጋ ፖሊሲን የመሳሰሉትን አስቸጋሪ ጉዳዮች በጥንቃቄ ነው የምንመለከተው። ግን ፈጣንና የተረጋጋ በሆነው የኤኮኖሚ ዕድገታችን መቀጠልም እንፈልጋለን። እርግጥ የጋራ ጥቅምና ሰላም በሰመረበት ሁኔታ!”

ሃቁ አሜሪካ ለኤኮኖሚዋ ቻይናን በምትፈልግበት መጠን ቻይናም አሜሪካን የምትፈልግ መሆኑ ነው። የእርስበርሱ ጥገኝነት ይቀጥላል። ምናልባት ጭብጥ አደጋ ቢኖር ከምንዛሪው ጦርነት ይልቅ ብሄራዊ ጥቅምን የማስከበሩ ሁኔታ ሊጠናከር መቻሉ ነው።

መሥፍን መኮንን
ነጋሽ መሐመድ