የዓለም የገንዘብ ተቋማት ጉባዔ | ኤኮኖሚ | DW | 23.04.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም የገንዘብ ተቋማት ጉባዔ

ዋሺንግተን ላይ ተቀማጭ የሆኑት ሁለቱ የገንዘብ ተቋማት የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም IMF የዓመቱ የጸደይ ጉባዔ

ጉባዔው ቀደም ካለው ጊዜ ሲነጻጸር ሁለቱ ተቋማት በአመለካከትም ሆነ በትንበያ ከቀድሞው ጊዜ ይልቅ ቆጠብ ያሉ መሆናቸው ጎልቶ የታየበት ነው።

የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም አስተዳዳሪ ክሪስቲን ላጋርድ ለምሳሌ በወቅት የዓለም ኤኮኖሚ ይዞታ ላይ እርካታ የሚሰማቸው አልሆኑም። ለዚህም ምክንያቱ የተለያዩት የዓለም አካባቢዎች ዕድገት በተለያየ ፍጥነት የሚጓዝ መሆኑ ላይ ነው። ታዳጊዎቹና በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ ያሉት ሃገራት በጠነከረ ሁኔታ በማደግ ላይ ሲሆኑ አሜሪካ በመካከለኛ ሁኔታ እንዲሁም ጃፓንና አውሮፓ ደግሞ በዝቅተኛ ደረጃ የተወሰኑ ናቸው።

ክሪስቲን ላጋርድ ይህን መሰሉ በሶሥት የተለያየ ፍጥነት የሚራመድ የኤኮኖሚ ማገገም ሁኔታ ጤናማ አይደለም ብለዋል። ላጋርድ ጨምረው እንደገለጹት የሚፈለገው በሙሉ ፍጥነት የሚራመድ የዓለም ኤኮኖሚ ነው። እንደርሳቸው አባባል ዕድገት ጽኑ፣ ቀጣይና ለሁሉም አረንጓዴ ማለትም የተፈጥሮ ይዞታን የጠበቀ መሆን ይኖርበታል። በተለይም የመጨረሻው በታዳጊ ሃገራት ዕድገት ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው ነው የሚፈለገው።

ታዲያ ይህ የጋራ የሆነ አረንጓዴ የኤኮኖሚ ዕድገት ምንም እንኳ መልካም ሕልም ቢሆንም የወቅቱ ሃቅ ግን ከዚህ የተለየ ሆኖ ነው የሚገኘው። በመሆኑም ላጋርድ እንደየሁኔታው የተለያየ ሃሣብ መሰንዘሩን መርጠዋል። የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም አስተዳዳሪ በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ የሚገኙት ሃገራት በገንዘብ መትረፍረፍ እንዳይዋጡ ሲያስጠነቅቁ ድሆች ሃገራት ደግሞ በመዋቅራዊ ልማት ላይ መዋዕለ-ነዋይ እንዲያደርጉ መክረዋል። ላጋርድ አሜሪካም የፊናንስ ሁኔታዋን አቅድ ባለውና በተረጋጋ ሁኔታ ስርዓት እንድታስይዝ ነው ያሳሰቡት።

በክሪስቲን ላጋርድ አመለካከት በፊናንስ ቀውስ የተወጠሩት አውሮፓውያን በአጭር ጊዜ ብዙ ዕርምጃ አድርገዋል። አሁን ደግሞ ቅድሚያ ሊሰጡ የሚገባቸው የባንክ ሕብረት፤ ማለትም የጋራ አቋም ያለው የአውሮፓ የባንክ ተቆጣጣሪ አካል ለመፍጠሩ ዓላማ ነው። በሌላ በኩል ይሁንና የፊናንሱ ገበዮች ማገገም ለሕዝብ ጠቃሚ ለሆኑት ለኤኮኖሚ ዕድገትና ለስራ መስኮች መከፈት አስተዋጽኦ አላደረገም።

ስለዚህም የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ከብሪታኒያ፣ ከአሜሪካ ወይም ከጃፓን ሲነጻጸር በኤውሮ ዞን ከፍ ብሎ የሚገኘውን መሪ ወለድ መቀነስ እንደሚበጀው ነው የተመከረው። እርግጥ እዚህ አስፈላጊው ነገር በዝቅተኛው ወለድ ቤተሰቦችና አነስተኛ ኩባንያዎችም ተጠቃሚ ሊሆኑ መቻላቸው ነው። ከዚህ በተጨማሪ የባንኩ ስርዓት መጠገን እንዳለበትም ፈረንሣዊቱ የምንዛሪው ተቋም አስተዳዳሪ አያይዘው አስገንዝበዋል።

ክሪስቲን ላጋርድ በበጀት ቀውስ ተወጥረው ከሚገኙት የኤውሮ-ዞን ሃገራት አንዷ በሆነችው በስፓኝም የለውጥ ጥድፊያ እንደማይጠቅም ነው ያስረዱት። ስፓኝ እንደ ግሪክ፣ ፖርቱጋል ወይም ኢጣሊያ በማቆልቆል ላይ በሚገኝ ኤኮኖሚና በስራ አጥነት ብዛት ከባድ ፈተና ላይ መሆኗ ይታወቃል። እናም እንደ ላጋርድ አባባል እርግጥ ስፓኝ የፊናንስ ይዞታዋን ማስተካከል ይኖርባታል። ሆኖም ግን ይህ ተግባር ቀድሞ በታቀደው ፍጥነት የመራመዱ አስፈላጊነት ለምንዛሪው ተቋም አይታየውም። በሌላ አነጋገር አገሪቱ የበለጠ ጊዜ ያሰፈልጋታል።

የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ጂም-ዮንግ-ኪም ደግሞ በአንድ በኩል ድርጅታቸው በዓለም ላይ አስከፊውን ድህነት እስከ 2030 ዓ-ም ለማስወገድ ለዚሁ ተግባር ለሚካሄዱ ፕሮዤዎች ገንዘብ እንደሚያቀርብ ቃል ሲገቡ በሌላ በኩልም በዚህ መንገድ የሚገኘው ዕድገት በተቻለ መጠን ለአካባቢ ተፈጥሮ የተስማማ መሆኑ የሚፈለግ መሆኑን ነው አያይዘው ያስረገጡት።

ኪም እንዳሉት የአካባቢ አየር መለወጥ የተፈጥሮ ጥበቃ ችግር ብቻ አይደለም። ዓለም አሁን በቁርጠኝነት ዕርምጃ ካልወሰደ የፕላኔታችን ሞቅታ አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱ የማይቀር ነው። በዚሁ የተነሣ ድህነትን በመታገሉ ረገድ የተገኘው የአሠርተ-ዓመታት ዕርምጃ ከንቱ ሊሆን ይችላል።

«ከዚህ ቀደም የተወሳሰበ ድርጅትን የመራን ማንንም ሰው መጠየቅ ይቻላል። ግልጽ ግብና ጭብጥ የጊዜ ገደብ ሳይኖር አንድም ዕርምጃ ማድረግ አይቻልም። ግልጽ ነው፤ ድህነት መጥፎ እንደሆነ ሁሉም ይናገራል። ግን ታዲያ ግፊት ሣይኖር የአሠራር ዘይቤን የሚቀይር ማንም የለም»

የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት አዲስ ግባቸውን ሲያስረዱ በከፋ ድህነት ደረጃ የሚገኘውን ወገን ድርሻ እስከ 2013 ድረስ ከዓለም ሕዝብ ቁጥር አንጻር ወደ ሶሥት በመቶ መቀነሱ ውጥናቸው መሆኑን ተናግረዋል። በነገራችን ላይ በከፋ ድህነት የሚኖሩ የሚባሉት ከ 1,25 ዶላር ባነሰች ገቢ የዕለት ኑሯቿውን የሚገፉት ናቸው። የዓለም ባንክ ለማንኛውም የሕልውናው ምክንያት የሆነውን ድህነትን የመታገሉን ዓላማ የግድ ማራመድ ይኖርበታል።

የዋሺንግተኑ የገንዘብ ተቋም በዚህ ሁኔታ ላይ በሚገኝበት ጊዜ ብሪክስ በሚል አሕጽሮት የሚታወቁት በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ የሚገኙት ሃገራት ብራዚል፣ ሩሢያ፣ ሕንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪቃ ደግሞ የራሳቸውን የልማት ባንክ ለማቋቋም መነሳታቸው የሚታወቅ ነው። ሆኖም ኪም ይህን ለባንካቸው ተፎካካሪ እንደሚሆን አድርገው አይመለከቱትም። ይህም ያለ ምክንያት አይደለም።

የብሪክስ ሃገራት ገና ታላቅ መዋቅራዊ ጉድለት አለባቸው። ሕንድ ብቻ በሚቀጥሉት ዓመታት ለመዋቅራዊ ፕሮዤዎች 1 ሺህ ሚሊያርድ ዶላር እንደሚያስፈልጋት ነው የተነገረው። ታዲያ ይህን ገንዘብ ደግሞ አንድ ተቋም ብቻውን፤ ሌላው ቀርቶ የዓለም ባንክ ራሱ እንኳ ሊያቀርብ የሚችል አይሆንም። ስለዚህም ኪም የብሪክስን ባንክ የሚመለከቱት የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦትን የሚያሰፋ ተጨማሪ አካል አድርገው ነው።

ቀደም ሲል እንደጠቀስነው የኤኮኖሚው ዕድገት ከአውሮፓ በተጻራሪ ጠንከር ባለ ሁኔታ ሲያድግ የሚታየው በእሢያ ነው። ግን ዕድገቱ የአካባቢው ሃገራት ይበልጥ በኤኮኖሚ ቢተሳሰሩ የበለጠ በሆነም ነበር። ይህም በገንዘብ ተቋማቱ ጉባዔ አኳያ ትኩረት ማግኘቱ አልቀረም። ከክሪስቲን ላጋርድ ምክትሎች አንዱ ናኦዩኪ ሺኖሃራ እንደተናገሩት እሢያ ውስጥ የሚደረገው ንግድ እርግጥ አርኪ ሊባል የሚችል ነው።

«እሢያ ውስጥ የሚካሄደው ንግድ ከ 2000 ዓ-ም ወዲህ በሶሥት ዕጅ ጨምሯል። በአንጻሩ ዓለምአቀፉ ንግድ በተመሳሳይ ጊዜ በእጥፍ ብቻ ነው ያደገው»

እርግጥ ጃፓናዊው የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የኤኮኖሚ ባለሙያ በዚህ መርካቱን አልመረጡም። ምክንያቱም የእሢያ ንግድ ገና በአብዛኛው ተሰርተው ባላለቁ ምርቶች ልውውጥ ላይ ተወስኖ ነው የሚገኘው። ለምሳሌ የተለያዩት ሃገራት ቻይና ውስጥ ለሚገጣጠሙ ኮምፒዩተሮች ተናጠል አካላትን ነው የሚያቀርቡት። በአንጻሩ ባለቁ ምርቶች የሚደረገው ንግድና የሚሰጠው አገልግሎት ገና ደካማ ሆኖ ነው የሚገኘው።

ይህ ደግሞ ብዙ የእሢያ ሃገራት ለእስካሁን ዕድገታቸው የተጠቀሙበት የዓለምአቀፉ አቅርቦት ነጸብራቅ መሆኑ ነው። ለአሜሪካና ለአውሮፓ ገበዮች በርካሽ ሲያመርቱ ኖረዋል። ሆኖም ግን አሁን ሆንግኮንግ ላይ ተቀማጭ የሆነው የፉንግ ዓለምአቀፍ ምርምር ኢንስቲቲዩት ፕሬዚደንት አንድሩው ሼንግ እንደሚሉት ሁኔታው እየተቀየረ በመሄድ ላይ ነው።

«የዓለምአቀፉ ምርት አቅርቦት ሁኔታ ከመሠረቱ እየተቀየረ ነው። እስካሁን እሢያ ውስጥ የሚካሄደው ምርት በምዕራቡ ዓለም ፍላጎት ላይ ጥገኛ ነበር። ግን አሁን ምዕራባውያን ኩባንያዎች ለእሢያ ገበያ ምርቶች መንደፍ እየጀመሩ ነው። የእሢያ ኩባንያዎችም እንዲሁ ለእሢያ ገበዮች ያመርታሉ»

ሼንግ እንደሚሉት ለዚህ ሂደት መንኮራኩር የሆነው በእሢያ ሃገራት የፍጆተኛው መካከለኛ መደብ እየሰፋ መምጣት ነው። ይህ ለብሄራዊው ኤኮኖሚ የሚኖረው ጥቅም ኩባንያዎች ጥራት የጠበቀ ምርት እንዲያወጡ በማድረጉ ላይ ይሆናል። የማሌይዚያ ማዕከላዊ ባንክ ሃላፊ ዜቲ-አክታር-አዚዝ እንደሚያስረዱት በርካታ የእሢያ ሃገራት ከሌሎች የዓለም አካባቢዎች ጋር የሚያደርጉትን ንግድ ያስፋፉ ሲሆን ዛሬ ያን ያህል በምዕራቡ ፍላጎት ላይ የግድ ጥገኞች አይደሉም።

«እሢያ ዛሬ ከአፍሪቃ፣ ከላቲን አሜሪካና ከአረቡ ዓለም ጋር ትነግዳለች። ለዚህም ነው የንግድ ሚዛናችን አትራፊ ሆኖ የሚገኘው። አውሮፓ ውስጥ በአንጻሩ የኤኮኖሚ ችግር አለ። አሜሪካ ውስጥ ዕድገቱ ደካማ ነው። እንግዲህ እነዚህ ነበሩ የንግድ ሸሪኮቻችን። አሁን ግን ከሌሎች በተፋጠነ ዕድገት ላይ ከሚገኙ ሃገራት ጋር ለምናካሂደው ንግድ ነው ክብደት የምንሰጠው»

በዚህ በኩል እርግጥ የንግድ መሰናክሎች እየተወገዱ መሄዳቸው በጣሙን አስፈላጊ ይሆናል። በዓለም ንግድ ድርጅት ጥላ ስር የተካሄደው ድርድር በመክሸፉ ለጊዜው በዚያ ደረጃ ዓለምአቀፍ ውል መስፈኑ የማይጠበቅ ነው። በአንጻሩ በርካታ የሁለት ወገንና የአካባቢ ስምምነቶች እየሰፈኑ ሲሆን እርግጥ ከምንም ቢሻሉም በሌላ በኩል ውስብስብነት አያጣቸውም። እናም ውሎቹ ከዓለም ንግድ ድርጅት ደምቦች ቢጣጣሙ የሚመረጥ ነው። ይህ ለዓለም ኤኮኖሚ መልሶ ማገገምም ጠቀሜታ ይኖረዋል።

መሥፍን መኮንን

ተeሌ የኋላ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች