የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር | ስፖርት | DW | 11.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር

በብራዚል በመካሄድ ላይ ባለውና ፣ የፊታችን እሁድ በሚያከትመው የዘንድሮው የዓለም የአግር ኳስ ዋንጫ ውድድር፣ ትናንት ማታ በተካሄደው ሁለተኛው የግማሽ ፍጻሜ ውድድር አርጀንቲናና ኔደርላንድ በ9o ው ደቂቃ ጨዋታና 30 ደቂቃም ተጨምሮ ባለመሸና

ነፋቸው በፍጹም ቅጣት ምት 4-2 በሆነ ውጤት አርጀንቲና ድል አድርጎ ለፍጻሜ ለማለፍ በቅቷል። ስለዚህ የፍጻሜው ግጥሚያ ፤ በጀርመንና በአርጀንቲና መካከል ይሆናል የሚካሄደው። ስለትናንቱ ጨዋታና ስለፍጻሜው የተሰናዳው ዘገባ ----

አርጀንቲና እ ጎ አ በ 1978 ዓ ም የዓለምን የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር አዘጋጅታ በፍጻሜ ግጥሚያ ኔደርላንድን 3-1 በሆነ ውጤት አሸንፋ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ ማግኘቷ የሚታወስ ነው። እ ጎ አ በ 1986 ፣ ሜክሲኮ ላይ በማራዶና አምበልነት አርጀንቲና ፣ ጀርመንን 3-2 በማሸነፍ ለሁለተኛ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን በቃች! አሁን ለ 3ኛ ጊዜ ለማግኘት ነው ሕልሟም ሆነ ጥረቷ!

ንዑሷ ሀገር ኔደርላንድ በ 1970ኛዎቹ ዓመታት በእነ ዮሓን ክሮይፍ ዘመን ፣ ማንኛውም ተጫዋች በሁሉም ቦታ መሰለፍ የሚችልበትን ማራኪ አጨዋወት «ቶታል ፉትቦል » (ሁለገብ እግር ኳስ ጨዋታ) የተባለውን ያስተዋወቀች ናት። በ 1974 ጀርመን ላይ በ 1978 አርጀንቲና ፣ በ 2010 ደቡብ አፍሪቃ በተሰናዳው የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ፣ ፍጻሜ ላይ ደርሳ ገደቢስ መሆኗ የሚታወስ ነው። ትናንት ፣ ግማሽ ፍጻሜም ላይ በጨዋታ ሳትበለጥ ዕድለቢስነት አሰናብቷታል። ታዲያ የፊታችን ቅዳሜ ለ 3ኛ ደረጃ በሚካሄደው ግጥሚያ መሳተፉ ደንታም እንዳልሰጣቸው አሰልጣኝ ልዊስ ፋን ኻል ገልጸዋል። 11 ቁጥር እውቅ ተጫዋች ፣ አርየን ሮበንም፣ «ትርጉም የለሽ ነው፣ ዋጋ ያለው የዓለም ሻምፒየን የሚያደርገው የአንደኛነቱ ዋንጫ ብቻ ነው» ማለቱ ተጠቅሷል። ግራም ነፈሰ ቀኝ ተጫዋቾቹ ያን ያህል ደስ ባይላቸውም የፊፋን ሕግ ማክበር ስላለባቸው ለ 3ኛነት ከብራዚል ጋር መጋጠም ይኖርባቸዋል። ብራዚሎች ፣ ከሞላ ጎደል መጽናኛ ሊያደርጉት አስበዋል። በሕብለ ሠረሰሩ ላይ ከደረሰበት ጉዳት ቀስ በቀስ በማገገም ላይ የሚገኘው ኔይማር በሜዳ ተግኝቶ ቡድኑን ሳያበረታታ እንደማይቀር ገልጿል።

ሌላው በቅጣት ሳቢያ ባለፈው ማክሰኞ ሳይለፍ በመቅረቱ ቡድኑን ክፉኛ የጎዳው በተከላካይነትና በአደራጅነት የታወቀው ቲያጎ ሲልቫ፤ ቅዳሜ ይሰለፋል።

ስለትናንቱ የኔደርላንድና አርጀንቲና ግጥሚያ ፤ አሪየን ሮበን ይህን ነበረ ያለው።

«እንደሚመስለኝ፤ አሁን ያን ያህል ዋጋ አይሰጠው ይሆናል፤ ምንልባትም መነገር የለበትም ይሆናል፤ ግን ከዚህ ቡድን ጋር ባገኘነው ውጤት ኩራት ሊሰማን ይገባል። ለግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ እንደምንደርስ የጠበቀ አልነበረም። ዛሬ ፤ እንደገና ጥሩ ጨዋታ አሳይተናል፤ ሆኖም ያሳዝናል ለፍጻሜ አላደረሰንም። ነገር ግን በዚህ በወጣቶች በተገነባው ቡድን እጅግ ፤ እጅግ ነው የኮራሁ!»

በጀርመን ቴሌቭዥን የአንደኛው የሥርጭት መሥመር ፣ የዘንድሮ ዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ሓያሲ ሆኖ የቀረበው የቀድሞው የጀርመን ብሔራዊ በድንና የባየርን ክለብ ተጫዋጭ የነበረው ሜሜት ሾል፤

የትናንቱን ጨዋታ ጀርመን ካሳየችው ጋር በማነጻጸር አለመርካቱንና ጀርመን ዋንጫ የማግኘት ተስፋዋ የጎላ መሆኑን ነው የተናገረው።

«ዛሬ ምንም የቡድን ጨዋታ አላየሁም፤ ሆላንዳውያንም ሆኑ አርጀንቲኒያውያን ጀርመን ያሳየችውን ዓይነት ጨዋታ አላሳዩምና የሚያሠጋን ያለ አይመስለኝም። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ፣ በብራዚል ቡድን ላይ እንዳደረገው በአርጀንቲናም ላይ ፈጥኖ ማስጨነቁን ከደገመው ሊሣካ ይችላል። ዋናው ጉዳይ ትልቅ ጥረት ማድረግ ነው ፤ እርግጠኛ ነኝ ጀርመን ትወጣዋለች።»

ጀርመን ፤ እ ጎ አ በ 1954 ዓ ም በርን ፣ ስዊስዘርላንድ ላይ በፍጻሜ ግጥሚያ ሃንጋሪን አሸንፋ ለመጀመሪያ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ከሆነች እንሆ 60 ዓመት ሆነ ። በ 60ኛው ዓመት ለ 4ኛ ጊዜ ዋንጫ ለማግኘት ቋምጣለች። ከተሳካላት፤ ከአትላንቲክ ማዶ በደቡብ አሜሪካም ሆነ በሰሜን አሜሪካ በተዘጋጁ የዓለም ዋንጫ ውድድሮች አውሮፓውያን ቀንቷቸው አያውቅም ነበር። ጀርመን ከተሳካላት በላቲን አሜሪካ የዓለምን ዋንጫ ያሸነፈች የመጀመሪያቱ አውሮፓዊት ሀገር ትሆናለች ማለት ነው።

አርጀንቲናውያን፤ አገራቸውን ብቻ ሳይሆን ላቲን አሜሪካን ጭምር ወክለው እንደሚጫወቱ ይሰማቸው ይሆናል። እስካሁን በተከላካዮች ቁጥጥር ጭምር ያን ያህል እንቅሥቃሴ ያላሳየው 4 ጊዜ የዓለም ኮከብ ተጫዋች የተሰኘው ፣ አሞካሺዎቹ ከዲየጎ አርማንዶ ማራዶና ጋር የሚያመሳስሉት ሊዮኔል ሜሲ ፣ ብዙ እየተጠበቀበት ነው ፤ ግን ፣ እስካሁን ካሳየው የላቀ ችሎታውን እሁድ ያሳይ ይሆን ? እርሱ ብቻ ሳይሆን ቡድኑ ባጠቃላይ ከጀርመን ጋር የሚመጥን ሆኖ ይገኛል ወይ ነው ጥያቄው! ። ጠብቀን የምናየው ይሆናል።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic