የዓለም የኤድስ ቀን | ጤና እና አካባቢ | DW | 03.12.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የዓለም የኤድስ ቀን

የዓለም የጤና ድርጅት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2011ዓ,ም አንስቶ የዓለም የኤድስ ቀን ሲታሰብ፤ ማንም በቫይረሱ የማይያዝባት ዓለምን የመፍጠር መርህ ነዉ ያስቀደመዉ። ዘንድሮም እንዲሁ ዕለቱ ሲታሰብ በተለይ ታዳጊ ወጣቶች ለHIV ቫይረስ የማይጋለጡበት መንገድ ተጠናክሮ ትኩረት እንዲደረግበት የሚለዉ አፅንኦት ተሰጥቶታል።

default

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ስለበሽታዉ ደፍሮ መናገር ነፍስን የሚቀስፍ ይመስል ነበር፤ ብዙዎች በዝምታ የጤና እክላቸዉ እንኳ ሳይገለጽ እንደዋዛ አሸለቡ። በሽታዉን የደበቀ መድሃኒት አይገኝለትም እንዲሉ፤ መደባበቁ ቀርቶ ስለHIV ቫይረስ ጥቂቶች አደባባይ ወጥተዉ መናገርን ጀመሩ፤ የበርካቶችን ቀልብ ሳቡ። እነሱ እንደሻማ ቀልጠዉ የሌሎች እድሜ እንዲረዝም ምክንያት ሆኑ። ዛሬ HIV ቫይረስ ስጋትነቱ አክትሟል ማለት ባይደፈርም እንደዱር አዉሬ ማስፈራራቱ ግን በመጠኑም ቢሆን ቀንሷል። ሰዎች ራሳቸዉን በመግዛት ህይወታቸዉን መምራትን ጨምሮ በህክምናዉም እየተረዱ ቫይረሱ በደማቸዉ እያለም ቢሆን ጤናማ ልጅ እየወለዱ መኖር ተችሏል። ይህ በአንድ ወገን የሚታይና የስኬት ርምጃ ነዉ። የተመ የሕፃናት መርጃ ድርጅት UNICEF የዘንድሮዉን የዓለም የኤድስ ቀን አስታኮ ባወጣዉ ዘገባ ከእናት ወደልጅ ቫይረሱ እንዳይተላለፍ የተደረገዉ ጥረት ዉጤት አሳይቷል። በዚህም 850 ሺህ ልጆች ከቫይረሱ ነፃ ሆነዉ ሊወለዱ መቻላቸዉ ተመዝግቧል። በተቃራኒዉ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2005ዓ,ም እስከ 2012ዓ,ም ድረስ ደግሞ በHIV AIDS ምክንያት የሚቀጠፉ ታዳጊ ወጣቶች ቁጥር መጨመሩን የድርጅቱ ዘገባ አመልክቷል። በተጠቀሰዉ ጊዜ ዉስጥም ቁጥሩ ከ71 ሺህ ወደ 110 ሺህ ማሻቀቡ ታይቷል። UNICEF እንደሚለዉም አዳዲስ በቫይረሱ ከተያዙ ልጆች 90 በመቶ የሚሆኑት በ22 ሃገራት የሚገNU ሲሆን ከአንዱ በስተቀር ሁሉም ከሰሃራ በስተደቡብ ያሉ ናቸዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች