የዓለም የስደተኞች ቀን እና ኢትዮጵያ | ኢትዮጵያ | DW | 20.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የዓለም የስደተኞች ቀን እና ኢትዮጵያ

ዛሬ፣ ሰኔ 13፣ 2008 ዓ/ም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የስደተኞች ቀን ወይም «Wold Refugee Day» በመባል እየታሰበ ይገኛል። ባሳለፍነዉ ሁለት ዓመታት ዉስጥ ኢትዮጵያ በርካታ ስድተኞችን በመቀበል ከኬንያ መቅደምዋን የተለያዩ ዘገበዎች ያመለክታሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:41

የስደተኞች ቀን

የተባበሩት መንግስታት የስድተኞች ከፍተኛ ኮምሽን ዘገባ እንደሚያሳየዉ ኢትዮጵያ በጎርጎረስያዊያኑ 2015 ዓ,ም 739, 156 የሚሆኑ ስደተኞችን ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከኤርትራና ከሌሎች ሃገራት ተቀብላ እንደምታስተናግድ ያትታል። እንደዘገባዉ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን ስደተኞችን ለማስተናገድ ባለፈዉ ዓመት 152 ሚሊዮን ዶላርን መድቦ እየረዳ ሲሆን በዚህ ዓመት ደግሞ የመደበዉ የገንዘብ መጠን 279 ሚልዮን ዶላር መሆኑን ዘገባዉ ያመላክታአል።

በኢትዮጵያ አምስት ክልል ዉስጥ «UNHCR» 24 ቢሮዎች እንዳሉት የሚገልፀዉ በጄኔቫ የሚገኘዉ የደርጅቱ ዋና መሥርያ ቤት ቃል አቀባይ፤ ኖራ ሽቱርም ኢትዮጵያ ድንበሯን ለስድተኞቹ ክፍት ማድረጓ እና ለስድተኞች ቦታ መስጠቷ፤ ለደርጅቱ ትልቅ ርዳታ መሆኑን ገልፀዋል። ኢትዮጵያ ከቱርክ፣ ፓኪስታን፣ ሌባኖስና ኢራንን ተከትላ በዓለም አቅፍ ደረጃ ስደተኞችን በማስተናገድ እንደምትታወቅ የገለፁት የድርጅቱ ቃል አቀባይ፤ ስደተኞችን መቀበሉ ከችግር ነፃ ነዉ ማለት እንዳልሆነ ገልፀዋል።

«በኢትዮጵያ ዉስጥ «UNHCR» ም ሆነ አጋር ድርጅቶችን እየገጠመ ያለዉ ዋነኛ ፈተና ገንዘብ ነዉ። ኢትዮጵያ ድንበሩን ክፍት በማድረግ እና ከለላ መስጠቱ ከስደተኞቹ ጋር ያለዉን አብሮነት ማሳየቱ ትልቅ ምሳሌ ነዉ። ይህ አብሮነት ሌላ አገር ዉስጥ እየጨመረ ያለዉን የፀረ-ስደተኞች ወይም «ዜኖፎቢያ» እንደማይታይ ያሳያል። ለዚህም ኢትዮጵያን እናመሰግናለን። ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ርዳታ አትፈልግም ማለት አይደለም። በሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞችን ለመርዳት የዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ አንድ ላይ ሆኖ የበለጠ የገንዘብ ርዳታ ለኢትዮጵያ መንግስት ማድረግ አለበት። ከዛ ያለፈ ደግሞ ስድተኞቹ ከሚመጡበት አገር የፖለትካ መፍቴን መፈለግ ነዉ። ይህም ለመሰደድ ምክንያት የሆነዉን እና ለምን ደቡብ ሱዳናዊያን ወይም ሶማሊያኖች እንደሚሰደዱ መልስ ይሰጣል። በሌላ በኩል አገራቸዉን ጥለዉ ለሚሰደዱ ስቃይና መከራ እንዳይደርስባቸዉ ሰላም፣ መልካም አስተዳደር፣ መረጋጋትን ነዉ የምንፈልገዉ።»የኢትዮጵያን የኤኮኖሚ አቅም ግምት ዉስጥ በማስገባት፣ ይህን ያህል ስድተኞችን መቀበል የቻለችዉ እንዴት ይሆን? ለዚህም ጥያቄ ቃል አቀባይ ኖራ ሲመልሱ፤ «ኢትዮጵያ የራሷ የገንዘብ ችግር ስላለባት ብቸዋን ይህን ግዴታ ልትወጣ አትችልም ካሉ በኋላ የዓለምአቀፉ ርዳታ ለኢትዮጵያ መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል። ስድተኛን ማስተናገድ ያለዉ ተፅኖ በተመለከተ በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ስልታዊ ጥናት ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ አበበ አይነቴ በበኩላቸዉ ቀላል እንዳልሆነ እና በደህንነቱ እና በኢኮኖሚዉ ላይ ተፅዕኖ እንዳለዉ ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል።

ይህን ጉዳይ በተመለከተ አብዛኞቹ የዶቼ ቬሌ የፊስ ቡክ ተከታታዮች በሰጡት አስተያየት፤ ገሚሱ ለኢትዮጵያ ደህንነት ሲባል ስድተኛ ባታስተናግድ ይሻላል ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ አገሪቱ ደኃም ሆና ስደተኞችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗ በራሱ ይበረታታል ሲሉ አስተያየተቸዉን ሰንዝረዋል።

መርጋ ዮናስ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic