የዓለም የስደተኞች ቀንና ኢትዮጵያ | ዓለም | DW | 20.06.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የዓለም የስደተኞች ቀንና ኢትዮጵያ

እስካለፈዉ የጎርጎሪዮሳዊ ዘመን ማጠቃለያ በዓለም የስደተኞች ቁጥር 45 ሚሊዮን መድረሱን የተመ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR አስታወቀ። UNHCR ዛሬ ለሚታሰበዉ የዓለም ስደተኞችን ቀን ያወጣዉ ዘገባ በተመሳሳይ ከፍተኛ የስደተኞች ቁጥር ከዛሬ 20ዓመታት በፊትም መመዝገቡን አመልክቷል።

 ያኔ ሩዋንዳ እና የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ዉስጥ የደረሰዉ የዘር ፍጅት፤ አሁን ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄደዉ ግጭት የስደተኛዉ ቁጥር መበራከት ምክንያት መሆኑ ተገልጿል። ባለፈዉ 2012ዓ,ም ብቻም ከሰባት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ቤቱን ጥሎ ለመሰደድ መገደዱንም UNHCR ጠቅሷል። የስደተኛዉን ቁጥር ካበራከተዉ ምክንያት አንዱ ሶርያና ማሊ ዉስጥ የቀጠለዉ ግጭት እንደሆነ ገልጿል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙት ስደተኞች መካከል ከፍተኛዉን ቁጥር የያዙት የአፍጋኒስታን፣ ሶማሊያ፣ ኢራቅ፣ ሶርያ እናየሱዳን ዜጎች መሆናቸዉን UNHCR አመልክቷል። ከእነዚህ መካከልም ባለፉት 32ዓመታት አፍጋኒስታን በአንደኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በዓለም ከአራት ስደተኞች አንዱ ከአፍጋኒስታን፤ ሲሆን ብዙሃኑም ፓኪስታንና ኢራን እንደሚገኙም ተገልጿል።

Hungersnot Afrika Dossierbild 1

ኢትዮጵያ ዉስጥ ከአራት መቶ ሺህ በላይ ስደተኞች በ18 የመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ

በአዲስ አበባ የUNHCR የሕዝብ መረጃ ክፍል ኃላፊ አቶ ክሱት ገብረ እግዚአብሔር ገልጸዉልናል። ኢትዮጵያ ከምታስተናግዳቸዉ ስደተኞች ከፍተኛዉን ቁጥር የሚይዙት ደግሞ የሶማሊያ ዜጎች ናቸዉ። ከዚህ ሌላም ከ71 ሺህ በላይ ኤርትራዉያን ከ60 ሺህ በላይ ደቡብ ሱዳናዉያን እንዲሁም ከ30ሺህ በላይ የሱዳን ዜጎች ኢትዮጵያ ዉስጥ ይገኛሉ። በተጨማሪም ከአራት ሺህ የሚበልጡ የተለያዩ አገር ስደተኞችም መኖራቸዉን አቶ ክሱት አብራርተዋል። ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገዱ ሂደት የሚገጥሙ የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም አሁንም በሯን እንዳልዘጋች አቶ ክሱት ገልፀዋል።

ወደኢትዮጵያ ከሚገቡ ስደተኞች መካከል በአንድ ወቅት ከሱዳን የመጡት ወደአገራቸዉ መመለሳቸዉ መነገሩ ይታወሳል። ደቡብ ሱዳን የራሷን መንግስት ከመሠረተች ወዲህ ደግሞ በሁለቱ ሱዳኖች መካከል በተነሳዉ አለመግባባት አሁንም ዜጎች ለስደት ተዳርገዋል። ደቡብ ሱዳን ህዝበ ዉሳኔ ካካሄደች በኋላ በተነሳ ግጭትም ወደሰላሳ ሺህ የሚሆኑ ሱዳናዉያን መኖሪያ ቀያቸዉን ትተለዉ ወደኢትዮጵያ ለመሰደድ ተገደዋል። አቶ ክሱት እንደገለፁትም 99 በመቶ የሚሆኑት የመጡት ከሰሜኑ የሱዳን ክፍል በተለይ ለኢትዮጵያ ከሚቀርበዉ ብሉናይል አካባቢ ነዉ።

Dossierbild 2 Hungersnot in Somalia

በሰሜን ኢትዮጵያ ከኤርትራ በኩል በየጊዜዉ የሰደተኞች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ነዉ የሚገነገዉ። ኤርትራ መንግስት ድንበር አልፈዉ ለመሰደድ የሚወጡ ዜጎችን ተኩሶ የመግደል መርህ እንደሚከተል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይገልፃሉ። አቶ ክሱት ገ/እግዚአብሔር እንደሚሉት በተለይ በቅርቡ ከኤርትራ የሚመጡ ስደተኞች ቁጥር በመበራከቱ ተጨማሪ የስደተኞች ማቆያ ጣቢያ ለመክፈት ተገደዋል።

ስደተኞች በገቡባቸዉ ሃገሮች ሁኔታዎች ተመቻችተዉላቸዉ ከመቆየት ሌላ በUNHCR አማካኝነት ወደሶስተኛ ሃገሮችም የሚያሻግሩበት ሁኔታም አለ። ለስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ቀዳሚዉ ምርጫ ሁኔታዎች ተመቻችተዉላቸዉ ስደተኞቹ ወደመጡበት ሃገር ቢመለሱ የሚለዉ ነዉ። ያ የማይሆን ሲሆን ደግሞ በገቡበት አገር ፈቃድ አግኝተዉ ከህብረተሰቡ ተዋህደዉ ቢኖሩ የሚለዉን ያስቀድማል። ወደሶስተኛ አገር መላኩ የመጨረሻ ምርጫዉ ነዉ። አቶ ክሱት ኢትዮጵያ ዉስጥም አይብዛ እንጂ ለመቀበል ዝግጁነታቸዉን ወደሚገልፁ ሃገሮች ስደተኞቹ የማሻገሩ ተግባር መኖሩን ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን ደቡብ ሱዳን ሌላ በአሁኑ ሰዓት ከሩዋንዳና ቡሩንዲ፤ እንዲሁም ከዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ የመጡ ከአራት ሺህ በላይ ስደተኞችን እንደምታስተናግድ አቶ ክሱት ገብረእግዚአብሔር የUNHCR የሕዝባዊ መረጃ አገልግሎት ኃላፊ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic