የዓለም የሰላም መዘርዝርና ኢትዮጵያ | ኢትዮጵያ | DW | 02.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የዓለም የሰላም መዘርዝርና ኢትዮጵያ

ከዓለማችን 162 ሃገራት በሰላም ረገድ ኢትዮጵያ 139 ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አንድ መዘርዝር አመለከተ። ጎረቤት ኬንያ ደግሞ 132ኛ ናት። ይኸዉ መዘርዝር ከሽብር ስጋት አኳያ ኢራቅን በአንደኛ ደረጃ ሲያሰፍር፣ አይስላንድ በዓለም ሰላም የሰፈነባት ሀገር ብሏታል። ኢትዮጵያ ከ157 ሃገራት 37ኛ ናት።

BdT Deutschland Wissenschaft Brieftaube

መዝርዝሩን ያዘጋጀዉ የኤኮኖሚና ሰላም ተቋም በእንግሊዝኛ ምህፃሩ IEP ነዉ። ያለፈዉን የጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የሚጠቅሰዉ ይኸዉ መዘርዝር፤ አመፅና የሰላም መደፍረስ የዓለም ሃገራት ካላቸዉ ዓመታዊ ገቢ 9,8 ትሪሊየን ዶላር እንደሚያስወጣቸዉ ያመለክታል። ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ 6,8 ሚሊዮን ዶላር በየዓመቱ ታወጣለች እንደዘገባዉ። የዓለም የሰላም መዘርዝር ማለትም ግሎባል ፒስ ኢንዴክስ 22 መስፈርቶችን በመያዝ የሃገራትን የፀጥታና የመረጋጋት ሁኔታ ይመዝናል እንደድርጅቱ ተመራማሪ ቶማስ ሞርገን ገለጻ። በዋነኝነትም በየሀገሩ ካለዉ የዉስጥና የዉጭ ግጭት፣ ዜጎች ካላቸዉ የደህንነትና የፀጥታ ሁኔታ፣ እንዲሁም ሃገራት ለወታደራዊ ጉዳይ ከሚያወጡት ወጪ አኳያ ይመዘናሉ። የሀገር ዉስጥና የዉጭ መመዘኛዎች መኖራቸዉን ያመለከቱት ሞርገን በተለይ የዉስጥ መመዘኛዎች ዋና ዋናዎቹን እንዲህ ዘርዝረዋል፤

Somalia Krieg Einzug der äthiopischen Truppen in Mogadishu

«በማኅበረሰቡ ዉስጥ ያለዉ የወንጀል ደረጃ/መጠን፣ በየአንድ መቶ ሺህ ህዝብ መካከል ያለዉ የፖሊስ ብዛት፣ የሚፈፀም ግድያ ብዛት፣ በእስር ቤት የሚገኙ ሰዎች ብዛት፣ ኅብረተሰቡ ዉስጥ አነስተኛ የጦር መሣሪያዎችን በቀላሉ የማግኘት ሁኔታ እንዲሁም ሀገር ዉስጥ የተደራጀ አመፅና በዚህ ምክንያት የሚጠፋዉ የሰዉ ህይወት ብዛት፣ አመፅ የተቀላቀለበት ሰልፍ የማካሄድ ሁኔታ፣ አመፅ የታከለበት የወንጀል መጠን፣ ያልተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ይህ መንግስትና የተቃዉሞ ፖለቲካዉ ምን ያህል ደህንነቱ የተጠበቀ ነዉ፤ መንግስት በህዝብ ላይ የሚፈፅመዉ የመብት ጥሰት ሁኔታ፣ ወደሀገር የሚገባዉ የጦር መሣሪያ መጠን፣ የሽብር ተግባራት ያሉበት ደረጃ የሀገር ዉስጥን የሰላም ሁኔታ መመዘኛዎች ናቸዉ።»

የዉጭዉን በተመለከተ ደግሞ እያንዳንዱ ሀገር ከዓመት አጠቃላይ ገቢዉ ለወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚያወጣዉ ወጪ፣ ግዙፍ የጦር ኃይል የመገንባት ሁኔታ፣ ለተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የሚደረገዉ የገንዘብ አስተዋፅኦ፣ የኒኩሊየርም ሆነ የከባድ ጦር መሣሪያ የመታጠቅ አቅም፤ የጦር መሣሪያ የመሸጥ፣ ካለዉ የህዝብ ብዛት አኳያ የተሰደዱም ሆነ የተፈናቀሉ ወገኖች ቁጥር፣ እንዲሁም ከጎረቤት ሃገራት ጋ ያለ ግንኙነት፣ ከዉጭ የሚደረግ ግጭትና የጠፋ ህይወት ብዛትን ጠቅሰዋል። የዓለም የሰላም መዘርዝሩ ኢትዮጵያን ከ162 ሃገራት 139ኛ ሲያሰፍር ሀገሪቱ በእርጥም ሰላም የሰፈነባት ናት እያለ አይደለምና ከተጠቀሱት መስፈርቶች አኳያ በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት ከሚንጣት ከጎረቤት ኬንያ የሰላም ደረጃዋ ዝቅ ያለበትን ምክንያት እንዲያስረዱ ለቀረበላቸዉ ጥያቄ ቶማስ ሞርገን ይህን ብለዋል፤

«በመጀመሪያ የምለዉ በሰላምና አመፅ መካከል ልዩነት ማድረግ እንደሚኖርብን ነዉ፤ የዓለም የሰላም መዘርዝሩ ኢትዮጵያ የሰላም ደረጃቸዉ ዝቅ ካሉ ሃገራት አንዷ ናት ይበል እንጂ አመፅ እጅግ የበዛባት ሀገር ናት ማለት አይደለም። መዘርዝሩ እንደገለፅኩልሽ በ22 መስፈርቶች ላይ የተመሠረተ ነዉ ግማሹ ከቀጥተኛ አመፅ ጋ የሚገናኝ ሲሆን ገሚሱ ደግሞ ከአመፅ ስጋት ጋ ይያያዛሉ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ መንግስት ለአመፅ ከሚሰጠዉ ምላሽ ጋ ይገናኛሉ። እናም ኢትዮጵያ በቀጥታ አመፅ የበዛባት ሀገር ላትሆን ትችላለች ነገር ግን የምትገኝበት አካባቢ እንደዚያ በመሆኑ በደረጃ አወጣጡ ተፅዕኖ ይኖረዋል።»

ቶማስ ሞርገን ይህን መዘርዝር ተቋማቸዉ ሲያወጣ አመፅ የሚለዉን ፅንሰ ሃሳብ የበየነዉ በኅብረተሰቡ ዉስጥ እና በመንግስት የሚፈፀም የአመጽ ድርጊትን እንደሚያመላክት በመግለፅም፣ የአመፅ አለመኖር እንዲሁም ሊኖር ይችላል የሚል ስጋት መጥፋት ሰላማዊነት መሆኑን አስረድተዋል። በመዘርዝሩ መሠረት ኬንያ ከኢትዮጵያ የተሻለ ሰላም ያለባት ሀገር ተብላለች። እንዴት እንዳነፃፀሩት ሞርገን ያስረዳሉ፤

«ባጠቃላይ ደረጃዉን ስንመለከት በደፈናዉ ተመሳሳይ ነዉ ሊባል የሚችል ዓይነት ነዉ፤ እንደ2014 የዓለም የሰላም መዘርዝር ኬንያ በሀገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ መጠነኛ ግጭቶች ናቸዉ ያጋጠሟት፤ ኢትዮጵያ ከኬንያ ከፍ የሚል የከባድ ጦር መሣሪያ ነዉ አቅም አላት፤ አሁን ኢትዮጵያ ከተመድ የሰላም ተልዕኮ ክፍያ ግዳጅዋ ከኬንያ በመጠኑ ወደኋላ ናት፤ በመጠኑ ከፍ ያለ የፖለቲካ አለመረጋጋትም አለባት፤ ይህን ካልኩ በኋላ ኬንያ ደግሞ ከኢትዮጵያ የከፋ ነጥብ የያዘችባቸዉን እንመልከት፤ ከፍተኛ የወንጀል መጠን መኖር፣ አመፅ የተቀላቀለበት ወንጀል መጠን መብዛት፣ ሽብርተኝነት ከኢትዮጵያ ይልቅ ለኬንያ ከፍተኛ ችግር ነዉ፣ እናም ሌሎች በርካታ ነገሮች አሉ የኬንያ ሁኔታ ከኢትዮጵያ የሚከፋበት።»

ሌሎች ሶስት የሰላም ደረጃቸዉ ዝቅ ያለ ሃገራት ደቡብ ሱዳን፣ አፍጋኒስታንና ሶርያ ሲሆኑ በቀጣይ የሰላም ሁኔታቸዉ ሊያሽቆለቁል ይችላል የተባሉ ሃገራት ደግሞ፣ ዛምቢያ፣ ሃይቴ፣ አርጀንቲና፣ ቻድ፣ ቦስኒያ ሄርዞጎቭኒያ፣ ኔፖል፣ ቡሩንዲ፣ ጆርጂያ፣ ላይቤሪያና ቀጠር ናቸዉ። በተቃራኒዉ እጅግ ሰላም የሰፈነባቸዉ ሶስት ሃገራት አይስላንድ፣ ዴንማርክ እና ኦስትሪያ መሆናቸዉ ተገልጿል።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic