የዓለም የሠራተኞች ቀንና ባህላዊ ክንዉኖች በጀርመን | ባህል | DW | 07.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የዓለም የሠራተኞች ቀንና ባህላዊ ክንዉኖች በጀርመን

በዓለማችን ሃገራት የጎርጎርዮሳዊዉ ግንቦት 1 ማለት ሜይ 1 «የዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን» በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮና ታስቦ ዉሎአል። በጀርመን ሃገር ይህ ዕለት ከሠራተኛ ማኅበራት እንቅስቃሴ ሌላ ልዩ ልዩ ባህላዊ ክንዉኖችም የሚታዩበትም ነዉ። በተለይ በደቡባዊ ጀርመን «ማይ ባዉም» የተሰኘ በቀለም ያሸበረቀ ዝንጣፊ ዛፍ ቆሞ ይታያል።


የዛሬ 125 ዓመት በዚህ ዕለት በዩናይትድ ስቴትስ ቺካጎ ከተማ ላይ ሰራተኞች ደም አፋሳሽ የተቃዉሞ ሰልፍ ካካሄዱ በኋላ፤

የዓለም ሰራተኛ ማሕበራት የጎርጎርዮሳዊዉን ግንቦት 1፤ ሠራተኞች ይበልጥ መብት እንዲኖራቸዉ የሠራተኛ ደምወዝ እንዲጨምር፤ በቀን የስምንት ሰዓታት ሥራ እንዲደነገግና ህፃናት ሥራ እንዳይሰሩ ሰላማዊ ሰልፍ የሚያካሂዱበትም ሆነ። በጀርመንም የዓለም የሠራተኞች ቀን በጀርመንኛ መጠርያዉ «1. Mai » ሲከበር የሰራተኛዉ ማኅበር ሰልፍ የሚወጣበት እንዲሁም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የተለያዩ ባህላዊ ክንዉኖች የሚፈፀሙበት ዕለት ነዉ።


ባለፈዉ ሳምንት ዓርብ በተለያዩ ሃገሮች የዓለም የሰራተኞች ቀን ተከብሮ ዉሎአል። በዩናይትድ ስቴትስ ቺካጎ የዓለም የሰራተኞች ንቅናቄ ከጀመረ ከ 125 ዓመት በኋላ ዛሬ ከ 80 በላይ ሃገራት ዕለቱን ብሔራዊ የበዓል ቀን ሆኗዋል። በኢትዮጵያም የዓለም የሰራተኞች ቀን ለ 40ኛ ግዜ በብሔራዊ ደረጃ መከበሩ ተመልክቶአል። በጀርመን በተለያዩ አካባቢዎች የሰራተኛዉ ማኅበር በሰላማዊ ሰልፍና የተለያዩ የዉይይቶች መድረኮችን በመዘርጋትና በመወያየት አስቦትና አክብሮት ዉሎአል። በሌላ በኩል ቀኑ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ባህላዊ ክንዉኖች ደምቆ ነዉ የሚዉለዉ።

በርሊን ማርቸዲስ ቤንዝ ዉስጥ የሚያገለግሉትና በኤኮኖሚክስ ትምርታቸዉን በጀርመን ተከታትለዉ የዶክተሪት ማዕረግን የያዙት ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ ብዙዉን የሕይወት ዘመኔን ጀርመን በማሳለፊ ከባህላቸዉ ከአኗኗራቸዉ ብዙ ነገር ቀስምያለሁ ሲሉ ይናገራሉ። በጀርመን ስለ ሠራተኛ ቀን አከባበር
«አብዛኛዉን ኑሮዬን ያሳለፍኩት በጀርመን ነዉ። ባለቤቴም ጀርመናዊትናት ፤ እኔም ሙሉዉን የሥራ ጊዜዬን የማሳልፈዉ ከጀርመናዉያን ጋር በመሆኑ የጀርመናዉያንን ባህል አዉቄአለሁ። ሃገራቸዉም በደንብ መኖር የምችለዉ ባህላቸዉን ሳዉቅና ሳከብር ነዉ። በእነሱ አቆጣጠር ግንቦት አንድ በእኛ ሚያዝያ 23 ዕለት በፈንጠዝያ የሚያከብሩት የግንቦት በዓላቸዉ ደማቅ ነዉ። ይህ በዓል በአብዛኛዉ ሲከበር የሚታየዉም በደቡባዊ ጀርመን ነዉ። በግንቦት፤ የግንቦት 1 ሰልፍ አለ። በዚህ ቀን የተለያዩ ዝግጅቶችም ያከናዉናሉ፤ ለምሳሌ በጋራ የእግር ጉዞ ያካሂዳሉ፤ ብስክሌት ይነዳሉ ተራራ ይወጣሉ፤ ጫካ ዉስጥ ሽርሽር ይላሉ፤ ተሰብስበዉ አብረዉ ይበላሉ ይጠጣሉ። የግንቦት ዛፍ የሚባለዉ ደግቦ እያንዳንዱ አካባቢ የራሱ ዛፍ አለዉ ይህን ዛፍ በማስጌጥ በዓሉን በድምቀት ያከብሩታል።»
የጎርጎርዮሳዊዉ ግንቦት 1 ማለት ሜይ 1 ሲደርስ ጀርመናዉያን በተለይ በደቡባዊ አካባቢ አንድ ወንደላጤ ረዘም ያለ ዝንጣፊ ዛፍ ላይ ከጨርቅም ሆነ ከወረቀት የተሰራ የተለያየ ቀለም ያለዉ ሪቫን ዝንጣፊ ዛፉ ላይ በማንጠልጠልና የፍቅረኛዉን ስም በመፃፍ ሰዉ ሳያየዉ ሴቲቱ በምትኖርበት ቤት አጥር ላይ አስደግፎ ሲያቆም ይታያል። ይህ ዛፍ ታድያ የግንቦት ዛፍ ወይም በጀርመንኛ መጠርያዉ «ማይ ባዉም» ይባላል።

እንደቀልድ በጀርመን ስኖር አርባ አምስት ዓመት ሞላኝ ያለን በበርሊን ነዋሪ የሆነዉ የዶይቼ ቬለ ጋዜጠኛ ይልማ ኃይለሚካኤል የሠራተኛ ቀን በሚከበርበት ዕለት እኛ ሀገር ግንቦት አንድ ቀን ከምናከብረዉ በዓል ጋር ተዛማጅነት አለዉ ሲል ያስረዳል።
« በግንቦት ወር መጀመርያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየዉ ድግስና ፈንጠዝያ እንዲሁም የተለያዩ ሰልፎች ሁሉ ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የጀርመን ባህል ላይ የተመሰረተ ነዉ። እንደሚታወቀዉ ጀርመኖች ብዙ ፈንጠዝያና የጭፈራ በዓላት እንደሌላቸዉ ግልጽ ነዉ። በዚህ ጉዳይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሃገሮች ይበልጡዋቸዋል። ጀርመናዉያን በተፈጥሮአቸዉ ቁጥብና ጭምት ከዝያም አልፎ ብዙዉን ጊዜያቸዉንና ህይወታቸዉን የሚያሳልፉት በሥራ ነዉ። ለምሳሌ ቅዳሜና እሁድን እንኩዋ እቤቱ አርፎ የሚቀመጥ የለም። ቤቱን ግቢዉን ያፀዳል፤ ሲላቸዉም ተሰብስበዉ በደቦ ጎዳና ይጠርጋሉ፤ ቆሻሻን ያነሳሉ። ይህ ሁሉ ታድያ ከነሱ ቱፊት፤ ልማዳቸዉ ጋር የተያያዘ ነዉ። እዚህ ላይ ታድያ ሜ ይ አንድ ማለት ግንቦት አንድ አራትና አምስት ወራት የቆየዉ የጨለማዉ ጊዜ የብርድ ጊዜ አልፎ ፀሃይ ብርሃንዋን የምትፈነጥቅበት አበቦች ማበብ የሚጀምሩነት የአእዋፍት ዝማሪ የሚሰማበት ጊዜ ነዉ። እንደተፈጥሮዉ ሁሉ በዚህ ወር ጀርመናዉያን ፊታቸዉ መፍካት ይጀምራል።


በጥንት ጊዜ ከክርስትና ኃይማኖት ወደ ጀርመን ሳይገባ ግንቦት ወር ላይ አከባበሩ እንዲህ እንደነበር ታሪክ ያመላክታል ያለን ጋዜጠኛ ይልማ ኃይለሚካኤል፤ የክርስትና ሐይማኖት ከገባ በኃላ ይላል በመቀጠል፤ « ጀርመናዉያን የክርስትና ሐይማኖትን ሲተዋወቁ በተለይ በደቡባዊ ጀርመን ካቶሊካዉያኑ ግንቦት አንድን የማርያም ቀን ብለዉ ነዉ። ከኛ ከኢትዮጵያዉያን ልደታ ጋር ልናያይዘዉ እንችላለን። በዚህ ቀን የሠራተና ማኅበራት ሰልፎችን ያደርጋሉ። የ ሜይ አንድ ማለት የዓለም የሠራተኞች ቀን የሚባለዉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረዉ ቀን አመጣጡ በ 1870 ዎቹ አካባቢ አንድ የ 16 ዓመት የጀርመን ተወላጅ ወደ አሜሪካ ቺካጎ ሄዶ ኖሮዉን ጀምሮ በቀን ከአስራ ስድስት ሰዓታት በላይ ይሠራ ስለነበር ይህን እጅግ ብዙ የሆነ የሥራ ሰዓት በመቃወም በቀሰቀሰዉ ንቅናቄ ነዉ ፤ ይህ የዓለም የሰራተኞች ቀን ሊመጣ የቻለዉ ሲል ጋዜጠኛ ይልማ ኃይለሚካኤል በዝርዝር አስረድቶአል። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ
ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic