የዓለም የምግብ ፕሮግራምና የዕሕል ዋጋ መናር | ኤኮኖሚ | DW | 27.02.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም የምግብ ፕሮግራምና የዕሕል ዋጋ መናር

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ተቋም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አያሌ ረሃብተኞችን ለመርዳት የሚሰጠው አገልግሎት በተለይም በዕሕልና በነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር ሳቢያ በጣሙን እየከበደ ነው።

default

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ፕሮግራም ተቋም በያመቱ የሚቀልባቸው የድሃ ድሃ የሆኑ ተረጂዎች ዘጠና ሚሊዮን ገደማ ይጠጋሉ። እነዚሁም በስደተኛ መጠለያዎች፣ በእርስበርስ ጦርነትና በጎርፍ በተጥለቀለቁ አካባቢዎች የሚገኙ ናችው። ፕሮግራሙ የሚካሄደው ደግሞ በተለይም ከለጋሽ ሃገራት በሚቀርብ የገንዘብ መዋጮ ነው። እርግጥ የገንዘብ አቅርቦቱ ሁልጊዜ የሰመረ ነው ለማለት አይቻልም። ይሁንና በወቅቱ በፕሮግራሙ ላይ የተደቀነው ችግር በዓለም ገበዮች ላይ የዕሕልና ለትራንስፖርት የሚያስፈልገው የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከመጠን በላይ መናር ነው።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የዕህል ምርቶች ዋጋ ንረት ባለፈው ዓመት በዓለምአቀፍ ደረጃ ከግማሽ ብዙም ባለነሰ ጨምሯል። ከ 2002 ዓ.ም. ሲነጻጸው የያንዳንዱ ቶን ዕህል ዋጋ ሰባ በመቶ መናሩ ነው። ዓለምአቀፉ ፍጆትም እንዲሁ እያደገ መሄዱን ቀጥሏል። ይህም የዓለም የምግብ ፕሮግራም ተቋምን የመርዳት አቅም የሚያመነምን እየሆነ ነው። ተቋሙ በዋጋው መናር ሳቢያ ለያዝነውና ለሚቀጥለው ዓመት ያቀደውን ዕርዳታ ዕውን ለማድረግ ተጨማሪ 840 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ነው ያመለከተው። ሃብታሞቹ አገሮች ይህን ገንዘብ ካላቀረቡ ግን የተረጂዎቹን ቁጥር በሰፊው መቀነሱ ግድ ሣይሆን አልቀረም። እንግዲህ ከረሃብተኛው ሕዝብ ሲሶ የሚሆነው ከዕርዳታው እንዳይገለል፤ አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስም እንዳይከሰት ብርቱ ስጋት አለ።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በጠቅላላው ያተኮረባቸው ተረጂዎች በዓለም ዙሪያ ከ 800 ሚሊዮን በላይ ይሆናሉ። አብዛኞቹ የሚገኙትም ከሣሃራ በስተደቡብ ባለው የአፍሪቃ ክፍል ነው። የተቀሩት ደግሞ በእሢያና በከፊልም በላቲን አሜሪካ አካባቢ ይገኛሉ። የፕሮግራሙ ዒላማዎችም የጀርመኑ ቅርንጫፍ የፕሬስ ክፍል ባልደረባ ራልፍ ዙድሆፍ እንደሚሉት የምግብ ፍላጎታቸውን በራሳቸው ማረጋገጥ የማይችሉት የድሃ ድሃ የተባሉት ወገኖች ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የተጀመረው አስቸኳይ ዕርዳታ አስፈላጊ ሆኖ በታየበት በ 60ኛዎቹ ዓመታት ነበር። ጊዜው በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት አገሮች በተለይም በዩ-ኤስ.አሜሪካ የምግብ መትረፍረፍ የሰፈነበት ነበር።
እና ይህንኑ ምርት አስቸኳይ ዕርዳታ አስፈላጊ በሆነባቸውና በዚያው መግዛት በማይቻልባቸው አካባቢዎች በአግባብ የመጥቀሙ ሃሣብ ግንዛቤ ያገኛል። ጅማሮው ይህን የመሰለ ሲሆን እንደ ራልፍ ዙድሆፍ ዛሬ ግን ሁኔታው እጅጉን ነው የተቀየረው። “ዛሬ የምንገኘው አንዳች የምግብ መትረፍረፍ በሌለበትና የምግብ ምርቶች ዋጋ በሰፊው በሚንርበት ወቅት ላይ ነው። በመሆኑም አሁንም በመጨመር ላይ ያለውን የረሃብተኛ ብዛት ለመቋቋም፤ በወቅቱ ቁጥሩ ከስምንት መቶ ሚሊዮን ይበልጣል፤ የምግብ ዕርዳታ ማቅረብ አለብን። እና ከመንግሥታት በምናገነው ጥሬ ገንዘብ ምርቶቹን በተቻለ መጠን ዕርዳታውን በምንሰጥባቸው አካባቢዎች ገበዮች ላይ በመግዛት ለረሃብተኞቹ በቀጥታ ለማቅረብ ነው የምንጥረው”

ራልፍ ዙድሆፍ እንደሚያስረዱት ችግሩ በተቋማችው የራስ የገንዘብ ችግር የተነሣ የተፈጠረ ነገር አይደለም። በጀቱ የተስተካከለ፤ በሚገባ ሚዛን የጠበቀ ነው። ዕዳም ሆነ መሰል ችግር የለበትም። ችግሩ ሊረዳው የሚችለው ረሃብተኛ ቁጥር ሊቀንስ ማስጋቱ ላይ ነው። “ባለፈው ዓመት አጋማሽ ለ 2008 እና ለ 2009 የበጀትና የሥራ ዕቅድ ማውጣታችን ይታወሣል። ከዚያን ወዲህ የምግብ ምርቶች ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ አርባ ከመቶ ያህል ነው ያደገው። እንግዲህ ባቀድነው በጀት የፈለግነውን ያህል ሕዝብ መርዳቱ የሚያዳግተን ይሆናል። ለዚያውም የታቀደው ዕርዳታ ከዓለም ረሃብተኛ ጥቂቱን ቢያዳርስ ነበር”

የዕርዳታው ፍላጎት እንደ ፍጆቱና እንደ ዋጋው መናር ሁሉ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም። እና በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ከሰባ እስከ ሰባ ሶሥት ሚሊዮን ሕዝብን ለማዳረስ ያለው ዕቅድ በእርግጥም አደጋ ላይ ነው የወደቀው። ብርቱ መዘዝም ይኖረዋል። “በተወሰኑ አገሮች ውስጥ ከመንግሥታት፣ ከኩባንያዎችና ከለጋሾች ገንዘብ ካላገኝን ሕጻናትን፣ እናቶችን፣ ነፍሰ-ጡሮችን፣ የሰለቦችንና በምግብ እጥረት የተጎዱ ሰዎችን ጨርሶ ለመርዳት ከማንችልበት ሁኔታ ላይ ልንደርስ እንችላለን”

ለነገሩ የበለጸጉት መንግሥታት የልማት ዕርዳታ ከቀድሞው ሲነጻጸር ባለፉት ዓመታት እየጨመረ መሄዱ አልቀረም። ለምሳሌ ጀርመን ባለፈው ዓመት በልማት በጀቷ ላይ ከ 700 ሚሊዮን ኤውሮ በላይ አክላለች። እርግጥ ጥያቄው በዚህ ገንዘብ ምን ይደረጋል የሚል ነው። ፍላጎቱ መለያየቱ አልቀረም። “እንደኛ ልምድ ከሆነ የድንገተኛ ጊዜ ዕርዳታ፤ ከምናወጣው ገንዘብ አብዛኛው 80 በመቶው የሚውለውም ለዚሁ ነው፤ በታሙን አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ባለፈው ዓመት አፍሪቃ ውስጥ እንደ ሞዛምቢክ የጎርፍ ሰለባ የሆኑ ረሃብተኞችን ለመደገፍ፣ በዳርፉር ተፈናቃዮችን ለመርዳት ወዘተ.. ጥረት አድርገናል”

የተፈጥሮ ቁጣም እየጨመረ የሄደ ጉዳይ ሲሆን እየበረከተ የሚሄደውን ተረጂ ለማገዝ የበለጠ ገንዘብ በሥራ ላይ መዋሉ ግድ መሆኑ ሌላው ሃቅ ነው። ራልፍ ዙድሆፍ ከዚሁ ተያይዞ ተረጂዎች በራሳቸው አቅም መቆም እንዲችሉ ለማብቃት ምግብን ለልማት ግብ ማዋሉም ትልቅ ጠቀሜታ አለው ይላሉ። “በትምሕርት ቤት የቅለባ ፕሮግራም ለምሳሌ ወላጆቻቸው አቅም የሌላቸው ሕጻናት በሌላ መንገድ ሊያገኙ የማይችሉትን የትምሕርት ተሃንጾ ዕውን ማድረግ ይቻላል። የ HIV-AIDS ሕመምተኞችም ፍቱን በሆነ መንገድ እንዲታከሙ አስፈላጊውን የምግብ ዕርዳታ ማግኘት ይገባቸዋል። አለበለዚያ ሁኔታውን ሊቋቋሙት አይችሉም። እና በኛ አመለካከት ምግብና የምግብ ዕርዳታው ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ማገዝ እንዲበቁ ለማድረግ፤ ለልማትም እንዲሁ ቁልፍ ጉዳይ ነው። ይህን መሰሉ ዕርዳታ ለሌሎች ዘርፎችም ስለሚጠቅም በይበልጥ መቅረብ ይኖርበታል ባይ ነኝ”

ለማንኛውም የዓለም የምግብ ፕሮግራም የምርቱ ዋጋ አየናረ ባለበት ሁኔታ በአስካሁኑ በጀት መሥራት ከተገደደ ይህን መሰሉን ተግባር ለማራመድ መቻሉ ዘበት ነው። ውጤቱ በብዙ አገሮች ራሺንን መቀነስ፤ የዕርዳታ ተግባሩንም በሰፊው ማለዘብ ነው የሚሆነው። ከሆነ በተለይ ጋምቢያን፣ ቶጎን፣ ቤኒንና ኤርትራን የመሳሰሉ አሥር ያህል የአፍሪቃ አገሮች ብርቱ ችግር እንደሚገጥማቸው ነው የሚጠበቀው። አንዳንዶቹ ከፍተኛ የዋጋ ንረትና የዕርዳታ ጥገኝነት የሚታይባቸው ሲሆን የተደራረቡ ችግሮች የተደቀኑባቸውም ናቸው። በድህነት አቅማቸው ምግብ ከውጭ ማስገባት ይገደዳሉ። በጥቅሉ ሲታይ እነዚህ አገሮች ሲበዛ በዕርዳታው ላይ ጥገኞች መሆናቸው ብቻ ሣይሆን የተረጂውም ቁጥር እየጨመረ የሚሄድባቸው ነው።

በመሆኑም በዓለም ሕብረተሰብ የምግብ ፕሮግራም የገንዘብ እጥረት ሳቢያ የከፋ ሁኔታ እንዳይከተል መሰጋቱ አልቀረም። እርግጥ ቀውስ የመፈጠሩ አደጋ ከዕውነት የራቀ ባይሆንም ራልፍ ዙድሆፍ መፍትሄም አይታጣም ባይ ናቸው። “ወሣኙ ጥያቄ ቀውሱን ማስወገድ እንፈልጋለን ወይ ነው። ይሄው የምግብ ዋጋ ንረትን ለመግታት የሚበጁ ዕርምጃዎች መወሰዳችውን ቅድመ-ግዴታ ያደርጋል። ለዚህ ደግሞ በዓለም ላይ ታላቁ ለሆነው የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅት ብቻ ሣይሆን በአጠቃላይ ለምግብ ዕርዳታው ዘርፍና ለገጠር ልማትም ገንዘብ ማቅረቡ ግድ ነው”

የገጠሩ ልማት በእርግጥም ችላ የተባለ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ለልማት ብድር አቅራቢ የሆነው የዓለም ባንክ ለምሳሌ ይበልጡን በከተሞች ልማት ላይ አተኩሮ ነው የቆየው። ባንኩ ራሱ ከጥቂት ሣምንታት በፊት ባወጣው ዘገባ ለተሳሳተ ዓላማ ቅድሚያ ሰጥቶ መኖሩን ተቀብሎታል። 80 በመቶው የዓለም ድሃ ሕዝብ የሚኖረው በገጠር ነው። ታዲያ እዚያው ባለበት ቆይቶ እንዲረዳ፤ የገቢ ምንጭ የሚያገኝበት ሁኔታም እንዲመቻች ማድረጉን የመሰለ የተሻለ ዘዴ ሊኖር አይችልም። ለነገሩ ይህ ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ ነገርም አይደለም። “በማይክሮ ክሬዲት፤ በአነስተኛ ብድር የምርት መሣሪያ እንዲኖረው፣ በጎርፍ የተጥለቀለቀ መሬቱን መልሶ ማረስ ይችል ዘንድ የሚተክለው ዘር እንዲያገኝ ማድረጉ አይገድም። ይህ ደግሞ በችግር ወደ ከተሞች ከመጉረፍ ይልቅ ባለበት እንዲቋቋም በጣሙን የሚረዳ ነው”

በሌላ አነጋገር ገጠሬው በመነጨበት አካባቢ ብሩህ የወደፊት ተሥፋ እንዲኖረው ይበልጥ ገንዘብን በሥራ ላይ ማዋል ታላቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል። መሠረታዊው ጉዳይም የዕርዳታው ጥገኝነት በልማትና በራስ መቻል መተካቱ ነው። ይህ እንዲሆን እርግጥ ካለፉት ጊዜያት የተለየ አዲስ አመለካከት የግድ ያስፈልጋል።