የዓለም የመረጃ ኅብረተ ሰብ ጉባዔ በቱኒዝያ | የጋዜጦች አምድ | DW | 22.10.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የዓለም የመረጃ ኅብረተ ሰብ ጉባዔ በቱኒዝያ

ከኅዳር ሰባት እስከ ኅዳር ዘጠኝ ድረስ በተመድ አዘጋጅነት ቱኒዝያ ውስጥ የዓለም የመረጃ ይዞታ ጉባዔ ይካሄዳል።

ጉባዔው በሁለት ዙሮች የተከፈለ ሲሆን፡ የመጀመሪያው ዙር ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት፡ ማለትም ታኅሳስ ዓም በዠኔቭ፡ ስዊትዘርላንድ የተካሄደ ሲሆን፡ የቱኒዝያው የመጨረሻው ይሆናል። ጉባዔው ዓለም አቀፉ ኤኮኖሚ በኢንዱስትሪው ላይ አትኩሮ የነበረውን መሠረቱን በመረጃ አቅርቦቱ ላይ መለወጥ ለያዘበት ድርጊት ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ ሕግ ነክ ሀሳቦችን የማቅረብ ዓላማ ይዞ ነው የተነሣው። ይሁን እንጂ፡ ጉባዔው በተጠቃሚዎች መብት ላይ፡ መረጃ በማግኘቱ አሠራር ላይ፡ በኢንተርኔት አጠቃቀም፡ ባጠቃላይ በዓለም አቀፉ የመረጃ አቅርቦቱ መዋቅር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሮዋል። ሁለተኛው ዙር ጉባዔ በሰብዓዊ መብት ይዞታዋ ብዙ ጉድለት በሚታይባት ቱኒዝያ ውስጥ እንዲደረግ መወሰኑ የጉባዔውን ዓላማ ትርጉም እንዳያሳጣው አሳስቦዋል። በርካታ የቱኒዝያ እና ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የቱኒዝያ መንግሥት የሰብዓዊ መብትን ይረግጣል በሚል ብርቱ ወቀሳ ቢሰነዝሩም፡ መፍቀሬ መንግሥት ያካባቢ ሲቪክ ድርጅቶች ወቀሳውን ለማስተናነስ ነው የሞከሩት። ብዙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የቱኒዝያን ሰብዓዊ መብት ይዞታ የሚያጣሩ የልዑካን ቡድን ወደዚችው ሰሜን አፍሪቃዊት ሀገር መላካቸውንና በብዙ የኑሮ ዘርፎች፡ በኢንተርኔት አጠቃቀሙ ጭምር ሁኔታው ይበልጡን እየከፋ መሄዱን ማረጋገጣቸውን ከተመድ ጋር በየጊዜው የሚመካከረውና አሁን በዠኔቭ የቱኒዝያን ጉባዔ በማዘጋጀቱ ተግባር ላይ ሰፊ ተሳትፎ ያለው የመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጉባዔ ፕሬዚደንት ሬናተ ብለም አስታውቀዋል። ሰሜን አፍሪቃዊቱን ሀገር ጎብኝተው የተመለሱት ይህም ቢሆን ግን፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፡ ከ1987 ዓም ወዲህ በሥልጣን ያሉት የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ዚኔ ኤል አቢዲን ቤን አሊ ተቃዋሚዎች የሆኑት ቱኒዝያውያኑ ጭምር፡ የጉባዔው ተሳታፊዎች ከጉባዔው እንዲርቁ አይደለም የሚጠይቁት። እነርሱ እንደሚያምኑት፡ የጉባዔው መደረግ የቱኒዝያ ሕዝብ ምን ዓይነት የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንደሚደርስበት ለዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ የሚያሳውቁበትን ዕድል ይከፍትላቸዋል። ድርጅቶቹ የቱኒዝያን ሰብዓዊ መብት ይዞታ አስከፊ መሆኑን ለማሳወቅ የጀመሩት ድርጊታቸው የሚችልበት ብዙ ሀገሮች ንዑሳን ባለሥልጣናት ብቻ የሚገኙበትን የልዑካን ቡድን እንዲልኩ ይገፋፋቸው ይሆናል፤ ይህም ፕሬዚደንት ቤን አሊን ቅር ሊያሰኝ ይችላል ባዮች ናቸው። አዘጋጅው ኮሚስዮን በዠኔቭ ካለፈው መስከረም ዘጠኝ ወዲህ እስከትናንት ዕለት ባካሄደው ስብሰባው ላይ በቱኒዝያ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ላይ የዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያርፍ አድርጎዋል። የቱኒዝያው ጉባዔ ከመጀመሩ በፊትና ከተጀመረም በኋላ መገናኛ ብዙኃን ስለዚሁ ርዕስ እንዲጽፉና እንዲዘግቡ፡ ሌሎች መንግሥታትም በቱኒዝያ መንግሥት ላይ ግፊት እንዲያሳርፉ መገፋፋት እንደሚቻል በመረጃ ይዞታው የግንኙነት መብት ቡድን አባል ሾን ኦ ሲዮኹሩ እምነታቸውን ገልፀዋል። ሲዮኹሩ እንዳመለከቱት፡ በጠበቃነት ይሠሩ የነሩት ሞሀመድ አቡ በቱኒዝያ የሚፈፀመውን የሰብዓዊ መብት በደል ወንጀል የዩኤስ አሜሪካ ጦር ኃይላት በኢራቅ መዲና ባግዳድ ባለው የአቡ ግሬይብ ወህኒ ቤት እሥረኞች ላይ ከፈፀሙት ዘግናኙ የቁም ሥቅል ማሳያ ሥቃይ ጋር በማመሳሰል አንድ ዘገባ በአንድ የኢንተርኔት ድረ ገፅ በማውጣታቸው ባለፈው ሚያዝያ ወር የሦስት ዓመት ተኩል እሥራት ተበይኖባቸዋል፤ ቀደም ባለው የመጋቢት ወርም ቲዩንዚን በመባል የሚታወቀው ድረ ገፅ ዋና አዘጋጅ የሆኑት ዙሄር ያህያዊ በቱኒዝያ መንግሥት ላይ ሒስ በመሰንዘራቸው ከታሠሩ በኋላ፡ በወህኒ እያሉ በደረሰባቸው የቁም ሥቅል ሕይወታቸው ያለፈበትም ድርጊት የሀገሪቱን ነዋሪዎች እጅግ እንዳስደነገጠ ሲዩኹር አክለው አስረድተዋል። በቱኒዝያ በቀጠለው የሰብዓዊ መብት ረገጣ መደዳ፡ የሀገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን ካለፈው ጳጉሜ አራት እስከ መስከረም አንድ ድረስ ሊያካሂደው ያቀደውን ስድስተኛውን ጉባዔ እንዳይደርግ ከጥቂት ጊዚያት በፊት በአንድ የቱኒዝያ ፍርድ ቤት እንደታገደ አሥራ አራት የመናገር ነፃነት ልውውጥ ቡድኖች ተጣምረው ያቋቋሙት የቱኒዝያ ተቆጣጣሪ ድርጅት መሪ ስቲቭ በክሊ አስታውቀዋል። የቱኒዝያ የጋዜጠኞች ኅብረትም እንደ ሰብዓዊ መብት ተማጋቹ ቡድን ስብሰባ እንዳይደርግ የታገደበትንም ውሳኔ በክሊ በማውገዝ፡ በሀጊቱ የፕሬስ ነፃነት እንደታፈነ አመልክተዋል። የቱኒዝያ መንግሥት አንድ በነፃ ይሠራ የነበረ የዳኞች ቡድንን ኅልውና ለማናጋት በማሰብ ለዘብተኞቹን የቡድኑን መሪዎች በመፍቀሬ መንግሥት ዳኞች ለመተካት መሞከሩን ነው በክሊ ያስታወቁት። ለዚህም ነው ብዙዎች በወቅቱ ይህ ዓይነቱ የሰብዓዊ መብት ረገጣ የሚካሄድባት ቱኒዝያ የዓለም መረጃ ኅብረተ ሰብ ጉባዔን ለማስተናገድ መብቃትዋን የተጠራጠሩት።