1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

ቅዳሜ፣ ኅዳር 8 2016

የዓለም ዜና

https://p.dw.com/p/4Z8QT
Gaza Opfer von Luftangriffen
ምስል Ahmad Hasaballah/Getty Images

የሕዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በጋዛ የአል ሻፊ ሆስፒታል የተጠለሉ ስቪሎች፣ ሐሙማን እና የሕክምና ሰራተኞች ሆስፒታሉን ለቀው እንዲወጡ ማዘዙን

የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በጋዛ የአል ሺፋ ሆስፒታል የተጠለሉ ስቪሎች፣ ህሙማን እና የሕክምና ሰራተኞች ሆስፒታሉን ለቀው እንዲወጡ አዘዘ። የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳለው በሆስፒታሉ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በጦርነቱ የቆሰሉና ጨቅላ ህጻናት ይገኛሉ።
እስራኤል፤ ሃማስ የሆስፒታሉ የወለል ክፍል ለወታደራዊ አላማ እያዋለው ነው ስትል ትከሳለች። ሀማስ ግን ይህን ያስተባብላል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ የእስራኤል ጦር ባለፈው ረቡዕ ወደ አካባቢው ከመንቀሳቀሱ በፊት በሆስፒታሉ 2,300 የሚሆኑ ተፈናቃይ ፍልስጤማውያን፣ ሕሙማንና የሕክምና ባለሙያዎች እንደነበሩ ግምቱን አስቀምጧል።
በሆስፒታሉ ተጠልለው ከነበሩት ህሙማን ጭምር በእግርና በተሽከርካሪ ወንበር ሆስፒታሉን ለቀው መውጣት የጀመሩ ሲሆን ወደ ደቡባዊ ጋዛ ለመድረስ የመጓጓዥ ስርአት ባለመኖሩ መቸገራቸውን ታውቋል ሲል አሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል።
እስራኤል ዛሬ በጋዛ ቀደምሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትምህርት ቤት የነበረ አሁን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በሆነ ትምህርትቤት ላይ ባካሄደችው ጥቃት 19 ሕጻናት የሚገኙባቸው ቢያንስ 50 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል። በጀበሊያ የስደተኞች ጣቢያ በተፈጸመ ተመሳሳይ ጥቃትም ከ80 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።
በሌላ ዜና በዛሬው ዕለት የፕረዚደንት መሐሙድ አባስ ፓርቲ ፋታሕ አባላት የሆኑ 5 ታጣቂዎች በዮርዳኖስ የባሕር ዳርቻ በእስራኤል የአውሮፕላን ድብደባ  መገደላቸውን  የፓርቲው ምንጮች አረጋግጠዋል።
በደቡብ ጋዛ እስራኤል በመኖሪያ ሕንጻዎች ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት 26 ስቪሎች ሲገደሉ 23 ደግሞ ክፉኛ  መቁሰላቸውን የናስር ሆስፒታል ዳይሬክተር ለአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ተናግሯል።

 

የሂዝቦላህና እስራኤል የቀጠለው ግጭት

ሂዝቦላህ እና እስራኤል ሊባኖስንና እስራኤልን በሚያወስን ድንበር አካባቢ ዛሬ ሚሳይሎችና ሮኬቶች አንዱ በሌላኛው መቶኮሳቸውን የሁለቱም ወገኖች ባለስልጣናት አስታወቁ። ይህ ጥቃት ያገረሸው ዩናይትድስቴትስ ጦርነቱ ወደሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሃገሮች እንዳይዛመት ውትወታዋን በቀጠለችበት ጊዜ ነው ተብሏል።
በኢራን ይደገፋል ተብሎ የሚከሰሰው ሂዝቦላህ ዛሬ ጠዋት በድንበር አካባቢ የእስራኤል ድሮን መትቶ መጣሉን አሳውቋል። የእስራኤል ጦር በበኩሉ በአካባቢው በሂዝቦላህ የተተኩሱ ሚሳይሎችና ሮኬቶች ማምከኑን ገልጿል ሲል ሮይተርስ ዘግባል።
እስራኤል ግጭቱ ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ሊባኖስ በጣም ዘልቆ የገባ በተባለው የዛሬው የአየር ጥቃት የኢንዳስትሪ ከተማ በሆነችው ናባትያህ ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ ህንጻ መመታቱን የሊባኖስ ባለስልጣናት ገልጸዋል። አሶሽየትድ ፕረስ ቆየት ብሎ ያወጣው ዘገባ ደግሞ የእስራኤል ድሮኖች በከተማዋ የሚገኘውን የአሉሚንየም ፋብሪካን መትተዋል። ስለደረሰ ጉዳት ግን ዜናው ያለው ነገር የለም። 
ይህ በሁለቱም ወገን የተሰጠ መግለጫ ከነጻ ምንጭ ማረጋገጥ እንዳልቻለ ሮይተርስ አመልክቷል። 
የጋዛ ጦርነትን ተንተርሶ በሂዝቦላህ እና እስራኤል መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች ከ70 በላይ የሂዝቦላህ ተዋጊዎችና 10 ስቪሎች ተገድለዋል። በእስራኤል ወገን ደግሞ አብዛኛዎቹ ወታደሮች የሆኑ 10 ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርቶች ያመላክታሉ።

 

የኤርዶጋን የጀርመን ጉብኝት

የቱርክ ፕረዚደንት ረሲብ ጠይብ ኢርዶጋን የጀርመን  ጉብኝት በሰላም መጠናቀቁን  የበርሊን ፖሊስ አስታወቀ። ጉብኝቱ በተቃዋሚዎች እንዳይታጎል የበርሊን ፖሊስ ተጨማሪ 2,800 አባላቱን ማሰማራቱን ታውቋል።
ኤርዶጋን በጉብኝታቸው ከመራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስና ከፕረዚደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር ጋር ተገናኝተው በጋራ ጉዳዮችና በጋዛው ጦርነት ላይ መክሯል።
በውይይታቸው በጋዛ የሰብአዊ ረድኤት ስለሚደርስበት ሁኔታ፣ ስለስደተኞችና በቱርክ በደረሰ ርዕደ መሬት የወደሙ ተቋማት መልሶ ግንባታ መነሳታቸውን ታውቋል።
በውይይቱ የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ጀርመን ከእስረኤል ጋር እንደምትቆምና ሃማስ ያደረሰውን የሽብር ጥቃት እንደምታወግዝ በግልጽ እንደነገሯቸው ነው የተሰማው።
ኤርዶጋን በበኩላቸው ሐማስ ``የነጻነት ተዋጊ`` እንጂ ``አሸባሪ`` ነው ብለው እንደማያምኑ በአንጻሩ እስራኤል መንግስታዊ ሽብር እንደምትፈጽም መናገራቸውን የዘገበው የጀርመን ዜና አገልግሎት DPA ነው።
በሌላ ዜና የቱርኩ ፕሬዚደንት ኤርዶጋን የጀርመን ቆይታቸውን አጠናቀው ሲመለሱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በእስራኤልና ሐማስ መካከል የቶክስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ሃገራቸው በጋዛ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት አስፈላጊውን እርዳታ እንደምታደርግ ተናግሯል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።

 

በደቡባዊ ፍሊፒንስ በተነሳው ከባድ ርዕደመሬት 7 ሰዎች መሞታቸውን

በደቡባዊ ፍሊፒንስ በተነሳው ከባድ ርዕደ-መሬት 7 ሰዎች መሞታቸውን የሃገሪቱ ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት አስታወቀ። የመሬት ነውጡ በሬክተር ስኬል መለኪያ 6 ነጥብ 8 ተመዝግቧል።
በዳቮ ኦሽዴንታል ግዛት ባጋጠመው የመሬት ነውጥ 2 ሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ሌሎች 2 ደግሞ ደብዛቸው አልተገኘም።
የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ቃል አቀባይ ኢድጋር ፖሳድስ ለጀርመን ዜና አገልግሎት DPA እንዳሉት አብዛኛውቹ የተጎዱት በፍርስራሾች ተመትተው ነው። በአደጋው 60 መኖሪያና ሌሎች 32 ሕንጻዎች መውደማቸውን ዜናው አክሏል። 

መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ፑቲን ሰላም ለማምጣት ቀዳሚ እርማጃ እንዲወስዱ ጠየቁ

የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ፤ በሩስያና ዩክሬይን ያለው ጦርነት ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት ፕረዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ቀዳሚ እርማጃ እንዲወስዱ ጠየቁ። ሾልስ በሁለቱም ሃገራት ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ ሩስያ ወታደሮቿን ከዩክሬይን ማስወጣት አለባት ነው ያሉት።
መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ከጀርመን ግዙፍ ግዛቶች አንዷ በሆነችው ብራንደንቡርግ ዛሬ ባደረጉት ጉብኝት በጋዜጠኞች ስለሩስያና ዩክሬይን የሰላም ድርድር ተጠይቀው በሩስያ በኩል ይህ አዝማሚያ አይታይም ብለዋል።
ፑቲን ጎረቤት ሃገራትን በሃይል የመጠቅለል አላማቸው አልተሳካም ያሉት ሾልስ፤ አገራቸው ለዩክሬይን የምታደርገው ወታደራዊ ድጋፍ የፈለገው ጊዜ ይውሰድ ትቀጥልበታለች ማለታቸውን የዘገበው ሮይተርስ ነው።

በስደተኞች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃት

በፓናማና ኮሎምቢያ ድንበር አቋርጠው ወደ አሜሪካ በሚሰደዱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ላይ ጾታዊ ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን አስታወቀ። እንደ ቡድኑ ሪፖርት  በዘንድሮው ዓመት ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ስደተኞች ቁጥር ወደ 400 ይጠጋል።
ከደቡብ አሜሪካ በሜክሲኮ በኩል ወደ ዩናይትድስቴትስ የሚሸጋገሩበት 260 ኪሎሜትር በሚረዝመው ጫካ ውስጥ በስደተኞቹ ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት በተለይ ከአለፈው ጥቅምት ወር በኋላ በአስደንጋጭ ሁኔታ መጨመሩን ነው የተነገረው።
የፓናማ ባለስልጣናት እንዳሉት እስከ አለፈው መስከረም ወር ድረስ ከ400,000 በላይ ስደተኞች  በዚህ አደገኛ ጫካ አቋርጠው ያለፉ ሲሆን፤ ከስደተኞቹ መካከል የቬንዙዌላ፣ ኢኳዶር፣ሃይቲ፣ቻይና፣ ካሜሩንና ቡርኪናፋሶ ዜጎች እንደሚገኙባቸው የዘገበው አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ነው።YG/EB