የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ | ስፖርት | DW | 06.07.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ

19ኛው የዓለም አግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ቀስ በቀስ ወደ መገባደጃው እየተቃረበ ሲሆን ከሁለቱ የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያዎች የመጀመሪያው ዛሬ ማምሻውን ኬፕ-ታውን ውስጥ ይካሄዳል።

default

ዲየጎ ፎርላን

ተጋጣሚዎቹ የሁለት ጊዜዋ የዓለም ዋንጫ ባለቤት ኡሩጉዋይና እስካሁን ለዚህ ክብር ከመቃረብ አልፋ አንዴም ያልበቃችው ኔዘርላንድ ናቸው። ኔዘርላንድ በሩብ ፍጻሜው ብራዚልን ካሽነፈች ወዲህ ወደፊት በመዝለቅ የዋንጫ ባለቤት ልትሆን እንደምትችል በብዙዎች ሲታመን ኡሩጉዋይ ደግሞ መናቋ ምናልባት ሊጠቅማት ይችል ይሆናል። ለማንኛውም ጨዋታው ትግል የተመላበት እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው።

በደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ ውድድር ያለፈው ሣምንት ሁሌም እንደተለመደው በአንድ በኩል ብዙ እንባ የፈሰሰበት በሌላም ፈንጠዝያ የታየበት ነበር። ታላላቁ የላቲን አሜሪካ የእግር ኳስ ተጠሪዎች ብራዚልና አርጄንቲና ገና በሩብ ፍጻሜው ባልተጠበቀ ሁኔታ ስንብት ሲያደርጉ ጋና ደግሞ በአፍሪቃ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለግማሽ ፍጻሜው ለመድረስ ያገኘችውን ዕድል ዕጅ የገባ ከመሰለ በኋላ መልሳ አጥታዋለች። በአንጻሩ ጀርመን፣ ስፓኝና ኔዘርላንድ ለግማሽ ፍጻሜ መድረሳቸው በነዚህ አገሮች ሕዝብን በአደባባይ አስፈንድቋል።
የአፍሪቃን ዕጣ ካነሣን ጋና በዛሬው ምሽት የግማሽ ፍጻሜ ተሳታፊ በኡሩጉዋይ ከተጨማሪ ጊዜ በኋላ በፍጹም ቅጣት ምት በለየለት ግጥሚያ 5-3 ስትረታ አሳሞዋህ ጂያን ቀደም ሲል በ 120ኛዋ ደቂቃ ላይ የሳታት ፍጹም ቅጣት ምት የመላውን ,አፍሪቃ ሕልም ቅዠት ነው ያደረገችው። የሆነው ሆኖ ለጋና የስንብት የሆነው ግጥሚያ ለኡሩጉዋይ ደግሞ ከአያሌ ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው የግማሽ ፍጻሜ ትንሣዔ መሆኑ ነው። ከዚህ አንጻር ኡሩጉዋይ ከአሁኑ ከጠበቀችው በላይ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሳለች የሚሉት ታዛቢዎች ብዙዎች ናቸው። ኔዘርላንድ በምሽቱ ግጥሚያ አሸንፋ ወደ ፍጻሜው እንደምታልፍ ከሚያምኑት የስፖርት ታዛቢዎች መካከል የዶቼ ቬለ ባልደረባ አርኑልፍ በትቸርም አንዱ ነው።

“ኔዘርላንድ ታሸንፋለች። የተሻለ ቡድንና የባየርን ሙንሺኑን ኮከብ አርየን ሮበንን መሰል ግሩም ተጫዋቾች ስላሏት ጨዋታውን መቆጣጠሩ የሚከብዳት አይሆንም። የኔዘርላንድ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫው ወድድር ሂደት እስካሁን ሁሉንም ግጥሚያዎቹን ነው ያሸነፈው። እርግጥ ቡድኑ በሁሉም ግጥሚያዎች አሸብርቆ አልታየም። ግን ዛሬ ይህን እንደሚያደርግና ከጀርመን ጋር ለፍጻሜ እንደሚደርስ ነው የምጠብቀው”

እርግጥ በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን የአትሌቲኮ ማድርድ ኮከብ የሆነው ግሩም አጥቂ ያላት የላቲን አሜሪካ ብቸኛ ተጠሪ ኡሩጉዋይም ተዓምር ልትሰራ የማትችልበት ምክንያትም አይኖርም። ኡሩጉዋይ 80 ዓመታት ባስቆጠረው የዓለም ዋንጫ ውድድር የመጀመሪያውን እ.ጎ.አ. በ 1930 በአስተናጋጅነት፤ እንዲሁም ሁለተኛውን በ 1950 ብራዚል ውስጥ ከብራዚል ነጥቃ ስታገኝ አሁን ለሶሥተኛ ድል በመብቃት ከኢጣሊያና ከጀርመን የመስተካከል ታላቅ ፍላጎት እንደሚያድርባት የሚጠበቅ ነው። ይሁንና የዶቼ ቬለ የስፖርት ፕሮግራም ባልደረባ አርኑልፍ በትቸር ኡሩጉዋይ ጨርሶ አታሸንፍም ይላል።

“አይመስለኝም። ኡሩጉዋይ ከላቲን አሜሪካ የቀረችው 3,5 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት ትንሿ ተወዳዳሪ አገር ናት። እርግጥ በውድድሩ ገና አለች። ሆኖም ቡድኑ ወደፊት የመዝለቅ ብቃት አለው ብዬ አላምንም። የአውሮፓው ሊጋ ዋንጫ ባለቤት የሆነው የአትሌቲኮ ማድሪዱ ኮከብ ዲየጎ ፎርላን እርግጥ ድንቅ ተጫዋች ነው። ግን በዛሬው ምሽት ለማሸነፍ አንድ ዲየጎ ፎርላን ብቻውን የሚበቃ አይሆንም”

የኔዘርላንድ የቆየ ድክመትስ? ምናልባት ይህ የኡሩዎች ዕድል ሊሆን አይችልም? የኔዘርላንድ ብሄራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫን በመሰለ ተከታታይ ግጥሚያዎች በሚካሄድባቸው ውድድሮች ከዚህ ቀደም ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ቋሚ ጥንካሬና ጽናት አለማሳየቱ አሁንም ካለ ለኡሩጉዋይ የተሥፋ ምንጭ የሚሆን ነው። የእስካሁኑ ልምድ ካልተወገደ የኔዘርላንድ ብሄራዊ ቡድን ከብራዚል ጋር ያሳየውን ታላቅ ጨዋታ መድገሙ በጣሙን የሚያጠራጥር ነው የሚሆነው። በሌላ በኩል የዶቼ ቬለ ባልደረባ አርኑልፍ በትቸር እንደሚለው ቡድኑ ካለፈው ተምሮ ከሆነ በዕውነትም በጥሩ አቅጣጫ እየተራመደ ነው።

“የኔዘርላንድ ተጫዋቾች አሁን ሲመለከቷቸው ከልምዳቸው የተማሩ ነው የሚመስለው። ይህን ስህተት ሁሌም ሲሰሩ እንደነበር፤ ጥሩ ከተጫወቱ በኋላ ድክመት ማሳየታቸውን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ግን አሁን እንደ ጀርመን ሁሉ በቡድንነት ተጠናክረዋል። አንዱ ለሌላው የሚታገል ነው። በጣም ይተባበራሉ። እናም ኡሩጉዋይን እንደሚያሸንፉ ግልጽ ነው። የማስበው ዛሬ እንዲያውም በዓለም ዋንጫው ውድድር የእስካሁን ሂደት ካደረጉት የበለጠ ግሩም ጨዋታ እንደሚያሳዩ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ብቃቱም አላቸው”

እርግጥ የኳስ ምሥጢር የረቀቀ እንደመሆኑ መጠን በተለይም ከብራዚልና ከአርጄንቲና ያልተጠበቀ አወጣጥ በኋላ የጨዋታውን ውጤት እንዲህ ብሎ መደምደሙ ጥቂትም ቢሆን የሚያዳግት ነው። ስለዚህም በዛሬው ምሽት ልክ ሶሥት ሰዓት ተኩል ላይ የሚጀምረው ግጥሚያ እስከሚያበቃ መጠበቁ ይመረጣል።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ