የዓለም ኤኮኖሚ ይዞታና አዝማሚያው | ኤኮኖሚ | DW | 04.02.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ኤኮኖሚ ይዞታና አዝማሚያው

የዓለም ኤኮኖሚ ሁኔታ የፊናንሱ ቀውስ ካስከተለው መዘዝ በቀላሉ ወይም በቅርብ መላቀቁ አሁንም አጠያያቂ ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው።

የዓለም ኤኮኖሚ ይዞታ

የዓለም ኤኮኖሚ ይዞታ

ዓለምአቀፉ ኤኮኖሚ ዛሬም በማቆልቆል ሂደቱ እንደቀጠለ ሲሆን በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በቻይና ሳይቀር የሥራ አጡን ቁጥር እያበራከተ በመሄድ ላይ ይገኛል። ቢቀር በበለጸገው ዓለም የያዝነው 2009 ዓ,ም. ቀላል ዓመት እንደማይሆን የሚገምቱት የምጣኔ-ሐብት ጠበብት ብዙዎች ናቸው። ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቁዋም ራሱ የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት ትንበያውን ባለፈው ሣምንት ለሁለተኛ ጊዜ ዝቅ በማድረግ ማረሙ ግድ ሆኖበታል።

ባለፈው ዓመት በአሜሪካ የተቀሰቀሰው የፊናንስ ቀውስ የዓለምን ኤኮኖሚ ማናጋት ከጀመረ ወዲህ ችግሩን ለመጋተር በበለጸገው ዓለም በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ነው የፈሰሰው። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ መንግሥታት በፊናንሱ ዓለም ዓመኔታን መልሶ ለማስፈን፤ ስርዓቱንም ግልጽና ለቁጥጥር የሚያመች አድርጎ ለመጠገን ባለፈው ታሕሣስ ወር ዋሺንግተን ላይ የመጀመሪያውን የዓለም የፊናንስ ጉባዔ አካሂደዋል። እነዚሁ ቡድን-20 መንግሥታት የተለያዩት ከሶሥት ወራት በኋላ በሚከተል ቀጣይ ጉባዔ ጭብጥ ደምቦችን ቅርጽ ለማስያዝ በመስማማት ነበር።

ይሁንና በፊናንሱ ገበዮች ላይ ከሁሉም በላይ የሚፈለገው ዓመኔታና የገንዘቡም ፍሰት ሂደት የሚገባውን ያህል ተሻሽሏል ለማለት አይቻልም። የቀውሱ መዘዝ ከተጠበቀው ወይም ከታሰበው በላይ ሥር እየሰደደ ሲሄድ የዓለም ኤኮኖሚ በማገገም ፈንታ በማቆልቆል ሂደት እየቀጠለ ነው የሚገኘው።፡ በዩ.ኤስ.አሜሪካ አጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት ሲቀንስ በአንጻሩ የሥራ አጡ ቁጥር መጨመሩን ቀጥሏል። ብሄራዊው ምርት ባለፈው ዓመት የመጨረሻ ሩብ 3,8 ከመቶ ሲያቆለቁል ይህም ከ 27 ዓመታት ገደማ ወዲህ ጠንካራው መሆኑ ነው።

ለትውስት ያህል የአሜሪካ ኤኮኖሚ የማቆልቆል ጉዞ የጀመረው በታሕሣስ 2007 ዓ.ም. ነበር። በቤት ባለቤቶች ብድርን መልሶ መክፈል አለመቻል ችግር የተነሣ በተከታዩ ዓመት በፊናንስ ገበዮች ላይ ውዥቀትና ውድቀት ይከተላል። ሌህማን ብራዘርስን የመሳሰሉት ታላላቅ የመዋዕለ-ነዋይ ባንኮች በሕዳርና ታሕሣስ ወራት በተከታታይ ክስረት ላይ ይወድቃሉ። ብዙዎቹን ከተመሳሳይ ውድቀት ለመሰወር የተቻለው በመንግሥት የገንዘብ ድጎማ ነበር። ግን ይህም ሆኖ ክስረት የፈጠረው የዓመኔታ እጦት በብድር አቅርቦት ረገድ ታላቅ ድክመትን ነው ያስከተለው። ውጤቱ የተጠቃሚው ሕዝብ ፍጆት መቀነስና ኩባንያዎች በሥራ ላይ የሚያውሉት መዋዕለ-ነዋይ እያነሰ መሄድ ነው የሆነው። የቨርጂኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ታይለር ኮወን እንደሚሉት የኩባንያዎቹ ቁጥብነት ቀውሱ የረጅም ጊዜ ተጽዕኖ ይኖረዋል ከሚል ግንዛቤም የመነጨ ነው።

“በርካታ ኩባንያዎች ብዙ ገንዘብ እንዲኖራቸው ሲሉ የራሳቸውን ካፒታል ከፍ ለማድረግ ይፈልጋሉ። ምክንያቱም ብዙዎቹ የሚያስቡት ቀውሱ ቢያንስ አምሥት ዓመታት ያህል ይዘልቃል ብለው ነው”

ይህ ሂደት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ሥራ አጥ እንዲሆኑ አድርጓል፤ ማድረጉንም እንደቀጠለ ነው። አዲሱ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ በ 819 ቢሊዮን ዶላር በጀት የአገሪቱን ኤኮኖሚ መልሶ በማነቃቃትና ከሶሥት እስከ አራት ሚሊዮን የሥራ መስኮችን በመክፈት ችግሩን ለማረቅ ቆርጠው ተነስተዋል።

“የኤኮኖሚው ቀውስ ለአሜሪካውያን ቤተሰቦች የለየለት ውድቀት ነው። በዚህ ረገድ የሚቀርበው አሃዝ አስከፊ ሲሆን ይበልጥ ዋናው ነገር ደግሞ በነርሱ ላይ ያለው ተጽዕኖ ይሆናል። ይህ በጣም አስከፊ ጉዳይ ነው”

የዋሺንግተን መስተዳድር ዕቅድ የተፈለገውን ፍሬ መስጠቱ ውሎ አድሮ የሚታይ ይሆናል። በሌላ በኩል በብሄራዊ የኤኮኖሚ ፈውስ ላይ ያተኮረው ማገገሚያ ዕቅድ አሜሪካ የውጩን የንግድ ድርሻ እንዳትገድብ በአውሮፓ ስጋት ማሳደሩ አልቀረም። ሰሞኑን ከዚህ ከአውሮፓ ኦባማ በዚህ ገዳቢ ይዘት ባለው ፖሊሲ ከገፉበት ዓለምን የመምራት ሚናቸውን ያጣሉ የሚል ትችት ሲሰነዘር ተሰምቷል። ሁኔታው ዓለምአቀፉን የፊናንስ ስርዓት ለመጠገን በሚደረገው ጥረት የበለጸጉትን መንግሥታት ትብብር አደጋ ላይ እንዳይጥል በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ማሳሰቡ አይቀርም።

ወደ ፊናንሱ ቀውስ መለስ እንበልና በዚሁ የተከተለው የኤኮኖሚ ችግር አውሮፓንና ቻይናን የመሰለች ባለፈው አሠርተ-ዓመት በተፋጠነ ዕድገት ስትራመድ የቆየች አገርም መፈታተኑን ቀጥሏል። በፊናንሱ ቀውስ የተነሣ ቻይና ውስጥ እስካሁን ቀያቸውን ለቀው በየኢንዱስትሪ ማዕከላቱ ይሰሩ የነበሩ ሃያ ሚሊዮን ተዘዋዋሪ ሰዎች ሥራቸውን አጥተዋል። ከአሜሪካና ከአውሮፓ በሚታዘዘው ምርት ማቆልቆል የተዘጉት ወይም የምርት ተግባራቸው ጋብ ማድረግ የተገደዱት ፋብሪካዎች ብዙዎች ናቸው። ለነዚህ ከጠቅላላው 15 ከመቶ ለሚሆኑት ሠራተኞችና በየመንደሩ ላሉ ቤተሰቦቻቸው በቅርቡ በተያዘው አዲስ ዓመት ሁኔታው ተሥፋ አስቆራጭ እየሆነ መሄዱ ነው የሚነገረው።

“ሁኔታው እንደቀድሞው አይደለም። በዘልማድ ወደ ሌሎች ስፍራዎች ሄዶ ከሚሠራው ሙያተኛ ለአዲስ ዓመት በዓል ወደቤቱ የሚሄደው ሲሦው ቢሆን ነበር። በዚህ ዓመት ግን 90 በመቶ ደርሷል። እርግጥ ብዙዎቹ ልጆቻቸውን ስለሚያዩ ደስ ቢሰኙም በሌላ በኩል ግን በወደፊቱ ዕጣቸው ተሥፋ መቁረጣቸው አልቀረም። ተጽዕኖው እጅግ ከፍተኛ ነው”

በአውሮፓም የሥራ ገበያው ሁኔታ እምብዛም የተለየ አይደለም። በዚህ በጀርመን ለምሳሌ ባለፈው ጥር ወር የሥራ አጡ ብዛት ሶሥት ወራት ቀደም ሲል ከነበረበት ሶሥት ሚሊዮን ወደ 3,5 ሚሊዮን ከፍ ብሏል። ይህ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው ሲነጻጸር በ 170 ሺህ ዝቅ ያለ ቢሆንም ፍጥነቱ ብርቱ ለሆነ ስጋት መንስዔ የሚሆን ነው። የጀርመን ኤኮኖሚ በተለይ በውጭ ንግድ ላይ ጥገኛ በመሆኑም አሁን ለያዝነው ዓመት ሂደት ከሚቀርበው የኤኮኖሚ ዕድገት ግምት አንጻር ሁኔታው መሻሻሉን አጠያያቂ ያደርገዋል።

የኤኮኖሚ ዕድገትን ካነሣን ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቁዋም IMF ለያዝነው የጎርጎሮሣውያኑ 2009 ዓ.ም. አድርጎት የነበረውን ትንበያ ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ለሁለተኛ ጊዜ ዝቅ አድርጎ ማስቀመጡ ግድ ሆኖበታል። በአጠቃላይ የዋሺንግተኑ ድርጅት የምርምር ዘርፍ ዋና ሃላፊ ኦሊቪየር ብላንቻርድ የምንገምተው የዓለም ኤኮኖሚ ባለበት ቀጥ እንዳለ እንደሚቆይ ነው ብለዋል።

እንደገንዘብ ድርጅቱ ከሆነ የዓለም ኤኮኖሚ በዚህ ዓመት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ከባድ የሆነ ማቆልቆል የሚታይበት ነው የሚሆነው። ከአሜሪካ በተነሣው የፊናንስ ቀወስ ሳቢያ በዓለምአቀፍ ደረጃ የ 2,2 ቢሊዮን ዶላር ኪሣራ እንደሚከተል ይጠበቃል። እርግጥ የፊናንሱ ቀውስ ዓለምን በሙሉ እኩል አይደለም የመታው። ቀውሱ በከፋበት በኢንዱስትሪው ዓለም የኤኮኖሚው ዕርምጃ ሁለት ከመቶ እንደሚቆረቁዝ ሲተነበይ በአውሮፓ እንዲያውም ለጀርመን የቀረበው ግምት ከአሜሪካ የባሰ ነው።

እንግዲህ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ከጦርነቱ ወዲህ ዝቅተኛው ወደሆነው መስፈርት ሲንሸራተቱ ታዳጊዎቹና በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት አገሮች በዚህ ለዓለም ኤኮኖሚ ከባድ በሆነ ዓመት ቢቀር 3,3 በመቶ ዕድገት ሊጠብቁ ይችላሉ። እርግጥ ይህ ባለፉት ዓመታት የልማት ዕርምጃ ለመቀጠል በቂ ዕድገት አይሆንም። ለምሳሌ አፍሪቃ በፊናንሱ ቀውስ አኳያ በተሻለ ሁኔታ ላይ ብትገኝም ከኢንዱስትሪው ዓለም ሲነጻጸር ችግሩን ለመጋተር ግን ደከም ባለ ይዞታ ላይ መሆኗን ነው የምንዛሪው ተቁዋም የምርምር ዘርፍ ምክትል ሃላፊ ቻርልስ ኮሊንስ ያስገነዘቡት።

“የአፍሪቃ አገሮች በኢንዱስትሪ ልማት እንደበለጸጉትና በተፋጠነ ዕድገት ላይ እንዳሉት ሃገራት ሰፊ የማነቃቂያ በጀት ለማውጣት በቂ አቅም የላቸውም። በዝቅተኛ ዕድገት ደረጃ ላይ በሚገኘው የካፒታል ገበያና ደካማ በሆነው የፊናንስ ፖሊስ ስርዓት የተነሣ አፍሪቃውያን መንግሥታት የፊናንስ በጀት ከመቁረታቸው በፊት ጉዳዩን በጥንቃቄ ማጤን ይኖርባቸዋል”

ኮሊንስ ጨምረው እንዳስረዱት ብዙዎች የአፍሪቃ አገሮች በላቲን አሜሪካና በእሢያ በከፊል በታየው መጠን እንኳ ለሕዝባቸው የፊናንስ ድጋፍ ለመስጠት ስለማይችሉ የሚከተለው የድህነት ይብስ መስፋፋት ነው። በሌላ በኩል በምንዛሪው ተቁዋም ግምት የፊናንሱን ቀውስ በተሻለ ሁኔታ ሊወጡት ከሚችሉት አገሮች አንዷ ቻይና ናት። ሕዝባዊት ቻይና በዚህ ዓመት 6,7 ከመቶ የኤኮኖሚ ዕድገት እንደምታደርግ ይተነብያል። ለዚሁ እንደ ምክንያት የተጠቀሰው የአገሪቱ ጠንካራ የፊናንስና የምንዛሪ ፖሊሲ እንዲሁም በማደግ የቀጠለው የምርት ፍጆት ነው። ለነገሩ በአሁኑ የፊናንስ ቀውስ ወቅት በቻይና የሚጠበቀው የኤኮኖሚ ዕድገት ከሌሎች ሲነጻጸር ምናልባት ጠንከር ብሎ ይታይ እንጂ በአገሪቱ ባለፉት ዓመታት ከተለመደው አሥር በመቶና ከዚያም በላይ ዕድገት ሲነጻጸር ከፍተኛ ማቆልቆል ነው።

“የቻይና የኤኮኖሚ ዕድገት ራሱ ከሁለት ዓመታት በፊት ከነበረው በጣሙን ዝቅ ያለ ነው የሚሆነው። ያኔ ገና 13 ከመቶ ይሆን ነበር። እና ዕድገቱ በሁለት ዓመት ውስጥ በግማሽ ማቆልቆሉ ከባድ ዝግታ ነው”

ለማንኛውም የምንዛሪው ተቁዋም የዓለም ኤኮኖሚ በተከታዩ 2010 ዓ.ም. በመጠኑም ቢሆን ሊያገግም እንደሚችል ያምናል። እርግጥ ሁለት ቅድመ-ሁኔታዎች ከተሟሉ! እነዚህም በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚወሰዱት የፊናንስ ፖሊሲ ዕርምጃዎች ፍቱን መሆናቸውና መስፋፋታቸው፤ እንዲሁም የአሜሪካ የቤት ገበያ መልሶ መረጋጋት ናቸው።

እዚህ ላይ ዓለምአቀፉን የፊናንስ ስርዓት ለመጠገን በተያዘው ጥረት በቂ ለውጥ ለማስፈን መቻሉና ታዳጊው ዓለምም ከአጥር ባሻገር ተመልካች ብቻ ሆኖ እንዳይቀር የሚያደርግ ተሃድሶ መስፈኑ ወሣኝ ነው። ጥረቱ በበለጸገው ዓለም ውስጣዊ ችግሮች ላይ ብቻ ከተወሰነ አጽናፋዊ ትስስር በሰፈነበት የዓለም ኤኮኖሚ ላይ መፍትሄ ይገኛል ማለቱ ዘበት ነው የሚሆነው። እርግጥ የፊናንሰ ቀውሱ ችግር የተቀሰቀሰው በምዕራቡ ዓለም ነው። ይሁንና ታዳጊው ዓለም ለችግሩ ተጠያቂነት ባይኖርበትም የችግሩ ሰለባ መሆኑ ግን አልቀረለትም።
የፊናንሱ ቀውስ ዓለምን በሙሉ እንደየሁኔታው አዳርሷል። ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ስርዓት ለውጥን ከሚጠይቅበት ደረጃ የደረሰ ጉዳይ ነው። በቅርቡ ብራዚል ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የዓለም ማሕበራዊ መድረክ ጉባዔ ላይ የተሳተፉት የጀርመን ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን የልማት ተግባር ባልደረባ ዩርገን ራይሽል እንዳሉት ዛሬ የሰውልጅ የሚገኘው በፊናንስ ሣይሆን በአጠቃላይ የሥልጣኔ ቀውስ ውስጥ ነው።

MM ,NM