የዓለም ኤኮኖሚ፣ የዋጋ ንረትና ተጽዕኖው | ኤኮኖሚ | DW | 07.05.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ኤኮኖሚ፣ የዋጋ ንረትና ተጽዕኖው

የምርቶች ዋጋ በተፋጠነ ሁኔታ እየናረ መሄድ በወቅቱ በዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት ላይ ብርቱ ፈተናን ደቅኖ የሚገኝ ጉዳይ ነው። የምግብ ምርቶች ዋጋ በአራትና በአምሥት ዕጅ ሲጨምር የነዳጅ ዘይትም ሰሞኑን እንደገና ወደ ላይ ተተኩሷል። በወቅቱ የአንድ በርሚል ጥሬ ዘይት ዋጋ 121 ዶላር ገደማ ሲጠጋ ይህም በመሠረታዊ ምርቶች ዋጋ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ቀላል የሚሆን አይመስልም።

default

የዓለም ኤኮኖሚ በአጠቃላይ ሲታይ በያዝነው ዓመትም ቀደም ያሉትን ጊዜያት ያህል አይሁን እንጂ ዕድገት እንደሚያሳይ የምዕራቡ ዓለም የምጣኔ-ሐብት ጠበብት ዕምነት ነው። ቢሆንም የምርቶች ዋጋ መናር ሂደቱን ጨርሶ አስተማማኝ አያደርገውም። የዓለም ኤኮኖሚ ብርቱ ፈተና ተደቅኖበት ነው የሚገኘው። የምግብ ዋጋ ከመጠን በላይ እየናረ መሄድ አያሌ ሕዝብን ለከፋ ረሃብ ባጋለጠበት ወቅት የነዳጅ ዘይት ዋጋ እንደገና በበርሚል ወደ 121 ዶላር ማሻቀቡ ደግሞ የኑሮ ውድነትን ይብስ እያጠነከረ እንዳይሄድ በጣሙን ያሰጋል።

ለሰሞኑ የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር የአሜሪካ ኤኮኖሚ ከገጠመው ችግር አለማገገም፣ በናይጄሪያ ዓመጽ ያስከተለው የምርቱ አቅርቦት መቀነስና የፖለቲካ ምክንያቶችም ይጠቀሳሉ። የጀርመን የምጣኔ-ሐብት ምርምር ተቋም ባልደረባ ክላውዲያ ኬምፈርት እንደሚሉት ትርፍ አጋባሾችም በዋጋው ንረት ላይ የሚያደርጉት ተጽዕኖ ራሱን የቻለ ድርሻ አለው። “የወቅቱ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ንረት መከተል ምክንያት በመጀመሪያ ደረጃ የዶላር በጣም መዳከም ነው። ከዚሁ ሌላ በገበያ ላይ የተፈጠረውን ውዥንብር በመጠቀም ዋጋውን ወደላይ ለመስቀል ጥረት ይደረጋል። ሆኖም የማስበው የነዳጁ ዋጋ ለጊዜው በወቅቱ ደረጃ ጸንቶ እንደሚቆይ ነው። እንደገና በማደግ መቀጠሉን መናገሩ ግን ያዳግታል”

ለማንኛውም የነዳጅ ዋጋ ዕድገት ከእጥረቱና ከፍጆቱ መጨመር የተነሣ በፍጥነት እየጨመረ እንደሚሄድ የሚያምኑት ታዛቢዎች ብዙዎች ናቸው። ምናልባት እስከ ዓመቱ መጨረሻ በበርሚል ከሁለት መቶ ዶላር ጣራ ላይ ሊደርስ ይችል ይሆናል። ለስጋት መንስዔ የሚሆኑ ተጨባጭ የፖለቲካ ምክንያቶችም እንዲሁ ተፈልገው አይታጡም። ለምሳሌ ምዕራባውያኑ ተጠቃሚ ወይም ገዥ መንግሥታት ነዳጅ ዘይት አምራች በሆኑት አገሮች ማሕበር በኦፔክ ውስጥ ሁለተኛዋ ታላቅ አምራች የሆነችው ኢራን ሃብቷን የፖለቲካ ግፊት መሣሪያ አድርጋ እንዳትጠቀምበት መስጋታቸው አልቀረም።

በነዳጅ ዘይት አምራች አገሮች ዘንድ ምርቱን በሰፊ በማውጣት የዋጋውን ንረት ለማለዘብ ለሚደረገው ዓለምአቀፍ ጥሪ አሁንም የሃሣብ እንድነት የለም። ኩዌይት ድርጅቱ በነዳጅ ዘይት ዋጋ ላይ በፊታችን መስከረም ከመደበኛው ጉባዔ የቀደመ ልዩ ስብሰባ እንደሚጠራና ምናልባትም ምርቱን በማሳደጉ ሃሣብ ሊነጋገር እንደሚችል ጠቁማለች። ሊቢያ በሌላ በኩል ኦፔክ ተጨማሪ ነዳጅ ሊያወጣ አይችልም ባይ ናት። ለነገሩ የኦፔክ አገሮች ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ጉባዔዎች ምርቱን ከፍ በማድረጉ ጉዳይ በተደጋጋሚ ቢነጋገሩም ተገቢውን ዕርምጃ ሲወስዱ አልታየም። አጠቃላዩ ሁኔታ የተፈራው የዋጋ ንረት የማይቀር መሆኑን የሚያመክት ነው።

የነዳጅ ዘይት መወደድ የትራንስፖርትና የምርት ተግባር ወጪን በመጨመር በወቅቱ የተፈጠረውን የምግብ ቀውስም ይበልጥ ሊያባብስ የሚችል ነው። የምግብ ዋጋ መናር ዛሬ በዓለም ዙሪያ ያስከተለው ችግር በቀላሉ የሚገመት አይደለም። የሕዝብ ቁጥር እየናረ ሲሄድ የዓለም የእህል ክምችት በአንጻሩ ከ 80ኛዎቹ ዓመታት ወዲህ እጅግ በጣም ነው ያቆለቆለው። የምግብ ዋጋ መናር በቅርቡ ከካሜሩን እስከ ቦርኪና ፋሶ፤ ከሜክሢኮ እስከ ሃኢቲ በየቦታው ዓመጽን ሲቀሰቅስ፤ በጠቅላላው ከሰላሣ የሚበልጡ አገሮች በሕዝብ ቁጣና ብሶት ተወጥረው ነው የሚገኙት። የሃብታምና የድሃው ልዩነት ይበልጥ እየጨመረ፤ በድህነት ላይ የባሰ ድህነት እየታከለ በመሄድ ላይ ነው።

ችግሩ እንደቀድሞው በደቡቡ የዓለም ክፍል ብቻ የተወሰነ አይደለም። እርግጥ ድህነት በሰሜንና በደቡብ አንጻራዊ ትርጉም ቢኖረውም ዛሬ በበለጸጉት መንግሥታት ዘንድ ሣይቀር ለወትሮው የከፋ ችግር የማያው ቀው መካከለኛው የሕብረተሰብ መደብም በኑሮ ውድነትና በሥራ አጥነት መብዛት የተነሣ ለድህነት አደጋ እየተጋለጠ መሄድ ይዟል። ለምሳሌ በዚህ በጀርመን በኑርንበርግ ዩኒቨርሲቲ የድህነት ጉዳይ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ጌርሃርድ ትራበርት እንደሚሉት መዘዙ የከፋ ሊሆን የሚችል ነው።

“መካከለኛው መደብ እየጠፋ መሄዱ፤ ብዙ ሰዎች አስተማማኝ ከነበረ የኑሮ ሁኔታቸው እየወጡ የገቢ ድህነት ላይ ሊወድቁ መቻላቸው ያለ ክስተት ነው። በሕብረተሰባችን ውስጥ ልጅ መውለድ ራሱ የድህነት አደጋን የሚደቅን ሆኖ መገኘቱ እጅግ ያሳፍራል። ለምሳሌ ለብቻቸው ሕጻናትን ከሚያሳድጉ ወላጆች ከሶሥት አንዱ፤ እነዚህም በአብዛኛው ሴቶች ናቸው፤ ለድህነት የተጋለጡ መሆናችውን እናውቃለን። ሶሥትና ከሶሥት በላይ ልጆች ያለው ቤተሰብም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ገና ከአሁኑ በሕብረተሰባችን ውስጥ በድህነት የሚኖሩት ሕጻናት ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን በልጧል”

በበለጸጉት አገሮች ሰፊው ፍጆተኛ የሆነው መካከለኛ መደብ እያነሰ መሄዱ በረጅም ጊዜ በኤኮኖሚው ዕድገት ላይ ብርቱ መሰናክል የሚፈጥር ነው የሚሆነው። በማሕበራዊው ኖሮ ላይም ጎጂ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ይህ የበለጸገው ዓለም ገጽታ ሲሆን በታዳጊው ዓለም ደግሞ የድህነት ገጽታ ይበልጡን የከፋ ነው። በእፍኝ በሚቆጠሩ ሃብታሞችና በብዙሃኑ ድሆች መካከል የፍጆት አቅም ያለው ሰፊ መካከለኛ መደብ የለም፤ አይታወቅም። አንድ ሚሊያርድ ሕዝብ፤ ከሁለት ዶላር በታች የዕለት ገቢ የሚተዳደረውን ሰፋ አድርገን ከወሰድን ደግሞ 2,5 ሚሊያርድ ሕዝብ ከድህነት መስፈርት በታች የሚኖር ነው።

የወቅቱን የምግብ ዋጋ መናር ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ደግሞ ይሄው አሃዝ ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል። የዓለም የምግብ ተቋም ባልደረባ ራልፍ ዙድሆፍ እንደሚሉት ችግሩ ማሕበራዊ ነውጽን ሊያስከትል የሚችል ነው። “የሚያስፈራው በተለይ ለአደጋው በተጋለጡት ከሰላሣ የሚበልጡ አገሮች አስቸኳይ ዕርዳታ ለማቅረብ ካልቻልን ሰፊ ማሕበራዊ ዓመጽ እንዳይከሰት ነው። እነዚህ ሁሉ ሰዎች ቀደም ባለው ጊዜ ከገቢያቸው ሶሥት-አራተኛውን ያህል ድርሻ ለምግብ ማውጣት ነበረባቸው። ዛሬ ደግሞ ምርቱ ከበፊቱ በእጥፍ ተወዷል። እና ተቃውሞንና ሰፊ ማሕበራዊ ዓመጽን ሊያቀጣጥል ይችላል። ለእኛም የደህንነት ችግርን የሚፈጥር ጉዳይ ነው”

መፍትሄው ምንድነው? በዋሺንግተን የዓለም የእርሻና የምግብ ፖሊሲ ኢንስቲቲቱት ሃላፊ ዮሃኢም-ፎን-ብራውን እንደሚሉት ዓለም የወቅቱን ችግር ለመቋቋም አቅድ ያለው ነገር የያዘ አይመስልም። “ቀውሱን ለማስወገድ በሚገባ የተቀናበረ ዕርምጃ መኖሩ ገና አይታየኝም። ምክንያቱም በብዙዎች ዘንድ ችግሩን በጥቂት አስችኳይ ዕርዳታ መቆጣጠር ይቻላል የሚለው አስተሳሰብ ጽኑ ይመስለኛል። ነገር ግን ችግሩን ለመቋቋም ሰፊ በጀት አስፈላጊ ነው። በተለይ በታዳጊ አገሮች የገጠር አካባቢዎች የእርሻ ልማትን ለማሳደግ”
በወቅቱ አንዱ መፍትሄ የምግብ ፍጆት በሰፊው በጨመረበት በዛሬው ጊዜ 400 ሚሊዮን የሚሆነው የዓለም አነስተኛ ገበሬ በተሻለ ሁኔታ አርሶ ተጠቃሚ እንዲሆን በዘመናዊ ቴክኒክ ላይ የተመሠረተ የእርሻ ልማትን ማራመድ ነው። ተገቢውን የመሬት ስሪት በማካሄድ አርሶ-አደሩ የርስት ባለቤት እንዲሆንና ለገበያ ተጠቃሚነት እንዲበቃ ማድረጉም ወሣኝነት ይኖረዋል። የመንግሥታት እስረኛ የሆነ ገበሬ እንኳንስ የሕብረተሰብን የምግብ ዋስትና ሊያረጋግጥ ቀርቶ ራሱን ለመቀለብ እንኳ የሚበቃ አይሆንም። ከዚህ በተጨማሪ በዓለምአቀፍ ደረጃ ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት ገሃድ መሆኑም ይበልጥ ወቅታዊ ነው።

ዛሬ የምግብ ዋጋ መናር በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብን ለባሰ ረሃብ አጋልጦ የሚገኝባትን አፍሪቃን ከተመለከትን ድህነትን በማለዘቡ ረገድ አንዱ ብርቱ መሰናክል ይሄው አርሶ-አደሩ የሚገኝበት አሳዛኝ ሁኔታ ነው። የአፍሪቃ ገዢዎች አንቀው ይዘውታል፤ የበለጸጉት መንግሥታትም ከራስ ጥቅማቸው አልፈው ሲራመዱ አይታይም። መሪሩ ሃቅ ይህ ሲሆን በሌላ በኩልም የወቅቱ የምግብ ዋጋ ንረት መዘዝ በታዳጊው ዓለም ተወስኖ የሚቀር እንደማይሆን ግልጽ ነው። ስለዚህም መፍትሄውን በጋራ መሻቱ አማራጭ የሌለው ተግባር ነው የሚሆነው። አለበለዚያ የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት ለዘለቄታው አስተማማኝ ሆኖ ሊቀጥል አይችልም።ተዛማጅ ዘገባዎች