የዓለም ኤኮኖሚ በአዲሱ ዓመት ወዴት? | ኤኮኖሚ | DW | 05.01.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ኤኮኖሚ በአዲሱ ዓመት ወዴት?

ዓመት አልፎ ዓመት በተተካ ቁጥር ያለፈውን መለስ ብሎ ማጤኑና በወደፊቱ ላይም ማተኮሩ የተለመደ ነው። የዓለም ኤኮኖሚ ባለፈው 2010 ዓ.ም. ከዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ማገገሙን ቀጥሎ ቢታይም ከፈተናው ግን ጨርሶ አልተላቀቀም።

default

አውሮፓ ውስጥ ባለፈው ዓመት ያልተጠበቀ ግሩም ዕድገት በማሣየት የኤኮኖሚውን ቀውስ በመቋቋሙ ረገድ ከማንኛውም አገር ይልቅ ለአርአያነት የበቃችው ጀርመን ብቻ ነበረች። በዩ.ኤስ.አሜሪካ በሌህማን ብራዘርስ ባንክ ክስረት በተከተለው የፊናንስ ቀውስ ሳቢያ የአክሢዮኑን ገበዮች የከዳው ዓመኔታ ቀስ በቀስ ሲመለስ ለተሥፋ ምንጭ እየሆነም ሄዷል። ዓለምአቀፉን የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ከሁሉም በላይ በሚገባ ለመቋቋም የቻለችው እርግጥ ሕዝባዊት ቻይና ናት። የአገሪቱ በራስ መተማመን ከኤኮኖሚዋ በፈጠነ ሁኔታ ማደጉ ነው ዛሬ የሚነገርለት። የዓለም ኤኮኖሚ በአዲሱ ዓመት ወዴት? ምላሽ ለመስጠት እንሞክራለን።

በአንድ አዲስ ዓመት መግቢያ ዋዜማና መጀመሪያ ላይ የኤኮኖሚን ሂደት ለማወቅ የተለየ ፍላጎት መኖሩ የሚታወቅ ነገር ነው። ጊዜው የባለሙያዎችና የምርምር ተቋማት ትንበያ ይበዛበታል። በአሁኑ ጊዜ ከያቅጣጫው የተሰነዘሩትንና የሚሰነዘሩትን ትንበያዎች ጎን ለጎን አስቀምጠን ብናጤን በኢንዱስትሪ ልማት ከበለጸጉት አገሮች መካከል በተለይ የጀርመን ዕርምጃ ከሁሉም ይልቅ ተሥፋን የሚያጠናክር ነው። እርግጥ የጀርመንንም ሆነ የመሰል ሃገራትን ዕርምጃ ቀጣይነት ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ አድርጎ መናገሩ ገና ብዙ ያዳግታል።

ይህ ባለፈው ዓመት በትንበያቸው ትክክልነት አድናቆትን አትርፈው የነበሩት የጀርመን ታላቅ መድህን ድርጅት የአሊያንስ የምጣኔ-ሐብት ባለሙያ የሚሻኤል ሃይዘም አመለካከት ነው። ሃይዘ ዓለምአቀፉን ቀውስ በጊዜው ስር ሰደድ ሳይሆን በሌህማን ብራዘርስ ባንክ ክስረት የደረሰ ጊዜያዊ ምታት እንደሆነ አድርገው ሲተረጉሙ ከዚሁ አያይዘው በመጨረሻ እንደሚወገድም ነበር የተነበዩት። ባለሙያው ታዲያ ባለፈው ዓመት በፋይናንሺያል-ታይምስ ጋዜጣ የጀርመን ቅርንጫፍ የትንበያ ንጉስ እስከመባል ቢደርሱም ሁሌም ትክክለኛ መሆን እንደማይቻል ማስጠንቀቃቸው አልቀረም።

“ለማስጠንቀቅ የምፈልገው ሰባት የጥጋብ ዓመታት እንደሚከተሉ ከመናገር መቆጠብ እንዲኖር ነው። በተለይ ደግሞ ይህ ከአንድ ወይም ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ድረስ ሰባት የችግር ዓመታት ከተነበዩት ወገኖች አፍ መውጣቱ ያስገርመኛል። በአንዴ ሁሉም ነገር ሊለወጥ አይችልም። ስለዚህም ጥንቃቄ እንዲኖር ነው የምመክረው”

Symbolbild Weltwirtschaft

በመሆኑም ሃይዘ የአዲሱን ዓመት የጀርመን ዕድገት ከባለተሥፋዎቹ አንዱ ቢሆኑም ጥንቃቄ በተመላበት መልክ ነው ያቀረቡት። የኤኮኖሚው ባለሙያ በአዲሱ ዓመት 2,6 ከመቶ ዕድገት ሊደረግ እንደሚችል ያምናሉ። የጀርመን መንግሥት በበኩሉ 1,8 በመቶ ዕድገት የሚጠብቅ ሲሆን የአሠሪዎቹ ማሕበር ፕሬዚደንት ዲተር ሁንድት ይህንኑ ወደ 2 ከመቶ ይጠቀልሉታል። ሃይዘ እርግጥ በዕድገቱ ላይ ከሁሉም የበለጠ ዕምነት ቢጥሉም በሌላ በኩል አደጋ መኖሩንም አላጡትም።

“የኤውሮ ምንዛሪ ቀውስ ገና አለመወገድ የማቆልቆል አደጋ መኖሩን የሚያሳይ ነው። ገና ከባድ ጊዜን ማሳለፍ ይኖርብናል። ዶላር የተረጋጋ ሆኖ ይቀጥል ወይም ያቆልቁል፤ በምንዛሪው ልውውጥ ረገድም በአሜሪካና በቻይና መካከል የሰፈነው ውጥረት ይርገብ አይርገብ ገና ማሰሪያ ያላገኘ ጉዳይ ነው። ከዚሁ ሌላ የጥሬ ዕቃዎች የዋጋ መናር ተሥፋችንን ከንቱ ሊያደርገው ይችላል”

ሃይዘን ከዶላር ማቆልቆልና ከጥሬው ዕቃ ዋጋ መናር የበለጠም የሚያሳስባቸው የኤውሮ ቀውስ አሁንም መፍትሄ አለማግኘትና አውሮፓ በፊናንስ ገበዮች አንጻር በአንድ ድምጽ ለመናገር ከምትችልበት ደረጃ ላይ አለመድረሷ ነው።

ወደ ጀርመን እንመለስና በወቅቱ የሚታየው የኤኮኖሚ ዕድገት ለወትሮው ተጠራጣሪነትንና ቁጥብነትን የሚመርጡትን የአገሪቱን ፖለተኞች ጭምር እያስፈነደቀ ነው። ጀርመን ከዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ለመላቀቅ በተያዘው ዕርምጃ በአውሮፓ የመንኮራኩርነቱን ሚና ይዛለች። ከበለጸጉት ቀደምት መንግሥት መካከል አንዱም በወቅቱ እንደ ጀርመን በስኬት ጎዳና ላይ አይገኝም።

ለጀርመን የኤኮኖሚ ዕድገት በተለይም ዋነኛው መሠረት የውጩ ንግድ ማበብ ነው። ግን ይህ ወደፊት ባለበት መቀጠል ይችላል ወይ? በተለይም የጀርመን ኩባንያዎች ደምበኞች በሆኑት ጎረቤት የአውሮፓ አገሮች ችግር ለዕድገቱ መሰናክል ቢሆንስ? የአገሪቱ ባለሙያዎች ይህን መሰሉ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ማስጠንቀቃቸው አልቀረም። እና በዚሁ የተነሣም ባለፉት ወራት የአገር ውስጡን ገበያ ፍላጎትና ፍጆት ለማጠናከር ብዙ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ለጊዜው የሥራ አጡ ቁጥር እየቀነሰና ፍጆቱም እያደገ በመሄዱ ጥረቱ የተሣካ እየመሰለ ነው።

በሌላ በኩል የጋራው ምንዛሪ ኤውሮ ይዞታ ምን ያህል አስተማማኝ ነው? የበጀት ችግር የገጠማቸው ዓባል ሃገራት ቢከስሩስ ምን ይከተላል? እነዚህ ባለፈው ዓመት በተደጋጋሚ ይነሱ የነበሩና በአዲሱም ዓመት መነሣት የቀጠሉ ቁልፍ ጥያቄዎች ናቸው። የአውሮፓ ሕብረት ባለፈው ዓመት ሂደት ግሪክንና አየርላንድን ከውድቀት ለማዳን በገንዘብ በመደገፍ ዕርምጃ ወስዷል። ፖርቱጋል፣ ስፓኛኝና ኢጣሊያም በተመሳሳይ ችግር ላይ የሚገኙ ሲሆን በአዲሱ ዓመት ተጨማሪ አገሮች እየከሰሩ ይሂዱ አይሂዱ ከወዲሁ እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር አይቻልም። ሆኖም አደጋው እንዳለ ነው የሚቀጥለው።

በአውሮፓ ይሄው የማዳኑ ተግባር ፍቱንነት ለአጠቃላዩ ዕድገት ምናልባትም ወሣኝ ቅድመ-ግዴታ ሲሆን በሌላ በኩል በአሜሪካ የፊናንሱ ገበዮች የሌህማን ብራዘርስ ባንክ ክስረት ቀውስ ካስከተለ ከሁለት ዓመታት በኋላ ቀስ በቀስ ዓመኔታ እያገኙ በመሄድ ላይ ናቸው። ይህ ደግሞ አላን ቫልዴስን በመሳሰሉት የዎል-ስትሪት የፊናንስ ገበያ ነጋዴዎች ዘንድ ተሥፋን ማዳበሩ አልቀረም።

“ለአዲሱ 2011 ዓ.ም. ተሥፋዬ በጣም ከፍተኛ ነው። ዓመቱ ታላቅ እንኳ ባይሆን ጥሩ ዓመት እንደሚሆን አምናለሁ። አቅጣጫው ትክክለኛ ለመሆኑ ግን ከወዲሁ ምንም ጥርጣሬ የለኝም”

የፊናንሱ ገበያ ሁኔታ ማገገሙ ሲነገርለት በሌላ በኩል ቀውሱ በመንግሥትና በፌደራል ክፍለ-ሐገራት ደረጃ ያስከተው የዕዳ ችግር ግን አሜሪካዊቱ የፊናንስ ባለሙያ ሜሬዲት ዊትኒይ እንደሚሉት በጣሙን ነው ችላ የተባለው። ይህም አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

“በዕዳው ጉዳዩ መንግሥት የሚያሳየው ግድየለሽነት በጣም የሚያስደነግጥ ነው። ይሄው አሜሪካ ውስጥ ከቤቶች ገበያ ጋር ሁለተኛው ከባድ ችግር ሲሆን ለኤኮኖሚያችንም ታላቁ አደጋ መሆኑ መዘንጋት የለበትም”

አሜሪካ ውስጥ ቀውሱ ከጀመረ ወዲህ ከገቢው ይልቅ በግማሽ ቢሊዮን ዶላር የበለጠ ገንዘብ በወጪነት ፈሷል። ለምሳሌ ካሊፎርኒያ እንኳ ዛሬ የ 19 ሚሊያርድ ዶላር ኪሣራ ተደቅኖባት ነው የምትገኘው። ችግሩ በሌሎች ፌደራል ክፍለ-ሐገራትም ይንጸባረቃል። የአሜሪካ ፌደራል ክፍለ-ሐገራት በጠቅላላው ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ዕዳ ተጭኗቸው ነው የሚገኙት። ባለፈው ዓመት ለፊናንሱ ገበዮች ማበብ ምክንያቱ እነዚሁ በአብዛኛው ከዋሺንግተን የገንዘብ ዕርዳታ ማግኘታቸው ነበር። አሁን ግን በአዲሱ ዓመት ኤኮኖሚውን ወደፊት ለማራመድ የመንግሥቱ ካዝና ባዶ ነው። እናም ችግሩን ለማቃለል የአሜሪካ ኢንዱስትሪዎች መዋዕለ-ነዋይ ማድረጋቸው ግድ ይሆናል።

የፊናንሱ ቀውስ በበለጸገው ዓለም ላይ ከባድ ተጽዕኖ ሲያደርግ ችግሩን ከአውሮፓና ከአሜሪካ ይልቅ በቀላሉ ለመቋቋም የቻለችው እርግጥ ቻይና ናት። ሁኔታው በቻይና የኤኮኖሚ ጠበብት መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለየ መፈክር እንዲስፋፋ ነው ያደረገው። “ከቻይና ኤኮኖሚ ይበልጥ ፈጥኖ የሚያድግ ነገር ቢኖር የቻይናውያን በራስ መተማመን ብቻ ነው” ይላሉ የአገሪቱ ጠበብት። ለዚህ ስሜት ደግሞ ብዙ ስኬቶች አስተዋጽኦ አላቸው።

ከብዙ በጥቂቱ ቻይና ከመንፈቅ በፊት በዓለም ላይ እስካሁን ታላቁን ኤክስፖ ሻንግሃይ ላይ ለማዘጋጀት ችላለች። ትዕይንቱን 78 ሚሊዮን ሕዝብ ሲጎበኘው ይህም ራሱን የቻለ አዲስ ክብረ-ወሰን ነበር። ቻይና ዛሬ በዓለም ላይ የታላቁ የፈጣን ባቡር ሃዲድ መረብ ባለቤትም ናት። በዓለም ላይ ፈጣኑን ባቡርም ራሷ ትሰራለች። ከዚሁ ሌላ በሰሜናዊው ቻይና የሚገኘውን ቲያንሄ የተሰኘ ኮምፒዩተር ያህል በፍጥነት የሚያሰላ ሌላ የለም። በአጠቃላይ በዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ የቻይና ተጽዕኖ፤ የምፍትሄ ድርሻም እንዲሁ ይበልጡን ነው የጨመረው።

የአገሪቱ ኤኮኖሚ በያመቱ በዘጠኝ ከመቶ ገደማ የሚያድግ ሲሆን የውጭ ምንዛሪ ክምቿቷም ግዙፍ እየሆነ ነው የመጣው። ቻይና ከዚህ አንጻር በአዲሱም ዓመት ከፊናንሱ ቀውስ ጨርሶ ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት ጠቃሚ ድርሻ እንደሚኖራት አንድና ሁለት የለውም። እርግጥ አዲሱ ዓመት ካለፈው የተሻለ ሆኖ ይገኝ አይገኝ ቢቀር መጪዎቹን ጥቂት ወራት ጠብቆ መታዘቡ ግድ ይሆናል።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ