የዓለም ኤኮኖሚ በአዲሱ አሠርተ-ዓመት | ኤኮኖሚ | DW | 06.01.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ኤኮኖሚ በአዲሱ አሠርተ-ዓመት

ያለፈው 2009 ዓ.ም. ዓለም በኤኮኖሚ ቀውስ ክፉኛ ተወጥሮ ውጣ-ውረድ ሲል የታየበት ነበር። የምጣኔ-ሐብት ጠበብት ትንበያውም ከመቼውም ይልቅ ሁለት-ወጥ ሆኖ ሲያሻማና ሲያከራክር መቆየቱን ታዝበናል። ጉዞው ወዴት ነው?

default

አሁን ስድሥተኛ ቀኑን በያዘው አዲስ ዘመን እርግጥ ባለፉት ወራት የታየው የማገገም አዝማሚያ ሥር እየሰደደ እንደሚሄድ በሰፊው ቢታመንም የሚቀጥሉት ዓመታት አዳዲስ ፈተናዎችን መደቀናቸው እንደማይቀር የሚናገሩት ጠበብት ብዙዎች ናቸው። ዓለም በአዲሱ አሠርተ-ዓመት የዕድገት አቅጣጫን ይዞ ለመዝለቅ ይችል ይሆን? ሁለት የኤኮኖሚ ጠበብት በአንድ ላይ ባሉበት ስፍራ ሁሉ ሁለት ወይም ሶሥት አመለካከት ይፈጠራል። ይህን ያሉት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዘመን የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርቺል ነበሩ። እርግጥም ዕውነት አላቸው። ያለፈው 2009 ዓ.ም. አጉልቶ ያሳየው ይህንኑ ሃቅ ነበር። በዚህ በጀርመን እንኳ መለስ ብለን ብናስታውስ ሁለት ቀደምት የኤኮኖሚ ምርምር ተቋማት በጥቂት ወራት ቢለያይም ያቀረቡት ትንበያ የሰማይንና የምድርን ያህል የተራራቀ ነበር የሆነው። አንዱ ፕሮፌሰር ኡዶ ሉድቪግ ባለፈው ዓመት መግቢያ ዋዜማ የበልግ ወራት የአገሪቱ ኤኮኖሚ ከቀውሱ አገግሞ ጥቂትም ቢሆን እንደሚያድግ ይተነብያሉ።

“የወቅቱ ሁኔታ በጥቅሉ የሚያሳየው አጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት የ 0,2 ከመቶ ዕድገት እንደሚያደርግ ነው”

በአንጻሩ የሚዩኒኩ ኢፎ ኢንስቲቲቱት ባልደረባ ካይ ካርስተንስ ደግሞ በሚያዚያ ወር ላይ ተሥፋን የሚያጨልም የተለየ ትንበያን ይዘው ይቀርባሉ።

“አጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት በ 2009 ዓ.ም. ከወዲሁ ቀድሞ እንደሚታየው ከሆነ በስድሥት ከመቶ ያቆለቁላል”

እርግጥ ይህ በዓመቱ መጨረሻ ከመጀመሪያው ትንበያ ይልቅ ለሃቁ የቀረበ ሆኖ ነው የተገኘው። የሆነው ሆኖ ግማሽ ዓመት በሚሆን ጊዜ ውስጥ በቀደምቱ ጠበብት መካከል ይህን መሰሉ የግምት ልዩነት መከሰቱ ብዙ ማስገረሙ አይቀርም። የጀርመን ጠበብት በዓመቱ ባደረጉት ትንበያ ብዙ የተራራቀ ግምት ያልታየበት ነገር የሥራ አጡ ቁጥር ነበር። ካለፈው ዓመት ሂደት የተገኘ አንድ ግንዛቤ ካለ ዘግየት ብሎ የቀረበው ትንበያ ቀደም ካለው ለትክክለኛነት የቀረበ መሆኑ ነው። የምርምር ተቋማቱ ሁሉም በአንድ አገር፤ ማለትም በጀርመን ኤኮኖሚ ላይ ያተኩሩ እንጂ በተሰባሰበው መረጃ ላይ ተመስርቶ በተቻለ መጠን ትክክለኛ ግምት ለመስጠት የሚጠቀሙበት የስሌት ዘዴና መንገድ ግን የተለያየ መሆኑ ታይቷል። እናም የጀርመን የምጣኔ-ሐብት ምርምር ኢንስቲቲዩት ሃላፊ ክላውስ ሲመርማን እንደሚሉት ጭብጥ ትንበያ ማድረጉ በጣሙን ከባድ ነው።

“ይህ ለኛ ብቻ ሣይሆን ለሁሉም የምርምር ተቋማት ከባድ ነገር ነው። ነገሩ የመስኩ ወይም የሣይንስ ችግር አይደለም። ይልቁንም አርቆ መተንበዩን አዳጋች ያደረገው የኤኮኖሚው ባህርይ አስቸጋሪነት ነው”

ለማንኛውም ተመራማሪዎች ለያዝነው አዲስ ዓመት የሚያቀርቡት ግምት ወይም ትንበያ ተሥፋ ሰጭ አዝማሚያን አጠናክሯል። በከፊል ከባድ ከነበረው የ 2009 ቀውስ በኋላ እንደገና የኤኮኖሚ ማንሰራራት ነው የሚጠበቀው። ሂደቱ እንዴት እንደሚቀጥል እርግጥ አሁንም በትክክል መናገሩ ያዳግታል። ምናልባት ከወዲሁ አንድ እርግጠኛ ነገር ቢኖር የኤኮኖሚው ቀውስ ለጊዜው ባለበት መቀጠሉ ነው። በኮሎኝ ከተማ ተቀማጭ የሆነው የጀርመን ኤኮኖሚ ኢንስቲቲዩት አስተዳዳሪ ሚሻኤል ሁተር በበኩላቸው ቀውሱ ቢያንስ ለሁለት ዓመት ያህል እንደሚቀጥል ያምናሉ። የኤኮኖሚው ባለሙያ የቀውሱ ሂደት በወቅቱ መገታቱን ሲናገሩ አያይዘው እንደሚሉት ከዚሁ ጨርሶ ለመላቀቅ ግን መንገዱ ረጅምና ያለማቋረጥ አደጋ የተደቀነበት መሆኑ የማይቀር ነው።

ይህ የሁተር የብቻ አስተያየት አይደለም። የኢፎ ኢንስቲቲዩት ፕሬዚደንት ሃንስ-ቨርነር-ዚን የጀርመንን ኤኮኖሚ አስመልክተው ሲናገሩ ከአፋፍ ላይ ቁልቁል ወድቀን መሬት ላይ ተጋድመናል፤ አሁን ለመነሣት በዳዴ ላይ ነን ሲሉ ነው መንግሥት ኤኮኖሚውን መልሶ ለማነቃቃት ገና ብዙ ማድረግ እንዳለበት ያስገነዘቡት። እርግጥ ይህ ቀላል ነገር አይደለም። በአንድ በኩል መንግሥት የበለጠ ግብር በማስገባትና ወጪውን በመቀነስ የበጀት ኪሣራውን እንዲያለዝብ የሚጠይቁ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ዕድገት ለማምጣትና የሥራ አጦችን ቁጥር ለመቀነስ መንግሥት በመጀመሪያ ግብርን ቢቀንስና ዘግየት ብሎ የበለጠ ግብር ቢጠይቅ ይሻላል የሚሉም አልታጡም። መቼ ምን ይደረግ፤ ትክክኛውን ጊዜ ለመምረጥ በጣም የሚያስቸግር የተወሳሰበ ጉዳይ ነው።

ለምሳሌ የጀርመን መንግሥት ባለፈው በልግ የምርጫ ወቅት በተገባው ቃል መሠረት ለያዝነው አዲስ ዓመት የግብር ቅነሣ ማድረጉ የሠርቶ-አደሩን ሕዝብ ሸክም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በማቃለል ረገድ ጥሩ ዕርምጃ ሆኖ ታይቷል። በአንጻሩ በፌደራል ክፍለ-ሐገራት በጀት ላይ ግን ከባድ ችግርን ነው ያስከተለው። ዕርምጃው በተገቢው ሰዓት የተወሰደ ትክከለኛ ነገር ይሁን-አይሁን እያደር የሚታይ ነው። የጀርመንን ኤኮኖሚ ይዞታ ጠለቅ ብለን ከተመለከትን በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ የክስረት አደጋ ላይ የወደቁ ባንኮችን ለማዳን፣ ኤኮኖሚውን መልሶ ለማነቃቃትና ኩባንያዎቻቸው የምርት ተግባራቸውን የቀነሱ ሠራተኞችን ለመደጎም የፈሰሰው በብዙ ሚሊያርድ የሚቆጠር ገንዘብ የመንግሥቱን ኪሣራ በስድሥት ዕጅ አሳድጓል። ማዕከላዊው መንግሥት፣ ፌደራሉ ክፍለ-ሐገራትና ከተሞች ያፈሰሱት ወጪ ከማሕበራዊው ዋስትና ጋር ተደምሮ ባለፈው መስከረም ከገቢያቸው በላይ በ 97 ሚሊያርድ ኤውሮ የሚበልጥ ነው። ለንጽጽር ያህል አንድ ዓመት ቀደም ሲል የበጀቱ ኪሣራ በ 17 ሚሊያርድ የተወሰነ ነበር።

Weltwirtschaft Symbolfoto

መጪው ጊዜም ቀላል የሚሆን አይመስልም። የመንግሥቱ የበጀት ኪሣራ ወይም ተጨማሪ ዕዳ በአዲሱ ዓመትም የኤኮኖሚውን ቀውስ ለመታገል በሚፈሰው ወጪና በግብር ቅነሣው የተነሣ ይበልጥ እንደሚያድግ ነው የሚጠበቀው። በመሠረቱ የፊናንሱን ዘርፍ የሚመለከተው የሕገ-መንግሥት አንቀጽ 115 የገቢና የወጪ ሚዛንን ለማጣጣም ብድር መውሰድን ይከለክላል። በሌላ አነጋገር መንግሥት ዕዳ ውስጥ መግባት የለበትም ማለት ነው። ይሄው ባለፈው ዓመት በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የተጠቃለለው አንቀጽ ከመጪው ዓመት 2011 ጀምሮ የሚጸና ሲሆን መንግሥት በዚህ ዓመት ከገባበት አዲስ ዕዳ አንጻር እንዴት እንደሚወጣ ለማሰብ ያዳግታል። የመንግሥቱ ክርስቲያን ዴሞክራቶች ሕብረት ባልደረባ የፊናንስ ሚኒስትሩ ቮልፍጋንግ ሾይብለ ሳይቀር ጉዳዩን ፈታኝ አድርገው መመልከታቸው አልቀረም።

“በወቅቱ የበጀት ዓመት ሰባ ሚሊያርድ ኤውሮ ገደማ የሚጠጋ ኪሣራ አለብን። ይህንኑ ኪሣራ ደግሞ በሕጉ መሠረት ከ 2011 አንስቶ በያመቱ በተመሳሳይ መጠን መቀነስና ማስተካከል ይኖርብናል። ይህም በያመቱ አሥር ሚሊያርድ ኤውሮ መሆኑ ነው። ጥረቱ ከዚህ ቀደም በተለመዱት የበጀት ማስተካከያ ዕርምጃዎች ሊሣካ ስለማይችልም እጅግ አስቸጋሪ ተግባር ነው የሚሆነው። በዚህ የሚጠራጠር ማንም ጉዳዩ የሚመለከተው ወገን የለም”

ታዲያ ከጉዳዩ ክብደት አንጻር ግዴታውን ማሟላቱ እንዴት ገቢር ሊሆን ነው? ሚኒስትሩ ከውስጣዊ የፖለቲካ ስሌት የተነሣ በዚህ ጉዳይ ከፊታችን ሰኔ ወር በፊት ጭብጥ የቁጠባ ጽንስ-ሃሣብ አያቀርቡም። ሂደቱ አሻሚ ሆኖ ይቀጥላል ማለት ነው። በሌላ በኩል የበርሊኑ ጥምር መንግሥት አካል የነጻው ዴሞክራቶች ፓርቲ ከ 2011 አንስቶም ሃያ ሚሊያርድ ኤውሮ ተጨማሪ የግብር ቅነሣ ለማካሄድ ነው የሚያቅደው። ይህ ሃሣብ በዋነኛው ተጣማሪ በክርስቲያን ዴሞክራቱ ሕብረት ውስጥ እምብዛም ተቀባይነት የለውም። ይሁንና የለዘብተኛው ፓርቱ የበጀት ባለሙያ ኦቶ ፍሪከ ዕርምጃው ለኤኮኖሚ ዕድገት ታላቅ ግፊት ይሆናል ባይ ናቸው።

“በዕድገት ብቻ ላይ ማመን የለብንም። እርግጥ ጥረቱ ያለ ዕድገት ሊሳካልን አይችልም። እኛ የዕድገትን ጥያቄ በተመለከተ ዕምነታችንን የምንጥለው በመንግሥት ላይ ሣይሆን በሕዝቡ፣ በኩባንያዎችና አንዲያም ሲል በገበያው ሁኔታ ላይ ነው። መንግሥታዊ መመሪያዎች ለዚህ ፍቱን እንዳልሆኑ ያለፈው ጊዜ አሳይቷል”

ከዚህ አንጻር አዲሱ ዓመት የፊናንስ ክርክር የተዋሃደው እንደሚሆን ከወዲሁ መገመቱ አያዳግትም። በየትኛው ዘርፍ ነው ገንዘብ መቆጠብ የሚቻለው? እንዴት ነው መንግሥት ተጨማሪ ገቢ የሚያገኘው? እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች አዘውትረው የሚነሱ ይሆናሉ። የሚቀረው ሁኔታው እንዳይባባስ ቀውሱ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ስንብት እንደሚያደርግ ተሥፋ መጣሉ ላይ ብቻ ነው። ይህ ካልሆነ የአዲሱ 2010 ዓ.ም. የበጀት ዕቅድ ብዙ ሳይቆይ ከንቱ እንዳይሆን የሰጋል።

በአጠቃላይ አዲሱ አሠርተ-ዓመት አሮጌ ችግሮች በአዲስ መልክ እየጎሉ ሊሄዱበት የሚችልም ነው። ዓለምአቀፉ ቀውስ አንድ ቀን ከተወገደ በኋላ የፖለቲካና የኤኮኖሚውን ዘርፎች ዘርፍ እንግዳ አይሁኑ እንጂ አዳዲስ ችግሮች ይጠብቋቸዋል። ታላቁ ፈተና የሚሆነው እርግጥ ለዓመታት የአጀንዳ ርዕስ ሆኖ የቆየው የአካባቢ አየር ለውጥ ነው። በዚህ ረገድ ዋናው ጥያቄ ፍቱን የሆነ ትክክለኛ የመፍትሄ መንገድ ማግኘቱ ይሆናል። ሌላው ባለፉት ዓመታት ችላ ተብሎ የቆየው በመለወጥ ላይ ያለ የሕዝብ ይዞታ ነው። በአዲሱ አሠርተ-ዓመት ውስጥ እርግጥ የተፈጥሮ ጸጋ፤ ማለት የኤነርጂ ምንጮች የከሰል፣ የነዳጅ ዘይትና የጋዝ፤ እንዲሁም የብረታ-ብረት ወዘተ. ክፍፍል ጥያቄም ዓቢይ ጉዳይ እንደሚሆን የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። ይህ እርግጥ ዓለምአቀፉን ስርዓት የሚመለከት ጥያቄ ነው። በተፈጥሮው ጸጋ ክፍፍል ረገድ ያለውን ችግር መንግሥታት በጋራ መፍታት መቻል ይኖርባቸዋል።

ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ አንድ የታየበት በጎ ገጽታ ካለ ምናልባትም በዓለምአቀፍ ደረጃ ትብብርን ማራመዱ ነው። ዛሬ ዓበይት ዓለምአቀፍ ውሣኔዎች የሚደረጉት እንደቀድሞው በስምንቱ ሃያላን መንግሥታት ክበብ ሣይሆን አዳጊ አገሮችን በጠቀለለው ቡድን ሃያ ነው። የትብብሩ ፍቱንነት ወደፊት በአካባቢ አየር ለውጥ፣ እያረጀ በሚሄደው ሕብረተሰብ ችግርና በተፈጥሮው ጸጋ ክፍፍል ወይም እንደገና የፊናንስ ቀውስን በመፍታት ረገድ ጠቃሚ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል አንድና ሁለት የለውም።

MM/DW /SL