የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ | ኤኮኖሚ | DW | 03.02.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ

በስዊትዘርላንድ መዝናኛ ስፍራ በዳቮስ ባለፈው ሣምንት የተካሄደው ዓመታዊ የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ ዓለም ካለፉት ዓመታት የፊናንስ ቀውስ በተወሰነ ደረጃ በማገገም ላይ እንደሚገኝ፤ ሆኖም ግን ሂደቱ ገና አስተማማኝ እንዳልሆነ ከአጠቃላይ የሃሣብ ስምምነት በመድረስ ተፈጽሟል።

default

አምሥት ቀናት በፈጀው ጉባዔ ላይ 2,500 ገደማ የሚጠጉ ከዘጠና ሃገራት የተጓዙ የፖለቲካ፣ የፊናንስ፣ የምጣኔ-ሐብትና የማሕበራዊ ዘርፍ ተጠሪዎች ሲሳተፉ መድረኩ እንዳለፈው ዓመት ሁሉ ዓለምአቀፉን የኤኮኖሚ ቀውስ ማዕከላዊ ርዕሱ ያደረገ ነበር። በፊናንሱ ዘርፍ ላይ የበለጠ ቁጥጥር ያስፈልጋል አያስፈልግም ብዙ ሲያከራክር የሥራ አጦች ቁጥር ቅነሣና የአካባቢ አየር ይዞታም ማነጋገራቸው አልቀረም። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት መድረክ በተፋጠነ ዕድገት ላይ ለሚገኙትና የመፍትሄው አካል ለሆኑት አገሮች ሚናም ከበድ ያለ ትኩረት ሰጥቷል። የዳቮሱ መድረክ ምንም እንኳ አሣሪ ውሣኔዎች የሚተላለፉበት ባይሆንም ውጤቱ ቢቀር በሃሣብ ደረጃ አቅጣጫ ጥቋሚ ሆኖ መታየቱ አልቀረም።

ዓለም በመሠረቱ ባለፉት ሶሥት የቀውስ ዓመታት ብዙ ጉባዔዎችን ሲያይ ነው ያሳለፈው። የቡድን-ሃያ የፊናንስ ጉባዔ በተከታታይ ተካሂዶ ዓለምአቀፉን የፊናንስ ቀውስ ለማሽነፍ በርካታ የዕርምጃ ነጥቦች ተረቀዋል። ገቢር ሊሆኑ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ስምምነቶች መደረጋቸውም አልቀረም። በተለይ የበለጸጉት መንግሥታት ባንኮችን ከውድቀት ለማዳን፣ የኤኮኖሚውን ቀውስ ለመቋቋምና የሥራ አጦችን ቁጥር መናር ለመገደብ መዓት ገንዘብም ነው ያፈሰሱት። ታዲያ አሁን በዳቮስም እንደገና እንደተነገረው የኤኮኖሚው አቆልቋይ ሂደት ተገትቶ ቀውሱ ጥቂት ይለዝብ እንጂ የወደፊቱ ገና አስተማማኝ አይደለም። በቅርቡ ኮፐንሃገን ላይ የተካሄደው የአካባቢ አየር ጉባዔም ከአንዲት መግለጫ አልፎ በጉጉት እንደተጠበቀው ጭብጥ ውጤትን ሳያስከትል መቅረቱን ነው ዓለም የታዘበው። ስለ አካባቢ አየር ጥበቃና ስለ ፊናንሱ ቀውስ እንግዲህ ብዙ ነው የተባለው። ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ከተከሰተ ከ 2008 ዓ.ም. ወዲህ አሥር ዓበይት የመንግሥታት ጉባዔዎች ተካሂደዋል። ይሁን እንጂ በአሕጽሮት ዊድ በመባል የሚታወቀው የኢንዱስትሪው ዓለም ተቺ ድርጅት ፔተር ቫል እንዳሉት የተደረገው ዕርምጃ በጣሙን ትንሽ ነው።

“ችግሩን እንዴት በሌላ መንገድ መቋቋም እንደሚቻል አሁንም ይታሰባል። ይህ የማሰብ ሂደት ደግሞ ገና ከግቡ አልደረሰም። በተግባር በሥራ ላይ መዋሉማ ጨርሶ የማይታለም ነው። እርግጥ በብሄራዊ ደረጃ ሕግጋትን በማውጣት የመጀመሪያ ዕርምጃ መደረጉ አልቀረም። ነገር ግን በተግባር በማንኛውም መንገድ የፊናንስ ገበያ ደምቦች ሰፍነዋል ለማለት አይቻልም’”

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ከሃሣብ ወደ ተግባር ለመዝለቅ በዳቮስ መድረክ ዋዜማ ባለፈው ሣምንት የመጀመሪያውን ዕርምጃ ወስደው ነበር። ኦባማ የቀውሱን ዋነኛ ተጠያቂዎች የባንኮችን ሥልጣን ወደፊት አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የፊናንስ ተቋማቱን በመሰነጣጠቅ ለመገደብ ነው የሚፈልጉት። በአሜሪካው ፕሬዚደንት ዕምነት አንድም ባንክ መላውን የፊናንስ ስርዓት አዘቅት እስኪጥል ድለር ማየል የለበትም። ቁርጠኛ አቋም ነው የወሰዱት።
“እነዚህ ሰዎች ትግል ከፈለጉ እኔም በበኩሌ ለዚሁ ዝግጁ ነኝ”

በዳሶሱ መድረክ በቀጥታ ለተሳተፉት የባንክ ተጠሪዎች ታዲያ ይህ የኦባማ መግለጫ የራስ ምታት መሆኑ አልቀረም። ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በባንድላይ ሆነው ወቀሧውን ሊያቋቋሙ ነው የሞከሩት። ለነገሩ በባንኮች ላይ ያተኮረው የትችት ዘመቻ እርግጥ በኦባማ መግለጫ ብቻ አላበቃም። የፈረንሣዩ ፕሬዚደንት ኒኮላይ ሣርኮዚይ እንዲያውም በፊናንሱ ዘርፍ ተጠሪዎች ላይ ከባድ ነቀፌታ ነው የሰነዘሩት። ሣርኮዚይ ፍቱን የሆነው ስርዓታችን በዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ ፊት ቁጥራቸው ጥቂት በሆነ ሰዎች እየወደመ ነው እስከማለት ደርሰዋል።

ኒኮላይ ሣርኮዚይ

ኒኮላይ ሣርኮዚይ

“የከበርቴውን ስርዓት፤ ካፒታሊዝምን ማስወገድ አለብን አይደለም የምለው። ግን የቱን የከበርቴ ስርዓት እንደምንፈልግ መወሰን አለብን። በወቅቱ ይሄው ስርዓት ፈሩን ሲለቅ እየታዘብን ነው። ካፒታሊስቱ ስርዓት በሕብረተሰብ እሴቶች ላይ የተመሰረተ ነው። ይህን በእግሩ የሚረግጥ የፊናንስ ካፒታሊዝም ግን እነዚህ እሴቶች የሉትም”

የፈረንሣዩ ፕሬዚደንት በዓለምአቀፉ የፊናንስ ወይም የምንዛሪ ስርዓት ላይ ይበልጥ የጠነከረ ቁጥጥር ሊሰፍን ይገባዋል ባይ ናቸው። የባንክ አስተዳዳሪዎች እንዳሻቸው የሚካብቱበት ሁኔታ፣ ባንኮች በፍጥነት ትርፍ ለማጋበስ ያላግባብ በገንዘብ መቆመራቸው ሊቀጥል አይገባውም። ሆኖም የዊድ ባልደረባ ፔተር ቫል በመድረኩ ዋዜማ እንዳሉት ምዝበራው እንዲቆም ቃል-መግባት ሣይሆን ጠንካራ ደምቦች የግድ መስፈን አለባቸው።

“በሞራላዊ የአሠራር ዘይቤ ላይ ውይይት መደረጉን እጠብቃለሁ። ደምቦችን በመቀሩም ላይ እንዲሁ! ይህ ምናልባት ወደ ውጭ ጠቃሚ ነጸብራቅ ሊሆን ይችላል። በእርግጥም ለጉዳዩ ማሰሪያ መስጠት አለብን። እና እስካሁን እንደነበረው እንዲህ አደርጋለሁ ብሎ ቃል መግባት ሣይሆን መፍትሄው ጠንካራ ደምቦችን ማስፈን ነው”

ባዳቮሱ መድረክ የባንኩ ወገን ተጠሪዎች በበኩላቸው ጠንካራ ደምቦች መስፈናቸውን አጥብቀው ሲቃወሙ ወይም ጎጂ ተጽዕኖ ይኖረዋል በማለት ሲከራከሩ ነው የሰነበቱት። ከነዚሁ መካከልም የዶቼ ቫንክ ሃላፊ ዮዜፍ አከርመን ይገኙበታል።

“ተጨማሪ አዳዲስ ደምቦችን፣ አዲስ ግብርንና ሌሎች ሃሣቦችንም ማቅረቡ ብልህነት የተመላው ነው ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ይህ አስተማማኝ ያልሆነ ሁኔታን ከማስከተሉ ባሻገር የፊናንሱን ዘርፍ መረጋጋትም የሚያግድ ነው የሚሆነው”

የሆነው ሆኖ አንድ ዓለምአቀፍ የባንኮች ቁጥጥር ደምብን በማስፈኑ ረገድ በመንግሥታት መካከል ያለው ልዩነት ጉዳዩን ቀላል እንደማያደርገው በዳቮሱ መድረክ ላይ እንደገና መታየቱም አልቀረም። እያንዳንዱ አገር የራሱን መንገድ ቢከተልስ ይበቃ ይሆን? ይህም ጥያቄ እንዲሁ ማነጋገሩ አልቀረም። ክርክሩ ይቀጥላል ማለት ነው። ለኤኮኖሚው ኖቤል ተሸላሚ ለጆሴፍ ስቴግሊትስ ግን በወቅቱ የሚቻለው የኋለኛው ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም።

“አንድ ዓለምአቀፍ ውል ቢሰፍን በተሻለ ነበር ለማለት ይቻላል። ግን የኔ ስጋት ለምሳሌ አሜሪካውያን አውሮፓውያን ዕርምጃውን መጀመር አለባቸው፤ አውሮፓውያኑ ደግሞ በፊናቸው አሁን ተራው የአሜሪካውያን ነው እንዳይሉ ነው። ባንኮች ይህን ይወዱታል። ምክንያቱም ስምምነት አይኖርም፤ ደምብም ሊሰፍን አይችልም። ስለዚህም በብሄራዊ ደረጃ መጀመር ይኖርብናል። እያንዳንዱ መንግሥት የራሱን ዜጎችና ኤኮኖሚ ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት”

ባዳቮሱ የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ከሁለት ወራት ገደማ በፊት በኮፐንሃገን ተሽመድምዶ የቀረው የአካባቢ አየር ጉባዔና የወደፊቱ ተሥፋም በሰፊው አነጋግሯል። የዓለም ሕብረሰተብ ከታላቁ ጉባዔ የጠበቀው ስምምነት ገሃድ አለመሆን ያስከተለው ቁጣ አሁንም ጨርሶ አልበረደም። ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ አየር ጉዳይ ኮሜሣር ኢቮ-ዴ-ቦር ሁሉም ነገር መጥፎ አልነበረም ሲሉ የብዙዎችን ትኩሳት ለማብረድ ደግመው ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

“የኮፐንሃገኑ ቀውስ አንድ ክፍል በቦታው 120 መንግሥታት ከመሰብሰባቸውና የአካባቢ አየር ለውጥን በተመለከተ ስጋታቸውን ከመግለጻቸው ጋር የተያያዘ ነበር። ከዚሁ ሌላ አንድ የተወሰኑ ሃገራትን ያቀፈ ቡድን ከፍተኛውን የሞቅታ መጠን የሚወስንና የገንዘብ ዕርዳታ ቃልን የጠቀለለ የፖለቲካ መግለጫ አውጥቷል”

የሆነው ሆኖ የኮፐንሃገኑ ጉባዔ መክሸፍ ግንዛቤ ከዳቮሱ የመድረክ ስብሰባ በፊት የነበረውን ያህል አሁንም በማግሥቱ ጸንቶ እንደቀጠለ ነው። የሚቀረው ተሥፋ በያዝነው ዓመት መጨረሻ ሜክሢኮ-ካንኩን ላይ የሚካሄደው ጉባዔ ነው። የሜክሢኮው ፕሬዚደንት ፌሊፔ ካልዴሮን ልዩነቱን ለማውጣጣት ገና ከአሁኑ በሚቀጥሉት ሣምንታት ከመንግሥታት መሪዎች ጋር ያልተቋረጥ ግንኙነት ማድረግ እንደሚጀምሩ በዳቮስ ተናግረዋል።

“ከኮፐንሃገን ስህተት መማር ይኖርብናል። በተለያዩት ወገኖች መካከል መተማመን መልሶ እንዲሰፍን ማድረግ አለብን። ለዚህም የሁሉንም ድምጽ ለመስማት፤ ሁሉንም አገሮች ወደ አንድ ጠረጴዛ ለማምጣት እፈልጋለሁ። ዓመቱን ሙሉ አብረን ለመስራት እንድንችል አንድ መደራደሪያ መንገድ ለማስፈን ነው የምጥረው”

ይህ መሳካቱን ጠብቆ መታዘቡ ግድ ነው።

MM/DW

Negash Mohammed