የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ በአፍሪቃ | ኤኮኖሚ | DW | 09.05.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ በአፍሪቃ

በአፍሪቃ ላይ የሚካሄደው የዘንድሮው የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ የሶሥት ቀናት ስብሰባ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተከፍቷል።

በአፍሪቃ ላይ የሚካሄደው የዘንድሮው የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ የሶሥት ቀናት ስብሰባ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተከፍቷል። ባለፈው አንድ አሠርተ-ዓመት ያልተቋረጠ የኤኮኖሚ ዕርምጃ እንዳሳየች የሚነገርላት አፍሪቃ ዘንድሮም በአማካይ 6 በመቶ ዕድገት እንደምታደርግ ነው የሚገመተው። በመጪው ጊዜ የኤኮኖሚና የፖለቲካ ዕርጋታን በማሻሻል ለረጅም ጊዜ የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት ጥርጊያን ለመክፈትና የፍጆት አቅም የሚኖረውን የሕብረተሰብ ክፍል ለማስፋት መታለሙም አልቀረም።

የመድረኩ ጉባዔ የሚካሄደው አፍሪቃ በታላቅ የሽግግር ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ እየተነገረ ባለበት ወቅት ነው። ጉባዔው ለመሆኑ ለአፍሪቃ ምን ትርጉም አለው? ምንስ ነው ከሂደቱ የሚጠበቀው? በመድረኩ ስብሰባና በአጠቃላዩ የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ይዞታ ላይ ያነጋገርኳቸው በደቡብ አፍሪቃ-ኬፕታውን የጀርመኑ ታዋቂ የንግድ ጋዜጣ የ «ሃንደልስብላት» ወኪል ቮልፍጋንግ ድሬክስለር እንዲህ ይላሉ።

«መድረኩ አፍሪቃ ውስጥ በፖለቲካና በኤኮኖሚ ተጠሪዎች መካከል የሃሣብ ልውውጥ ለማካሄድ የተለየ አጋጣሚ ይመስለኛል። ይህ ከስንት አንዴ የሚገኝ ዕድል ነው። እርግጥ በያመቱ ወይም በዓመት ሁለቴ የሚደረግ የአፍሪቃ ሕብረት ስብሰባም አለ። ሆኖም በሕብረቱ ጉባዔ ላይ የሚሳተፉት በአመዛኙ ፖለቲከኞች ብቻ ናቸው። በዓለም ኤኮኖሚው መድረክ ላይ ግን ትልቅ የንግድና የኤኮኖሚ ተጠሪዎች ስብስብ ነው የሚገኘው። እናም መድረኩ የአፍሪቃን ችግሮች በቅርብ ለማጤንና ለመታገል ጥሩ አጋጣሚ ይሆናል»

መድረኩ ለነገሩ ከሃያ ዓመታት ወዲህ ያለ ሲሆን እርግጥ ቀደምቱን የፖለቲካና የምጣኔ-ሐብት ዘርፍ ተጠሪዎች እንደ መረብ ለማስተሳሰር ግሩም መሣሪያ ሆኖ መታየቱ አልቀረም። ግን የሚያሳዝነው እስካሁን ባለፉት ዓመታት ብዙም ጭብጥ ነገር ሲፈልቅ አለመታየቱ ነው።

«በመሠረቱ ጭብጥ ዕርምጃ መጠበቅ አይቻልም። እንዲህም ሆኖ ግን ባለፉት ዓመታት ለምሳሌ ሁነኛ መዋቅራዊ ለውጥ፣ የተሻለ የኤኮኖሚ ዕድገትና የአፍሪቃን ንግድ ለማፋጠን የሚበጁ ዕርምጃዎችን ባይ ደስ ባለን ነበር። በዚህ ረገድ ጥቂት ውጤት ብቻ ነው የተገኘው። የሆነው ሆኖ በጥቅሉ መድረኩ በአፍሪቃ መካሄዱ በክፍለ-ዓለሚቱ የሚደረገውን የልማት ውይይት በሃቅ ለማራመድ እንደሚጠቅም አልጠራጠርም። መድረኩ አሁን አዲስ አበባ ላይ፤ በመጪው ዓመት ደግሞ በኬፕታውን ነው የሚካሄደው። እንግዲህ ስብስባው በኬፕታውንና በአንድ ሌላ የአፍሪቃ ከተማ የሚፈራረቅ ሲሆን የረባ ዕርምጃ መኖሩ እያደር የሚታይ ነገር ነው»

የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች በወቅቱ የመድረኩን አስተናጋጅ አገር ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪቃ ሃገራት ላይ ያማሩ አስተያየቶችን ነው የሚሰነዝሩት። በአፍሪቃ መዋዕለ-ነዋይ ማድረግ ሳይዘገይ ዛሬ ነው የሚሉት ጥቂቶች አይደሉም። በሌላ በኩል ግን ለባለሃብቶች አስፈላጊ ከሆነው የንብረት ዋስትና ሕግ አንጻር በአፍሪቃ ያን ያህል የረባ መሻሻል ተደርጓል ለማለት በጣሙን ነው የሚያዳግተው። እንደ ቮልፍጋንግ ድሬክስለር ከሆነ ይህን ሁኔታ ደግሞ የመድረኩ ስብሰባም ሊለውጠው አይችልም።

«ለመድረኩ ይህን ማድረጉ ከባድ ነው የሚሆነው። ለመዋዕለ-ነዋይ አያያዝ መሠረት መጣል ያለባቸው ለነገሩ እያንዳንዱ ሃገራት ራሳቸው ናቸው። ተገቢውን ፖሊሲ በመከተል! እዚህ ላይ ጠቃሚ ነጥብ ነው ያነሳኸው። አፍሪቃ ውስጥ መዋዕለ-ነዋይ ማድረግ የሚሹ የውጭ ኩባንያዎች ከሁሉም በላይ ሕጋዊ ስርዓት የሰፈነበት መሠረታዊ ሁኔታ መኖሩን ይፈልጋሉ። ይህ እዚህ አፍሪቃ ውስጥ ብዙም አይታወቅም»

በሌላ አነጋገር የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ገንዘባቸውን ምን ቦታ በስራ ላይ እንደሚያውሉ ማወቃቸውና የንብረት ዋስትና ማግኘታቸውም ወሣኝ ነው። ገንዘቡን ለመነጠቅ የሚፈልግ ኩባንያ የለም። በመሠረቱ ይህን መሰሉን ጉዳይ የሚመለከቱ ፍርድቤቶችም የግድ አስፈላጊ ሲሆኑ በአፍሪቃ የዋስትናው ስርዓት ገና ብዙ ነው የሚጎለው። ይህ በዓለም ላይ የተረጋገጠ ደምብ በእሢያና በላቲን አሜሪካ ሳይቀር በተሻለ ሁኔታ ተራምዷል።

«ከሁሉም በላይ በእሢያና በአሁኑ ጊዜ በላቲን አሜሪካም ምንም እንኳ በአንዳንዶቹ ሃገራት ገና ችግር ባይታጣም እየተጠናከረ ነው። በአፍሪቃ ግን የዋስትናው ጉዳይ ትልቅ ችግር እንደሆነ ይቀጥላል። እንግዲህ አንድ መድረክ ለውይይት ሃሣብ ከማቅረብና መሪዎችን ከማወያየት አልፎ ሁኔታውን ሊለውጥ አይችልም። መንግሥታቱ ኢትዮጵያንም ጨምሮ ለመዋዕለ-ነዋይ አስፈላጊውን ሁኔታ ማመቻቸት አለባቸው። እዚህ ላይ ገና ብዙ ዕርምጃ ነው የሚጎለው»

ቮልፍጋንግ ድሬክስለር በሌላ በኩል አፍሪቃ ዛሬ ደጋግሞ እንደሚጠቀሰው ቻይና የዛሬ ሃያ ዓመት ከነበረችበት የልማት ደረጃ ደርሳለች የሚለውን አነጋገር ሲበዛ በጥርጣሬ ዓይን ነው የሚመለከቱት። እንደርሳቸው አባባል አፍሪቃ በእሢያና በላቲን አሜሪካ እግር ለመተካት ትችል ዘንድ ብዙ ነገሮች በሚገባው መጠን አልተሟሉም። ክፍለ-ዓለሚቱ ባለፉት ዓመታት ዕርምጃዋ በመቀጠል በ 5 እና በ6 ከመቶ ዕድገት ትቀጥላለች ቢባልም ይሄው ለከፍተኛ ልማት በቂ ሊሆን አይችልም።

«አፍሪቃ ከየት ተነስታ እንደመመጣችና ዕድገቱ ቀድሞ ምን ያህል እንደነበር ካየን ዛሬ በእጥፍ ጨምሮ ቢሆን እንኳ ትልቅ ነገር አይደለም። በጣም አነስተኛ ነው። አፍሪቃ ከ5 እና ከ 6 በመቶ በበለጠ መጠን፤ እንበል ቢያንስ በእጥፍ በሰፊው ማደግ ይኖርባታል። ድህነትን ለመቀነስ እንዲቻል ደግሞ ይሄው ዕድገት ሳያቋርጥ ለአሥር ዓመታት ያህል መራመዱ ግድ ነው»

ግን ይህ እስካሁን አልተሳካም። የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ዕድገት ሁሌም በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ጥገና ሆኖ ነው የኖረው። የዓለም ኤኮኖሚ በጥሩ ሁኔታ ላይ በሆነና የጥሬ ዕቃ ፍላጎት በጨመረ ቁጥር የአፍሪቃ የዕድገት መጠንም ከፍ ባይ ነው። በሌላ በኩል እንዳሁኑ የዓለም ኤኮኖሚ ሊያቆለቁል በሚያሰጋው ጊዜ ደግሞ ዕድገቱ መልሶ ይቀንሳል። ሃቁ ይህ ሲሆን በዚህ ረገድ እስካሁን የተደረገ መሠረታዊ ለውጥ የለም።

አፍሪቃ ያለማቋረጥ በማደግ፤ በመመንደግ ላይ ናት ቢባልም ድህንትንና ረሃብን ለማሸነፍ ሁነኛ ጥርጊያን የሚከፍት ዕርምጃ ግን ዛሬም እንደ ትናንቱ ደብዙም አይታይም። ሃቁ አብዛኞቹ የአፍሪቃ ሃገራት በተለያዩ ዓለምአቀፍ የልማት መስፈርቶች ዝቅተኛውን ቦታ እንደያዙ ነው የሚገኙት። በተፋጠነ ዕድገት ላይ ናቸው ከሚባሉት አንዷ ኢትዮጵያ ለምሳሌ አሁንም የድሃ ድሃ ተብለው ከሚመደቡት የአፍሪቃ ሃገራት ሰፈር አልወጣችም።

ሰፊ ስራ አጥነት፣ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥና የሕዝብ ቁጥርም በፍጥነት እየጨመረ መሄድ ደግሞ የወደፊቱን ሂደት ቀላል አያደርጉትም። ከዚህ አንጻር እንግዲህ አፍሪቃ ቻይናና ሕንድ ከሃያ ዓመታት በፊት ይግኙ ከነበረበት የልማት ደረጀ ደርሳለች መባሉ ከልብ ቢመኙት እንኳ ሊቀበሉት ያዳግታል።

«የለም፤ ይሄ ሃቁን ያገናዘበ ነገር አይደለም። ቻይናና ሕንድ ለምን እንዲህ እንዳደጉ ብንመለከት በተለይ ሁለት ነገሮች ወሣኝነት እንዳላቸው እንረዳለን። ሁለቱም ሃገራት፤ በተለይም ቻይና ጠንካራ ቢሮክራሲ ነው ያላት። ቻይና፣ በግሩም ዕድገቷ የምትታወቀው ሲንጋፑር ወይም ቪየትናም ለብሄራዊ ብልጽግና ከልብ የተነሱ፣ በጋራ ብልጽግና የሚያምኑና መሠረታዊ ለውጦችን ወደፊት የሚያራምዱ መሪዎች ነው ያሏቸው። መሪዎቻቸው ሃብት በስተጀርባ ወደ ፓርቲያቸው ካዝና እንዲፈስ አለማድረጋቸው፣ ለራሳቸው ሊካብቱበት አለመከጀላቸው ወይም በውጭ የባንክ ሂሣባቸው እንዲገባ አለመሻታቸው ትልቅ ነገር ነው። በአጭሩ ዓመጽ እንዲፈጠር የማይፈልጉ ለዕድገት የቆረጠ ቢሮክራሲ ያላቸው ናቸው»

ስለ አፍሪቃ መሪዎች ምናልባት በእጣት ከሚቆጠሩ አልፎ ይህን ለማለት አይቻልም። ይልቁንም ዓመጽ፣ ውዝግብና መንግሥታዊ ሙስና ማሕበራዊ ዕድገትን አንቆ መቀጠሉ ነው ጎልቶ የሚታየው። አፍሪቃ በቻይናና በሕንድ እግር መተካት እንዳትችል የሚያደርጋት ሌላው ምክንያት ደግሞ እንርሱ ያላቸው የመቋቋም ወግ የሚጎላት መሆኑ ነው።

«ቻይናና ሕንድ በጣም ጠንካራ የሆነ ኩባንያን የማቋቋም ወግ አላቸው። ኩባንያን የማቋቋምና የማስፋፋት ቁርጠኝነት አይጎላቸውም። ይህ በአፍሪቃ በጣም በጥቂቱ ወይም በጅምር ደረጃ ብቻ ነው የሚታየው። እናም የአፍሪቃ ዕድገት በሌሎች ሃገራት፤ በምዕራቡ ዓለም ወይም አሁን ደግሞ በቻይና ኩባንያዎች ዕድገት ላይ ጥገኛ ነው። እንግዲህ የሚገኘው ዕድገት ራሱ አገር-በቀል አይደለም። ይህን የግድ መቀየር ያስፈልጋል»

በእሢያው ግዙፎች እግር መተካት መቻሉን እጅጉን የሚያከብድ የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ድክመት ገጽታ ዋና መለያ ሆኖ የኖረ ሌላም ቁልፍ ምክንያት አለ።

«ሌላው ምክንያት በአፍሪቃ ጠንከር ባለ ሁኔታ በአንድ ዓይነት ጥሬ ሃብት ላይ ጥገኛ መሆን ነው። ማዕድናት፣ ነዳጅ፣ ጥጥ፣ ቡና፣ ኮኮ ወዘተ-! አንድ አገር በአንድ ጥሬ ሃብት ላይ ብቻ ጥገኛ ከሆነ ሁኔታው አስቸጋሪ ነው። የአፍሪቃ ሃገራት በመካከላቸው በሚገባም አይነግዱም። በአማካይ ሲሰላ የአፍሪቃው ውስጣዊ ንግድ ከባሕር ማዶው የውጭ ንግድ ከሚገኘው ገቢ አሥር በመቶው ድርሻ ቢሆን ነው። 90 በመቶው እንግዲህ ወደ አውሮፓ ወይም ወደ እሢያ የሚደረገው የጥሬ ሃብት ንግድ ይሆናል። ይህ ደግሞ ጤናማ ነገር አይደለም። ስለዚህም አፍሪቃ ውስጣዊ ንግዷን የኤኮኖሚ ዕድገቷ መንኮራኩር ማድረግ ይኖርባታል»

እርግጥ በአፍሪቃ ጨርሶ አንዳች ዕርምጃ አልተደረገም ማለት አይደለም። ችግሩ ዕድገቱ በጥቂት የተወሰነ ወይም ደግሞ በማሕበራዊ ኑሮ መሻሻል ሊከሰት ያልቻለ መሆኑ ላይ ነው። አፍሪቃ በወቅቱ ከኮንጎ እስክ ሣሄል፤ ከሣሄል እስከ ሱዳን በዓመጽና በግጭት ስትወጠር ሙስና በኬንያ እንደገና እያነጋገረ ነው። ረሃብና መፈናቀልም የአፍሪቃ ቀንድ መለያ እንደሆነ ቀጥሏል። ስኬት ከተባለ ጋና በትክክለኛ ምርጫ ለዕድገት የሚያመች የፖለቲካ ዕርጋታን ስታሰፍን እንደ ታንዛኒያ ወይም እንደ ሞዛምቢክ የተወሰነ ዕርምጃ ያደረጉት በእጣት የሚቆጠሩ ናቸው። መድረኩ እነዚህ መሠረታዊ ችግሮች የሚነሱበት ቢሆን ምንኛ በበጀ ነበር።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዮ ለገሰ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 09.05.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14rtW
 • ቀን 09.05.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14rtW