የዓለም ኤኮኖሚና የአዲስ ቀውስ ፍርሃቻ | ኤኮኖሚ | DW | 28.09.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ኤኮኖሚና የአዲስ ቀውስ ፍርሃቻ

የዓለም ባንክና የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የአይ.ኤም.ኤፍ ዓመታዊ የበልግ ጉባዔ የመንግሥታት የዕዳ ችግርና የአዲስ የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስ ፍርሃቻ በጋረደው ሁኔታ ባለፈው ዕሑድ ተጠቃሏል። በተቋሙ ጥናት መሠረት የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት በያዝነውና በመጪው ዓመት አቆልቋይ እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው።

default

የኤውሮ-ዞን መንግሥታትና የአሜሪካ የዕዳ ቀውስ የጉባዔው ዓቢይ መከራከሪያ ጉዳይ ሆኖ ሲሰነብት መዘዙ ወደ ታዳጊና በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ ወደሚገኙ አገሮች እንዳይዛመት ብርቱ ስጋትን ነው የተፈጠረው። በመሆኑም የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ሮበርት ዞሊክና የምንዛሪው ተቋም አዲስ ሃላፊ ፈረንሣዊቱ ክሪስቲን ላጋርድ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ችግሩን ለመቋቋም ወሣኝ ዕርምጃ እንዲወስዱ አስገንዝበዋል። ሮበርት ዞሊክ እንዲያውም አስፈላጊው ዕርምጃ በጊዜው ካልተወሰደ ቀውሱ የታዳጊ አገሮችም ቀውስ ሊሆን ይችላል ሲሉ ነው አጥብቀው ያስጠነቀቁት።

ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም በጉባዔው ዋዜማ አዲስ የዓለም ኤኮኖሚ ሂደት ጥናቱን ያቀረበው “አቆልቋይ ዕድገት፣ የሚያይል አደጋ” በሚል ርዕስ ነበር። የምንዛሪው ተቋም የኤኮኖሚ ባለሙያ ኢሎቪየር ብላንቻርድ ጥናቱን ዋሺንግተን ላይ ሲያቀርቡ የዓለም ኤኮኖሚ በአዲስና እጅግ አደገኛ በሆነ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ነው ያስገነዘቡት። ዓለምአቀፉ የማገገም ሂደት ሲዳከም የማቆልቆሉም አደጋ በጣሙን ነው የጨመረው። እናም በጥናቱ እንደተመለከተው የዕድገቱን ዕድል መልሶ ለማሻሻል አስተማማኝ የፖለቲካ ዕርምጃዎች የግድ አስፈላጊ ይሆናሉ።

የጃፓኑ የመሬት ነውጽና ትሱናሚ፣ በአንዳንድ ነዳጅ ዘይት አምራች አገሮች የተፈጠረው ዓመጽ፣ በኤውሮ-ዞን አገሮች የተፈጠረው የዕዳ ቀውስና ግዙፉ የአሜሪካ የበጀት ኪሣራ፤ በዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም አመለካከት የዓለም ኤኮኖሚን የማገገም ሂደት የሚገቱ ናቸው። እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች በርካታ ምክንያቶችም አሉ። ተቋሙ በተለይም የኤውሮ-ምንዛሪን ክልል ሁኔታ በስጋት ነው የሚመለከተው። የዕዳው ቀውስ ከትናንሾቹ ወደ ታላላቆቹ አገሮች የሚዛመት ከሆነ የዓለምአቀፉን የፊናንስ ገበዮች እርጋታ እንዳያናጋ በጣሙን ያስፈራል። የምንዛሪው ተቋም ከወቅቱ ሁኔታ በመነሣት ለያዝነውና ለሚቀጥለው ዓመት የኤኮኖሚ ዕድገት ትንበያውን ወደታች ዝቅ አድርጎ አርሟል። በዚሁ ጊዜ የዓለም ኤኮኖሚ በአማካይ ቀደም ሲል በታሰበው 4,5 በመቶ ፈንታ በአራት ከመቶ ብቻ ቢያድግ ነው።
የፊናንሱን ባለሙያ ብላንቻርድን ይበልጥ ያሳሰበው በተለይ በፍጥነት በሚራመዱት ቻይናን በመሳሰሉት ሃገራትና በበለጸጉት መንግሥታት ዘንድ ሚዛኑ የተዛባ ሆኖ መቀጠሉ ነው። በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ የሚገኙት አገሮች በያዝነው 2011 ዓ.ም. በአማካይ 6,5 ከመቶ ዕድገት የሚያሳዩ ሲሆን በበለጸጉት አገሮች የሚጠበቀው 1,6 በመቶ ብቻ ነው። የምንዛሪው ተቋም ይህንን ያልስተካከለ ሚዛን ለማጣጣም ጠንካራ የፖለቲካ ዕርምጃ ካልተወሰደ በፍጥነት ዕድገት እንደሚያቆለቁል፣ የበጀትና የባንኮች ቀውስ ሊከሰት እንደሚችልም ያምናል። እንግዲህ የዕድገት’ዝቅተኛ መሆን የበጀት ይዞታን ማረጋጋቱን ከባድ ነገር ያደርገዋል።

የገንዘብ ተቋማቱ ጉባዔ በተለይም በመጨረሻ ቀኑ የአሜሪካና የአውሮፓ ቅራኔ የተንጸባረቀበት ሆኖም ነው ያለፈው። አንዱ ወገን ሌላውን ለችግሩ መባባስ ተጠያቂ ማድረጉ አልቀረም። ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ለምሳሌ እንደ ፊናንስ ሚኒስትራቸው እንደ ቲሞቲይ ጋይትነር ሁሉ የአውሮፓን ሕብረት መንግሥታት የዕዳ ቀውሣቸውን በቁርጠኝነት አይታገሉም፤ ይህም ዓለምን ስጋት ላይ እየጣለ ነው በማለት ጠበቅ አድርገው ተችተዋል።

“አውሮፓውያኑ በወቅቱ ዓለምን በሚያስፈራ የፊናንስ ቀውስ ላይ ነው የሚገኙት። እርግጥ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት መጣራቸው አልቀረም። ሆኖም ግን በዕርምጃቸው የሚገባውን ያህል ፈጣን አይደሉም”

ይህን የጀርመኑ የባንክ ባለሙያ ሃይንሪሽ ሃሢስ ጨርሶ አይቀበሉትም። ባለሙያው አሜሪካ አውሮፓን ለወቅቱ ቀውስ ተጠያቂ ማድረጓ ከራሷ ችግር ለማዘናጋት ባላት ፍላጎት ነው ባይ ናቸው። እርግጥ አሜሪካም በራሷ የበጀት ኪሣራ ወይም የዕዳ ቀውስ ተወጥራ እንደምትገኝ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። አገሪቱ የመንግሥቱን የዕዳ ጣራ ከፍ ለማድረግ ባትወስን ኖሮ መንግሥት አሁን ከሰሞኑ የክፍያ አቅም አጥቶ ምናልባትም በታሪኩ ታይቶ ከማይታወቅ ከለየለት ቀውስ ላይ በወደቀ ነበር። አውሮፓውያን በበኩላቸው ቀደም ያለው የፊናንስ ቀውስ የተከሰተው በዚያው በአሜሪካና የተቀሰቀሰውም በአብዛኛው በአገሪቱ ባንኮች እንደነበር ያመለክታሉ።
በጊዜው ለተከሰተው ዓለምአቀፍ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ፤ እንዲያም ሲል አሁን ለምንታዘበው የዕዳ ችግር ደግሞ አሜሪካን ነው መነሻ አድርገው የሚመለከቱት። እርግጥ አውሮፓውያንም የኤውሮን-ዞን ሲመሠርቱ ስህተት መስራታቸው አልቀረም። ብዙው ነገር የተድበሰበሰ ሆኖ ነው የኖረው። ይሁን እንጂ የጀርመኑ የፊናንስ ሚኒስትር ቮልፍጋንግ ሾይብለ የዓለም ኤኮኖሚ በአዲስ አደገኛ ደረጃ ላይ ነው በሚለው የምንዛሪው ተቋም ማሳሰቢያ ብዙ መሸበር አይገባም ባይ ናቸው።

“አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መሆናችን ግልጽ ነገር ነው። ሆኖም በአንድነት ለመታገል ቁርጠኞች ነን። በሁኔታው ከሚገባው በላይ የሚያስበረግግ ምንም ምክንያት አይኖርም። ሁኔታው መጋነን የለበትም። በያዝነው መንገድ በቁርጠኝነት ከተራመድን የዓለምን ኤኮኖሚ በቅርቡ እንደገና ለማረጋጋት እንችላለን”

በዋሺንግተኑ የገንዘብ ድርጅቶች የበልግ ጉባዔ በጥቅሉ እንደታየው የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ዓባል ሃገራት በወቅቱ ቀውስ የተነሣ በዓለም ኤኮኖሚ ላይ የተፈጠረውን አደጋ በጋራ ለመቋቋም እንደሚሹ አመልክተዋል። የዓባል መንግሥታቱ የየግል ሁኔታ ከመሠረቱ የተለያየ ቢሆንም በሌላ በኩል ኤኮኖሚያቸው በጥብቅ በአንድ መረብ የተሳሰረ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው፤ የብሪታኒያው የፊናንስ ሚኒስትር ጆርጅ ኦስቦርን በጉባዔው ላይ እንዳስረዱት።

“ዓለምአቀፉ የዕዳ ቀውስ አደገኛ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ እዚህ ተገቢው ዕውቅና አለ። ግን እኔ ችግሩን ለመፍታት ትክክለኛውን መንገድ ይዘናል ባይ ነኝ። የቀውሱ ማዕከል የሆኑት የኤውሮ-ዞን አገሮች ቁርጠኛ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው የሚረዱ ይመስለኛል። እና የተቀረው ዓለምም ሊረዳቸው ዝግጁ ነው”

IWF Christine Lagarde

የምንዛሪው ተቋም ሃላፊ ክሪስቲን ላጋርድ በበኩላቸው እንደጠቀሱት ድርጅታቸው አይ.ኤም.ኤፍ. ይህን መሰል ትልቅ ቀውስ ለመታገል እርግጥ የገንዘብ አቅም የለውም። ይሁንና ከፊሉ ተግባር ከወዲሁ መከናወኑን በማመልከት ለወደፊቱ ተሥፋቸውን ነው የገለጹት።

“ወቅቱ እጅግ አስቸጋሪ ቢሆንም በአስተሳሰቤ ተሥፋ አይለየኝም። ለነገሩ ለዓለም ኤኮኖሚ የሚያስፈልገው ስራ ከወዲሁ በከፊል ተጠናቋል። የፊናንስ ደምቦቹን፣ የቀውስ አያያዙንና በኤውሮ-ዞን ያለውን የተሻሻለ አስተዳደር፤ እንዲሁም የባንኮችን ካፒታል የማጠናከሩን ተግባር ከተመለከትን ይህ ሁሉ የተጠናቀቀ ነገር ነው። እርግጥ ገና በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ነን። ግን ግማሹን መንገድ ስናቋርጥ ከግባችን ለመድረስ የሚያስፈልገው ጥቂት ጠንከር ያለ ግፊት ይመስለኛል”

የምንዛሪው ተቋም ሃላፊ ይህን መሰል አረጋጊ ቃል ሲሰነዝሩ የዓለም ባንኩ ፕሬዚደንት ሮበርት ዞሊክ በበኩላቸው ዓለም በአደጋ ክልል ውስጥ እንደሚገኝና ችግሩ ታዳጊ አገሮችንም ሊያዳርስ እንደሚችል ጠበቅ አድገው ነው ያስጠነቀቁት። ዞሊክ በ 2008 ዓ.ም. ብዙዎች የፊናንሱን ቀውስ ቀድሞ መተንበዩ የሚቻል አልነበረም ማለታቸውን በመጥቀስ አሁን ፖለቲከኞች ይህን ምክንያት ይዘው ሊቀርቡ እንደማይችሉ አስገንዝበዋል። እርግጥ አብዛኞቹ ታዳጊ አገሮች የያኔው የፊናንስ ቀውስ ያስከተለውን ችግር ሊቋቋሙት ችለዋል። ግን አሁን ያ አቅም የላቸውም። ለዚህም ነው የዓለም ባንኩ ባለሥልጣን እንዳሉት የበለጸገው ዓለም ቀውስ ወደ ታዳጊዎቹ መሻገሩ የሚያሰጋው።

የአውሮፓና የአሜሪካ መንግሥታዊ የዕዳ ቀውሶች በሮበርት ዞሊክ ግምት የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም ዕቅድ ከግብ ማድረሱንም አዳጋች የሚያደርጉ ናቸው። በተቀሩት አራት ዓመታት፤ ማለትም እስከፊታችን 2015 ዓ.ም. እንደታቀደው ድህነትንና ረሃብን በግማሽ ለመቀነስ መቻሉ ሲበዛ ያጠያይቃል። በተለይም ላይቤሪያንና ሃኢቲን የመሳሰሉት በእርስበርስ ጦርነት መዘዝና በተፈጥሮ ቁጣ የተጎዱ አገሮች ከስምንት ከአንዱም ግብ ሊደርሱ አይችሉም። ይህ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

አዳጊ አገሮችን ካነሣን የበለጸጉትና በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ሃገራት ስብስብ ቡድን-ሃያ መንግሥታትም ድሆች አገሮችን ለበለጠ ብልጽግና ለመርዳት እንደሚፈልጉ በዋሺንግተኑ ጉባዔ አኳያ ገልጸዋል። እርግጥ ጭብት በሆነ መልክ የገቡት ቃል የለም። የዓለም ባንክ ግን በፊናው ለአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ረሃብተኞች የሚሰጠውን ዕርዳታ ወደ 1,9 ቢሊዮን ዶላር ከፍ አድርጓል። ይህም ከቀድሞው ሲነጻጸር አራት እጥፍ መሆኑ ነው።

በገንዘብ ተቋማቱ ዓመታዊ ጉባዔ ላይ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት በተለይም በአሕጽሮት ብሪክስ በሚል መጠሪያ የሚታወቁት ብራዚል፥ ሩሢያ፣ ሕንድ፥ ቻይናና ደቡብ አፍሪቃ ዘንድሮ የበለጠ ትኩረት አግኝተዋል። ይህም ያለ ምክንያት አይደለም። እነዚህ አገሮች በኤኮኖሚ ትልቅ እመርታ ሲያደርጉ የፊናንስ ይዞታቸውም የተረጋጋ ነው። በቢሊዮኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪን ያሰባሰቡ በመሆናቸውም የከሰሩትን የኤውሮ ባለ ዕዳ አገሮች ምናልባትም ለዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ተጨማሪ ካፒታል በማቅረብ በተዘዋዋሪ መንገድ ሊያግዙ ይችላሉ። የምንዛሪው ተቋምም 187 ዓባል ሃገራቱን የክፍያ ችግር ሲኖራቸውና በዕዳ ሲዋጡ የማገዝ ሃላፊነት አለበት።
ለሁሉም ነገር አሁን ለተፈጠረው የዕዳ ችግር መፍትሄ ለማስፈን ቁልፉ በአሜሪካና በአውሮፓ መንግሥታቱ ከባድ የሆነ የኤኮኖሚ ችግራቸውን በመቋቋም የበጀት ቀውሣቸውን ማለዘብ መቻላቸው ነው። አለበለዚያ ችግሩ ይበልጥ እያደገ ነው የሚሄደው። ይህን ዝም ብሎ መታዘቡ ደግሞ ሃላፊነት የጎደለው ይሆናል።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic