የዓለም ኤኮኖሚና የምንዛሪው ተቋም | ኤኮኖሚ | DW | 20.04.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ኤኮኖሚና የምንዛሪው ተቋም

የዓለም ኤኮኖሚ እርግጥ ከቀውሱ ቢያገግምም በሌላ በኩል ግን የፊናንስና የኤኮኖሚው ስርዓቱ ገና ጨርሶ ከውድቀት አደጋ አላመለጠም።

default

የምግብ ዋጋ መናር ደግሞ በተለይም ድሆች አገሮችን ከባሰ ችግር ላይ እንዳይጥል አስግቷል። ይህ ባለፈው ሣምንት ዋሺንግተን ላይ ተካሂዶ የነበረው የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋምና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ጉባዔ ከስብሰባው በኋላ የደረሰበት ድምዳሜ ነው። አሁንም በቀውስ ውስጥ እንዳለን ነው። የዓለም ኤኮኖሚ አዲስ አደጋ ተደቅኖበታል! የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋምና የዓለም ባንክ ጉባዔ ባለፈው ሰንበት ያበቃው ይህን ማስጠንቀቂያ በመሰንዘር ነበር።

“በዛሬው ዕለት አጉልቼ ለማሳሰብ የምፈልገው በእርካታ መጠመድ እንደማይገባን ነው”

የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም አስተዳዳሪ ዶሚኒክ-ሽትራውስ-ካህን! የምግብ ዋጋ መናር መልሶ የራስ ምታት መሆኑ አልቀረም። የነዳጅ ዘይት ዋጋም እንዲሁ በወቅቱ እያደገ በመሄድ ላይ ነው። በኤኮኖሚ በበለጸጉት መንግሥታት መካከል ያለው የሚዛን መፋለስ፣ የመንግሥት ዕዳ ከመጠን በላይ ማደግና የፊናንሱ ዘርፍ ቁጥጥር ደግሞ ገና በሚገባ አለመስፈን፤ እነዚህ ሁሉ ብዙ አነጋግረዋል።

ከዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ዱብ ዕዳ ከሶሥት ዓመታት ገደማ በኋላ ችግሩ በአስተማማኝ ሁኔታ አለማለፉ ነው የሚታየው። በወቅቱ በሰሜን አፍሪቃና በመካከለኛው ምሥራቅ የሰፈነው የፖለቲካ ነውጽ፣ የኑሮ ውድነት መየል፣ የጥሬ ዕቃዎች ዋጋ እየጨመረ መሄድና ምናልባትም ጃፓንን ያጠቃው የተፈጥሮ ቁጣ ተደማምረው ሂደቱን ቀላል አያደርጉትም። ይሄ ሁሉ የሚያሰው የዓለም የፊናንስና የኤኮኖሚ ሁኔታ ተገቢውን ዓቅድ ያልያዘ መሆኑን ነው። የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ሮበርት ዞሊክ በተለይ ከሁሉም በላይ የጎርጎሮሣውያኑ 2008 ዓ.ም. የምግብ ምርቶች ቀውስ እንዳይደገም ነው ያስጠነቀቁት።

“የምግብ ምርቶችን ዋጋ በተመለከተ በወቅቱ ከአንድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰናል። ዋጋው ካለፈው ዓመት ሲነጻጸር በአሁኑ ጊዜ 36 በመቶ ከፍ ብሎና ከ 2008-ቱ ደረጃ ተጠግቶ ነው የሚገኘው። ካለፈው ሰኔ ወር ወዲህ ተጨማሪ 44 ሚሊዮን የዓለም ሕዝብ ከዝቅተኛው የድህነት መስፈርት በታች ወድቋል። እነዚህ ሰዎች በቀን 1,25 ዶላር በሆነች ገቢ ለመኖር መታገል ይኖርባቸዋል ማለት ነው። የምግብ ዋጋው እንደገና በአሥር ከመቶ ያህል ከጨመረ ሌላ አሥር ሚሊዮን ሕዝብ ከድህነቱ መስፈርት በታች እንደሚያቆለቁል ነው የምንገምተው”

የዋጋው ንረት ሰላሣ በመቶ ከፍ ቢል ደግሞ 34 ሚሊዮን ሕዝብን ለከፋው ድህነት ይዳርጋል። አጠቃላዩ አሃዝ እንግዲህ ወደ 1,2 ሚሊያርድ ሕዝብ ከፍ ይላል ማለት ነው። ለወቅቱ የዋጋ መናር የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ የተነሣ ምርት መጓደሉ አንዱ ነው። ከዚሁ ሌላ የባዮ ነዳጅ ምርት እየጨመረ መሄድ፣ የምግብ የክምችት ጉድለት፣ የሕዝብ አየመጋገብ ዘይቤ መቀየርና የትርፍ አጋባሾች ተንኮልም ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው። የዚህ ሁሉ ሰለቦች ደግሞ ሁሌም የታዳጊው ዓለም ድሃ ሕዝብ እንጂ ሌላ አይደለም።

“የዓለማችን ድሆች ለመጠበቅ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ አይገኙም። በዚህ በዋና ሕንጻችን ፊት አንድ የረሃብ መቁጠሪያ ሰዓት ሰቅለናል። አንድ ሚሊያርድ ገደማ የሚጠጋ ሕዝብ በቂ ምግብ እንደማያገኝ የሚያሳይ ነው። ይህ አሃዝ ደግሞ በየደቂቃው በ 68 ሰዎች እንደሚጨምር መታወቅ ይኖርበታል። በሤኮንድ ከአንድ ሰው በላይ ማለት ነው። እንግዲህ ጊዜ ማባከን የለብንም። አንድ ጠቅላላ ትውልድን እንዳናጣ ከፈለግን ጥረታችንን ማጠናከር ይኖርብናል”

የዓለም ባንኩ ፕሬዚደንት ሮበርት ዞሊክ ፈረንሣይ በቡድን-ሃያ መንግሥታት ርዕስነት ዘመኗ በወቅቱ ይህን የምግብ ዋጋ መናር ጉዳይ ዓቢይ ርዕስ በማድረጓ በጣሙን ነው የተደሰቱት። የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋምም በፊናቸው በዓለም የእርሻ ምርት ገበዮች ላይ የትርፍ አጋባሾችን ተንኮል ለመቋቋም ዕርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገብተዋል። ጀርመንም የአገሪቱ የልማት ሚኒስትር ዲርክ ኒብል እንደሚሉት የዓለም ባንክ በዓለም ዙሪያ የምግብ ዋጋን ለመቀነስ በሚያደርገው ጥረት ለማገዝ ዝግጁ ናት።

“ጀርመን እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ በጠቅላላው በገጠር ልማት 2,1 ሚሊያርድ ኤውሮ፤ ማለት ሶሥት ሚሊያርድ ዶላር በሥራ ላይ ለማዋል ታስባለች’”

በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት ሃገራት ላይ እናተኩርና በተለይም ዩ,ኤስ.አሜሪካ በዋሺንግተኑ የገንዘብ ተቋማት ስብሰባ ላይ ወደደችም ጠላች ብዙ ትችት ማድመጡ ግድ ነው የሆነባት። ከሩሢያና ከብራዚል ተጠሪዎች በኩል እንደተጠቀሰው አሜሪካና መሰሎቿ በዓለም ኤኮኖሚና በሌሎች አገሮች ላይ አደገኛ ሊሆን የሚችል የዕዳ ፖሊሲን ነው የተከተሉት። የአሜሪካው የገንዘብ ሚኒስትር ቲሞቲይ ጋይትነር በበኩላቸው መንግሥታቸው ቁርጠኛ በሆነ የቁጠባ መርህ በያዝነው ዓመት የበጀት ኪሣራውን 11 ከመቶ እንደሚቀንስ ቃል ገብተዋል። ጥያቄው ሃሣቡ ገቢር መሆኑ ላይ ነው።

የምንዛሪው ተቋም የአይ.ኤም.ኤፍ. ሃላፊ ዶሚኒክ-ሽትራውስ-ካህን ከኤውሮ ምንዛሪ አገሮች የዕዳ ቀውስ እስከ ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ዕድገት የሚዛን ዝቤት ያለውን ሁሉ በመጥቀስ ችግሩን በሚገባ መወጣት እንዳልተቻለ ነው ያስገነዘቡት። የዓለም ኤኮኖሚ ምንም እንኳ በመሻሻል ሂደት ላይ ቢሆንም አዳዲስ የሥራ መስኮችን ሊፈጥር አለመቻሉን በተለይ አሳሳቢ አድርገው መመልከታቸውም አልቀረም።

“የምንፈልገው ሥራ ነው። ሥራ፣ ሥራ ያስፈልገናል። የኤኮኖሚው ማገገም በሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ መሻሻል በመከሰት ፈንታ በጥቅል የኤኮኖሚ አሃዞች የሚገለጽ ከሆነ ይህ ጥሩ ነገር አይደለም። ግብጽንና ቱኒዚያን እንደ ምሳሌ እንውሰድ! የነዚህ አገሮች የብሄራዊ ኤኮኖሚ ዕድገት መጠን ግሩም ነበር። ነገር ግን ሕዝቡ የተሻለ ነገር አላየም። የለውጥ ስሜት ሊሰማውም አልቻለም”

በኢንዱስትሪ ልማት ወደበለጸጉት ቀደምት ሃገራት እንመለስና በውስጣቸው ባለው ንጽጽር ከዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በኋላ ከሁሉም ይልቅ በጤናማ የኤኮኖሚ ሁኔታ ላይ የምትገኘው ጀርመን ናት። በያዝነው ወር መጨረሻ ስንብት የሚያደርጉት የአገሪቱ ፌደራል ባንክ ፕሬዚደንት አክስል ቬበር እንዳረጋገጡት የጀርመን ኤኮኖሚ ወደፊትም በዕድገት መስመሩ የሚቀጥል ነው። ብሄራዊው ኤኮኖሚ በዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ፈጣን ዕድገት ታይቶበታል።
ኤኮኖሚውን የማረጋጋቱ ጥረት ካልተዳከመም እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ የበጀት ኪሣራውን ወደ 2 ከመቶ ዝቅ ለማድረግ እንደሚችል አክስል ቬበር ተንብየዋል። ይህም በማስትሪሽት ውል ለአውሮፓ ሕብረት አገሮች ከተቀመጠው ሶሥት በመቶ የበጀት ኪሣራ መስፈርት እጅጉን ዝቅ ያለ መሆኑ ነው። የጀርመኑ የኤኮኖሚ ዕድገቱ ብዙዎች የአውሮፓ አገሮች በወቅቱ ሊያስቡት ቀርቶ ሊያልሙት እንኳ የሚችሉት ነገር አይደለም።

ለማንኛውም ዓለምአቀፉን የኤኮኖሚ ስርዓት በአጠቃላይ አስተማማኝ ለማድረግ በቡድን-ሃያ ውስጥ የተጠቃለሉት የበለጸጉና በተፋጠነ ዕድገት ላይ ያሉ ሃገራት ሰሞኑን በአንድ መርሀ ተስማምተዋል። ይህም ለምሳሌ አንድ አገር ትልቅ ከሆነ የንግድ ኪሣራ ላይ ሲወድቅ ወይም የዕዳው መጠን በጣም ከፍ ብሎ ሲገኝ ቀድሞ ለመለየት መቻል ነው። በዚህ መንገድ ወደፊት ፍቱን የጋራ ዕርምጃን ለመውሰድ እንደሚቻል ዕምነት አለ።

በአፍሪቃ ላይ ካተኮርን ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ያመለከተው ከደቡብ አፍሪቃ መጎተት በስተቀር አብዛኞቹ አገሮች ባለፈው 2010 ዓ.ም. ጠንካራ የኤኮኖሚ ዕድገት ማድረጋቸውን ነው። በጥቅሉ ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል በዚህ ዓመት በአማካይ 5,5 ከመቶ፣ እንዲሁም በሚቀጥለው ዓመት 6 ከመቶ ዕድገት እንደሚያደርግ አዲስ ግምት ተሰጥቷል። እርግጥ የነዳጅ ዘይትና የምግብ ዋጋ መናር በተወሰኑ የአፍሪቃ አገሮች ዕድገትን ሊጫን እንደሚችል አብሮ መጠቀሱም አልቀረም።

የደቡብ አፍሪቃ ዕድገት በ 3,5 ከመቶ ሲገመት ትልቁ የዕድገት ድርሻ ያተኮረው በምዕራው አፍሪቃይቱ ጋና ላይ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነዳጅ ዘይት አምራች ለመሆን የበቃችው አገር በ 13,75 ከመቶ ከፍተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት እንደምታደርግ ይጠበቃል። ኬንያና ኢትዮጵያም የተፋጠነ ዕድገት ያደርጋሉ ከተባሉት መካከል ናቸው። በጠቅላላው ነዳጅ ዘይት አምራች የሆኑት የአፍሪቃ አገሮች በዋጋው መጨመር መልሰው አትራፊ እንደሚሆኑ ነው የተጠቀሰው።
የምንዛሪው ተቋም በሌላ በኩል አፍሪቃ ውስጥ ዘንድሮ 17 ብሄራዊ ምርጫዎች ሊካሄዱ መታቀዳቸውን በማመልከት የአንዳንድ አገሮች ዕድገት በፖለቲካ ዓመጽ ሳቢያ ሊሰናከል እንደሚችልም አስጠንቅቋል። ያም ሆነ ይህ የሰሞኑ የዋሺንግተን ጉባዔ አጠቃላይ መልዕክት የዓለም ኤኮኖሚ በማገገም ላይ ነው፤ ግን ጨርሶ ከቀውስ አላመለጠም የሚል ነው።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ