የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እና አዲሱ ተሿሚው | ኤኮኖሚ | DW | 11.03.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እና አዲሱ ተሿሚው

የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ዳይሬክተር የነበሩት ጀርመናዊው ሆረስት ከህለርን የሚተካው ሰው በመልማት ላይ ካሉ ሃገሮች እንዲሆን ጥሪ ቀረበ ። ከህለርን የሚተካው ሰውን ለመምረጥም የሚደረገው የቀለም እና የዘር ምርጫ ቀርቶ በሙያ ብቃቱ እና ችሎታው በግልፅ ውድድር እንዲሆን ‘’ ጂ ሃያ አራት ‘’ የተሰኘው ቡድን ጠይቋል ። በመልማት ላይ ካሉ ሃገሮች ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች እንዳሉም በመጠቆም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን የሚመሩት ከበከፀጉት ሃገራት

የመሆኑ ተግባር እንዲቀር አሳስቧል ።

ከህለር በመጪው ግንቦት የጀርመን ርዕሰ ብሄር ዮሃንስ ራውን እንዲተኩ መታጨታቸው ቢታወቅም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ የበላይ ኃላፊነታቸው ቀድመው የመልቀቃቸው ጉዳይ ግን ያልተጠበቀ ነው ። ስልጣን እንደሚለቁ ያስታወቁትም ልክ የዛሬ ሳምንት ነበር ። ከአምስት ዓመቱ የሥራ ዘመናቸው አንዱን በመተው ስልጣን የለቀቁት በሃገራቸው የተቃዋሚ ማህበራት ለታጩበት ፕሬዝዳንትነት እርግጠኛ ሆነው ለመሆኑ ግን የጊዜን ማረጋገጫ ይጠይቃል ። ሆኖም ከሶሻል ዲሞክራት እጩዋና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ጌይሰን ሻቫን ጋር ይፎካከራሉ ። ከህለር በለቀቁት ቦታ ማን ይቀመጥ የሚለው ጉዳይ እያነጋገረ ነው ። ጀርመን ሌላ የሃገሯ ሰው ቦታውን እንዲተካ መፈለጓ አይቀርም ። እንዲሁም እንደ እስከዛሬው ልምድ ቦታው እንዲያዝ የሚፈለገው በኢንዱስትሪ ከበለፀጉት ከምዕራባውያን ሃገራት ነው ። ሆኖም ይህ ልምድ መቀየር እና መለወጥ አለበት ሲሉ በመልማት ላይ ያሉ ሃገራት ዘመቻ ላይ ናቸው ።

‘’ጂ ሃያ አራት’’ የተባለው እና በዓለም የገንዘብ ድርጅት እንዲሁም በዓለም ባንክ ውስጥ እንደ አንድ አካል የሚቆጠረው ቡድን ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ። ቡድኑ የሚወክለው በመልማት ላይ ያሉትን ሃገራት ነው ። የቡድኑ ዳይሬክተር ፤ የሜክሲኮ ተወላጅ እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አርያል ቡይራ እንዳሉት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማቱ ባላቸው ኃላፊነት ዓለምን በአጠቃላይ ይወክላሉ ማለት አይቻልም ። ችሎታ ያለው በምዕራባውያኑ ዘንድ ብቻ ነው የሚል የተሳሳተ አመለካከት በመኖሩም የገንዘብ ተቋማቱን የሚመሩት በተለይም ከአውሮጳውያን ዘንድ የሚመረጡ ብቻ ናቸው ብለዋል ። ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ በመልማት ላይ ያሉ ሃገራት ተሳትፎ የሚገለፀው ከአበዳሪ ሃገሮች የሚገኘውን ገንዘብ በመጠቀም ብቻ ነው ። የገንዘብ ተቋማቱ ከፍተኛ ተጠቃሚዎች እንደመሆናችንም ከአመራሩም መጋራት አለብን የሚሉት ቡይራ ከሰማንያ እስከ ሰማንያ አምስት በመቶ ያህል የሚሆኑት ከፍተኛ የገንዘብ ተቋማቱ የስልጣን እርከኖች የተያዙት በእንዱስትሪ በበለፀጉት ሃገራት ሰዎች እንደሆነም ገልፀዋል ።

የጂ ሃያ አራት ቡድን አባላትን የሚያስጨንካቸው ሌላ ጉዳይ አለ ። አብዛኛው የዓለም የገንዘብ ድርጅት በጀት ዩናይትድስቴትስን ጨምሮ የጥቂቶቹ የበለፀጉት ሃገራት መዋጮ በመሆኑ መንግስታት ገንዘቡን ለማግኘት መዋቅራዊ ለውጥ እና ማስተካከል ግዴታ ስለሚጣልባቸው ማህበራዊ መናጋት እየተፈጠረ ነው ። አለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ዋናዎቹ አበዳሪዎች በመሆናቸውም በመልማት ላይ ያሉት ሃገራት ለተቋማቱ ግዴታዎች መገዛታቸው የግድ ነው ። በመሆኑም ወቅቱ የሌሎች አበዳሪዎች መጠናከርን ጠይቋል ። ነገር ግን ‘’ ለጂ ሃያ አራት ’’ ቡድን ቀደሚው ጉዳይ ከህለርን የሚተካው ሰው ማን ይሁን ? የሚለው ጥያቄ ነው ። ቡድኑ እንደ ከዚህ ቀደም ሁሉ በዘር ላይ ያልተመሰረተ ውድድር እና ግልጽ ቃለመጠይቆች እንዲኖሩ ይፈለጋል ። ከህለርን መተካት የሚገባውም ከጂ ሃያ አራት ቡድን አባላት ሃገራት ውስጥ መሆን አለበት የሚል አቋም እየተንፀባረቀ ነው ። በቂ ችሎታ ያላቸው ዕጩ ተዋዳዳሪዎች አሉን በማለትም ሰዎች ተጠቁመዋል ። ቡይራ ለጊዜው ያስታወሱዋቸውን ስሞች ሲገልፁ እንዳሉት ከዕጩ ተዋዳዳሪዎቹ ውስጥ የቀድሞ የህንድ የገንዘብ ሚንስትር ማንሞሃን ሲይንግ ፣ ሁለቱ ብራዚሊያውያን ፔድሮ ማላን እና አርሚኒዮ ፍራጋ እንዲሁም የቀድሞው የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ኤርኔስቶ ዜዲሎ ይገኙበታል ። በአውሮጳ በኩል እጩ ሆነው ይቀርባሉ ተብሎ እየተነገረላቸው የሚገኙት የስፓኝ የገንዘብ ሚንስትር ሮዲሪጎ ራቶ ናቸው ።

የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት እንደተመሰረተ ከግዛቷ ውጭ የተረፈ ሃብት ያላት ብቸኛ ሃገር ዩናይትድስቴትስ ነበረች ። ዛሬ ግን በመልማት ላይ ያሉ ሃገሮች ፤ በተለይም በእስያ አበዳሪ እና ከፍተኛ ላኪ ሃገራት ተፈጥረዋል ። ለምሳሌ ብዙ ህዝብ ያላት ደቡብ ኮሪያ በምርት ላኪነት እና ሃብት በማካበት ከዴንማርክ ጋር ስትወዳደር ከፍተኛ ብልጫ ያላት ሲሆን በዓለም የገንዘብ ድርጅት በአይ ኤም ኤፍ ውስጥ ያላት የኮታ ድርሻ ግን እጅግ አነስተኛ ነው ። እንዲሁም ቤልጄም ከላቲን አሜሪካ ሃገሮቹ ከብራዚል እና ከሜክሲኮ ጋር ስትነጻፀር በአይ ኤም ኤፍ ውስጥ ያላት የኮታ ድርሻ ከፍ ያለ ነው ። ሆኖም የቤልጄም የምጣኔ ሃብት ዕድገት ጠቋሚ መረጃ እንደሚያሳየው ከሁለቱ ሃገራት እጅግ አንሶ ይገኛል ። ስለዚህም ይላሉ ቡይራ እነዚህ ጉዳዮች በሙሉ ግምት ውስጥ ገብተው አዲሱ ተሿሚ ሊመረጥ ይገባል ።