የዓለም ንግድ ድርጅት ጉባዔ መክሸፍ | ኤኮኖሚ | DW | 17.09.2003
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ንግድ ድርጅት ጉባዔ መክሸፍ

ባለፈው ሣምንት በሜክሢኮ የቱሪስት መዝናኛ ሥፍራ ካንኩን ላይ የተካሄደው የዓለም ንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባዔ ከታሰበው ግብ ሳይደርስ ቀርቷል። የድርጅቱ 148 ሃገራት ሚኒስትሮች ያካሄዱት ክርክርና ጽኑ የሃሣብ ልዩነት ከዚህ ቀደም ያልተለመደ ጥንካሬ የተከሰተበት ነበር። የታዳጊው ዓለም ተጠሪዎችም እንዳሁኑ አንድ ሆነው የቆሙበትና በኢንዱስትሪ ልማት ለበለጸጉት መንግሥታት ግፊት አንንበረከክም ያሉበት ጊዜ አይታወስም። ታዳጊዎቹ አገሮች ጥቅማቸውን ለማስከበር ያደረጉት ትግልና ያሳዩት ቁርጠኛነት እስካሁን በሃብታሙ ወገን ዘዋሪነት ሲንቀሳቀስ ለቆየው የዓለም ንግድ ሥርዓት መለወጥ ዋዜማውን ማብሰሩ ይሆን? ለማንኛውም የታዳጊዎቹ ሃገራት ተጠሪዎችና ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች የጉባዔውን በዚህ መልክ መክሸፍ እንደ አንድ ታላቅ ድል አድርገው ነው የተመለከቱት። የዛሬው ዝግጅታችን ይህንኑ ጉዳይ መነሻ-መድረሻ ያደረገ ይሆናል።

ሜክሢኮ-ካንኩን ላይ የተካሄደው የዓለም ንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባዔ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው የታዳጊውና የበለጸገው ዓለም ቅራኔ የጋረደው ሆኖ ነው ያለፈው። ስለዚህም ውሣኔዎችን በአንድ ድምጽ ብቻ የማስተላለፍ መርህ ያለው የዓለም ንግድ ድርጅት አስታራቂ ከሆነ ስምምነት መድረሱ እንደሚያዳግት በጉባዔው ሂደት ቀደም ብሎ መታየት የጀማመረው ጉዳይ ነበር። እንደተፈራውም አልቀረም የጉባዔው አመራር ታዳጊዎቹ አገሮች ቅድሚያ የሰጡትን የእርሻ ምርት ገበያ ጉዳይ ትቶ የኢንዱስትሪው መንግሥታት ቀረጥ ቅነሣንና የንግድ ማቃለያ ዋስትናን አስመልክተው ያሣዩትን ፍላጎት በማጉላት ሃሣብ በማቅረቡ ብዙዎች የሶሥተኛው ዓለም ልዑካን ባለፈው ቅዳሜ ጉባዔውን ለቀው ይወጣሉ። የጉባዔው መክሸፍ በዚሁ ሲደመደም ዕጣቸውን አንድ አድርገው የተሟገቱት የታዳጊው ዓለም መንግሥታት ግፊቱን በመቋቋም እስከመጨረሻው በሕብረት ይቆማሉ ብሎ የጠበቀም ሆነ ያመነ አልነበረም።

ለነገሩ ባለፈው ሣምንት ረቡዕ ጉባዔው ሲከፈት ከያቅጣጫው የተሰማው ንግግርና የበጎ ሃሣብ መግለጫ ሙሉ ዋስትናን አይስጥ እንጂ ተሥፋ የሰመረበት ነበር። ጉባዔውን መርቀው የከፈቱት የእተናጋጇ ሜክሢኮ ፕሬዚደንት ቪንቼንቴ ፎክስ ለተሰበሰቡት የ 146 መንግሥታት ልዑካን ባሰሙት ንግግር ዓለምአቀፉን የንግድ ሥርዓት በማለዘብ ብልጽግናን ለማሳደግ ጭብጥ ዕርምጃ ይወሰድ ዘንድ ማሳሰባቸው አልቀረም። ሆኖም የዓለም ንግድን ግንኙነት ለማለዘብ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ካታር ርዕሰ-ከተማ ዶሃ ላይ የተደረገው ስምምነትና የተጀመረው ጥረት ሊከሰት ሳይችል ቀርቷል። የበለጸጉት መንግሥታት ለታዳጊ አገሮች ገበዮቻቸውን እየከፈቱ ለመሄድና የውጭ ንግድ ምርት ድጎማቸውን ለማቆም የገቡትን ቃል በተሟላ ሁኔታ ሊወጡ አለመሻታቸው የቅርብ አዋቂዎችን እምብዛም ባያስደንቅም ለጉባዔው መከሸፍ ዋነኛው ተጠያቂ መሆናቸው ብዙዎችን ነው ያስገረመው። ታዳጊዎቹ አገሮች ከእንግዲህ ለኢንዱስትሪው ዓለም ተጽዕኖ አንንበረከክም በቃን ባሉበትና የበለጸጉት መንግሥታትም አቋማቸውን ለማለዘብ እምብዛም ፈቃደኛ ባልሆኑበት በአሁኑ ወቅት ጉዳዩ ወደፊት በምን መልክ እንደሚቀጥል በውል ለመናገር ያዳግታል።

በመሠረቱ ዛሬ የዓለም ዕጣ በአንድ የተሳሰረ ሆኖ በሚገኝበት “ዘመነ-ግሎባላይዜሺን” ለብዙዎች አገሮች ልማት ጠንቅ ሆኖ የሚገኘውን ዓቢይ ችግር ድህነትን በጋራ ለማስወገድ ከመጣር የበለጠ ዓቢይ ጉዳይ ሊኖር ባልተገባው ነበር። ይህ በተለይ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ጉባዔዎች በተካሄዱባቸው ቦታዎች ሁሉ በያጋጣሚው ሲለፈፍ የቆየ ጉዳይ ነው። በገቢር ግን ሁኔታውን ሊለውጥ የሚችል የረባ ዕርምጃ ሲወሰድ አልታየም። ድሀነትና ኋላ ቀርነትን ማስወገዱን ዒላማው ያደረገው የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒዬም ዕቅድ፣ የዕዳ ምሕረት፣ ታዳጊ አገሮች በዓለም ገበያ ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎ መሻሻል፤ ሌሎችም ድህነትን ለማለዘብና ልማትን ለማፋጠን የሚጠቅሙ ዕርምጃዎች አስፈላጊነት በየጊዜው ተነግሯል። የካንኩኑ ጉባዔ የከሸፈው የበለጸገው ዓለም በየጊዜው የገባው ቃል ገቢር ባለመሆኑና ታዳጊዎቹ አገሮችም በዚህ ፍትህ በጎደለው የዓለም ንግድ ሁኔታ ከማይቀጥሉበት ደረጃ በመድረሳቸው ነው። ሃብታሞቹ ከድጎማ ፖሊሲያቸው ሊላቀቁ አልፈለጉም፤ ዘጠና ገደማ የሚጠጉት ታዳጊ አገሮችም የኢንዱስትሪውን ዓለም ሞኖፖል ተሸክመው ሊቀጥሉ የሚችሉበት ዘመን አልፏል።

ዛሬ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ገበዮቻቸውን አጥረው በመያዛቸው ታዳጊው ዓለም የዕርሻ ምርቱን ወደዚሁ ክልል አስገብቶ ሊሸጥና ሊጠቀም በሚችልበት ሁኔታ ላይ አይገኝም። ሃብታሞቹ አገሮች ለራሳቸው ገበሬዎች መደጎሚያ በመክፈልና የታዳጊውን ዓለም ገበያ በርካሽ ምርት በመሙላት የሚከተሉት ፖሊስም ድሃው አርሶ-አደር ከማይችለው ፉክክር ላይ እንዲወድቅ ነው ያደረገው። ትርፉ የባሰ ድህነት፣ የልማት ተሥፋ እጦት መሆኑን ቀጥሏል። በካንኩኑ የዓለም ንግድ ጉባዔ የታዳጊው ዓለም ልዑካን ሊደርሱበት የፈለጉት ግብም በተለይ ይህንኑ የድጎማ ፖሊሲ ማስወገድ ነበር። G-21 በሚል ስያሜ ለጥቅማቸው በጋራ የቆሙት በዝቅተኛና በመለስተኛ የዕድገት ደረጃ የሚገኙ ታዳጊ አገሮች የበለጸጉት መንግሥታት ይህንኑ መደጎሚያ በያመት በሶሥት መቶ ሚሊያርድ ዶላር በመቀነስ እንዲያስወግዱ ጠይቀዋል። ብራዚልን፣ ሕንድንና ቻይናን የመሳሰሉት አገሮች በግንባር ቀደምነት የሚመሩት ቡድን በአቋም የሚወክለው አካባቢ ግማሹ የዓለም ሕዝብ የሚኖርበት ነው። ይህ ብቻ አይደለም፤ አብዛኛው የዓለም የተፈጥሮ ሃብትና የወደፊቱም ሰፊ ገበያ በዚያው እንደሚገኝ ይታወቃል።

በዓለም ላይ ከአንዲት ዶላር ባነሰች የቀን ገቢ የዕለት ኑሮውን የሚገፋው የምድራችን አንድ ሚሊያርድ ሕዝብ በዚሁ ታዳጊ እየተባለ በሚጠራው የዓለም ክፍል ነው የሚኖረው። የጤና ጥበቃውና የትምሕርቱ ሁኔታ ያልተሟላ ሲሆን ብዙዎች በበሽታና በአመጋገብ ጉድለት ይሞታሉ። ይሄው የከፋ ድህነት ደግሞ የልማትን ተሥፋ የመነመነ አድርጎት ይገኛል። በአንጻሩ ሃብታሙ የዓለም ሰሜናዊ ክፍል በተትረፈረፈ ምርት በድሎትና ቅንጦት ነው የሚኖረው። ይህ ፍትሃዊ ያልሆነ ሃቅ ካልተለወጠ ዛሬ በዓለም ላይ ያለው እየሰፋ የሚሄድ የዕድገት ልዩነት ሊጠብና ድህነትን ተከትሎ መስፋፋት የያዘው ቀውስ-ሽብርም ሊገታ መቻሉ ሲበዛ ያጠራጥራል። ችግሩ-መዘዙ ከረጅም ጊዜ አንጻር ለመላው ዓለም የሚተርፍ እንጂ ተጽዕኖው በታዳጊ አገሮች ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይሆንም። በካንኩኑ ጉባዔ ከአፍሪቃ እስከ ላቲን አሜሪካ የታዳጊው ዓለም ተጠሪዎች ያሰሙት ጩኽት ይህ ባለበት ሊቀጥል አይገባውም! በቃ! የሚል ነበር መልዕክቱ። ታዲያ በኢንዱስትሪ የበለጸጉት መንግሥታት ይህን ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ ጸንቶ የቆመው ወገን ያስተላለፈውን መልዕክት በሚገባ ተረድተውት ይሆን? ከሆነ ግሩም!

እንደሚታወቀው ሃብታሞቹ መንግሥታት እስካሁን በተለመደው ተጽዕኗቸው የዓለምን የፖለቲካና የኤኮኖሚ ሥርዓት እንዳሻቸው ለራሳቸው ጥቅም መሣሪያ አድርገው ሲገለገሉበት ቆይተዋል። ወደፊት ግን የግድ የሃሣብ ለውጥ ማስፈለጉ ላይቀር ነው። የካንኩኑ ጉባዔ መክሸፍ የዓለምን ንግድ ግንኙነት ለማለዘብ በተያዘው ጥረት ለሁሉም ሽንፈት መሆኑ ባያጠያይቅም ለሃብታሞቹ አገሮች ተጽዕኖና ግፊት አልፈታም ብሎ በአንድነት ለጸናው ለታዳጊው ዓለም ቡድን የመንፈስ ድል ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ከእንግዲህ የዓለም ንግድ ድርጅት የሃብታሞች ጥቅም ማራመጃ ነው ተብሎ እንዳይነቀፍ ከተፈለገ የበለጸጉት መንግሥታት ወደፊት በሚከተሉ ተመሳሳይ ድርድሮች ፍትሃዊ ሆነው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል። በዓለም የንግድ ሥርዓት ፍትሃዊ ሆኖ መስተካከል ተጠቃሚዎቹ ደግሞ ታዳጊዎቹ አገሮች ብቻ ሣይሆኑ የበለጸገው ክፍልም መሆኑ ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ ነው። በጉባዔው ውጤት-ዓልባ መሆን በወቅቱ ቀውስ ተጠናውቶት ለሚገኘው የዓለም ኤኮኖሚ በተለይም ለበለጸገው ዓለም የምጣኔ-ሐብት ችግር መለዘብ እጅግ አስፈላጊ የነበረው ማበረታቻ ምልክት ሊታይ ሳይችል ቀርቷል።

የሆነው ሆኖ የጀርመንን መንግሥትና ኢንዱስትሪዎች የመሳሰሉ አንዳንድ ወገኖች ወደፊት በሚከተሉ ተመሳሳይ ድርድሮች ከዚህ ቀደም የተገኙ ጠቃሚ ውጤቶች ጽናት ኖሯቸው እንደሚቆዩና ዕርምጃም እንደሚኖር ተሥፋ ያደርጋሉ። የአገሪቱ የምጣኔ-ሐብት ሚኒስትር ቮልፍጋንግ ክሌመንት እንዳስረዱት የጀርመን መንግሥትና በአጠቃላይም የአውሮፓው ሕብረት ተጨባጭ አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁዎች ናቸው። እርግጥ አውሮፓውያኑ መንግሥታትም ሆኑ አሜሪካ ያሉትን ይበሉ ወደፊትም ጥያቄው ዝግጁነቱ ከካንኩን የበለጠ ገፍቶ መሄዱና ታዳጊዎቹን አገሮች ሊያረካ መቻል-አለመቻሉ ላይ ነው። በካንኩን ጉባዔ ዋዜማ ብዙ ተነግሮ-ተዘክሮ ነበር። ግን ካንኩንም ካንኩን፤ ዶሃም ዶሃ ሆነው፤ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ጥቂት እንኳ ወደፊት ፈቀቅ ለማለት ሳይቻል ቀርቷል። ፋታ የማይሰጠው ድርድር እንዴትና በምን መንፈስ ሊቀጥል እንደሚችል ጀኔቫ ላይ ተቀማጭ የሆነው የዓለም ንግድ ድርጅት በሚቀጥለው ዓመት የሚያካሂደው ስብሰባ እስከሚደርስ ጠብቆ መታዘቡ ግድ ነው።