የዓለም ንግድ ድርጅት ጉባዔና የዶሃ ዙር | ኤኮኖሚ | DW | 02.12.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ንግድ ድርጅት ጉባዔና የዶሃ ዙር

ጄኔቫ ላይ ባለፈው ሰኞ የተከፈተው የዓለም ንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ስብሰባ በዛሬው ዕለት ይጠቃለላል።

ፓስካል ላሚይ

ፓስካል ላሚይ

የጉባዔው ዋና ዋና የአጀንዳ አርዕስት የድርጅቱን ደምቦች የዓለም ኤኮኖሚ ሂደት ከደቀነው ጊዜያዊ ሁኔታ ማጣጣም፣ የአካባቢ አየር ለውጥ ተጽዕኖና በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ሃገራት ፍላጎት ናቸው። ይሁን እንጂ የዓለም ንግድን ፍትሃዊ ለማድረግ ከስምንት ዓመታት በፊት የተጀመረውን የዶሃን ድርድር ዙር መልሶ ማነቃቃቱና ማሰሪያ የሚያገኝበትን መንገድ ማፈላለጉም ከበስተጀርባ ብዙ እያነጋገረ ያለው ጉዳይ ነው። በሌሎች ስብሰባዎች እንደተለመደው ሁሉ እስከሚቀጥለው ዓመት የጊዜ ገደብ የተጣለለት ድርድር ከግቡ እንዲደርስ አሁንም መወትወቱ አልቀረም። ለመሆኑ ስምምነቱ ቀርቶ ከወቅቱ ጉባዔ ጥርጊያ ከፋች ጭብጥ ዕርምጃ እንኳ ሊጠበቅ ይችላል ወይ? የብዙዎች ታዛቢዎች ዕምነትም ሆነ የሰሞኑ የስብሰባ ሂደትም ያን ያህል ተሥፋን የሚያጠነክር ሆኖ አይገኝም።

የዓለም ንግድ ድርጅት ሰባተኛ የሚኒስትሮች ስብሰባ በዛሬው ዕለት ሂደት የሚጠናቀቅ ሲሆን በተለይ ብዙዎች ታዳጊ አገሮች እንደሚጠይቁት የዓለም ንግድን ፍትሃዊ ለማድረግ ሲጓተት የኖረውን የዶሃን ድርድር ዙር መልሶ ማነቃቃት መቻሉ የሚያጠራጥር ነው። በጉባዔው አኳያ የዶሃ ጉዳይ መልሶ እንዳይሽጋሸግ ወይም ጨርሶ እንዳይተው ለማድረግ ሰሞኑን የረባ ዕርምጃን የሚጠቁሙ ምልክቶች አልታዩም። የዶሃው ድርድር ታዳጊ አገሮች በአንድ በኩል የእርሻ ምርቶቻቸው ያለ ገደብ ወደ ምዕራቡ ገበዮች እንዲዘልቁ በሌላም ሃብታሞቹ አገሮች ታዳጊዎቹ የኤኮኖሚ ፖሊሲያቸውን ለበለጸጉት መዋዕለ-ነዋይና የአልግሎት ዘርፍ እንዲከፍቱ በየፊናቸው የሚያደርጉት ግፊት ባስከተለው ቅራኔ የተነሣ ስምንት ዓመታት ሲጓተት ቆይቷል። ሁኔታው በዛሬው የኤኮኖሚ ቀውስ ወቅት ደግሞ ይብስ እንደሆን እንጂ መሻሻሉ ብዙም አይጠበቅም።

የዓለም ንግድ ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ፓስካል ላሚይ እንኳ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ስኬት-አልባ ሆነው ከታዩት አምሥት የሚኒስትሮች ስብሰባዎች በኋላ ተሥፋ በመስጠቱ ረገድ ቆጠብ ማለታቸው አልቀረም። በዕውነትም መለስ ብሎ ላስታወሰ የዓለም ንግድ ድርጅት ጉባዔዎች በየጊዜው የተጠበቀባቸውን ዕርምጃዎች ማስከተሉ ቀርቶ ጥርጊያ አመቻች ለመሆን እንኳ የበቁ አልነበሩም። እ.ጎ.አ. በሕዳር ወር. 1999 ዓ.ም. በአሜሪካ-ሴአትል ላይ የተከፈተው የድርጅቱ የሚኒስትሮች ስብሰባ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የዓለምአቀፉ ኤኮኖሚ ስርዓት ተቃዋሚዎች ባደረጉት ግፊት ይቋረጣል። የዓለምን ንግድ ፍትሃዊ ለማድረግ በሚል የዶሃ ድርድር ዙር ጥሪ ከተሰነዘረ ከ 2001 በኋላ የተከተሉት አራት የሚኒስትር ስብሰባዎችም እንዲሁ ከተባለው ግብ ለማድረስ ያበቁ አልነበሩም። በጉዳዩ ተራ በተራ ነው የከሽፉት። ፓስካል ላሚይ እንደገለጹት በወቅቱም የሚኒስትሮች ስብሰባ ዋዜማ የድርጅቱ 153 ዓባል መንግሥታት የንግድ ልዑካን እስካለፈው አርብ ያደረጉት ውይይት ምናልባት ጥቂት ቴክኒካዊ ዕርምጃ ታይቶበት እንደሆን እንጂ ወሣኝ የፖሊሲ እመርታ ተደርጎበታል ለማለት አያስደፍርም አልነበረም።

“ከመስከረም ወዲህ የሚካሄደው ድርድር በጥቅሉ ሲመዘን እርግጥ በአንዳንድ ቴክኒካዊ ዝርዝሮች ላይ ዕርምጃ ማድረጋችንን ያሳያል። በዓበይት ርዕሶች ላይ ያሉትን ልዩነቶች ግን አሁንም ለማስወገድ አልቻልንም። በዚህ ረገድ ጥረቱ መጠናከር ይኖርበታል ማለት ነው”

ፓስካል ላሚይ አያይዘው እንዳስረዱት በዶሃው የድርድር ዙር አብዛኛው፤ ማለት 80 በመቶ የሚሆነው መደራደሪያ ጉዳይ ማሰሪያ አግኝቷል። ሆኖም የተቀረው መንገድ ቅርብ የመምሰሉን ያህል ድርድሩም እየከበደ መሄዱም የሚታይ ነው። ችግሩን ለማቃለል ሁሉም በወቅቱ የሚጠብቁት የአሜሪካን ዕርምጃ ነው። የአሜሪካ መንግሥት በመሠረቱ ከአንድነት የተደረሰበትን የንግድ ማቃለያ ፓኬት ጥያቄ ላይ ጥሎታል። ዋሺንግተን ራመድ ካሉት አገሮች ከሕንድ፣ ከቻይናና ከብራዚል ጋር አዲስ ድርድር ጀምራለች። ምርቶቿ ወደነዚሁ ሃገራት ገበዮች ይበልጥ የሚገቡበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው የምትፈልገው። ግን በተለይ ሕንድ ለአሜሪካ ግፊት በረላሉ የምትንበረከክ አልሆነችም። የሁለቱ ወገን ተጠሪዎች በጄኔቫው ስብሰባ አኳያ ደጋግመው ቢነጋገሩም እስካሁንወደፊት ፈቀቅ አላሉም።
ባለፈው 2008 ዓ.ም. የዓለም ንግድ ድርጅት ስምምነት ሊሰፍን ከተቃረበ በኋላ በመጨረሻ መክሸፉ ይታወሣል። የድርጅቱ ጠቅላይ ጸሐፊ ፓስካል ላሚይ አሁን ግፊት የሚያደርጉት ስምምነቱ ለሚቀጥለው 2010 ዓ.ም. በተጣለው የጊዜ ገደብ ውስጥ ዕውን እንዲሆን ነው። ይህ እንዲሆን በተለይ የአሜሪካ አቋም’ ለዘብ ማለቱ ምርጫ የሚኖረው አይመስልም። በሌላ በኩል እንደ አውሮፓው ሕብረት ልዑክ እንደ ኤካርድ ጉት ከሆነ የሚጠበቀው ስምምነት በሕብረቱ የሚሰናከል አይሆንም። አውሮፓ ለአስታራቂ መፍትሄ ዝግጁ ናት ማለት ነው።

Schweiz Anti WTO Demonstration

ጉባኤዉን የተቃወመ ሰልፍ በጄኔቭ

“በ 2008 ዓ.ም. ጠረጴዛ ላይ ቀርቦ የነበረው ፓኬት እንደ መላው የድርድር ፓኬቶች ሁሉ ማንንም ሙሉ በሙሉ የሚያረካ አልነበረም። እንዲሁ ደግሞ ማንም ጨርሶ የሚንቀውም አይደለም። ለነገሩ የአውሮፓ ሕብረት በይዘቱ ብዙ ችግር ነበረው። እንዲህም ሆኖ ግን እያንዳንዱ የተወሰነ ወስዶ የተወሰነም የሚሰጥበት አስታራቂ መፍትሄ እንዲገኝ ሲል የሚመጣውን ድርድር ውጤት ተቀብሎ ለመኖር ፈቃደኛ ነው”

ይሁንና ጠቅላይ ጸሐፊ ፓስካል ላሚይ የረባ የድርድር ዕርምጃ አለመታየቱን በማጤን የሰሞኑን የሚኒስትሮች ስብሰባ መሰላል ሆን ብለው ዝቅ አድርገው ነው ያስቀመጡት። ባለፉት አሥር ዓመታት ሲያከራክሩ የቆዩት ጥያቄዎች በሚኒስትሮቹ ስብሰባ ላይ ቢቀር ግንባር-ቀደም የአጀንዳ ርዕስ እንዲሆኑ አልፈለጉም። ከዚሁ ይልቅ ጉባዔው ከወቅቱ የዓለም የኤኮኖሚ ቀውስ አንጻር ጠቃሚ በሚላቸው ጉዳዮች እንዲነጋገር ዕድል ለመስጠት ነበር የተወጠነው። የሆነው ሆኖ ኦክስፋምንና አታክን የመሳሰሉ የዓለምአቀፉ ኤኮኖሚ ስርዓት ተቺ ማሕበራት በተለያየ ሰልፍ በጉባዔው ላይ ግፊት ለማድረግ ሞክረዋል። እነዚሁ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸገው የሰሜኑ ዓለም ድርድሩን በመጠቀም ታዳጊ አገሮች የእርሻ ገበዮቻቸውን ይበልጥ እንዲከፍቱ፤ የአገልግሎቱን መስክም፤ የትምሕርትና የውሃውን መስክ ሳይቀር በግል ዕጅ እንዲያስገቡ ግፊት ያደርጉበታል የሚል ስጋት አላቸው።
እነዚሁ ድርጅቶች፤ እንዲሁም የዓለም ንግድ ድርጅት የአፍሪቃ የእሢያና የላቲን አሜሪካ ዓባል ሃገራት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት የራሳቸውን የእርሻ ገበዮች እስካሁን ካለው በበለጠ ለታዳጊው የደቡቡ ዓለም ምርቶች ለመክፈትና ለገበሬዎቻቸው የሚሰጡትን የውጭ ንግድ ድጎማ ለማቆም ዝግጁ አይደሉም ሲሉም ይወቅሳሉ። ኦክስፋም ለምሳሌ በአውሮፓ ሕብረት የሚደጎም የዱቄት ወተት በባንግላዴሽ እያደረሰ ያለውን ተጽዕኖ በቅርቡ ባካሄደው አንድ ጥናት ውጤት አመልክቷል። በጥናቱ መሠረት በወቅቱ በድጎማ የሚመረተው የሕብረቱ ዱቄት ወተት በባንግላዴሽ ከሚመረተው ትኩስ ወተት ሲነጻጸር ርካሽ ነው። መዘዙም ለብዙዎች መትረፉ አልቀረም። በአውሮፓ ሕብረት የተያዘው የዋጋ ማጣጣል ባንግላዴሽ ውስጥ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብን ብርቱ ከሆነ የሕልውና አደጋ ላይ ጥሏል።

በአጠቃላይ ዛሬ በሚገባደደው የጀኔቫ የሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ የዶሃን ዙር በተመለከተ ወሣኝ ዕርምጃ አይጠበቅም። ለመጠበቅ የሚያበረታታ ሁኔታም አልታየም። በዚህ በጀርመን የኪል የምጣኔ-ሐብት ኢንስቲቲዩት ምክትል ፕሬዚደንት ሮልፍ ላንግሃመር እንደሚሉት በተለይ በዚህ የቀውስ ወቅት ከአንድ ግብ ለመድረስ ሁኔታው ቀላል አይደለም። የዓለም ንግድ ባለፈው ዓመት ከአሥር በመቶ በላይ ነው ያቆለቆለው። በሚቀጥለው ዓመትም ምናልባት ሻል ይበል እንጂ ድርድሩን ክብ ለማድረስ ፍላጎት መኖሩ በጣሙን የሚያጠራጥር ነው። የዶሃው ድርድር ዙር እስከ 2010 በተጣለው የጊዜ ገደብ ከግቡ መድረሱ እንግዲህ የሚሆን አይመስልም።

ትልቁ መሰናክል ደግሞ በእርሻው ዘርፍ ያለ ሲሆን ወደፊት ድርድሩ ከግቡ ይደርሳል ከተባለ እንኳ ለድሆቹ ታዳጊ አገሮች ልማት በሚበጅ መንገድ መገባደዱ ግድ ነው የሚሆነው። ስምምነቱ ቢሰፍን የዓለምን ኤኮኖሚ በያመቱ በ 170 ቢሊዮን ዶላር ሊያካብት በቻለ ነበር። ሆኖም ዛሬ ከጀኔቫ እንደተነገረው ቅራኔው ባለበት ነው የቀጠለው። ከሁለቱም ወገን በሚገባው መጠን በአስታራቂ አቅጣጫ ፈቀቅ ለማለት የፈለገ አልተገኘም። ሕንድና ብራዚል የሚገኙበት ሃያ አገሮችን የጠቀለለ የታዳጊ አገሮች ተደራዳሪ ቡድን በበኩሉ ለድርድሩ የመጨረሻ ግፊት ለመስጠት በሚቀጥለው ዓመት ጸደይ ላይ የሚኒስትሮች ስብበባ እንዲጠራ ጥሪ ሰንዝሯል። ጊዜው ምን ያመጣል፤ እንደገና ጠብቆ ከመታዘብ ሌላ ምርጫ የለም።

በሌላ በኩል በጄኔቫው ስብሰባ አኳያ አበረታች ነገር ቢገኝ 22 አዳጊ አገሮች በመካከላቸው የቀረጥ ቅነሣ ስምምነት ማድረጋቸው ነው። ስብሰባውን በሊቀ-መንበርነት የመሩት የአርጄንቲናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆርሄ ታያና ስምምነቱን ለደቡብ-ደቡቡ ትብብር እጅግ ጠቃሚ ዕርምጃ ነው ብለውታል። ባለሥልጣኑ ታዳጊ አገሮች ከስምምነት ለመድረስ ፍላጎቱና ብቃቱ እንዳላቸው በመጥቀስም ለዶሃ ዙር መጓተት ሌላውን ወገን ተጠያቂ አድርገዋል። የ 22ቱ መንግሥታት ስብስብ ከሕንድ፣ ከብራዚልና ከአርጄንቲና ሌላ ደቡብ ኮሪያን፣ ኢራንን፣ ቪየትናምንና ናይጄሪያን የመሳሰሉ ጠንከር ያሉ አገሮችም የሚጠቀልል ነው። በስምምነቱ መሠረት ተፈራራሚዎቹ አገሮች ከጠቅላላው ምርታቸው ሰባ በመቶ በሚሆነው ላይ ሃያ ከመቶ ቀረጥ መቀነስ ይኖርባቸዋል። የተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ጉባዔ ሃላፊ ሱፓቻይ ፓኒችፓክዲ እንደሚገምቱት ከሆነ ውሉ የነዚህን አገሮች ንግድ ቢያንስ በስምንት ቢሊዮን ዶላር የሚያሰፋ ነው።

MM/SL