የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድር መክሸፍ | ኤኮኖሚ | DW | 25.07.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድር መክሸፍ

በቅርቡ በሩሢያ ሣንት-ፔተርስቡርግ ላይ ተካሂዶ በነበረው የዓለም የኤኮኖሚ ጉባዔ የሥምንቱ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ ቀደምት መንግሥታትና የዋና ዋናዎቹ ታዳጊ ሃገራት መሪዎች በዓለም ንግድ ድርጅት ድርድር ከአንድነት እንዲደረስ ጥረት ማድረጋቸው ይታወቃል። ሆኖም አሁን በዓለም ንግድ ድርጅት መቀመጫ በጀኔቫ በተደረገው ዝርዝር ንግግር ድርድሩ መክሸፉ ግድ ነው የሆነበት።

ፓስካል ላሚይ ከጀኔቫው ስብሰባ በኋላ

ፓስካል ላሚይ ከጀኔቫው ስብሰባ በኋላ

ከእንግዲህ ተዓምር ካልተፈጠረ በስተቀር የዓለም ንግድን ለማለዘብ የተነሣው የዶሃ የድርድር ዙር በመሠረቱ አከተመለት ማለት ነው። ለነገሩ በወቅቱ የዓለም ንግድ መጠን መጨመሩን እንደቀጠለ ነው። በዓለም ንግድ ድርጅት አሰላል ይሄው የንግድ ልውውጥ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የአሥር ቢሊዮን ዶላር ወሰንን አልፎ ከፍ ለማለት በቅቷል። ሆኖም ቀደምቱ ባለ ኢንዱስትሪ መንግሥታትና ዋነኞቹ አዳጊ አገሮች ውጣ ውረድ የበዛውን የዶሃ የድርድር ዙር መልሶ ለማንቀሳቀስ ያደረጉት ጥረት መክሸፉ አልቀረለትም። የድርድሩ መክሸፍ የሚያስከትለው ጉዳት ቀላል አይሆንም። በዓለምአቀፍ ደረጃ በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የተጫነውን ቀረጥ ለማስወገድ፣ የአልግሎት ገበዮችን ለመክፈትና የበለጸጉ መንግሥታትን የእርሻ ድጎማ ለመቀነስ የነበረው ዕቅድ ዕውን ሊሆን አይችልም።

የዓለም ንግድ ድርጅት ገና የዶሃው ዙር እንደጀመረ ከዓለም ንግድ መጨመር ብቻ እንኳ በያመቱ 300 ሚሊያርድ ዶላር ገቢ እንደሚገኝ ነበር የገመተው። ግን አሁን በተፈጠረው ሁኔታ የታሰበው የሥራ ቦታዎች መስፋፋትና የገቢ መጨመር በተፋጠነ ሁኔታ ሊከሰቱ የማይችሉ ነገሮች ናቸው። እርግጥ የዓለም ንግድ ድርጅት ጠቅላይ አስተዳዳሪ ፓስካል ላሚይ የድርድሩን መክሸፍ በቀላሉ ለመቀበል አይፈልጉም። የዶሃውን የድርድር ዙር ለጊዜው አቋርጠው የዓለም ንግድን ለማለዘብ በተሥፋ የተሻለ ጊዜ መጠበቁን ይመርጣሉ።

በቀረጥ መወገድና የተሰወሩ የንግድ መሰናክሎችን በማስወገድ ብልጽግና እንደሚገኝ ጨርሶ አያጠያይቅም። ሆኖም ከዚህ ዕርምጃ እኩል የሚጠቀሙት ሁሉም ተሳታፊዎች አይደሉም። ሃብታሞቹ ይበልጥ ሃብታሞች፤ ድሆችም ይብሱኑ ድሆች ሊሆኑ ይችላሉ። ለዚህም ነበር በ 2001 የዶሃ ድርድር ዙር መጀመሪያ ለታዳጊዎቹ አገሮች የልማት ንግግር ቃል የተገባው። ማለት ታዳጊዎቹ አገሮች ከድርድሩ ይበልጥ መጠቀም ነበረባቸው። ግን የድርድሩ ዝርዝር ሂደት ልዩነቱ በታላሎቹ የኢንዱስትሪና የታዳጊ ሃገራት ቡድኖች መካከል ብቻ ሣይሆን በቡድኖቹ ውስጥም የጥቅም ልዪነት መኖሩን አጉልቶ አሣይቷል።

ለምሳሌ ጀርመን በእርሻ ፖሊሲው ዘርፍ ከፈረንሣይ ይልቅ ለአስታራቂ ሃሣብ ዝግጁ ናት። ለዚህም ምክንያቱ በውጭ ንግድ ላይ ጥገኛ የሆነችው ጀርመን በኢንዱስትሪ ምርቶች ቀረጥ መወገድና በአገልግሎት ሰጭ ገበያው መከፈት ይበልጥ ተጠቃሚ መሆኗ ነው። እርግጥ በታዳጊ አገሮች መካከልም አንድነት አለመኖሩም ሊዘነጋ አይገባውም። በተለይ የድሃ ድሃ የሚባሉት ታዳጊ አገሮች በአውሮፓ የእርሻ ገበዮች መከፈት ተጎጂ ነው የሚሆኑት። ምክንያቱም እነዚህ አገሮች ከአሁኑ ወደ ታላላቁ የአውሮፓ ገበዮች የመዝለቅ ነጻነት አላቸው። የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ አድርጎ ያስቀመጠው የዋጋ ዋስትና ተጠቃሚዎችም ናቸው።

እነዚህ አገሮች የዓለም የጨርቃ-ቀርቅ ንግድ ውል እንዳበቃ ቻይና በአጭር ጊዜ ውስጥ ታላቅ የገበያ ድርሻ ለመውሰድ መብቃቷን አይተውታል። ለምሳሌ በዶሃ የድርድር ዙር ስምምነት የአውሮፓ የስኳር ገበያ ቢከፈት በመሠረቱ ይበልጡን ተጠቃሚ የምትሆነው ብራዚል ናት። የድሃ ድሃ የሆኑት አገሮች ከአውሮፓውያን የስኳር ተክል ገበሬዎች ጋር የለውጡ ተጎጂዎች ይሆናሉ ማለት ነው። ከዚህ የጥቅም ውስብስብ የተነሣ ለዓለም ንግድ ድርጅት ድርድር መክሸፍ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉትን መንግሥታት ብቻ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም። ብዙዎች የገበያውን መከፈት የማይሹ ታዳጊ አገሮችም አሉ።
የዶሃ ድርድር ዙር መክሸፍ ውጤቱ ምን እንደሚሆን ግልጽ ነው። ታላላቆቹ የድርድሩ ተሳታፊዎች ወደፊት በዓለም ንግድና በዓለምአቀፍ የንግድ ሁኔታ መቃለል ላይ የሚኖራቸው ፍላጎት እየቀነሰ በአንጻሩ የሁለት ወገን የነጻ ንግድ ውል እያደገ ነው የሚሄደው። በወቅቱ 200 የሁለት ወገን፤ ማለት ባይላተራል ውሎች ዕውን ሆነው ይገናሉ። ልምድ እንደሚያሣየው ከሆነ በዚህ የሁለት ወገን ውል ይበልጥ ተጠቃሚው ጠንካራው ወገን ነው። በሌላ በኩል ብዙሃን አገሮችን ያካተተ የዓለም ንግድ ድርጅትን የመሰለ ዓለምአቀፍ ውል ለደካሞቹ አገሮች ጥቅምም ትኩረት የሚሰጥ ነው የሚሆነው። ስለዚህም በዶሃው ዙር መክሸፍም ሆነ መሸጋሸግ ይበልጥ ተጎጂዎቹ ታዳጊ አገሮች ይሆናሉ።