የዓለም ንግድ ድርጅት ወዴት? | ኤኮኖሚ | DW | 05.02.2013
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ንግድ ድርጅት ወዴት?

የዓለም ንግድ ድርጅት ባለፉት ዓመታት በደረሰበት የስኬት እጦት የተነሣ ዛሬ ወደ ቀድሞ ጥንካሬና ማንነቱ ለመመለስ ሲጥር ነው የሚታየው። አዲስ የዓለም ንግድ ውል ለማስፈን በድርጅቱ አማካይነት ከ 12 ዓመታት ወዲህ ሲካሄድ የቆየው ድርድር አንዳች ዕርምጃ ሳይታይበት መቅረቱ

ይታወቃል። ይህ ደግሞ በርካታ ጀኔቫ ላይ ተቀማጭ የሆነው የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል መንግሥታት ከድርጅቱ ውጭ ስምምነት ለማስፈን እንዲወስኑ ማድረጉ አልቀረም።

እና አዲሱ የጎርጎሮሳውያኑ 2013 ዓ-ም ግቡ የዓለም ንግድን ማለዘብና ተሳታፊዎቹን በሙሉ ለዓለም ገበያ ተሳትፎ ማብቃት ለሆነው ድርጅት ወሣኝ ዓመት እንደሚሆን ነው የሚታመነው። የድርጅቱ ጠቅላይ አስተዳዳሪ የፓስካል ላሚይ የሥልጣን ዘመን በቅርቡ የሚያበቃ ሲሆን ዛሬ በተተኪነት ለመመረጥ ዘጠን ዕጩዎች ቀርበዋል። እነዚህም ትናንት በድርጅቱ ሸንጎ ፊት ቀርበው ተደምጠው ነበር። ከዕጩዎቹ መካከል ከአፍሪቃ የጋናው አላን ክዋዶና ኬንያዊቱ አሚና ሞሐመድ፤ ከላቲን አሜሪካ የኮስታሪካዋ አናቤል ጎንዛሌስና የብራዚሉ ሮቤርቶ ካርቫልዮ፤ እንዲሁም የሜክሢኮው ሄርሚኒዮ ብላንኮ የሚገኙበት ሲሆን የተቀሩት የኢንዶኔዚያ፣ የደቡብ ኮሪያ፣ የኒውዚላንድና የዮርዳኖስ ተወላጆች ናቸው።

ትናንት የተጀመረው የምርጫ ወይም የማውጣጣት ሂደት በጣሙን ጠንካራ ሲሆን የድርጅቱ ተግባር ለአዲሱ ባለሥልጣን ከባድ እንደሚሆንም የሚጠበቅ ነው። በተለይ ድርጅቱን ማዳንና ሕያው አድረጎ ማቆየቱ የተመራጩ ጠቅላይ አስተዳዳሪ ዋነኛ ተግባር እንደሚሆን ጨርሶ አያጠራጥርም። መለስ ብሎ ለማስታወስ የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል መንግሥታት ከ 12 ዓመታት በፊት በጎርጎሮሳውያኑ 2001 ዓ-ም ታላቅ የወደፊት ተሥፋና ቁርጠኝነት የሚታይባቸው ነበሩ። እናም ዶሃ ላይ ለአዲስ የድርድር ዙር የመሠረት ድንጋይ ይጥላሉ። ይህም የዶሃ ድርድር ዙር በመባል ይታወቃል።

በጊዜው አዲስ የዓለም ንግድ ድርጅት ዕቅድ ከድርድሩ በተለይም ታዳጊ ሃገራት ተጠቃሚ መሆን ነበረባቸው። የካታር ዋና ከተማም የፍትሃዊና ነጻ ንግድ መለያ እንድትሆን ለማድረግ ይታሰባል። ይሁንና ድርድሩ የተጠበቀበትን ውጤት በማስከተል ፈንታ ከንቱ ሆኖ ነው የቀረው። የዶሃ ድርድር ዙር ሞቷል ወይም ሊሞት እያጣጣረ ነው ሲሉ ዕርማቸውን ያወጡት ጥቂቶች አይደሉም። ድርድሩመሞቱን መቀበል ያዳገተው ምናልባትም ድርጅቱንና ጠቅላይ አስተዳዳሪውን ፓስካል ላሚይን ነው።

እንደሚታወሰው የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል ሃገራት በመሠረቱ ግዙፍ በሆነው የለውጥ ፓኬት ላይ የሚያካሄደውን ድርድር እስከ 2005 ዓ-ም ማጠናቀቅ ነበረባቸው። ግን ከስምንት ዓመታት በኋላም አንዳች ዕርምጃ ሳይታይ ይቀራል። ለአንዳንድ የዓለም ንግድ ጠበብት የዶሃው-ዙር ገና ቀደም ብሎ ሲከሽፍ እርግጥ በአንጻሩ ዛሬም ተሥፋ ያልቆረጡ ጥቂቶች አይታጡም።

«የዶሃው ዙር መሞቱ ከተረጋገጠ ይህ ለጠቅላላው የዓለም ንግድ ድርጅትና እንዲያም ሲል ለዓለም ንግድ ስርዓት አሁን ካለው መሰናከል የላቀ ታላቅ ችግር ነው የሚሆነው። ለዚህም ነው ማዳን የሚቻለውን ሁሉ ለማዳን ጥረት የሚደረገው። ምንጊዜም ተሥፋ መቁረጥ አያስፈልግም። አሁን በመሃሉ የምንገኘው አከራካሪ በሆኑ ዓበይት ጥያቄዎች ላይ መነጋገር ባበቃበት ወቅት ላይ ነው። ቢቀር ዛሬ ይህ የለም»

ይህን የሚናገሩት በምሥራቃዊው ጀርመን ሃለ ላይ የሚገኘው የማርቲን ሉተር ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ክሪስቲያን ቲትዬ ናቸው።

ለዶሃው ዙር መክሸፍ ወይም መሰናከል ትልቁ መንስዔ በተለይም በእርሻ ልማት ዘርፍ አኳያ በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉትና በታዳጊ ሃገራት መካከል ያለው አለመግባባት ነው። የበለጸጉ መንግሥታት የእርሻ ድጎማቸውን ማብቃት አለባቸው? ታዳጊዎቹ ሃገራትስ የምርቶቻቸውን ሕልውና ለመጠበቅ ወደ አገር በሚያስገቧቸው ዕቃዎች ላይ ቀረጥ መጣል ይችላሉ ወይ? ይህ ብዙ ሲያከራክር የቆየ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል። በየድርድሩ ሂደት ደግሞ ደጋግሞ መነሣቱም አልቀረም።

የሆነው ሆኖ መሠረታዊው የዶሃ ዙር ችግር ከሃያ የሚበልጡ ጉዳዮች በአንድ ፓኬት እንዲጠቃለሉ ለማድረግ መሞከሩ ላይ ነው። የእርሻ ምርቶች፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶችና የአገልግሎት ዘርፍ ደምቦች በተናጠል ሣይሆን በጥቅሉ እንዲለዝቡ ለማድረገ ነው የተፈለገው። ከዚሁ በተጨማሪ የውጭ መዋዕለ ነዋይን በመሳሰሉ ነጥቦች የድምጽ አሰጣጥና የዕርምጃ መርሆች የለውጥ ሃሣብ ሲቀርብ የዓለምአቀፉ የንግድና የልማት ጥናት ማዕከል ባልደረባ ሪካርዶ-ሜሌንዴዝ-ኦርቲዝ እንደሚሉት ሌላም ተጨማሪ እክል አልታጣም።

«ያኔ በ 2001 ዓ-ም የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል መንግሥታት በተጨማሪ የተናጠል ውሣኔ አሣሪነት እንዲኖረው ነበር የተስማሙት። ማለት ማንኛውም የዙሩ የድርድር ጉዳይ በአንድ ውሣኔ በጋራ መተላለፍ አለበት። ይህ ደግሞ አጠቃላዩን ሁኔታ የሚያከብድ ነው። ምክንያቱም ሁሉም በሁሉም ነገር መስማማት አለባቸውና»

የዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ ዙር መክሸፍ ከጊዜ ብዛት እያደር ለዓለም ንግድ ድርጅት የብዙሃን ውል አማራጭ ተፎካካሪ ሞዴል እየፈጠረ መምጣቱም አልቀረም። በርካታ ሃገራት ከዓለም ንግድ ድርጅት ደምብ ውጭ የሁለት ወገን ውሎችን እያሰፈኑ ነው። በዓለም ላይ በወቅቱ የነጻ ንግድ ውል መረብ በመዘርጋት ላይ ይገኛል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህን መቆጣጠሩም እጅግ ከባድ ነገር ነው።

ችግሩ ተዋዋዮቹ ወገኖች ድርድሩን በራሳቸው ማካሄድ አለባቸው። እርግጥ ብዙዎች የሁለት ወገን ስምምነቶች በዓለም ንግድ ድርጅት ደምቦች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ነገር ግን ደምቦቹን የሚወስኑት ራሳቸው ተደራዳሪዎቹ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ እርግጥ የዓለምዓቀፍ ንግድና ልማት ባለሙያ የሆኑት ሪካርዶ ኦርቲዝ እንደሚሉት በመጨረሻ የሃይል ሚዛንን ሊያዛባ የሚችል ነገር ነው።

«በአንድ በኤኮኖሚ ታላቅ በሆነ የአውሮፓን ሕብረትን በመሰለ ወገንና አነስተኛ በሆኑ ሃገራት ወይም ቡድን መካከል የሚካሄዱ ድርድሮች ጠንካራው ወገን ለጥቅሙ የበለጠ ተጽዕኖ ወይም ግፊት ማድረጉ ስለማይቀር ግንኙነቱ ፍትህ የጎደለው ሊሆን ይችላል። ታዲያ በተለይ ለዚህ ነው የዓለም ንግድ ድርጅትና የዕኩልነት መርሁ ወደፊትም የሚያስፈልጉን»

በሜሌንዴዝ አነጋገር እንግዲህ ይህን ሂደት መለወጡ ጊዜው አሁን ይሆናል። ሳይውል ሳያድር በዓለም ንግድ ድርጅት አማካይነት ድርድሩ በሰፊ ዙር መልሶ እንዲንቀሳቀስ ማድረግና የጋራ መፍትሄ መሻት ያስፈልጋል። ሆኖም ፕሮፌሰር ክሪስቲያን ቲትዬ እንደሚያስገነዝቡት የአያያዝ ለውጥ መኖሩ ደግሞ ግድ ነው።

«በዶሃው መግለጫ ተናጠል መፍትሄዎችን በመፈለግ ፈንታ አንድ ጥቅል ፓኬት ለማስፈን መታሰቡ የተጋነነ ነገር እንደነበረ የኋላ ኋላ በግልጽ ታይቷል። ዕርምጃው እዚህም እዚያም ክርክር እንዲቀሰቀስና ዓላማውም ጥያቄ ላይ እንዲወድቅ ነው ያደረገው። አሁን ግን ቀስ በቀስ ስለ አንድ ወጥ ፓኬት ብቻ መወራቱ እየተተወ ከሄደበት ደረጃ ተደርሷል»

ከዚህም የተነሣ ለዓለምአቀፉ ንግድ አጣዳፊ በሆኑ ተናጠል ነጥቦች ላይ ለማተኮር ነው የሚሞከረው። ለምሳሌ የቀረጥ ተግባር አፈጻጸምን የመሳሰሉ ቴክኒካዊ ጥያቄዎችን ከጠቅላላው ፓኬት ነጥሎ በማውጣት ተናጠል መፍትሄ መሻት ጠቃሚነቱ ታምኖበታል።

የዓለም ንግድ ድርጅት ከእንግዲህ በድርድር ውጣ ውረድ እንደገና አሥር ዓመታት ሊያሳልፍ አይችልም። ስለዚህም የዓለም ዓይን በኢንዶኔዚያ ደሴት በባሊ ላይ በተሥፋ አተኩሮ ነው የሚገኘው። በነገራችን ላይ የሚቀጥለው የዓለም ንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ስብሰባ በዓመቱ መጨረሻ በዚያው ይካሄዳል።

እናም ትብትብ የበዛውን የዶሃውን ቋጠሮ ባሊ ላይ በመፍታት በወቅቱ ከተወሳሰበው ድርድር መውጫ ቀዳዳ ለማግኘት ነው የሚታለመው። ይህ መፍትሄ ለነገሩ ገና ድሮ ገሃድ መሆን በተገባው። የዓለም ንግድ ድርጅት አዲስ አስተዳዳሪ እንግዲህ ማንም ይሁን ማ ቀላል ተግባር አይጠብቀውም። የጀኔቫው ዓለምአቀፍ ድርጅቱ ክብደቱን ጨርሶ እያጣ እንዳይሄድ ከሚያሰጋ ደረጃ ላይ ሲሆን የወደፊት አቅጣጫውን ማስተካከሉ የሕልውና ጉዳይ ነው። የዓለም ንግድ ዕጣ ከዕጁ ወጥቶ በተለይም የታዳጊ ሃገራት ዕጣ የሁለት ወገን ነጻ ንግድ ክልል ለሚያራምዱ መተው የለበትም።

መሥፍን መኮንን

ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 05.02.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17TkR
 • ቀን 05.02.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17TkR