የዓለም ንግድ ድርጅት፣ ላሚይና የዶሃ ዕጣ | ኤኮኖሚ | DW | 02.09.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ንግድ ድርጅት፣ ላሚይና የዶሃ ዕጣ

የዓለም ንግድ ድርጅት ዛሬ ከተባበሩት መንግሥታት ቀጥሎ ሁለተኛው ታላቅ ዓለምአቀፍ ድርጅት ነው። የተመሠረተው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊ ሃያል መንግሥታት በተለይም በጊዜው የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ነጻ ለሆነ የዓለም ንግድ ደምቦች ለማስፈን የወሰዱትን ዕርምጃ ተከትሎ ነበር።

ፓስካል ላሚይ

ፓስካል ላሚይ

የዓለም ንግድ ድርጅት ሕያው የሆነው እርግጥ በጦርነቱ ፍጻሜ ማግሥት እ.ጎ.አ. በ 1947 ዓ.ም. የሰፈነውን በአሕጽሮት GATT የተሰኘ አጠቃላይ የንግድና የቀረጥ ስምምነት ተከትሎ በዘጠናኛዎቹ ዓመታት አጋማሽ ነው። ጀኔቫ ላይ ተቀማጭ የሆነው ድርጅት ዛሬ 153 ዓባል ሃገራት ሲኖሩት ዋና ጸሐፊው ፓስካል ላሚይ ከትናንት አንስቶ ሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸውን ጀምረዋል። ያለፈው የላሚይ የሥልጣን ዘመን በተለይም በዶሃው የድርድር ዙር መጓተትና መክሽፍ የተነሣ ውጣ ውረድ የበዛው ነበር። ስለዚህም ባሉበት መቀጠላቸው ጥቂትም ቢሆን ሳያስገርም አይቀርም።

ጀኔቫ ላይ ተቀማጭ የሆነው ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊውን ደግሞ ሲመርጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ይህም ለድርጅቱ አዲስ ነገር መሆኑ ነው። ለነገሩ ላሚይ ባለፉት አራት ዓመታት ለድርጅቱ ተግባር ያን ያህል ስኬታማ አመራር ሰጥተዋል ለማለት አይቻልም። በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው አዲስ የዓለም ንግድ ስምምነት ለማስፈን የተካሄዱት ንግግሮች ሁሉ የወደፊት ዕርምጃ የታየባቸው አልነበሩም።

ከዚህ አንጻር ለጀኔቫው ባለሥልጣን በመጪው ሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸውም ከባድ ሥራ የሚጠብቃቸው ነው የሚመስለው። በመጀመሪያ ደረጃ አንዳንዶች አልተቀበረም እንጂ ሞቷል ሲሉ እንዳከተመለት የተናገሩለትን ተሰናክሎ የቆየውን የዶሃን የዓለም ንግድ ድርድር ከግቡ ለማድረስ ጥረቱን እንደገና ማንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። እንደ መጀመሪያ ውጥኑ ቢሆን ኖሮ የታዳጊ አገሮችን ጥቅምም የጠበቀ ፍትሃዊ የንግድ ሥርዓትን ለማስፈን ታስቦ በ 2001 የተጀመረው የዶሃው ድርድር ዙር ሁለት ዓመታት ዘግየት ብሎ ሜክሢኮ-ካንኩን ላይ በተካሄደው የዓለም ንግድ ድርጅት ጉባዔ ላይ በተጠቃለለ ነበር። ሆኖም ድርድሩ ዕልባት ሳያገኝ ይሄው ከካንኩን በኋላ እንኳ ስድሥት ዓመት ሆነው።

ፓስካል ላሚይ እርግጥ ይህም ሆኖ ዛሬም ተሥፋ አልቆረጡም። የዓለም ንግዱ ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ በቅርቡ ለዓባል መንግሥታቱ ባስተላለፉት መልዕክት ተሥፋ በማይለየው ባሕርያቸው ከግባችን ልንደርስ ብዙም አልቀረንም ነበር ያሉት።

“እስካሁን ረጅም መንገድ ተጉዘናል። እናም ከጉዟችን ግብ ለመድረስ ብዙም እንዳልቀረን ነው የማምነው”

ችግሩ ዕምነታቸው የብዙዎች ዕምነት አለመሆኑ ላይ ነው። ይህም መጪ ተግባራቸውን የሚያቀልላቸው መሆኑ ያጠራጥራል። ከዓለም ንግድ ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ዓበይት ተግባራት መካከል አንዱ በተለያዩት ቡድኖች መካከል ከአንድ አስታራቂ ሃሣብ እንዲደረስ በተከታታይ ንግግሮች ማማከል ነው። በወቅቱ ደግሞ በድርጅቱ ውስጥ ሁለት ተቀናቃኝ’ ወገኖች በመኖራቸው ጉዳዩ ቀላል አይደለም። በአንድ በኩል አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረትና ጃፓን አሉ። እነዚህ የበለጸጉት መንግሥታት ቀድሞ የድርድሩን ዕጣ የሚወስኑት፤ ችግር ካለም በንግግር የሚፈቱት በራሳቸው መካከል ነበር። የተቀሩት የንግድ ድርጅቱ ዓባል ሃገራት በአንጻሩ ምንም እንኳ እኩል ድምጽ ቢኖራቸውም ሃያላኑ የወሰኑትን ወደዱም ጠሉ ውጦ ከመቀበል ሌላ ምርጫ አልነበራቸውም።

ግን አሁን ጊዜው’ ተለውጧል። ታዳጊና ራመድ ያሉትን አገሮች ያሰባሰበው ሁለተኛው ቡድን በአግባብ አቅሙን ካስተባበረ ከዘጠናኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ወዲህ በተለይም ብራዚል፣ ሕንድና ደቡብ አፍሪቃ ጠንካራ ተደራዳሪና የደቡቡ ዓለም አፈ-ቀላጤዎች እየሆኑም ነው የመጡት። ቻይና በአንጻሩ ከጊዜ ወደጊዜ ለዘብ ማለቱን ስትመርጥ ነው የታየችው። እንግዲህ የሃይል አሰላለፉ ይህን የመሰለ ሲሆን የድርጅቱን የንግድ ድርድሮች በፊታችን መስከረም አጋማሽ ላይ በአሜሪካ ፒትስበርግ ላይ በሚካሄደው በኤኮኖሚ የተራመዱ የቡድን-ሃያ መንግሥታት ጉባዔ ላይ መልሶ ለማነቃቃት ይታሰባል።

የዓለም ንግድ ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ፓስካል ላሚይ እንደሚመኙት በወቅቱ የዶሃው ድርድር ዙር በስኬት መጠናቀቅ ከመቼውም የበለጠ ጠቃሚ በሆነ ነበር። ለዚህም ምክንያት አላቸው። የዓለም ኤኮኖሚ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በቀጣይነት እያደገ ሲመጣ ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በወቅቱ ፈተና ላይ ጥሎት ነው የሚገኘው።

“በዚህ አስተማማኝ ያልሆነ ሁኔታ የተነሣ ብዙ የዓለም መሪዎች የዶሃውን ድርድር ዙር በፍጥነት ከግብ ለማድረስ ዝግጁነት ማሣየታቸው የሚያበረታታ ነው። በመንግሥታት መሪዎችና በሚኒስትሮች ደረጃም ለድርድሩ ስኬት ጥረቱ ተጠናክሯል። እርግጥ የወቅቱ የኤኮኖሚ ቀውስ በስፋት፣ ጥልቀትና ዓለምአቀፍ ተጽዕኖው አቻ የሌለው መሆኑን ሁላችንም ስለምናውቅ ነገሩ ሊያስደንቀን አይገባም”

በዕውነትም ዓለምአቀፉ ንግድ በከባድና ፈታኝ በሆነ ወቅት ላይ ነው የሚገኘው። በዓለም ንግድ ድርጅት መረጃዎች መሠረት ዓለምአቀፉ የውጭ ንግድ በያዝነው ዓመት የመጀመሪያ ሶሥት ወራት ቀደም ካለው ሲነጻጸር በሲሶ ነው ያቆለቆለው። በዓለም ንግድ ድርጅት በሚደረግ አዲስ ስምምነት ቀረጦች የሚቀንሱ ከሆነ የዓለም ንግድና ኤኮኖሚ መልሶ እመርታ ሊያሳይ ይችላል። ይህ በተለይ በውጭ ንግዷ የዓለም ሻምፒዮን የሚል ቅጽል ለሚሰጣት ለጀርመን እጅግ በጠቀመ ነበር። የአገሪቱ የውጭ ንግድ ፌደራል ማሕበር ፕሬዚደንት አንቶን ቦመር ድርድሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ አጥብቀው መጠየቃቸውም ለዚህ ነው።

“ድርድሩ በፍጥነት ቢጠናቀቅ የዓለምን ንግድን ሽክም በዓመት በ 300 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ ሊያቃልል በቻለ ነበር። ይህም ራመድ ያሉት፣ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉትና ታዳጊ አገሮች ሁሉም የሚጠቀሙበት የዓለም ኤኮኖሚ እመርታን የሚያስከትል ነው።”

የጀርመንን የውጭ ንግድ እመርታ ካነሣን በዓመቱ መጀመሪያ ክፉኛ ካቆለቆለ በኋላ አሁን በቅርቡ ባለፈው ሰኔ ወር የሰባት በመቶ ዕድገት አሳይቷል። ይህም ከሶሥት ዓመታት ወዲህ ጠንካራው መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ያለ እሢያ ገበዮች ሊታሰብ ባልቻለም ነበር። በተለይ አዳጊዎቹ አገሮች ቻይናና ሕንድ እሢያንም ከመታው ዓለምአቀፍ ቀውስ ወዲህ ወደ ከፍተኛ ዕድገታቸው መመለስ ይዘዋል። በሰሜናዊው ጀርመን የኪል የዓለም ኤኮኖሚ ምርምር ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ፕሮፌሰር ሄኒንግ ክሎድት እንደሚሉት እርግጥ የአገሪቱ የውጭ ንግድ ድርሻ በእሢያ ከዘጠኝ ከመቶ ያለፈ አልነበረም። ሆኖም የወቅቱ ዕድገት ያለ እሢያ የሚታሰብ አይደለም።

“እሢያ የግድ በኤኮኖሚ ክብደቷ ሣይሆን ከሁሉም በላይ ቀውሱ ባስከተለው ለውጥ የተነሣ ማዕከላዊ ሚና አላት። ምክንያቱም ባለፉት ጊዜያት በዚህ በጀርመን በመላው ገበዮች ጠንካራ የማቆልቆል ሂደትን ነው የታዘብነው። አሁን ግን እንደገና ከእሢያ የውጭ ንግድ ገበዮች የመጀመሪያውን የተሥፋ ጭናንጭል እያየን ነው። እና ከቀውሱ የሚያላቅቀው መንገድ አሁን በእሢያ በኩል ነው የሚያቀናው”

የበለጸገው ዓለም ኤኮኖሚ በአዳጊው ዓለም ገበዮች ጥገኛ መሆኑም በዓለም ንግድ ላይ የተለወጠውን የሃይል ሚዛን የሚያሳይ ነው። ቻይና እንዲያውም ጀርመን ከ 2003 ዓ.ም. ወዲህ በዓለም ላይ ይዛ የቆየችውን የውጭ ንግድ የዓለም ክብረ-ወሰን በመስበር በዚህ ዓመት ሂደት በቦታዋ መተካቷ እንደማይቀር ነው የሚጠበቀው። የዓለም ንግድ ድርጅት በቅርብ ያወጣው መረጃ እንዳመለከተው የቻይና የውጭ ንግድ በዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጀርመን ልቆ ተገኝቷል።
ማለቂያ ወዳጣው ወደ ዓለም ንግዱ የዶሃ ድርድር ችግር እንመለስና የተለዩት ወገኖች፤ ማለት የበለጸገው ዓለምና የአዳጊዎቹ ሃገራት ፍላጎት አሁንም እጅግ የተራራቀ ሆኖ ነው የሚገኘው። የአውሮፓ ሕብረትና አሜሪካ ለኢንዱስትሪ ምርቶች የውጭ ንግዳቸውና የአልግሎት ዘርፋቸው በደቡቡ ዓለም የቀረጥ ደምቦች የበለጥ እንዲለዝቡ ይፈልጋሉ። ታዳጊዎቹ አገሮች ገበዮቻቸውን ይበልጥ መክፈት አለባቸው ማለት ነው። ዋሺንግተንና ብራስልስ በሌላ በኩል ለገበሬዎቻቸው በሚሰጡት የእርሻ ልማት ድጎማ ለመቀጥልና ይህንኑ ለመጠበቅም ነው የሚሹት። ግን ይህ ብራዚልን በመሳሰሉት ራመድ ያሉ አገሮች ዘንድ ተቀባይነት የለውም። እነዚህ አገሮች ከሰሜኑ ዓለም በሚገቡ ምርቶች ላይ የጣሉትን ቀረጥ ለመቀነስ ዝግጁ የሚሆኑት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት በፊናቸው ገበዮቻቸውን ለደቡቡ የእርሻ ምርቶች ሲከፍቱ ብቻ ነው።

የዶሃውን ድርድር ዙር ለዓመታት አንቆ የያዘው በተለይ ይህ ቅራኔ ነበር። ሌላው ተጨማሪ ችግር ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር የዶሃው ድርድር ተሥፋ አስቆራጭ በሆነ ሁኔታ ሲከሽፍ ሁለት ጠቃሚ የነበሩ ተደራዳሪ ባለሥልጣናት ከመድረኩ ገሸሽ ማለታቸው ነው። በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ የነጻ ንግድ ተሟጋች የነበሩት የሕብረቱ የንግድ ኮሜሣር ፔተር ማንደልሰን በብሪታኒያ የጎርደን ብራውን ሚኒስትር ለመሆን ብራስልስን ሲለቁ ለዋሺንግተን ለዓመታት በግንባር ቀደምነት ሲደራደሩ የቆዩት የአሜሪካ የንግድ ተጠሪ ሱዛን ሽዋብ ደግሞ ወደግሉ የኤኮኖሚ ዘርፍ ማሸግሸጉን መርጠዋል። በዚሁ እንግዲህ ፓስካል ላሚይና የብራዚሉ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቼልሶ አሞሪን ብቻ የቀሩት በንግግሩ የሚቀጥሉት ባለሥልጣናት መሆናቸው ነው።
በሌላ በኩል ታዳጊ አገሮችንና ራመድ ያሉትን አዳጊ አገሮች በተለይ ያስቆጣው የዶሃው ድርድር ዙር ሲጸነስ ከጅምሩ የልማት አጀንዳ ይዞ መነሣቱ ጨርሶ የማይጠቀስ ጉዳይ እየሆነ መሄዱ ነው። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ከመስከረም 2001 የሽብርተኞች ጥቃት በኋላ ብዙ ሳይቆይ ድርድሩ በተለይም ታዳጊ አገሮችን የሚጠቅም፤ በፍትሃዊ ንግድ ላይ ያለመ እንደሚሆን ቃል መግባታቸው አይዘነጋም። ግን የተገባው ቃል ሁሉ ገቢር አልሆነም። ለዶሃው ድርድር ሰባት ዓመታት ያህል መጓተትና መሰናከል ዋነኛው ምክንያትም ይሄው ነው። አዳጊዎቹ አገሮች በቀላሉ ዕጃቸውን የሚሰጡ አልሆኑም፤ የበለጸጉት መንግሥታትም የዓለም ንግድ ድርጅትን እንዳሻቸው የሚዘውሩበት ጊዜ እያለፈ ሄዷል። ለፓስካል ላሚይ መጪው ጉዞ ከባድ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም።

MM/DW/WTO

Negash Mohammed