የዓለም ንግድ ድርድር መክሽፍና የወደፊት ዕጣው | ኤኮኖሚ | DW | 04.08.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ንግድ ድርድር መክሽፍና የወደፊት ዕጣው

የዓለም ንግድ ስርዓትን በማለዘብ ፍትሃዊ ለማድረግ ጀኔቫ ላይ ሲካሄድ የሰነበተው ድርድር ባለፈው ሣምንት መክሸፉ አይዘነጋም።

ፍትሃዊ ንግድን በማስፈን በተለይ የታዳጊ አገሮችን ልማት ለማፋጠን ታስቦ በዓለም ንግድ ድርጅት ሲካሄድ የቆየው የዶሃ ድርድር ዙር በሰባት ዓመት ዕድሜው በተደጋጋሚ ሲወድቅ ሲነሣ፤ ሲያጣጥር ሲከሽፍ ከተደራዳሪዎቹ ወገኖች በኩል ሞቱን ለመቀበል የፈለገ አንድም አልነበረም። ግን ሞቱ ያለመፈለጉን ያህል ፍትሃዊ ስምምነት እንዲሰፍን ተገቢውን ሁኔታ በማመቸቸቱ ረገድ ሕልውናውን ለመጠበቅ በተፈለገው መጠን ልዩነቶቹን ለማጥበብ በቂ ቅንነት አልታየም።

ሰሞኑን ጀኔቫ ላይ ሲካሄድ የሰነበተው የዓለም ንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ስብሰባ የተመደበለት ጊዜ አብቅቶ በጥቂት ተጨማሪ ቀናት ሲራዘም ለዓመታት ሲጠበቅ የቆየው ስምምነት የተቃረበ ነበር የመሰለው። ግን እንደታሰበው አልሆነም። የድርድሩ መክሽፍ በዓለም ንግድ የወደፊት ሂደት ላይ ጎጂ ተጽዕኖ ይኖረዋል። የእስካሁኑን ድርድር ዕርምጃም በጥቅሉ ከንቱ እንዳያደርግ የሚያሰጋ ነው። የድርድሩ መክሽፍ በዓለም ንግድ ድርጅት ብቻ ሣይሆን በተለያዩ መንግሥታት ዘንድም ቅሬታን አሳድሯል። ሆኖም የድርጅቱ ጠቅላይ ጸሕፊ ፓስካል ላሚይ በሁኔታው ብርቱ ሃዘን እንደተሰማችው ባይሸሽጉም አንዱን ወገን አንስተው ጥፋተኛ ለማለት አልፈለጉም።

“ከኔ በኩል ወቀሣ የለም” ነው ያሉት።

የጀኔቫ ድርድር ክሽፈት በዓለም ንግድ ድርጅት ውስጥ መለወጥ ከያዘው የሃይል ሚዛን አንጻር የተለየ ራዕይ ማስፈለጉን ነው እንደገና ግልጽ ያደረገው። ቻይናንና ሕንድን የመሳሰሉት በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚገኙ አገሮች ዛሬ ኢንዱስትሪዎችንም በማስፋፋት ላይ የሚገኙ ናችው። በመሆኑም እንደበለጸጉት አገሮች ሁሉ የራሳቸውንም የገበያ ጥቅምና ድርሻ የመጠበቅ ፍላጎት አላችው። ጊዜው ከመቼውም በላይ አዲስ የዓለም የንግድ ስርዓትን የሚጠይቅ ነው። ከጥቂት ቀናት በፊት ለስምምነት የቀረበ መስሎ የነበረው ድርድር የከሸፈውም በተለይ ቻይናና ሕንድ በአንድ በኩል አሜሪካ ደግሞ በሌላ ሆነው በተፋጩበት የእርሻ ምርቶች ንግድ ሁኔታ ነው። አሜሪካ ለገበሬዎቿ የምትሰጠውን ድጎማ በመቀነሱ በኩል እስካሁን የወሰደችው ዕርምጃ ለቻይናና ለሕንድ በቂ አልሆነም።
በአንጻሩም ታዳጊ አገሮች የገበሬዎቻቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ በበለጸገው ዓለም የእርሻ ምርቶች ላይ ገደብ የሚያበጅ የቀረጥ ደምባችውን ጨርሶ ለማንሣት ፈቃደኛ አለመሆናችውን አሜሪካ አልፈቀደችውም። ምዕራፉ የተዘጋው በዚሁ ነበር። በነገራችን ላይ በድርድሩ መክሸፍ ከድርጅቱ ዓባል ሃገራት 130 ሚሊያርድ ዶላር ያህል ነው ከዕጃችው የሾለከው። ማለት በቀረጥ ቅነሣው ይቆጥቡት የነበረው ገንዘብ!
የሆነው ሆነ፤ ለመሆኑ በሌላ በኩል የዓለም ንግድ ድርድር ዙር ይቀጥላል ውይ? መቀጠል ከቻለስ እንዴት? የድርጅቱ ጠቅላይ ጸሕፊ ፓስካል ላሚይ ትናንት የድርድሩን መክሽፍ በገለጹበት ወቅት እርግጥ ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት አልደፈሩም። በአጭሩ የዓለምን የንግድ ስርዓት ዘመናዊ ገጽታ ለመስጠት መጣር እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት። እርግጥ የሰሞኑ የድርድር ማራቶን የበተነው አቧራ አረፍ ሲል!

”ለጊዜው የተነሣው አቧራ እንዲያርፍ ማድረግ ይኖርብናል። በወቅቱ ራቅ ብሎ የወደፊቱን መመልከቱ ከባድ ነገር ነው። የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል ሃገራት የተበታተነው እንዴት መልሶ ሊያያዝ እንደሚችልና ከናካቴው መቻሉን ለመወሰን የተረጋጋ ዕይታ ያስፈልጋችዋል”

ፓስካል ላሚይ ከናካቴው ከአንድ ስምምነት የሚደረስ ቢሆን እንኳ ይሄው በአጭር ጊዜ የሚደረስበት እንደማይሆን ተረድተውታል። አሜሪካ ውስጥ በፊታችን ሕዳር ወር አዲስ ፕሬዚደንት ይመረጣል። ግን አሸናፊዎቹ ሬፑብሊካኖችም ሆኑ ዴሞክራቶች የዋሺንግተን የንግድ ፖሊሲ እምብዛም መለወጡ የሚያጠራጥር ነው። ያለፉ ልምዶች እንዳሳዩት ዴሞክራት ፕሬዚደንቶችም ቢሆን ከለዘብተኛ የንግድ ስርዓት ይልቅ የራስ ገበያን ወደሚያጥር ወደ ብሄራዊ ጥቅም ጥበቃ ያዘነበሉ ነበሩ። እንግዲህ ከዋሺንግተን በኩል ከምርጫውም በኋላ ብዙ ለውጥ አይጠበቅም ማለት ነው። የአሜሪካ ተደራዳሪ ሱዛን ሽዋብ ድርድሩ በከሸፈ ማግሥት ጀኔቫ ላይ በሰጡት መግለጫ ድርድሩ መክሽፉን ሆን ብለው በቃል ከመጥቀስ ተቆጥበዋል። ሆኖም አሜሪካ ያቀረበችው ሃሣብ በጠረጴዛው ላይ እንዳለ ይቆያል ሲሉ በተዘዋዋሪ ቻይናንና ሕንድን የመሳሰሉትን አገሮች ፈቀቅ ማለቱ የናንተ ፈንታ ነው ለማለት ነበር የሞከሩት። ታዳጊዎቹ አገሮች የገበሬዎቻቸውን ጥቅም ለማስከበር ገደብ መሻታቸውም አልተዋጠላችውም።

“በዓለም ላይ እየናረ ከሄደው የምግብ ዋጋ አንጻር በዚህ ድርድር በምን ፍጥነትና መጠን የቀረጥ ማገጃ ማነጽ እንደሚቻል መወሣቱ እንቆቅልሽ ነው የሆነብኝ”

ሆኖም ተጠያቂነቱን ከአሜሪካና ከአውሮፓ ለማራቅ የሚደረገውን ሙከራ ታዳጊዎቹ አገሮች አልተቀበሉትም። የአርጄንቲና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆርሄ-ታያና ድርድሩ የከሽፈው በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ጥቂት እየሰጡ ብዙ በመፈለጋቸው ነው ሲሉ ብዙዎቹ ታዳጊ አገሮች የሚያስቡትን በግልጽ አስቀምጠውታል። ሱዛን ሽዋብ በጀኔቫው ድርድር መክሽፍ የዓለም ንግድ ስርዓትን ሰላሣ ዓመታት ወደ ኋላ የሚመልስ አደጋ እንደተፈጠረም ተናግረዋል። የአውሮፓው ሕብረት የንግድ ኮሜሣር ፔተር ማንደልሶን በበኩላችው በአነስተኛ የአሃዝ ልዩነት ድርድሩ እንዲከሽፍ መደረጉ አሳዝኖኛል ነው ያሉት። ከስምምነት ባለመደረሱ ይበልጥ ተጎጂው ማን እንደሚሆንም ሳይጠቅሱ አላለፉም።

“የድርድሩ መክሽፍ ለሁሉም አገሮች ሽንፈት ነው። ሆኖም ተጽዕኖው ለሁሉም እኩል አይሆንም። በአብዛኛው የሚጎዳው የድሃ ድሃ የሆኑትን አገሮች ነው። ማለት የዓለም ንግድ ድርድር ስኬት ይበልጥ ያስፈልጋቸውና ይገባቸው የነበሩትን ታዳጊ አገሮች”

በዚህ በጀርመንም የአገሪቱ የንግድና የኢንዱስትሪ ም/ቤት ፕሬዚደንት ሉድቪግ ብራውን መላው የዓለም ኤኮኖሚ ታላቅ ዕድል እንዳመለጠው ሲናገሩ የፌደራሉ ምጣኔ-ሐብት ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ሚኒስትር ዴኤታ በርንድ ፋፈንባህም የድርድሩ በስኬት መፈጸም ለዓለም ኤኮኖሚ በትክክለኛው ሰዓት ትክክለኛው ምልክት በሆነ ነበር ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። የድርድሩ መክሽፍ ከመንግሥት ነጻ በሆኑ ድርጅቶች ዘንድም ብርቱ ቅሬታን ነው ያስከተለው። እነዚሁ በተለይ የበለጸገውን ዓለም ለሁኔታው ተጠያቂ ያደርጋሉ።

የዓለምአቀፉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት የኦክስፋም ኢንተርናሺናል ሃላፊ ጀረሚይ ሆብስ እንደገለጹት እንደዛሬው የምግብና የነዳጅ ዋጋ ንረት ባየለበት፣ የዓለም ኤኮኖሚ ሂደት አስተማማኝ ባልሆነበትና ድሃው ሕዝብ ለችግር በተጋለጠበት ጊዜ ፍትሃዊ የንግድ ስምምነት እየከፋ የሚሄደውን ድህነትን ለማስወገድ ዕድል በሰጠ ነበር። የሌላው ድርጅት የ ActionAid ባልደረባ አፍታብ ካን ደግሞ ወደፊት ለሚደርሰው ሁሉ ሃላፊነቱ በታዳጊ አገሮች ውስጥ የበለጠ ገበያውን ለመቆጣጠር ከራሳቸው የንግድ ጥቅም ባሻገር የማያስቡት የአሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት ነው ብለዋል። እንደርሳቸው አነጋገር ለድርድሩ መክሽፍ ቻይናንና ሕንድን ተጠያቂ ማድረጉ ሲበዛ አስቂኝ ነው የሚሆነው።

ያም ሆነ ይህ የዶሃን ድርድር ዙር መልሶ ለማነቃቃትና ከስምምነትም ለመድረስ የተጣለው ተሥፋ አሁንም እንደገና ከንቱ ሆኗል። የዶሃው የፍትሃዊ ንግድ ጽንሰ-ሃሣብ ለዘብ ባለ መልክ እንኳ ወደ መቃብሩ እየተወሰደ ነው ቢባል ብዙም ማጋነን አይሆንም። በድርድሩ መክሽፍ የሚወቀሱት ምዕራባውያን በዓለም ንግድ ድርጅት ጥላ ስር ከሚሰፍን የጋራ ስምምነት ይልቅ ከታዳጊው ዓለም መንግሥታትና ስብስቦች ጋር በተናጠል የሁለት ወገን ባይላተራል የነጻ ንግድ ስምምነት በመፈራረም ከዶሃው ጽንሰ-ሃሣብ ገሽሽ ካሉ ቆይተዋል። ይህ አዝማሚያ እየጠነከረ ሲሄድም የሚታይ ነው። ግን ሂደቱ ለድሆቹ ታዳጊ አገሮች ጠቀሜታ አይኖረውም። የድርድር አቅምን የሚያሳጣ ነው። በዓለም ንግድ ድርጅት ስር የሚሰፍን ስምምነት በአንጻሩ የሁሉንም ጥቅም በጋራ የሚያስጠብቅ በሆነ ነበር።