የዓለም ንግድ የዶሃ ድርድርና የውድቀት አዝማሚያው | ኤኮኖሚ | DW | 08.08.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ንግድ የዶሃ ድርድርና የውድቀት አዝማሚያው

የዓለም ንግድ ድርጅትን የዶሃ ድርድር ዙር ከግቡ ለማድረስ ውጣ-ውረድ ሲባል ስድሥት ዓመታት አልፈዋል። የንግድ ደምቦችን በማለዘብ የታዳጊ አገሮችን ተሳትፎ ለማዳበር የተወጠነው ድርድር በበለጸጉት መንግሥታትና በሶሥተኛው ዓለም ቅራኔ ሳቢያ ከዓመት በፊት መቋረጡም የሚታወቅ ነው።

የዓለም ንግድ ድርጅት

የዓለም ንግድ ድርጅት

የዶሃን ድርድር መልሶ ለማንቀሳቀስ አሁን በቅርቡ በአንድ አስታራቂ ተብሎ በቀረበ ሃሣብ በመመሥረት ጀኔቫ ላይ ንግግር ተከፍቷል። ሆኖም በንግግሩ እስካሁን የረባ ዕርምጃ ለመታየቱ ምንም ምልክት የለም። ችግሩ ምንድነው? የወደፊት ዕጣውስ? ለድርድሩ ስኬት ማጣት በተለይ መሰናክል የሆኑት ለገበሬዎቻቸው የእርሻ ድጎማ በመስጠት የታዳጊውን ዓለም አርሶአደር የመፎካከር ብቃትና የዕድገት ዕድል ያሳጡት የበለጸጉት መንግሥታት መሆናቸው በሰፊው የሚታመንበት ጉዳይ ነው። ድርድሩ ለምን ተጓተተ፤ ተሥፋውስ ምን ያህል ነው? ለዚህ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለማግኘት በቅድሚያ የዓለም ንግድ ድርጅት እንዴት እንተቋቋመና እንዴት ከዛሬው ደረጃ እንደደረሰ ጥቂት መለስ ብሎ መመልከቱ ጠቃሚ ግንዛቤን ይሰጣል።

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅትና ዋዜማው የዓለም አኮኖሚ በጣም የተዳከመበት ነበር። በመሆኑም ከጦርነቱ በኋላ ሁኔታውን ለማረጋጋት ሁለቱን መንትያ የገነዘብ ተቋማት የዓለም ባንክንና የምንዛሪ ተቋም የመመሥረቱ አስፈላጊነት ግንዛቤ ውስጥ ይገባል። በዓለምአቀፍ ደረጃ ንግድ መልሶ እንደሚያንሰራራ፤ ብዙ አገሮች እንደሚከተሉትም የታመነበት ጉዳይ ነበር። እና ብዙዎች ሃገራት በአንድ ዓይነት የንግድ ጽንሰ-ሃሣብ ቢመሩ ሁሉም ሊጠቀሙ ይችላሉ የሚለው አመለካከት እየዳበረ ሄዶ በ 1948 ዓ.ም. የዓለም ንግድ ድርጅት ቀዳሚ የሆነው የዓለም ንግድና የጉምሩክ ስምምነት በአሕጽሮት GATT ሕያው ይሆናል።
የዓለም ንግድ ድርጅት የኋላ ኋላ ድርጅታዊ መዋቅር ኖሮት የተቋቋመው ከ 1986 እስከ 1994 ዓ.ም. ብዙ ጥልቅ ውይይት ከተደረገበት ከኡሩጉዋዩ ዙር በኋላ ነበር። በኡሩጉዋዩ ዙር በርካታ የታዳጊው ዓለም አገሮች ሲሳተፉ ትኩረታቸው በዓለም ገበያ በተለይም በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት አሃገራት ገበዮች ላይ የዕርሻና የጨርቃ-ጨርቅ ምርቶቻችውን ለመሸጥ እንደሚችሉ ዕምነት መጸነሳቸው አልቀረም። እርግጥ እስከዚያው ድረስ ግን ባለ ኢንዱስትሪው መንግሥታት በእርሻ ምርቶች ላይ የሚጥሉትን ቀረጥ እንዲያነሱ ታዳጊ አገሮች ሃሣብ ቢያቀርቡም ጉዳዩ በሃብታሞቹ አገሮች ግትርነት የተነሣ መቋጠሪያ ሊያገኝ አልቻለም ነበር። ድርጅት 151 ዓባል ሃገራትን በመጠቅለል አሁን ካለበት መስፋፋት ቢደርስና በርካታ ታዳጊ አገሮችን ቢያቅፍም በአንጻሩ የዶሃው ድርድር መጓተት በተለይ በታዳጊው ዓለም ላይ ብርቱ ተጽዕኖን መፍጠሩ በግልጽ የሚታይ ነው።
ከስድሥት ዓመታት በፊት በ 2001 ገሃድ የሆነው የካታርን ርዕሰ-ከተማ መነሻው ያደረገ ከልማት ጋር የተያያዘ ታዳጊ አገሮች ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ንግድ ውስጥ እንዲካተቱና ደምቦቹን ይበልጥ ልቅ በማድረግ ምርቶቻቸውን ሊያራግፊ በሚችሉበት ሁኔታ ከስምምነት ይደረሳል። ግን ችግሩ የበለጸጉት መንግሥታት ስምምነቱን ተከትለው እንደሚፈለገውና እንደሚጠበቀው ተገቢውን ዕርምጃ አለመውሰዳቸው ነው። በሌላ በኩልም በተለይ ሕንድ፣ ብራዚል፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪቃ በኤኮኖሚያቸውና በድርድራቸው እየጠነከሩ በመምጣታችው ለኢንዱስትሪው ዓለም ግፊት በቀላሉ የሚንበረከኩ አልሆኑም። ጭቅጭቁና ክርክሩ እየጠነከረ መጥቷል ማለት ነው።

ባለፈው ሰኔ ወር 2007 ዓም. ድርድሩን ለማራመድ ዓቢይ ክብደት የሚሰጣቸው ወገኖች የብራዚል፣ የሕንድ፣ የአውሮፓ ሕብረትና የአሜሪካ ተጠሪዎች በዚህ በጀርመን ፖትስዳም ከተማ ላይ ተገናኝተው ችግሩ መፍትሄ በሚያገኝበት ሁኔታ ተከራክረው ነበር። ግን አሁንም በኢንዱስትሪው ዓለም የአቋም ግትርነት ሳቢያ ነገሩ ዕልባት ሳያገኝ በመቅረቱ ነገሩ አክትሞለታል ያሉ ወገኖችም አልታጡም። የበለጸጉት መንግሥታት የዕርሻ ድጎማቸውንም ሆነ የጣሉትን ቀረጥ የሚገባውን ያህል ለማለዘብ ብዙም ቅን ባልሆኑበት በዛሬው ወቅት በአንጻሩ ታዳጊዎቹም አገሮች ለኢንዱስትሪው ዓለም ምርቶች ገበዮቻችሁን ጨርሳችሁ ክፈቱ መባላቸው የሚዋጥላቸው ነገር ሆኖ አይገኝም። በዕውነትም አሁን ባለው ሁኔታ ታዳጊ አገሮች ገበዮቻቸውን ቢከፍቱ የውስጥ አምራቾችን ይበልጥ ማዳከም ነው የሚሆነው።

የዶሃው ድርድር እየተጓተተ በሄደባቸው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሃብታም አገሮች ከተናጠል ወይም የአካባቢ ስብስብ ሃገራት ጋር ባይላተራል ውሎችን በማስፈን አማራጭ መንገድ ላይ አተኩረው ነው የቆዩት። ይህ ደግሞ የታዳጊዎቹን አገሮች የመደራደር አቅም ይበልጥ ማዳከሙ አልቀረም። በዓለም ንግድ ድርጅት ውስጥ በሚደረግ ስምምነት የጋራ ጥቅም ከማግኘት ይልቅ በተናጠል ይመታሉ የሚልም ስጋት አለ። የበለጸጉት መንግሥታት ይህን መንገድ የመረጡበት ምክንያት፤ ግብም አላቸው። በታዳጊዎቹ አገሮች ላይ ግፊት ማድረጉ አንዱ ነው። ከዚህ አንጻር የዶሃው ድርድር ዙር መልሶ ሕያው ሊሆን መብቃቱ ሲበዛ የሚያጠያይቅ ነው።
በወቅቱ አስታራቂ ተብሎ የቀረበው አዲስ የንግግር ሃሣብ ሁለቱን ወገኖች ሊያቀራርብ ይችላል ብለው የሚያምኑ ካሉ በጣም ጥቂቶች ናቸው። የዓለም ንግድን ፍትሃዊ መሆን መሠረተ-ዓላማ አድርጎ የተነሣው ድርድር እስካሁን የሚገባውን ያህል ፍትሃዊነት ጎልቶ አልታየበትም። ሃቁ ይህ ሲሆን እንግዲህ የዶሃ ነገር መክሸፉ ይሆን? የወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ የተሻለ ነገር አያመለክትም። ምናልባት ለዓለም ንግድ ድርጅት የሚቀረው ምርጫ አዲስ መንገድና ዘዴ ማፈላለግ ይሆናል።