የዓለም ንግድ፤ አቤቱታና የጥቅም ሽኩቻ | ኤኮኖሚ | DW | 03.06.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ንግድ፤ አቤቱታና የጥቅም ሽኩቻ

በአንድ በኩል በቤይጂንግና በምዕራቡ ዓለም መካከል የተነሣው የጨርቃ-ጨርቅ ንግድ ውዝግብ መካረሩን እንደቀጠለ ሲሆን አሁን ደግሞ የቻይናን የውጭ ንግድ ማየል ለመቋቋም በአንድ ጎራ የተሰለፉት አሜሪካና የአውሮፓው ሕብረት በአውሮፕላን ኩባንያዎቻቸው የጥቅም ውዝግብ ሳቢያ እርስበርስ እየተወናጀሉ ነው። የተፋጠነ አስታራቂ መፍትሄ የማግኘቱ ዕድል እስከምን ድረስ ነው? የዓለም ንግድ ድርጅት የብያኔ ሥልጣንና ብቃትስ?

ለቻይናና ለምዕራቡ ዓለም ውዝግብ መካረር መንስዔ የሆነው ከያዝነው 2005 ዓ.ም. መጀመሪያ ወዲህ በዓለም የጨርቃ-ጨርቅ ገበዮች ላይ የውጭ ንግዱን መጠን የሚገድብ ኮታ አለመኖሩ ነው። ለዓመታት ሲሰራበት የቆየው ውል የጽናት ዘመን ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ማክተሙ ይታወቃል። ከዚያን ወዲህ ቻይና በአውሮፓው ሕብረትና በአሜሪካ ገበዮች ላይ የምታራግፈው የአልባሣት ምርት እጅግ ከፍተኛ በሆነ መጠን ነው የጨመረው።
በዚሁ በቤይጂንግ የውጭ ንግድ ማየል የተነሣ ታዲያ በርካሽ ዋጋ በተጥለቀለቀው የዓለም ገበያ ላይ መፎካከር ያቃታቸው የአውሮፓና የአሜሪካ ኩባንያዎች ብዙዎች ናቸው። ከአሁኑ በርከት ያሉ ፋብሪካዎች እየከሰሩ ተዘግተዋል፤ ብዙዎች የሥራ መስኮች እንዳነበሩ መሆናቸውም ግድ ሆኗል። በአሜሪካ ብቻ ከአሥር ሺህ የሚበልጡ የጨርቃ-ጨርቅ ፋብሪካዎች ሕልውና ሲያቆም ሁኔታው 16 ሺህ የሚሆኑ ሙያተኞችን ለሥራ አጥነት መዳረጉ ነው የሚነገረው።

የአውሮፓው ሕብረትና አሜሪካ ጉዳዩን ቀላል አድርገው አልተመለከቱትም። ለዚህም ነው የገበዮቻቸውን መጥለቅለቅ ለመግታት ከቻይና በሚገባው ጨርቃ-ጨርቅ ምርት ላይ ገደብ የመጣልና ቀረጥ የመጨመር ዕርምጃዎችን ለመውሰድ፤ ያለውንም ለማጠናከር የሚያቅዱት። ይሁንና ዕርምጃው ቻይናን የሚያስፈራራ ሆኖ አልተገኘም። የቤይጂንግ ባለሥልጣናት ምላሽ እንዲያውም ሁኔታው እየተካረረ መሄዱ እንደማይቀር የሚያመለክት ነው።

የአገሪቱ የንግድ ሚኒስትር ቦ-ሺላይ የሕብረቱንና የዋሺንግተንን ዕርምጃዎች የዓለምአቀፉን ንግድ ደምቦች የሚጥስና ሕጋዊ መሠረት የጎደለው ነው ሲሉ አጥብቀው ነቅፈዋል። ቤይጂንግ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ዕርምጃው መታሰቡ ገንቢ አይደለም ያሉት ሚኒስትር በሌላ በኩል ቻይና የንግዱን ውዝግብ በሰላም ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን ሳያማመልከቱም አላለፉም።

ቀደም ሲል የቻይና የምጣኔ-ሐብት ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ካለፈው ጥር መጀመሪያ ወዲህ በጨርቃ-ጨርቅ ምርቶች ላይ የሚሰራበትን የውጭ ንግድ ቀረጥ ወደ ኋላ እንደሚስብ አስታውቆ ነበር። ቻይና ከዚሁ ሌላ ከሁለት ሣምንታት በፊት በ 74 የምርት ዓይነቶች ላይ ከተተወ ወዲህ እንደገና ተጭኖ የነበረውን ቀረጥም መልሳ አንስታለች።
በሚኒስትሩ መሥሪያ ቤት መግለጫ መሠረት የአውሮፓው ሕብረት ኮታ ሊጥልባቸው በሚያስበው የምርት ዓይነቶች ላይ ቀደም ሲል እንደታሰበው ተጨማሪ የውጭ ንግድ ግብርም አይኖርም። ቦ ሺላይ እንዳሉት ይህ የሚደረገው የቻይና አምራቾች ድርብ ጫና እንዳይፈጠርባቸው በማሰብ ነው። ሕዝባዊት ቻይና ገና ባለፈው ሰንበት ነበር የአውሮፓው ሕብረት በዓለም ንግድ ድርጅት ዘንድ ሊከሣት ባደረገው ውሣኔ ቁጣዋን የገለጸችው።

እርግጥ የቻይናው ባለሥልጣን የሕብረቱን አርአያ በመከተል ለዓለም ንግድ ድርጅት የበኩላቸውን ክስ ለማቅረብ አይፈልጉም። ሆኖም ግን መብቱን ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ማስገንዘባቸው አልቀረም። ቤይጂንግ አሜሪካ እስካሁን ወደ ገበያዋ የሚገባውን የቻይና ምርት በመገደቧ ሁለት ሚሊያርድ ዶላር ገቢ አጥታለች። በአውሮፓ ገበያም ሶሥት መቶ ሚሊዮን ዶላር ሲቀርባት ቦ የሚናገሩት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረው የአገራቸው ጨርቃ-ጨርቅ ፋብሪካ ሠራተኛ ሕልውና አደጋ ላይ እንደወደቀ ነው።

ቻይና በውዴታዋ የውጭ ንግዷን መገደቧ ጥያቄ ውስጥ እንዳማይገባ የገለጹት ቦ እንዳሉት “ቻይና የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ዓመታት የፈጀ የድርድር ጊዜ ወስዶባታል። ስምምነቱ መብትና ግዴታን እኩል የያዘ ነው። ቻይና ገበዮቿን ለመክፈት ባሣየችው ዝግጁነት ያገኘችው ማካካሻ ጨርቃ-ጨርቅ አምራቾቿ ኮታው ካበቃ በኋላ ያለውን መብት ሁሉ እንዲጠቀሙ የሚፈቅድ ነበር። የአውሮፓ ሕብረትና አሜሪካ ቃል እንደገቡት ግዴታዎቻቸውን ቢወጡና ቀደም ብለው የጨርቃ-ቀርቅ ኮታን ቢያስወግዱ ኖሮ ዛሬ ይህ ችግር ባልተፈጠረም ነበር።” በቻይናው የውጭ ንግድ ሚኒስትር ዕምነት!

ብራስልስና ዋሺንግተን በበኩላቸው ቻይና ወደ ውጭ የምትልከውን ርካሽ የጨርቃ-ጨርቅ ምርት እንድትገድብ ባለፉት ሣምንታት በተደጋጋሚ ሲያሳስቡ ቆይተዋል። የገበዮቹ በዚህ ምርት መጥለቅለቅ በአገር ኢንዱስትሪዎች ለተጨማሪ የሥራ መስኮች መዘጋት ምክንያት እንዳይሆን ፍርሃታቸው ከፍተኛ ነው። ቻይና በአንጻሩ የነጻ ንግድ መብቷን በማስረገጥ በጨርቃ-ጨርቅ ኢንዱስትሪዎቿ ተሰማርተው የሚገኙትን 19 ሚሊዮን ሠራተኞች ሕልውና ለመጠበቅ እንደምትፈልግ ነው የምትናገረው።

የጨርቃ-ጨርቅ ንግዱ ኮታ ካከተመ ካለፈው ጥር ወር መጀመሪያ ወዲህ የቻይና ፋብሪካዎች ወደ አውሮፓና አሜሪካ የሚያሻግሩት ምርት እጅግ ከፍ ብሏል። የአውሮፓ ሕብረት እንደሚለው በዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ወደ ዓባል ሃገራቱ የገባው የቻይና ምርት መጠን በአንዳንድ የአልባሣት ዓይነቶች ከአምሥት ዕጅ በልጧል። በመሆኑም ዋሺንግተንና ብራስልስ የቻይና የገበያ ድርሻ በዓለም ንግድ ድርጅት መርህ መሠረት ቢበዛ ከ 7.5 ከመቶ በላይ መሆን እንደማይገባው ያስገነዝባሉ። ቻይና ለዚሁ የምትሰጠው ምላሽ ምዕራባውያኑ መንግሥታት ገበያ የመዝጋት ዓላማ እያራመዱ ነው የሚል ነው። ሁኔታው አስታራቂ መፍትሄ በቅርብ የመገኘቱን ተሥፋ የሚያጠነክር አይደለም።

የቻይናና የምዕራቡ ዓለም የጨርቃ-ጨርቅ ገበያ ውዝግብ ማለቂያ አጥቶ በቀጠለበት ወቅት በሌላ በኩል ደግሞ ከቤይጂንግ አንጻር በአንድ ወገን በተሰለፉት በአሜሪካና በአውሮፓው ሕብረት መካከል የአውሮፕላን ኩባንያዎቻቸውን የኤየርቡስንና የቦይንግን የገንዘብ ድጎማ አስመልክቶ የተነሣው ሙግት አይሏል። የአውሮፓ ሕብረት ባለሥልጣናት ባለፈው ማክሰኞ ከብራስልስ እንዳስታወቁት ቀደም ሲል የዋሺንግተን መንግሥት እንዳደረገው ሁሉ በዓለም ንግድ ድርጅት ዘንድ የክስ ማመልከቻ ለማቅረብ ተነስተዋል።

የሕብረቱ የውጭ ንግድ ኮሜሣር ፔተር ማንደልሶን እንደገለጹት ይህ ውዝግብ በዓለም ንግድ ድርጅት ታሪክ ውስጥ ከባዱና ብዙ ወጪን የሚጠይቀው ሣይሆን አይቀርም። ለረጅም ጊዜ ውስጥ-ውስጡን’ ሲጋይ የቆየው የንግድ ውዝግብ አሁን በአዲስ መልክ የተቀጣጠለው ኤየርቡስ ኩባንያ A 350 ለተሰኘው የረጅም ርቀት በራሪ አውሮፕላኑ ግንቢያ በአራት የአውሮፓ መንግሥታት ዘንድ የብድር ዕርዳታ በማመልከቱ ነው።

ማንደልሶን እንዳስረዱት መንግሥታዊውን የገንዘብ አቅርቦት በሲሶ ለመቀነስ ዝግጁ መሆናቸውን ለአሜሪካ መንግሥት አስታውቀዋል። ሆኖም የኤየርቡስ ተፎካካሪ ቦይንግ መላው የገንዘብ አቅርቦት መሰረዝ ይኖርበታል ሲል በመጽናቱ አስታራቂ መፍትሄ ለማስፈን አልተቻለም። ኮሜሣሩ እንደሚሉት ዋሺንግተን የዕርቅ ፍላጎት የላትም፤ ከአውሮፓ ጋር የውዝግቡን መንገድ ነው የመረጠችው።

ቦይንግ ኩባንያ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንግሥታዊ ድጎማ እንደሚያገኝ ለማንም የተሰወረ ነገር አይደለም። ይህም የአውሮፕላን ግንቢያን አስመልክቶ እ.ጎ.አ. በ 1992 ዓ.ም. የሰፈነው ትራንስ-አትላንቲክ ስምምነት ያስቀመጠውን ገደብ ከሁለት እስከ ሶሥት ዕጅ የሚያጥፍ ነው። በብራስልስ መግለጫ መሠረት ቦይንግ ለአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር መሥሪያ ቤትና ለጠፈር ምርምሩ ተቋም ናሣ ባለፉት አሠርተ-ዓመታት ባካሄዳቸው የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ዕድገትና የሶፍትዌር ግንባታ ተግባራት 22 ሚሊያርድ ዶላር መንግሥታዊ ድጎማ አግኝቷል።

ይህ ደግሞ ለኤየርቡስ ኩባንያ እንደሚቀርበው ብድር ተመልሶ የሚከፈል አልነበረም። ቦይንግ ድጎማውን እስካሁን መልሶ አልከፈለም፤ አይከፍልምም። በማንደልሰን አባባል ኩባንያው ላቀደው Dreamliner 787 የተሰኘ አውሮፕላን ዕድገት ከሚያስፈልገው ወጪ 70 በመቶውን ድርሻ የሚያገኘውም ከአሜሪካ ሕዝብ ከሚሰበሰበው ግብር ይሆናል።

በአውሮፓው ሕብረት የንግድ ኮሜሣር ዕምነት እንደ ዕውነቱ ቦይንግ ውዝግቡን የመረጠው ድጎማውን በመጻረር ሣይሆን ፉክክሩን በመፍራት ነው። የአሜሪካ መንግሥት በሃቅ ለነጻ ገበያና ፉክክር የቆመ ከሆነ የብሄራዊው ሸንጎ እንደራሴዎች ም/ቤት ያቀረበውን ሃሣብ ተቀብሎ ለምሳሌ በአሕጽሮት EADS በመባል የሚጠራውን አውሮፓዊ የኤየርቡስ እናት ኩባንያ ከአሜሪካ አየር ሃይል የጦር መሣሪያ ኮንትራት ከማግለል መቆጠብ ይጠበቅበታል።
ንግዱ 23 ሚሊያርድ ዶላር ወጪን የሚጠይቁ የአንድ መቶ ነዳጅ መሙያ አውሮፕላኖችን ግንቢያ የሚመለከት ሲሆን እስካሁን ብቸኛው አቅራቢ በነበረው በቦይንግ ውስጥ በተፈጥረ የጉቦ ክስ የተነሣ አዲስ የጨረታ ማስታወቂያ እንደሚወጣ ነው የሚጠበቀው። ውሣኔው የወቅቱ የብራስልስና የዋሺንግተን ትራንስ-አትላንቲክ ውዝግብ የጋረደው እንዳይሆን በጣሙን ያሰጋል።