የዓለም ባንክ በአዲስ አመራር | ኤኮኖሚ | DW | 04.07.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ባንክ በአዲስ አመራር

የዓለም ባንክ የቀድሞ ፕሬዚደንት ሮበርት ዞሊክ ባለፈው ዕሑድ ሥልጣናቸውን ለተተኪያቸው ለጂም-ዮንግ-ኪም አስረክበዋል።

የዓለም ባንክ የቀድሞ ፕሬዚደንት ሮበርት ዞሊክ ባለፈው ዕሑድ ሥልጣናቸውን ለተተኪያቸው ለጂም-ዮንግ-ኪም አስረክበዋል። ከኮሪያ የመነጩት የአሜሪካ ዜጋ የፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ዕጩ ሲሆኑ በተፋጠነ ዕድገት ላይ በሚገኙ ሃገራት የምዕራቡ ዓለም ጥቅም አስጠባቂ እንዳይሆኑ በመጠኑም ቢሆን በጥርጣሬ ዓይን መታየታቸው አልቀረም። ታዲያ አዲሱ ባለሥልጣን እያደር በነዚሁ ሃገራት ዘንድ ብቁነትና ሚዛናዊነታቸውን ማሳመኑ ይሳካላቸው ይሆን?የዋሺንግተኑን ተቋም ሁኔታ ለሚያውቅ ጂም-ዮንግ-ኪም ቀላል ሃላፊነት አይደለም የተቀበሉት። ቀደምታቸው ሮበርት ዞሊክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የሆነውን ባንክ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ወቅት ድህነትን ለመታገል እንዲችል አድርገው መምራት ነበረባቸው። በሰሜናዊው ጀርመን ኪል ከተማ ውስጥ የሚገኘው የዓለምኤኮኖሚ ምርምር ኢንስቲቲዩት ምክትል ፕሬዚደንት ሮልፍ ላንግሃመር እንደሚሉት ተግባሩ ለዞሊክም ቀላል አልነበረም።

«ዞሊክ ትልቅ አሻራ ጥለው ለማለፍ አልቻሉም። ለዚህም ምክንያቱ በጥቂቱም ቢሆን በዓለም ኤኮኖሚ ላይ የደረሰው ነውጽ ነው ብዬ አስባለሁ። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት የራሳቸው ችግር ነበራቸው፤ አሁንም አላቸው። በዚህ ረገድ የኤውሮ ዞንን፤ አሜሪካን ወይም ጃፓንን መጥቀስ ይቻላል። እናም የዓለም ባንክ ከዚህ አንጻር ለአዳጊ ሃገራት ችግር ብዙም ማድረግ የሚችለው ነገር የለም ማለት ነው»በሌላ በኩል ዊድ የተሰኘው የጀርመን ከመንግሥት ነጻ የሆነ ድርጅት ባልደረባ ፔተር ቫል እንደሚሉት ዓለምአቀፉ ቀውስ ጥሩ ነገር መቀስቀሱም አልቀረም።

«የፊናንሱ ቀውስ በገበዮች ላይ ጭፍን ዓመኔታ መጣሉ መውጫ ቀዳዳ ያሳጣ ነገር እንደነበርም አሳይቷል። በፊናንሱ ቀውስ ሂደት አንዳንድ አግባብ ያላቸው ዕርምጃዎችም ተወስደዋል። ለምሳሌ ድሆች ሃገራት የፊናንሱን ቀውስ ተጽዕኖ ማለዘብ እንዲችሉ ዕርዳታ ቀርቦላቸዋል። እነዚህ እንግዲህ ጠቃሚ ዕርምጃዎች ነበሩ። በዚህ በኩል የዓለም ባንክ የተወሰነ ትምሕርት ማግኘቱም አልቀረም»

የዓለም ባንክ በሮበርት ዞሊክ አመራር ስር በደረሰበት ድምዳሜ መሠረት በዓለም ላይ አስከፊ የሆነው ድህነት ለዘብ ብሏል። በጥናቱ መሠረት በዓለም ላይ በከባድ ድህነት የሚኖረው ሕዝብ ቁጥር ከጎርጎሮሳውያኑ 1981 እስከ 2008 ከሁለት ወደ 1,3 ሚሊያርድ ነው የቀነሰው። በሌላ አነጋገር ከ $1,25 ባነሰች የዕለት ገቢ ኑሮውን የሚገፋው ሕዝብ ቁጥር በ 700 ሺህ ቀንሷል ማለት ነው። ግን ስኬቱ በጥቅሉ በዓለም ባንክ ብቻ የተገኘ ነበር ማለት አይደለም«ሌላው ሃቅ የታዳጊ ሃገራት ስኬት ዛሬ ዓለምአቀፍ አበዳሪዎች ከሚሰጡት ድጋፍ ይልቅ በአብዛኛው በራሳቸው ጥረት የተገኘ ነው። ይህ የዓለም ባንክን ድጋፍም ይመለከታል»

ይህ ሂደት ደግሞ የዓለም ባንክን ተፈላጊነትም ሆነ ተሰሚነት ከባድ ከሆነ ችግር ላይ እየጣለ መሄዱ አልቀረም። ቻይናን፣ ሕንድን ወይም ብራዚልን የመሳሰሉት ሃገራት በዛሬው ጊዜ ራሳቸው ለታዳጊ ሃገራት ብድር ለመስጠት በቂ ሃብት አላቸው። ቻይና ለምሳሌ በ 2010 ለታዳጊ ሃገራት ብድር በማቅረብ የዓለም ባንክን ለመደረብ በቅታ ነበር።

«የዓለም ባንክ ከሁሉም በላይ በሥልጣን ክፍፍልና በዕቅድ አወጣጡ ረገድ እነዚህን የተለወጡ ሁኔታዎች የግድ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል። በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ሃገራት ዛሬ የንግድ ተባባሪዎች ብቻ አይደሉም። ጠቃሚ የሆኑ የገንዘብ ምንጮችም ጭምር እንጂ! የራሳቸውን መንገድ ተከትለው የሚራመዱ ናቸው። እናም የዓለም ባንክና በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት ለጋሽ ሃገራት ለዚህ ዕውቅና ካልሰጡ የሚከተለው ክፍፍል ይሆናል። አደጋው ታዲያ የዓለም ባንክን የሚያገል ሁኔታ መፈጠሩ ነው»

ሆኖም ከመንግሥት ነጻ የሆነው ድርጅት የዊድ ባልደረባ ፔተር ቫል እንደሚያምኑት ይህም ሂደት ፉክክር ገበያን ያደራል እንደሚባለው ዕድል ከፋች ሊሆን የሚችል ነው።«የዓለም ባንክ ላለፉት አያሌ ዓመታት፤ በመሠረቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የነበረውን ሞኖፖል እያጣና ከብዙዎች መካከል አንዱ እየሆነ ነው። አሁን በአሕጽሮት ብሪክስ በመባል የሚታወቀው ብራዚልን፣ ሕንድን፣ ቻይናን፣ ሩሢያንና ደቡብ አፍሪቃን የጠቀለለው ስብስብም የራሱን የልማት ባንክ ለማቋቋም ወስኗል። ይህ ደግሞ በእርግጥ የዓለም ባንክን ሚና የሚለውጥ ነው። ባንኩ ከሌሎች ጋር ለፉክክር መቅረብ ግድ ይሆንበታል። ይህም መሠረታዊ አዲስ ፈተናው ነው የሚሆነው»

የዓለም ባንክ በቀድሞው ጊዜ እንደ እህት ድርጅቱ እንደ ዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ሁሉ በታዳጊ ሃገራት የኤኮኖሚ ፖሊሲን በማለዘብ፣ማጣጣምና የግል ባለንብረትነት በማስፈን መስፈርቱ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸገውን ዓለም ጥቅም ያራምዳል በመባል ይወቀስ ነበር። ዋነኛ ግቡ የልማት ዕርዳታው ሣይሆን ታዳጊ ሃገራትን በኢንዱስትሪ ልማት ለበለጸጉት መንግሥታት የሚመቹ ገበዮች እንዲሆኑ አድርጎ ማነጽ መሆኑም ተነግሯል። ይሁንና ይህ ወቀሣ ዛሬ እንደቀድሞው ብዙ ጎልቶ አይሰማም። ለነገሩ ያለ ምክንያትም አይደለም። የኪሉ የዓለም ኤኮኖሚ ጥናት ኢንስቲቲዩት ባለሙያ ሮልፍ ላንግሃመር በበኩላቸው ባንኩ ስልታዊ ለውጥ አድርጓል ባይ ናቸው።

«እነዚህ መስፈርቶች፤ የግል ባለንብረትነት፣ የኤኮኖሚ ፖሊሲ መለዘብና የገበያ መከፈት ጥያቄዎች ሲነሱ በቀጥታ አንድ ልብስ ለሁሉም እንዴት ልክ ይሆናል የሚል ትችትን ሲቀሰቅሱ ቆይተዋል። የዓለም ባንክ ዛሬ ይህን መሰሉ ፕሮግራም በሚኖረው ተጽዕኖና በተለይም በድሃ-ድሃው ሕዝብ ሁኔታ ላይ አተኩሮ ነው የሚገኘው»ይሁን እንጂ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ዕርዳታ ጉዳይ ሃላፊ የነበሩት አዲሱ የባንኩ ፕሬዚደንት ጂም-ዮንግ-ኪም ለገንዘብ ተቋሙ ተግባር ተስማሚው ሰው መሆናቸውን በተፋጠነ ዕድገት ላይ ላሉት ሃገራት ማሳመን መቻላቸው በወቅቱ ያልለየለት ነገር ነው። የሆነው ሆኖ ፔተር ቫል በበኩላቸው አዲስ መጥረጊያ የተሻለ ያጸዳል በሚለው አነጋገር መንፈስ ኪም እንደሚሳካላቸው ተሥፋ ጥለዋል።

«የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ግቦች እንደታቀደው እስከ 2015 የማይደረስባቸው መሆኑን አዕዋፍ ሳይቀር ከጣራ ላይ ሆነው የሚያፋጩት ነገር ነው። ገደቡ የቀረው ሶሥት ዓመት ብቻ ነው። እናም ሃሣቡን በከፊል እንኳ ለማሳካት ትልቅ ጥረት ያስፈልጋል። እንግዲህ የዓለም ባንክም በተለይ አሁን ከቻይና ወይም ከብሪክስ ስብስብ ጋር በተፈጠረው ፉክክር የሚፈለግ መሆኑን ማጤኑ ግድ ነው»የኪሉ የኤኮኖሚ ጥናት ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ሮልፍ ላንግሃመርም ቢሆን ከዚህ የተለየ አስተሳሰብ የላቸውም።

«ጂም-ዮንግ-ኪም ከሮበርት ዞሊክ ይልቅ በተፋጠነ ዕድገት ላይ ከሚገኙት ሃገራት ጋር ግንኙነት እንደሚሹና የተፈጥሮ ጸጋን መመንመን የመሳሰሉ ብሄራዊ ድንበርን የሚሻገሩ ጥያቄዎችን እንደሚያነሱ ተሥፋ አደርጋለሁ። ይህ ችግር ከፊታችን ላይ ተደቅኖ ነው የሚገኘው። የዓለም ባንክ በዕድገትና በተፈጥሮ ጥበቃ ችግሮች መካከል ባለው ግንኙነት ላይ አጥብቆ ሊያተኩር ይገባል። እንደማስበው ኪም የተፈጥሮ ጸጋን መመንመና ይሄው አላቂ መሆኑንም ዓቢይ ርዕሳቸው ቢያደርጉ ለባንኩ የሚስማማ ነው»

ያም ሆነ ይህ ጂም-ዮንግ-ኪም እስካሁን በታዳጊው ዓለም ላይ አተኩሮ የኖረውን የባንኩን አሰራር በማስፋፋት ግሪክን የመሳሰሉ ሃገራትን ጭምር ለመርዳት ማሰባቸውን ግልጽ አድርገዋል። ኪም እንዳሉት ይህን የሚያደርጉት የዓለም ኤኮኖሚ ይዞታ ያሳሰባቸው በመሆኑ ነው። አዲሱ የዓለም ባንክ አመራር ያደጉ ሃገራትን ለመርዳት መነሳቱ እስካሁን ከነበረው የባንኩ ፖሊሲ አንጻር መሠረታዊ የአቅጣጫ ለውጥ ይሆናል። ይሄው እስካሁን ባንኩ ያተኩርባቸው በነበሩት አዳጊ ሃገራት ላይ ምን ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል በወቅቱ እንዲህ ብሎ ለመናገር አይቻልም።

ለማንኛውም ኪም ባለፈው ሰኞ ሥልጣናቸውን በተረከቡበት ወቅት የቀደምታቸውን የሮበርት ዞሊክን የእስካሁን መርህ ከስር መሠረቱ በሚጻረር ሁኔታ ነበር የዓለም ባንክ እንደ ኤውሮ ዞን መንግሥታት መዋቅራዊ ችግሮች ለሚገጥማቸው ሃገራት ቴክኒካዊ ዕርዳታ እንደሚያደርግና በአማካሪነትም ከጎናቸው እንደሚቆም ያስረገጡት። ዞሊክ ቀደም ሲል ለዓለም ባንክ አደገኛ ሊሆን አንደሚችል በማመልከት ግሪክን ከመርዳት መራቁን መምረጣቸው ይታወሳል።

በሕክምና ሙያ የሰለጠኑት ኪም በዛሬው ለዓለም ኤኮኖሚ ወሣን በሆነ ወቅት ባንኩ ያደጉ ሃገራትንም ከውድቀት መጠበቁ ዋና ተግባራቸው መሆኑን ነው ያስረዱት። ባንኩ እስካሁን በገንዘቡና ብቃቱ የድሃ ድሃ የተባሉ ሃገራትን በዋነኝነት ሲያስቀድም በተፋጠነ ዕድገት ላይ ባሉት ሃገራት ላይም አተኩሮ ነው የኖረው።ጂም-ዮንግ-ኪም በዓለም ባንክ አመራራቸው አዲስ አቅጣጫን ይዘው ለመራመድ ተነስተዋል። ስሌታቸው የተሃድሶ ፍላጎት ይሁን ወይም በፉክክር ብዛት ክብደቱን እያጣ የሚሄደውን የገንዘብ ተቋም በማዳን ላይ ያለመ በወቅቱ በትክክል እንዲህ ብሎ ለመናገር አይቻልም። ጥያቄው ኪም ጠንካራውን የፖለቲካ ተልዕኮ ሊወጡት ይችላሉ ወይ ነው።

አዲሱ የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት እንደ 11 ቀደምቶቻቸው የተፈተሹ የፖለቲካ ሰው አይደሉም። ባንኩ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በአሜሪካዊ ሹም ሲመራ ኪም ምንም እንኳ የማሸነፍ ዕድል ባይኖራቸውም ለመጀመሪያ ጊዜ ከታዳጊው ዓለም የቀረቡ ተፎካካሪዎች ነበሩባቸው። ይህም በዘልማድ የአሜሪካ ሆኖ በቆየው ሥልጣን ሌሎች ለፉክክር መቅረባቸው ዋሺንግተን በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙትን ሃገራት ለማግባባት በማሰቧ ነው። እንግዲህ በተለወጠ ሁኔታ የባንኩን ሥልጣን የተረከቡት ኪም ስኬት እንዲያገኙ በአዳጊውና በበለጸገው ዓለም መካከል ሚዛንን ለመጠበቅ መቻላቸው ወሣኝ የሚሆን ይመስላል።

መሥፍን መኮንን

ሒሩት መለሠ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 04.07.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15Qdf
 • ቀን 04.07.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15Qdf