የዓለም ባንክና ጸረ-ሙስና ትግሉ | ኤኮኖሚ | DW | 15.09.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ባንክና ጸረ-ሙስና ትግሉ

የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ዛሬ ሢንጋፑር ላይ ዓመታዊ ጉባዔያቸውን ከፍተዋል። የዓለም ባንክ በታዳጊ አገሮች ሙስናን ለመታገል የሚያደርገው የተጠናከረ ጥረት በይፋ ባይነገርም ከጉባዔው አጀንዳ ዓበይት አርዕስት መካከል አንዱ ነው።

ፓውል ዎልፎቪትስ

ፓውል ዎልፎቪትስ

የባንኩ ፕሬዚደንት ፓውል ቮልፎቪትስ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ጸረ-ሙስናውን ትግል ከዋና ዋና ተግባሮቻቸው እንዱ ማድረጋቸው ይታወሣል። ሆኖም ይህ በተለይ በታዳጊ አገሮች ዓለምአቀፍ የልማት ገንዘብን በማባከኑ ረገድ በጅምላ የመጠርጠር ስሜትን አሳድሮ ነው የሚገኘው። ፓውል ቮልፎቪትስ ዛሬ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባሰሙት ንግግር ቀደም ሲል ባሰፈኑት መሥመር የሚገፉ መሆናቸውን እንደገና አረጋግጠዋል። የዓለም ባንኩ ፕሬዚደንት በታዳጊ አገሮች ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ድህነትና መከራ ለማስወገድ መውጫ መንገድ እንዳለ ጽኑ ዕምነታቸው ነው።
እርግጥ በጎ የአስተዳደር ዘይቤ መስፈን ይኖርበታል፤ ለትምሕርት፣ ለጤና ጥበቃና መንግሥታዊ መዋቅራት መስፋፋት ሰፊ ገንዘብ መቅረቡ፤ በተለይ ደግሞ ቁርጠኛ የሆነ ጸረ-ሙስና ትግል መደረጉ ወሣኝነት አላቸው። ቮልፎቪትስ ቀደም ሲል በኢንዶኔዚያ ለሶሥት ዓመታት ያህል የአሜሪካ አምባሣደር ሆነው ባገለገሉበት ጊዜ የልማት ተራድኦው ሙስና ሳይወገድ ለታሰበለት ድሃ ሕዝብ ጥቅም ሊውል እንደማይችል ጥሩ ትምሕርት ቀስሜያለሁ ባይ ናቸው። በርሳቸው አነጋገር የልማት ገንዘብ የሚቀርበው ሆስፒታሎችንና ትምሕርት ቤቶችን ለማነጽ፤ እንዲሁም መዋቅራዊ ግንባታን ለማካሄድ እንጂ የፖለቲከኞችንና የባለሥልጣናትን የባንክ ሂሣብ ለመሙላት መሆን የለበትም።

በእርግጥም የልማት ተራድኦው ገንዘቡ አቅራቢ ወገን፤ ማለትም ግብር ከፋዩ የኢንዱስትሪው ዓለም ሕዝብ የሚለግሰው ዕርዳታ ላሰበው ግብ በተግባር መዋሉን ማወቅ ይፈልጋል። አለበለዚያ የልማት ዕርዳታው አስፈላጊነት በለጋሽ አገሮች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያጣ ነው የሚሆነው። የፓውል ቮልፎቪትስ ጸረ-ሙስና ትግልም ይህንኑ ግንዛቤ መሠረት ያደርጋል።

“ዓላማው የልማት ዕርዳታን መቀነስ አይደለም። ዓላማው ይልቁንም ሁኔታውን ለመሻሻል ጥረትን ማጠናከር፣ ገንዘብ ማቅረብና መርዳት ነው። ግልጽ እንዲሆን፤ ግብር ከፋዩ ሕዝብና የዓለም ባንክ መሠረታዊ ደምቦች ገንዘቡ ለተፈለገው ተግባር ሥራ ላይ መዋሉን ይጠይቃሉ”

ፓውል ቮልፎቪትስ ጸረ-መስና ትግልን በቃል ብቻ ሣይሆን በተግባር ጭምር የዓለም ባንክ ፕሬዚደንትነት ዘመናቸው መለያ አድርገዋል። በብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ብድር መስጠቱንም ሆነ ለማቅረብ መስማማቱን መግታታችውም አልቀረም። ይህ ዕርምጃቸው ደግሞ በተለይ ኢትዮጵያን፣ ሕንድን፣ ቻድን፣ ኬንያን፣ ኮንጎንና ባንግላዴሽን የመሳሰሉትን ይመለከታል። ሌሎች አገሮችም ገንዘቡ እንዳይቆረጥባቸው መፍራታቸው አልቀረም። ሆኖም የዓለም ባንኩ ፕሬዚደንት ዓላማ ራሳቸው እንዳሉት የበለጠ ገንዘብ ማውጣት እንጂ መቆጠብ አይደለም። “አሃዞቹ ራሳቸው ዕርዳታውን ለመቁረጥ እንደማንፈልግ ይናገራሉ ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።

ያለፈው ዓመት ለዓለም ባንክ አካል ቡድኖች በተለይ የዓለምአቀፉ የልማት ወኪል International Development Agency ርካሽ የልማት ብድር ሲታይ አዲስ ወሰን ላይ የተደረሰበት ነበር። የብድር አቅርቦቱ ዘጠኝ ከመቶ በማደግ ወደ 9.5 ሚሊያርድ ዶላር ከፍ ሲል ይህም ከዚህ ቀደም ከነበረው ሁሉ ከፍተኛው መሆኑ ነው። ከዚህ ገሚሱ፤ በትክክል 4.7 ሚሊያርዱ የተላለፈው ደግሞ ወደ አፍሪቃ ነበር። ሃያ በመቶ ዕድገት መሆኑ ነው። ለግሉ ዘርፍ የሚቀርበው የዓለምአቀፉ ፊናንስ ተቋም International Finance Corporation ብድር እንዲያውም 25 በመቶ ወደ 6.5 ሚሊያርድ ዶላር በመጨመር ከአዲስ ደረጃ ላይ ደርሷል።
የዓለም ባንክ ራሱ ለታዳጊ አገሮች 14.2 ሚሊያርድ ዶላር ብድር ለመስጠት ሲወስን ይህም ከሰባት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛው መሆኑ ነው። ፓውል ዎልፎቪትስ የባንኩን ብድር ወደፊትም በማሳደግ እስካሁን ከነበረው በበለጠ ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

“ከሣሃራ በስተደቡብ ያለው የአፍሪቃ ክፍል ከዓለም ባንክ በኩል ቀደምት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብዬ አምላለሁ። ባለፉት 25 ዓመታት በዓለም ዙሪያ 400 ሚሊዮን ሕዝብ ከዝቅተኛው የድሕነት ደረጃ ሲያመልጥ በአፍሪቃ በአንጻሩ 600 ሚሊዮን ሕዝብ ይብሱን ድሃ ነው የሆነው። ይህ ደግሞ ለነዚህ ወገኖች አሳዛኝ ሃቅ፤ ለመላው ዓለምም አስከፊ ሂደት ነው”