የዓለም ባንክና የድህነት ቅነሣ | ኤኮኖሚ | DW | 21.03.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ባንክና የድህነት ቅነሣ

የተባበሩት መንግሥታት ዓባል ሃገራት እስክ ጎርጎሮሳውያኑ 2015 ዓመተ-ምሕረት ድረስ በምድራችን ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን አስከፊ ድህነት በግማሽ ለመቀነስ በያዝነው ሚሌኒየም መግቢያ ላይ መስማማታቸው ያታወሳል።

የተባበሩት መንግሥታት ዓባል ሃገራት እስክ ጎርጎሮሳውያኑ 2015 ዓመተ-ምሕረት ድረስ በምድራችን ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን አስከፊ ድህነት በግማሽ ለመቀነስ በያዝነው ሚሌኒየም መግቢያ ላይ መስማማታቸው ያታወሳል። የዓለም ባንክ በቅርቡ ባወጣው ዘገባው ድህነትን በመታገሉ በኩል ከወዲሁ ትልቅ ዕርምጃ መደረጉን በማመልከት የሚሌኒየሙ ግብ እንደሚሳካ ተሥፋውን ሲገልጽ እርግጥ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች ጉዳዩን አጠያያቂ ማድረጋቸው አልቀረም።

የዓለም ባንክ በምድራችን ላይ የሚገኘው ድሃ ሕዝብ ቁጥር ከጎርጎሮሳውያኒ ዓመት 1990 እስካለፈው 2010 ድረስ በግማሽ መቀነሱን በቅርቡ አመልክቷል። ይህም የሚሌኒየሙ ግብ ከተመደበለት ጊዜ አምሥት ዓመት ቀድሞ ከወዲሁ በ 2010 ተደርሶበታል ማለት ነው። ዕውነት? እጅግ በጣም ያጠራጥራል።

ዛሬ አዳጊ እየተባሉ በሚጠሩት ድሆች አገሮች ከአንድ ሚሊያርድ የሚበልጥ ሕዝብ ኑሮውን የሚገፋው ከአንድ ዶላር ሃያ አምሥት ሣንቲም ባነሰች የቀን ገቢ ነው። የዓለም ባንክ ይህን  የአንድ ዶላር ከሃያ አምሥት ሣንቲም መስፈርት የወሰደው በ 15 የድሃ ድሃ የተባሉ ሃገራት ሁኔታ ላይ ተመስርቶ መሆኑ ተጠቅሷል። ምንም እንኳ የዓለም ባንክ የዓለምአቀፍ ድህነት አጥኚ ቡድን መሪ ማርቲን ራቫሊዮን የድሃው ቁጥር መቀነሱን ቢያስረግጡም አሁንም አሃዙ በቀላሉ የሚገመት አይደለም።

« በግልጽ ለማስቀመጥ እፈልጋለሁ። በ 2010 የዓለም የድህነት ድርሻ፤ ከአንድ ዶላር ሃያ አምሥት ሣንቲም ባነሰች የዕለት ገቢ መተዳደር የነበረበት ድሃ ሕዝብ መጠን ከ 1990 ሲነጻጸር በግማሽ ቀንሷል»

የሚሌኒየሙ ግቦች ሂደት የሚለካው እንግዲህ 1990-ን መሠረት በማድረግ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአዲሱ ሚሌኒየም ስምንት ግቦችን እስከ 2015 ድረስ ዕውን ለማድረግ መነሳቱ ይታወሳል። አሁን እንደሚባለው ከሆነ ታዲያ የመጀመሪያው ግብ፤ ድህነትን በግማሽ መቀነሱ ተሳካ ማለት ነው።

«በመላው የዓለም ባንክ አካባቢዎች አጠቃላይ የድህነት ቅነሣ መደረጉን ሰንገልጽ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ይህ ጥሩው ዜና ነው። ግን በተመሳሳይ ጊዜ ገና እጅግ ድሃ  የሆነ ብዙ ሕዝብ መኖሩን መዘንጋት የለብንም»

ይህን የሚሉት የዓለም ባንክ የድህነት ጉዳይ መርማሪ ማርቲን ራቫሊዮን ናቸው። የባንኩ ባለሙያ ሌላው ቀርቶ ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኘው የአፍሪቃ ክፍልም ትልቅ ዕርምጃ እንደተደረገ ነው የሚናገሩት።  በርሳቸው አባባል አስከፊው ድህነት በጠቅላላው በዚህ አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ 50 በመቶ በታች ዝቅ ሊል በቅቷል።                               

ይህ ድምዳሜ ድህነትን ለመታገል የተወሰዱት ዕርምጃዎች በሚገባ ፍሬያማ ሆነዋል የማለትን ያህል ነው የሚሆነው። ይሁን እንጂ በዚህ በቦን የጀርመን የልማት ፖሊሲ ኢንስቲቲዩት የድህነት ጉዳይ ተመራማሪ የሆኑት ኒኮል ሪፒን በዓለም ባንክ አባባል ትክክለኝነት በጣሙን ተጠራጣሪ ናቸው። እናም የቀርቡትን አሃዞች በጥሞና መመርመር ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ። እንደርሳቸው ከሆነ፤

«ከ 1990 ዓመተ-ምሕረት ወዲህ ከከፋው ድህነት ከተላቀቀው 620 ሚሊዮን ሕዝብ 510 ሚሊዮን ገድማ የሚደርሰው የሚገኘው ቻይና ውስጥ ነው»

እናም ሪፒን ዕርምጃውን የአካባቢ እንጂ ዓለምአቀፍ በሎ መናገሩን አይፈቅዱትም። ቻይናን ነጥለን በቅንፍ ውስጥ ብናስቀምጥ የድህነቱ ቅነሣ በ 110 ሚሊዮን ብቻ የተወሰነ ነው የሚሆነው። ይህም በ 18 ዓመት ጊዜ ውስጥ! ከሣሃራ በስተደቡብ አፍሪቃ ለምሳሌ በ 2008 386 ሚሊዮን ሕዝብ በከፋ ረሃብ ይኖር ነበር። ከ1990 አንጻር 96 ሚሊዮን የበለጠ መሆኑ ነው። እርግጥ ከ 18 ዓመታት በፊት ከነበረው ሲነጻጸር ዛሬ በ 620 ሚሊዮን ያነሰ ሕዝብ በከፋ ድህነት መኖሩ እሰይ የሚያሰኝ ነው። ሆኖም አጠቃላዩ ሁኔታ ከፌስታ ስሜት መቆጠብን ይጠይቃል።

በተለይም ከሣሃራ በስተደቡብ ያለውን የአፍሪቃ ክፍል በተመለከተ የድህነት መጠን በግማሽ ለመቀነሱ ጭብጥ ማስረጃዎች ማቅረቡ ለዓለም ባንክም ቢሆን ቀላል ነገር አይሆንም። በአንዳንድ የአፍሪቃ አገሮች ባለፉት ዓመታት ያልተቋረጠ የኤኮኖሚ ዕድገት መታየቱ ቢነገርም ይሄው በሕረተሰብ ማሕበራዊ ኑሮ መሻሻል ሲንጸባረቅ አለመታየቱ አባባሉን ለማመን የሚያዳግት ያደርገዋል።

የተፋጠነ ዕድገት በማድረግ ላይ ናቸው በሚባሉት ኢትዮጵያን በመሳሰሉት የአፍሪቃ  ሃገራት ዛሬም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከዓመት ዓመት የውጭ የምግብ ዕርዳታ ጥገኞች ናቸው። የሥራ አጡ ቁጥር በተለይም የወጣቱ ሥራ አጥ ጣራ የነካ ሲሆን የመሠረታዊ ምግብ ዋጋ ግሽበትም እጅግ ከፍተኛ ነው። ኑሮ ይበልጥ እየከበደ መጥቷል።                                                                     

ይህ ደግሞ ድህነትን መቀነሱን ቀላል ነገር አያደርገውም። እዚህ ላይ ከ 1990 ወዲህ ያለው የሕዝብ ቁጥር በሰፊው መጨመርም ታክሎ ሊታሰብ ይገባዋል። ለነገሩ በአፍሪቃም ድህነት በግማሽ ቀንሷል ከተባለ ይህን ለመለየት በዙ ባላዳገተም ነበር። የዓለም ባንክ ከአንድ ዶላር ከሃያ አምሥት መስፈርቱ ባሻገር በዙዎች ማሕበራዊ ሃቆችን በጥናቱ ካላካተተ ትክክለኛ ቀርቶ ለትክክለኝነት ከቀረበ ውጤት መድረስ መቻሉ ዘበት ነው።       

እርግጥ የዓለም ባንክ የአሁኑን መሰል ዘገባ ሲያቀርብ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። እንደ ባንኩ አባባል በሚያዚያ ወር 2007 የዓለም ድሃ ሕዝብ ቁጥር ዓለምአቀፍ ክትትል ከተጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ሚሊያርድ በታች ሲያቆለቁል ድህንትን በግማሽ የመቀነሱ የሚሌኒየም ግብ ሊሳካ የተቃረበ ነበር የመሰለው። ይሁን እንጂ ደስታው ዕድሜ አልነበረውም። ነሐሴ 26 ቀን ሕልሙን ድንገት ቅዠት ያደርገዋል።                                                                              

የድሃው ሕዝብ ቁጥር አንድ ቀን ቀደም ሲል ከነበረው ድንገት በ 430 ሚሊዮን ሕዝብ ይጨምራል። ይህ የሆነው እርግጥ ያልተጠበቀ ዱብ ዕዳ ወይም የተፈጥሮ ቁጣ ደርሶ አልነበረም። የዓለም ባንክ ትችት እያደገበት መሄዱን ምክንያት በማድረግ የድህነት መስፈርቱን እንደገና በማረሙ እንጂ!     

የዓለም ባንክ ዘገባ ከድህነት ቅነሣው አሃዝ ባሻገር ያለው ሌላው ችግር የጀርመኑ የልማት ፖሊሲ ኢንስቲቲዩት ተመራማሪ ኒኮል ሪፒን እንደሚሉት ለመግዛት አቅም ሰንጠረዥ ብቻ ትኩረት መስጠቱ ነው።  የመጀመሪያው የሚሌኒየም ግብ ከተነሣ ይህ አሃዝ የግድ ውሣኝነት የሚኖረው አይደለም።

«አንደኛው የሚሌኒየም ግብ በመሠረቱ  ሶሥት ክፍሎችን ይጠቀልላል። የከፋውን ድህነት መቀነሱ አንዱ ብቻ ነው። የተቀሩት ሁለቱ ደግሞ፤ አንደኛው ሴቶችንና ወጣቶችን ጠቅሎ ለሁሉም ስብዓዊ ክብርን የጠበቀ የሥራ ግንኙነትን መፍጠርና በሁለተኛ ደረጃም የረሃብተኞችን ድርሻ በግማሽ መቀነስ  ናቸው»

በነዚህ በመጨረሻዎቹ ሁለት አካል ግቦች እስካሁን አንዳች ዕርምጃ አልተደረገም። በመሠረቱ ከሰንጠረዡ በስተጀርባ ያለው የድህነት አተረጓጎምም በዚሁ ሳቢያ በብዙ ተመራማሪዎች ዘንድ ጥያቄን እያስነሣ ነው። ድህነት በገንዘብ ከመተመን በላይ በተለይ በሕዝብ የምግብ፣ የትምሕርትና የጤና ጥበቃ አገልግሎት ላይ ጥገኛ የሆነ ነገር ነው።

ለምሳሌ ለራሱ ለኑሮ የሚያስፈልገውን ምግብ መግዛት የሚችል እንደነገሩም ቢሆን ከአንዲት ዶላር ባነሰችገቢ በሰንጠረዥ አመለካከት የበለጠ ገንዘብ ኖሮት ከሚራብ የተሻለ ሊኖር ይችላል። ጥያቄው በድሆቹ አዳጊ ሃገራት ከናካቴው ከአንድ ዶላር ከሃያ አምሥት ባነሰች የዕለት ገቢ መኖር ይቻላል ወይ ነው። ይህ ከባድ መሆኑን የዓለም ባንኩ ባልደረባ ማርቲን ራቫሊዮን እንኳ አይክዱትም።

«ይህ እርግጥ በቁጥብነት የተወሰነ መሆኑን እናውቃለን። ግን ከአምሥት አንዱ የድሆች አገሮች ዜጋ የሚኖረው ደግሞ እንዲያውም ከዚህ የድህነት መስፈርት በታች ነው»

ይህን አመለካከት Germanwatch የተሰኘው ከመንግሥት ነጻ የሆነ ድርጅት ባልደረባ ሉድገር ሮይከም ይጋራሉ። ሮይከ በሰንጠረዥ ደረጃ የድህነት በግማሽ መቀንስ እንደነበር ሲናገሩ ይሁንና ከዚሁ ተያይዞ የፊናንሱ ቀውስ ትጽዕኖ አብሮ በጉዳዩ ባለመጤኑ ጊዜው አልፎበታል ባይ ናቸው። 

«ቀደም ባለው መረጃ እንደተጠቀሰው ከሚሌኒየሙ ግቦች የመጀመሪያው እስክ 2008 ተሳክቷል ቢባል ትክክል ነው። ግን እስከ 2010 የተተባለው ስህተት ነው የሚሆነው። ምክንያቱም በመካከሉ በከፋ ድህነት የሚኖረው ሕዝብ ቁጥር በጣሙን መጨመሩ ነው»

እርግጥ የዓለም ባንክም ቢሆን ዳታዎቹ ወቅታዊ አለመሆናቸውን አላጣውም።

«ከሚሌኒየሙ ግብ ብንደርስ እንኳ የቀን ገቢው ከአንድ ዶላር ከሃያ አምሥት በታች የሆነ አንድ ሚሊያርድ ሕዝብ ገና ይኖራል። ይህ ደግሞ ተቀባይነት የለውም። እናም ሁኔታውን ለማሻሻል መጣር ይኖርብናል»

ለማንኛውም የዓለም ባንክ ፈጠነም ዘገየ ከያቅጣጫው ለሚሰነዘሩት ትችቶች ትኩረት መስጠትና ዘጋባውን ማረሙ የማይቀርለት ነው የሚሆነው። በተለይም የቅርቡ የምግብ ዋጋ ንረት ትልቅ ተጽዕኖ ይኖረዋል። የዓለም ባንክ ስሌቱን ግልጽ ቢያደርግም ለሁሉም የሚጠቅም ነው። አለበለዚያ በአንድ ሌሊት እንደገና የድሃው ቁጥር አድጎ እንዳይገኝ ያሰጋል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic

 • ቀን 21.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14OHO
 • ቀን 21.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14OHO