የዓለም ረሃብተኞችና የሚጣለው ምግብ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 16.01.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የዓለም ረሃብተኞችና የሚጣለው ምግብ

በያመቱ ከሚመረተው 4 ቢሊዮን ሜትሪክ ቶን ያህል ምግብ ፣ ዛሬ የሚራቡ እንዳሉ እየታወቀ፣ በዓለም ዙሪያ ለምግብነት ከሚውለው ምርት መካከል፤ 50 ከመቶው ፤ ማለትም 2 ቢሊዮን ቶን ፤ ሥጋ ፣ አሣ ፣ ጥራጥሬ ፣ ፍራፍሬ አትክልትና የመሳሰለ የምግብ ዓይነት ፣ እንደ ቁሻሻ ተቆጥሮ መጣሉ አያስደነግጥም ፤ አያሳዝንምም ማለት አይቻልም።

EAT sandwich shop in London throw out several bags of unsold food, including salads and sandwiches in London. This comes as the priminister urges consumers not to waste food. Some street people help themselves to the food. Ref: B125_116256_0009. Date: 07/07/2008. Foto: Jon Almasi/UPPA/Photoshot +++(c) dpa - Report+++

ሰዎች ሳይመገቡት የተጣለ ምግብ

የዓለም ህዝብ አኀዝ ፣ በአሁኑ ጊዜ 7,06 ቢሊዮን እንደሆነ ይገመታል። እ ጎ አ በ 2050 ቁጥሩ ከ 7,5 እስከ 10,5 ቢሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ነው የሚታሰበው። ታዲያ፤ በአሁኑ ጊዜ ፣ በዓለም ዙሪያ 900 ሚሊዮን ገደማ መሆኑ የሚነገርለት፤ በረሃብ የተጠቃው ህዝብ ፤ ከ 37 ዓመት በኋላ ፣ ወደ 3 ቢሊዮን ከፍ ማለቱ እንደማይቀር ጠንከር ያለ ግምት አለ። ታዲያ በያመቱ ከሚመረተው 4 ቢሊዮን ሜትሪክ ቶን ያህል ምግብ ፣ ዛሬ የሚላስ የሚቀመስ አጥተው የሚራቡ እንዳሉ እየታወቀ፣ በዓለም ዙሪያ ለምግብነት ከሚውለው ሰፊ የተለያየ ምርት መካከል፤ 50 ከመቶው ፤ ማለትም 2 ቢሊዮን ቶን ፤ ሥጋ ፣ አሣ ፣ ጥራጥሬ ፣ ፍራፍሬ አትክልትና የመሳሰለ የምግብ ዓይነት ሰዎች ሳይመገቡት ፣ እንደ ቁሻሻ ተቆጥሮ የሚጣልበት ሁኔታ አያስደነግጥም ፤ አያሳዝንምም ማለት አይቻልም።
ዋና ጽ ቤቱ በለንደን ብሪታንያ የሚገኘው Institution of Mechanical Engineers የተሰኘ ድርጅት ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ዘገባ፣ በመሠረተ ልማት ኋላ-ቀርነት፤ በምግብ ማቆያ ጎተራዎችና የመሳሰሉ እጥረቶች፤ ምግብ የሚቆይበት ጊዜ መገደቡ፣ በነጋዴዎች የጉትጎታ ዘዴ ፣ ሸማቾች የምግብ ዓይነት በሰፊው የሚገዙበት ሁኔታና እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ ሁኔታዎች፤ አላስፈላጊ ፣ የበሰለና ያልበሰለ ፣

በአጭር ጊዜ ውስጥ ለምግብነት የሚውል የተለያየ ምግብ ፤ የምግብ መደብሮችን እንዲያጣብብ ፣ በመኖሪያ ቤቶችም እንዲከማች ሳይገፋፋ አልቀረም።
በኢንዱስትሪ ከበለጸጉት ሃገራት መካከል ለምሳሌ ያህል ብሪታንያ፤ በያመቱ ከ 300 ሚሊዮን ቶን በላይ ምግብና የተለያየ ቁሻሻ የምትጥል ስትሆን፤ የምግቡ መጠን ብቻ 15 ሚሊዮን ቶን ገደማ ነው። ከዚህም መካከል 50 ከመቶው፤ ሸማች ዜጎች ከገዙ በኋላ የሚጥሉት መሆኑ ታውቋል። ቢያንስ 60 ከመቶ ሜትሪክ ቶኑ ምግብ ሳይባክንም ሆነ ሳይጣል ህዝብ እንዲመግባ ለማድረግ ባላዳገተ ነበር። በአጠቃላይ ብሪታንያ ውስጥ፤ በያመቱ 10 ቢሊዮን ፓውንድ ወይም 12 ቢሊዮን ዩውሮ ያህል የሚያወጣ ምግብ ከቁሻሻ ጋር ይጣላል። በዩናይትድ እስቴትስ ደግሞ፣ በያመቱ፣ 4o ከመቶው የተዘጋጀ ምግብ፤165 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ መሆኑ ነው ከቁሻሻ ጋር ይወረወራል።
ለምሳሌ ያህል ፤ በ4 አገሮች ፤ ዩናይትድ እስቴትስ፤ ካናዳ አውስትሬሊያና ንው ዚላንድ፤ በኅብረት የሚባክነውም ሆነ ከጥቅም ውጭ የሚሆነው የምግብ መጠን ሲሰላ፤ ፍራፍሬና ቅጠላ ቅጠል ---52 ከመቶው ሲጣል ለምግብነት የሚወለው 48 ከመቶው ብቻ ነው።

ከባህር የሚገኝ አሣና የመሳሰለው ምግብ፣ 50 ከመቶው ሲበላ ቀሪው 50 ከመቶ እንደማንኛውም ቁሻሻ ነው የሚጣለው። ጥራጥሬ እኽል ---38 ከመቶው እንደሚጣልና
62 ከመቶው ለምግብነት እንደሚውል ተመልክቷል። ሥጋ 22 ከመቶ ይጣላል ለምግብነት የሚውለው 78 ከመቶው ነው። ወተት 20 ከመቶው ይደፋል፤ 80 ከመቶው ለምግብነት ይውላል።
በተለያዩ የአውሮፓው ኅብረት አገሮች በጀርመን ጭምር ማለት ነው ፤ ምግብ ተትረፍርፎ የሚጣልበት ሁኔታ ጡር ሆኖ አይታይም። ጀርመን ውስጥ በያመቱ 11 ሚሊዮን ቶን ምግብ በተለይ የሰላጣና ጎመን ዘር፤ ፍራፍሬና ዳቦ ፤ ኬክና ብስኩት ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ ይወረወራል። ይህን የተገነዘቡት

የጀርመን የግብርና ሚንስትር ወ/ሮ ኢልዘ አይግነር፤ «በአማካይ እያንዳንዱ የጀርመን ኑዋሪ በያመቱ 81,6 ኪሎግራም ምግብ ይጥላል፤ ከዚህ ውስጥ 2/3ኛውን ማትረፍ ባላቃተ ነበር። 4 ሰዎች በሚኖሩበት ቤተሰብ መካከል፣በያመቱ፣ 935 ዩውሮ የመያወጣ ምግብ ነው ቁሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ የሚጣለው » ሲሉ ተናግረው ነበር። ከዚህ ርእስ ጋር በተያያዘም እንዲህ ማለታቸው የሚታወስ ነው።
«የህዝብ ቁጥር ባፋጣኝ በመጨመር ላይ ነው። በ 2050 ከሞላ ጎደል በዝች ምድር 10 ቢሊዮን ህዝብ ይሆናል የሚኖርባት፤ እነዚህ ሰዎች ሁሉ ድግሞ ፣ ባጣዳፊ ሁኔታ ምግብ የሚያሻቸው ናቸው።»
በአውሮፓ ኅብረት ሃገራት ፤ እንደሚገመተው በያመቱ 89 ሚሊዮን ቶን ምግብ ነው ፣ ሰው ሳይመገበው ወደ ቁሻሻ ማጠረቀሚያ የሚወረወረው። ምግቡ ተበላሽቶ የሚጣለው፤ በግል መኖሪያ ቤቶችና በምግብ መደብሮች በገፍ ከመገዛቱም ሌላ ከመጠን በላይ እየተዘጋጀ ስለሚትረፈረፍ መጣል ግድ ይሆናል ነው የሚባለው። ምግብ መባከን የሚጀምረው ከሚመረትበት ቦታ አንስቶ ነው። ለምሳሌ ያህል በፍራፍሬ፤ ሰላጣና ዱባን በመሳሰሉ የእርሻ ቦታዎች፤ ቅርጹ አያምርም ፤ ቀለሙ ትንሽ ለየት አለ እየተባለ እንኳ የሚወረወረው ጥቂት አይደለም። Stop Wasting Food የተሰኘው የደንማርክ እንቅሥቃሤ መሥራች ወ/ሮ ሰሊና ጁል እንዲህ ይላሉ።
«ማባካን የሚጀመረው በእርሻ ቦታ ነው። ለምሳሌ ያህል በዚያው ቦታ ቢቻል ማዘጋጀት ይኖርብሃል። የሚመረተው የምግብ ዓይነት ፣መጠኑ የተለያየ በመሆኑም ፣ በሱቅ፤ በምግብ መደብር አይደለም መስተካከል ያለበት። ለዚህም ነው፣ ተበላሽቶ የሚቀረው። በምግብ አሻጊ ኢንዱስትሪዎች፤ 20 ከመቶው ምግብ ከጥቅም ውጭ ይሆናል።»
በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚበላሽ ምግብን ፣ ገና ለገና ፤ በረሃብ የሚጠቁ አገሮች አሉ ብሎ ወደዚያ መላክ ሳይሆን ማሰቡ ራሱ፤ በሞራልም በህግም ከቶ የሚደገፍ አይደለም። ሰሊና ጁል አያይዘው እንዲህ ነበረ ያሉት።


«ማሰብ ፤ ማስታወስ ያለብን፤ የተበላሸ ምግብ፤ ወደ አፍሪቃ መላክ አንችልም። የማይታሰብ የማይሞከር ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል እንዲሁ በነባቤ -ቃል የምንገነዘበው፤ ምግብ ይበልጥ ሲባክን፤ ከጥቅም ውጭ ሲሆን፤ የምግብ ዋጋ መናሩ አይቀሬ መሆኑን ነው።»
ችግሩን ተገንዝቤአለሁ የሚለው፤ የአውሮፓው ኅብረት፤ እ ጎ አ እስከ 2025 ዓ ም፤ ድረስ 50 ከመቶ የምግብን ብክነት ለመቀነስ አልሟል። በመሆኑም ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር አንስቶ፣ « ለማኅበራዊ ኑሮ ተኃድሶ፣የምግብን ብክነት የመግቻ ስልት » በሚል መፈክር አንድ ፕሮጀክት ቀርጿል። በዚህ እንቅሥቃሴ፤ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና ግብርና ድርጅት (FAO) ጨምሮ የመንግሥት ያልሆኑ ድርጅቶች፤ ከአውሮፓ የተውጣጡ ኩባንያዎች፤ እንዲሁም 20 የአውሮፓ ዩንቨርስቲዎች ተሳታፊዎች ናቸው። ከጀርመን የሆኸንሃይም ዩንቨርስቲ ነው የተወከለው። የፕሮጀክቱ አስተባባሪ፤ ከኔደርላንዱ Wageningen የግብርና ዩንቨርስቲ Toine Timmermans እንዲህ ይላሉ።
«እናውቃለን፤ ትልቅ ጉዳይ መሆኑን ማንም ሰው ይስማማበታል። በአማካይ ፤ በ 25 እና 30 ከመቶ መካከል የምግብ ምርት ፤ ሰው እንዲመገበው የታሰበው ሁሉ፤ በአቅርቦት ሰንሰለት ባክኖ ይቀራል።»
ፈረንሳይንና ብሪታንያን የመሳሰሉ አገሮች፤ከእስካንዲኔቪያ አገሮች ጋር ሲነጻጸሩ፤ ቀጣይነት ላለው የግብርና ዑደት ንቃተ-ኅሊናቸው ዝቅ ያለ ነው። ብዙዎቹ ዜጎቻቸውም የሚኖሩት ምግብ ማባከን የተለመደ በሆነባቸው በታላላቅ ከተሞች ውስጥ ነው ።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic