የዓለም ምጣኔ ሐብት ጉባኤ | ኤኮኖሚ | DW | 04.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ምጣኔ ሐብት ጉባኤ

የጉባኤተኞቹ መብዛት፤ የጉባኤዉ አዘጋጆች እንደሚሉት፤ የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት የብዙዎችን ቀልብ ለመሳቡ ዋቢ ነዉ።በርግጥም JLL በሚል ምሕፃሩ የሚጠራዉ ዓለም አቀፉ የምጣኔ ሐብት አጥኚ ተቋም እንደሚለዉ ባለፉት አስራ-አምስት ዓመታት የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት ከአጠቃላዩ የዓለም ምጣኔ ሐብት በሰወስት በመቶ የሚበልጥ ዕድገት አሳይቷል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:07
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:07 ደቂቃ

የአፍሪቃን የምጣኔ ሐብት ዕድገት፤ ያጋጠሙ መሠናክሎችንና የወደፊት ጉዞዉን የሚቃኝ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ትናንት ኬፕ ታዉን-ደቡብ አፍሪቃ ተጀምሯል።የዓለም ምጣኔ ሐብት መድረክ ያዘጋጀዉ ጉባኤ አላማ አዲስ አበባ ዉስጥ ለሚደረገዉ የልማት ጉባኤ የሚረዱ ሐሳቦችን ለማሰባሰብ ነዉ።ነገ-ማምሻዉን ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀዉ ጉባኤ ላይ ከ1250 በላይ የመንግሥት ባለሥልጣናት፤የኩባንያ ባለቤቶችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።የጉባኤዉ አዘጋጆች እንደሚሉት ጉባኤዉ የበርካታ ተሳታፊዎችን ትኩረት መሳቡ የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት ዕድገት አማላይ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቋሚ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ የዜና መልዕክቶችን አሰባስቧል።

የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት ጄኮብ ዙማን ጨምሮ የዘጠና መንግሥታት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤የሰማንያ-ሰወስት ዓለም አቀፍ ኩባንያ ተጠሪዎች፤ በመቶ የሚቆጠሩ ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች ተወካዮች በጉኤዉ ተካፍለዋል።አፍሪቃ ሥለ አፍሪቃ ምጣኔ ሐብት የሚመክር ትልቅ ጉባኤ ስታስተናግድ ያሁኑ የመጀመሪያዋ ነዉ።

የጉባኤተኞቹ መብዛት፤ የጉባኤዉ አዘጋጆች እንደሚሉት፤ የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት የብዙዎችን ቀልብ ለመሳቡ ዋቢ ነዉ።በርግጥም JLL በሚል ምሕፃሩ የሚጠራዉ ዓለም አቀፉ የምጣኔ ሐብት አጥኚ ተቋም እንደሚለዉ ባለፉት አስራ-አምስት ዓመታት የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት ከአጠቃላዩ የዓለም ምጣኔ ሐብት በሰወስት በመቶ የሚበልጥ ዕድገት አሳይቷል።ከዉጪ በቀጥታ በሚፈሰዉ መዋዕለ ነዋይ፤ በከተሞች መስፋፋትና አዳዲስ በሚፈጠረዉ መካከለኛ መደብ የሚገፋዉ የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት JLL እንደሚለዉ ሞዛምቢክ፤ዛምቢያ፤እና ኢትዮጵያን በመሳሰሉት የአፍሪቃ ሐገራት በፍጥነት «እየተንቻረረ» ነዉ።

ይሕ ማለት ግን አብዛኛዉ አፍሪቃዊ ከዕድገቱ ይቋደሳል ማለት አይደለም።አፍሪቃ የረሐብ፤ የበሽታ፤የድሕነት ተምሳሌትነቷ ተለወጠ ወይም ባጭር ጊዜ ይለወጣል ማለት አይደለምም።ሚሊዮነ-ሚሊዮናት አፍሪቃዉያን ዛሬም ድሆች ናቸዉ።በኬፕታዉኑ ጉባኤ ላይ የሚሳተፉት የብሪታንያዉ ግብረ-ሠናይ ድርጅት የኦክስፋም ሐላፊ ዊኒ ባይኒያማ እንደሚሉት ደግሞ የአፍሪቃ መሪዎች ከዛሬዉም በላይ ለነገ ማሰብ አለባቸዉ።

«በሚቀጥሉት 25 ዓመታት መስራት የሚችለዉ አፍሪቃዊ ሕዝብ ቁጥር በእጥፍ አድጎ አንድ ቢሊዮን ይደርሳል።ይሕ ለአፍሪቃ መሪዎች የማስጠንቀቂያ ደወል ነዉ።የወጣቱ ቁጥር ማደጉ ለአፍሪቃ ዕድገት ጥሩ ዕድል፤ ታላቅ ቅምጥ ሐብትም ነዉ።ወጣቱ ተምሮና ሠልጥኖ የሥራ ዕድል ካልገተፈጠረለት ግን የትዉልድ ቦምብ ነዉ-የሚሆነዉ።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈዉ ዓመት ያሳተመዉ ጥናት እንዳስታወቀዉ ከዓለም ሕዝብ የ2,2 ቢሊዮኑ ኑሮ አንድም ከድሕነት ጠገግ በታች፤ አለያም ጠገጉን ለመዉረድ የተንጠለጠለ ነዉ።85ቱ የዓለም ሐብታም ግለሠቦች የሚቆጣጠሩት ሐብት ባንፃሩ ከ3,5 ቢሊዮን የሚበልጠዉ የዓለም ሕዝብ ካለዉ ገቢ ይበልጣል።

አብዛኛዉ ደሐ ሕዝብ ደግሞ የዓለም አቀፉ ድርጅት ጥናት እንደሚለዉ አፍሪቃዊ ነዉ።«የአፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ዕድገት የሕዝቡን አስከፊ ኑሮ ለመቀየር መዋል አለበት።» የመብት ተሟጋቾቹ ጥያቄ።የኦክስፋም ባለሥልጣን እንደሚሉት ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገቱ የአፍሪቃ ሕዝብን ከጉስቁልና ለማዉጣት እንዲዉል የአፍሪቃ ፖለቲከኞች ለሕዝባቸዉ የሚጠቅም መርሕ መንደፍ፤ አፍሪቃ ዉስጥ የሚሠሩ ዓለም አቀፉ ኩባዮችም ተገቢዉን ግብር መክፈል አለባቸዉ።

«የአፍሪቃ የተፈጥሮ ሐብት በብዛት እየወጣ ነዉ።በርካታ ኢንዱስትሪዎችም አፍሪቃ ዉስጥ እየተተከሉ ነዉ።ሁሉም ግን የሚገባዉን ግብር ሳይከፍሉ የሚያገኙት ትርፍ በገፍ እየወጣ ነዉ።»

OXFAM Logo

የወይዘሮ ባይንይማ ድርጅት ኦክስፋም ሰሞኑን ባወጣዉ ጥናቱ እንዳስታወቀዉ አፍሪቃዉ ዉስጥ የሚሰሩ የዉጪ ኩባንዮች እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ2010 ብቻ ለአፍሪቃ መክፈል የነበረባቸዉን አሥራ-አንድ ቢሊዮን ዶላር ግብር አልከፈሉም።አስራ-አንድ ቢሊዮኑ ዶላር ኩባንኖቹ ግብርን ላለመክፈል ከሚጠቀሙባቸዉ የተለያዩ ማጭበርበሪያዎች ባንደኛዉ ብቻ አፍሪቃ የከሰረችዉ ነዉ።

«እኛ ባሰላነዉ መሠረት አፍሪቃ በ2010 ብቻ አስራ-አንድ ቢሊዮን ዶላር የግብር ገንዘብ አጥታለች።አሥራ-አንድ ቢሊዮን ዶላር።ግብርን በማጭበርበሪያ አንድ ዘዴ ብቻ።»

ከአስራአንድ ቢሊዮኑ ዶላር ስድስት ቢሊዮኑን የወሰዱት «በኢንዱስትሪ የበለፀጉት የሠባቱ ሐገራት ኩባንዮች ናቸዉ።» ይላል ኦክስፋም። የአፍሪቃ ፖለቲከኞች በገንዘብ ተደልለዉ፤ ሥልጣናቸዉን እንዳያጡ ፈርተዉ ወይም ባለማወቅ ባይተባበሩ ኖሩ አፍሪቃ ይሕን ያክል ገንዘብ ባልከሰረች ነበር።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

 

 

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች