የዓለም ማሕበራዊ መድረክ | ራድዮ | DW | 12.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ራድዮ

የዓለም ማሕበራዊ መድረክ

አብይ መፈክሩ በርግጥ ጠንካራ ነዉ።ወይም ይመስላል።«ሌላ ዓይነት ዓለም እንፈልጋለን» ይላል።ዓላማዉም አልተለወጠም።የዓለም ድሆች ከዓለም ሐብት መጋራት ዓለባቸዉ ባይ ነዉ።የተሳታፊዎቹ ቁጥር ግን በእጅጉ አሽቆልቁሏል።50 ሺሕ ብቻ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:01

የዓለም ማሕበራዊ መድረክ

የካፒታሊስቱን የምጣኔ ሐብት ሥርዓት በተለይም «ግሎባላይዜሽን» የተሰኘዉን ትስስርን የሚቃወመዉ የዓለም ማሕበራዊ መድረክ ዓመታዊ ጉባኤ ባለፈዉ ሮብ ሞንትሪያል ካናዳ ዉስጥ ተጀምሯል።ግሎባላይዜሽን በደኸዉ ሕዝብ ላይ የሚያደርሰዉን ተፅዕኖ የሚቃወመዉ መድረክ ከተመሠረተ አስራ-አምስተኛ ዓመቱ ነዉ።መድረኩ ባለፉት አስራ-አምስት ዓመታት ከጠራቸዉ ጉባኤዎቹ ሁሉ አነስተኛ ቁጥር ያለዉ ተሳታፊ የተገኘበት ግን የዘንድዎሮዉ ጉባኤ ነዉ።መድረኩ በኢንዱስትሪ በበለፀገች ሐገር ጉባኤ ሲያዘጋጅም ዘንድሮ የመጀመሪያዉ ነዉ።የጉባኤተኛዉ ማነስና የጉባኤዉ ሥፍራ እያነጋገረ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ዘገባ አለዉ

የዛሬ አስራ-አምስት ዓመት ሲመሰረት ፖርቶ አልጌር-ብራዚል ላይ አንድ መቶ ሺዎችን አሳድሞ ነበር።በዓራተኛ ዓመቱ አራተኛዉ ስብሰባዉ ሲጠራ ደግሞ 120 ሺሕ ተካፋዮች ነበሩ።የዓለም ማሕበራዊ ጉባኤ።ያኔ ያነሳቸዉ ሐሳቦች፤ መፈክሮች፤ያሳተፋቸዉ ሰዎች ጥራት፤ ፅናትና ብዛት በርግጥም ዓለምን ለጠቀለለዉ ካፒታሊዝም ታላቅ ተቃዋሚ፤ ዳቮስ ሲዊትዘርላንድ ለሚሰየመዉ የምጣኔ ሐብት መድረክ ለተሰኘዉ የሐብታሞች ጉባኤ ደግሞ ዋና

ተቀናቃኝ መስሎ ነበር።

ዘንድሮም-አብይ መፈክሩ በርግጥ ጠንካራ ነዉ።ወይም ይመስላል።«ሌላ ዓይነት ዓለም እንፈልጋለን» ይላል።ዓላማዉም አልተለወጠም።የዓለም ድሆች ከዓለም ሐብት መጋራት ዓለባቸዉ ባይ ነዉ።የተሳታፊዎቹ ቁጥር ግን በእጅጉ አሽቆልቁሏል።50 ሺሕ ብቻ።ለድሆቹ አጓጊ አማራጭ፤ ለሐብታሞቹ አስጊ-አደናቃፊነቱ የመዳከሙ ምልክት ይሆንአይደለም» ይላሉ ዳቦ ለዓለም (Bröt für die welt) የተሰኘዉ የጀርመን ግብረ-ሠናይ ድርጅት የበላይ ዶክተር ሉዊዘ ሽታይንቫክስ።

«የዓለም ማሕበራዊ መድረክ ሲመሰረት፤ ዳቮስ የሚደረገዉ የዓለም የምጣኔ ሐብት መድረክን የሚቃረን፤ ዓለም አቀፍ የሲቢል ማሕበራትን ለተቃዉሞ፤ ለሥልጠናና ለፈጠራ የሚያደራጅ መድረክ ነበር።»

ከጥቂት ዓመታት ወዲሕ ግን ለድሆች የሚቆረቆሩ ማሕበራትን የሚያሰባስበዉ መድረክ የቀድሞዉ ምግባሩን እያጣ መጣ።ምግባሩን ግን አይደለም።ቀጠሉ ሽታይቫክስ

«ካለፉት ስምንትና ዘጠኝ ዓመታት ወዲሕ በቀጥታ በዓለም ምጣኔ ሐብት መድረክ ላይ ያነጣጠረ ተቃዉሞዉን ለወጠ።ጉባኤዉንም፤ የዓለም ምጣኔ ሐብት በሚደረግበት ወቅት ማድረጉን አቆመ።ይሁንና ባሁኑ ወቅት የመብትና የእኩልነት አቀንቃኞች ሐሳብ የሚለዋወጡበት፤ አዳዲስ ፈጠራዎችን የሚያስተዋዉቁበት ጠንካራ መድረክ ሆኗል።»

ይሕ ምናልባት ለተሳታፊዎች ቁጥር ማነስ አንዱ ምክንያት ይሆን ይሆናል። በሐብታሙ የሰሜን ንፍቀ ክበብ እና በደሐዉ የደቡብ ንፍቀ-ክበብ መካከል የነበረዉን ልዩነት የሚያጠቡ የጋራ ችግሮች መፈጠራቸዉ ሌላ ምክንያት ሳይሆን አልቀረም።አሸባሪነት፤ የስደተኞች መብዛት፤የዓየር ንብረት ለዉጥ አለያም ቀረጥ ማጭበርበር ሐብታሞቹ የሚፈጠሩት እና የሐብታሞቹ ሐገራት ችግሮች ብቻ አይደሉም።ይሕም ለጉባኤተኛዉ ቁጥር መቀነስ ተጨማሪ ምክንያት ነዉ።

ሌላም አለ።

መድረኩ መንግሥታዊ ካልሆኑ ማሕበራት፤ድርጅቶችና ተቋማት በተጨማሪ በጉባኤዉ የሚጋብዛቸዉ የድሆቹንና በማደግ ላይ ያሉ ሐገራት መንግሥታት ተወካዮችን ነዉ።ከድሮ ተጋባዦቹ ቻይና በምጣኔ ሐብት እየፈረጠመች፤የአየር ንብረትንም ክፉኛ እየበከለች፤ ቱጃሩን ዓለም ስትቀየጥ ከዚያ የድሆችና የተቆርቋሪዎቻቸዉ ስብሰብ መሐል የምታንቧችርበት ምክንያት የለም።

ጉባኤዉ በኢንዱስትሪ በበለፀገ ሐገር ሲደረግ የዘንድሮዉ የመጀመሪያዉ ነዉ።ሞንትሪያል-ካናዳ።ለድሆቹ ሐገራት ጉባኤተኞች ወደ ሐብታሚቱ ሐገር መጓዝ ሲበዛ ከባድ ነዉ፤-በሁለት ምክንያት። አንደኛዉ ወጪዉ ብዙ ነዉ።ሁለተኛ የመግቢያ ፍቃድ አያገኙም።የካናዳ መንግሥት፤ መንግሥታዊ ላልሆኑ የድሐ ሐገራት ድርጅቶች ወይም ለሲቢል ማሕበራት ተወካዮች ቀርቶ ለመንግሥት ባለሥልጣናት እንኳ የመግቢያ ፈቃድ ቪዛ ከልክሏል።

በትንሽ ግምት ሁለት መቶ ጉባኤተኞች ቪዛ ተከልክለዋል።ከነዚሕ መካከል የአፍሪቃና የእስያ ሐገራት የምክር ቤት እንደራሴዎች ይገኙበታል።ዳቦ ለዓለም ከተሰኘዉ የጀርመን ግብረ-ሠናይ ድርጅት ጋር ተባብረዉ የሚሰሩ ድርጅቶች ባልደረቦችም ቪዛ ተከልክለዋል።

«ምክንያቱ አይታወቅም።የምናዉቀዉ የኛ ተሻራኪዎች ቪዛ እንዲሰጣቸዉ አመልክተዉ፤ፓስፖርታቸዉንም (ለኤምባሲ) ሰጥተዉ ነበር።መልስ ግን አልተሰጣቸዉም።የገንዘብ እጥረት አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል።ከኛ ጋር የሚሰሩት ግን ገንዘቡ ችግር እንደማይሆን ግልፅ ተደርጓል።»

ምክንያቱ ብዙ ነዉ።በዛም አነሰ ግን የዓለም ማሕበራዊ መድረክ በአስራ-አምስት ዓመት ታሪኩ ዝቅተኛዉን ጉባኤ ያስተናገደዉ ዘንድሮ ነዉ።የመድረኩ ደጋፊዎች ግን የጉባኤተኞቹ ቁጥር ማነስ የመድረኩን ዓላማ የሚያዳክም፤ ሕልዉናዉንም የሚያቀጭጭ አይደለም ባይ ናቸዉ።ምክንያቱም የዓለም የሲቢል ማሕበራትን የሚያስተሳስር ብቸኛዉ መድረክ ነዉና።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ

 

 

Audios and videos on the topic