የዓለም ሕዝብ ፈጣን ጭማሪ | ኤኮኖሚ | DW | 30.09.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዓለም ሕዝብ ፈጣን ጭማሪ

የተባ መ ድ ዘንድሮ ያቀረበው ዘገባ እንደሚያመለክተው፣ የዓለም ሕዝብ ጭማሪ በየጊዜው እየገዘፈ ነው የሚሄደው። እንዲያውም፥ እጅግ ድሆች በሆኑት ሀገሮች ውስጥ እ ጎ አ እስከ ፪ሺ፶ ድረስ የሕዝቡ አሃዝ በ፫ እጅ የሚጨምር እንደሚሆን ነው የሚገመተው። በያመቱ በ፸፮ ሚሊዮን የሚጨምረው የዓለም ሕዝብ አሃዝ እስከ ፪ሺ፶ ድረስ ከ6.4 ሚሊያርድ (ካሁኑ ይዘቱ ማለት ነው) ወደ 8.9 ሚሊያርድ ሳያሻቅብ አይቀርም ነው የሚባለው። ከዚሁ ፈጣን የሕዝብ ጭማሪ 96 በመቶው የሚደረጁት

�ገሮች ድርሻ ሆኖ ነው የሚታየው።

በዓለሙ ድርጅት ጥናት መሠረት፣ እጅግ ድሆች በሚባሉት ሃምሳ ሀገሮች ውስጥ እ ጎ አ በ፪ሺ፶--በ፵፭ ዓመታት ውስጥ ማለት ነው--1.7 ሚሊያርድ ሕዝብ እንደሚኖር ነው የሚጠበቀው፥ ይህም የ፫ እጅ ጭማሪ መሆኑ ነው። በድሆቹ ሀገሮች ውስጥ የሕዝቡን ጭማሪ ተፋጥኖ የሚያገዝፈው፥ ከ፪፻ ሚሊዮን የሚበልጡ ሴቶች ዘመናዊውን ከላኤ-ጽንስ ዘዴ የሚጠቀሙበት ቆሳቁሳዊ አቅም ስለሌላቸው ነው ይላል የድርጅቱ ዘገባ። ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ብዙ ሀገሮች የምጣኔ-ቤተሰብእ እቀዳ አገልግሎታቸውን ቢያጠናክሩትም፣ በፊናንሱ እጥረትና በሴቶች ጭቆና ምክንያት ሁኔታው ሊሻሻል አልበቃም። ስለዚህ፣ ለምጣኔ-ቤተሰብ እቀዳው አገልግሎት የፊናንስ ድጋፍም መታከል እንዳለበት ድርጅቱ ያስገዝባል። በድርጅቱ ጠበብት አመለካከት መሠረት፥ በሚረጁት ሀገሮች ውስጥ የከላኤ-ጽንስ ርዳታና ስርጭት ከተጠናከረ፣ የሕዝቡን ጭማር ሂደት በአንድ-ሦሥተኛ ዝግ እንደሚያደርገው ነው የሚታሰበው። ሥነሕዝብን ያመላከተው ጉባኤ ከአሥር ዓመታት በፊት ካይሮ ላይ በተካሄደበት ወቅት ለምጣኔ-ቤተሰብ እቀዳ መደገፊያ የተወሰነው የፊናንሱ መዋጮ እስካሁን ድረስ መሟላት ተስኖት ሲንጠባጠብ መቆየቱን የዓለሙ ድርጅት አሁን በከፍተኛ ቅሬታ ነው የሚያስገነዝበው። ጀርመንም በበኩሏ ለዚሁ የምጣኔ-ቤተሰብ እቀዳ ማጠናከሪያ በያመቱ ፪፻፶ ሚሊዮን ኦይሮ እንደምትለግስ ቃል ብትገባም፣ እስካሁን ከዚሁ ሂሳብ ግማሽ ያህሉን ብቻ ዝግጁ ማድረጓ ነው የተመለከተው።

ዘገባው ቀጥሎ፥ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በእናቶች ላይ የሞት አደጋ በሚደርስበት ሁኔታ ረገድ እምብዛም የተለወጠ ነገር እንደሌለ ያስረዳል። በያመቱ ግማሽ ሚሊዮን ያህል ሴቶች በእርግዝናና በውልደት ጊዜ በሚደርስ የጤን’ነት እክል ምክንያት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ነው የሚመለከተው። በምዕራብ አፍሪቃ ብቻ በእርግዝናና በውልደት ጊዜ የሐኪም ርዳታ ከመጓደሉ የተነሳ ከየሁለቱ ሴቶች አንዷ ሕይወቷን ታጣለች ነው የሚባለው። የዓለሙ ድርጅት በዚያው ዘገባው እንደሚለው፣ ቀሳፊውን በሽታ ኤድስን ለመግታት በሚደረገውም ትግል ረገድ ተመሳሳይ ሁኔታ ነው የሚታየው። በመላው ዓለም ውስጥ በኤድሱ ተሃዋሲ የተያዙት ሰዎች አሃዝ ወደ ፵ ሚሊዮን የሚጠጋ ሲሆን፣ ከመላው ሕዝቦች መካከል ራሳቸውን ከበሽታው ለመከለል ዕድል የሚያገኙት አንድ-አምስተኛው ብቻ እንደመሆናቸው መጠን የሕሙማኑ ቁጥር ጭራሹን የሚገዝፍ ነው የሚሆነው። አደገኛው ተሃዋሲ አዲስ ከሚይዛቸው ሰዎች መካከል ግማሽ ያህሉ በ፲፭ እና በ፳፬ ዓመታት ዕድሜ መካከል የሚገኙ እንደሆኑ ዘገባው ያመለክታል።


ዘገባው እንደሚለው፣ በሦሥተኛው ዓለም ውስጥ ገጠሬው ሕዝብ የተሻለ ኑሮ የሚያገኝ እየመሰለው ወደ ከተሞች የሚሸሽበት ሁኔታ፣ ከተሞቹ በየጊዜው እንዲገዝፉ ያደርጋቸዋል። በዚህ አኳኋን፥ እጎአ ከ፪ሺ፯ ጀምሮ ከጠቅላላው የዓለም ሕዝብ መካከል ብዙው ከፊል በከተሞች ውስጥ እንደሚኖር፣ እጎአ በ፪ሺ፴--በ፳፭ ዓመታት ውስጥ ማለት ነው--በመላው የዓለም ኣካባቢዎች ከገጠሬዎቹ ይልቅ የከተሜዎቹ አሃዝ የሚያመዝን እንደሚሆን ነው የሚመለከተው። ይኸውም፣ በሚቀጥሉት ፳፭ ዓመታት ውስጥ ከጠቅላላው የዓለም ሕዝብ ሁለት-ሦሥተኛው በከተሞች ውስጥ የሚኖር እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው። አሁን ግን፣ ለሥነ-ምኅዳር ምርምር ቋሚ የሆነው የተባ መ ድርጅት እንደሚለው፣ ግማሽ ያህሉ ነው በከተሞችና በከተሞች አካባቢ የሚኖረው። እጎአ በ፪ሺ ዓ.ም.--ይኸውም ከአምስት ዓመታት በፊት መሆኑ ነው-- - የከተማ ነዋሪዎች አሃዝ 2.86 ሚሊያርድ የነበረ ሲሆን፣ በ፳፭ ዓመታት ውስጥ ግን ይኸው የከተማ ነዋሪዎች አሃዝ ወደ አምስት ሚሊያርድ የሚወጣጣ ይሆናል--የድርጅቱ ዘገባ እንደሚለው። ይህም በሚሆንበት ጊዜ፣ ድህነት የሚባባስ፣ የማኅበራዊው ኑሮ አገልግሎትም የሚዳከም ሆኖ ነው የሚታየው። በጥናቱ መሠረት፥ ዓምና በዓለም ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጡ ነዋሪዎች የነበሩዋቸው ከተሞች ፴፱ ነበሩ፣ ከአሥር ሚሊዮን የሚበልጡ ነዋሪዎች የሠፈሩባቸው ከተሞች አሃዝ ደግሞ ፲፮ ደርሶ ነበር የተገኘው። ዝንባሌው ታዲያ፣ የከተሞች ቀጣይ ግዝፈትን የሚጠቁም መሆኑ ነው።

ዘገባው እንደሚለው፥ ድህነት የሚባባስ ሆኖ የሚታየው፣ በሐብታሞቹ ሀገሮች ትልልቅና ግዙፍ ከተሞችም ውስጥ ነው። ይኸው ዝንባሌ ብልጽግና ያለበትን ምዕራቡን ጭምር የሚመለከት መሆኑ ነው። ለምሳሌ ዓምና በክረምት ምዕራብ አውሮጳ ውስጥ ቤትአልባ ሆነው የተገኙት ችግረኞች አሃዝ ፫ ሚሊዮን ደርሶ የተገኘ ሲሆን፣ ይኸው የድሆች ይዘት ከ፶ ዓመታት ወዲህ ታይቶ አይታወቅም ይላል የዓለሙ ድርጅት ዘገባ። በሐብታሚቱም ዩኤስ-አሜሪካ፥ ቤትአልባ ከሆኑት ሦሥት ሚሊዮን ተኩል ነዋሪዎች፣ አንድ ሚሊዮን ከሩብ የሚደርሱቱ ሕፃናት ናቸው። ከታላላቆቹና ግዙፎቹ የዓለም ከተሞች መካከል፥ ለምሳሌ ሜክሲኮ-ሲቲ ከ፲፰ ሚሊዮን የሚበልጡ ነዋሪዎች ናቸው ተሚተራመሱባት፣ የብራዚል እንዱስትሪ-ከተማ ሳዎ ፓውሎ ወደ ፲፰ ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች አሏት፣ የአርጀንቲና ርእሰከተማ ቡኤኖስ አይረስ ደግሞ ነዋሪዎቿን አሁን ፲፪ ሚሊዮን አድርሳለች።


የከተሞች ግዝፈት ከጉስቁልናም ጋር የተያያዘ ነው። የተባ መ የሕፃናት መርጃ ድርጅት/ኡኒሴፍ እና የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ሰሞኑን ዠኔቭ ውስጥ ባቀረቡት መረጃ መሠረት፥ ከጠቅላላው የዓለም ሕዝብ ግማሽ ያህሉ የንጽሕና መጠበቂያ ተቋማት የሉትም፤ አንድ ሚሊያርድ የሚደርስ ሕዝብ የንፁሕ ውሃ አቅርቦት አያገኝም። ዘገባው እንደሚለው፥ በያመቱ በተቅማጥ በሽታ ምክንያት ሕይወታቸውን ከሚያጡት 1.8 ሚሊዮን ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ከአምስት ዓመታት ዕድሜ በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው። እርግጥ፣ ይላል የድርጅቶቹ ዘገባ፣ እጎአ በ፲፱፻፺ እና ፪ሺ፪ ዓ.ም. መካከል--በ፲፪ ዓመታት ውስጥ ማለት ነው--የንፁሕ ውሃ አቅርቦት የሚያገኙት ሰዎች አሃዝ ከ፸፯ በመቶ ወደ ፹፫ በመቶ ከፍ ብሏል፣ እንዲሁም በእነዚሁ ፲፪ ዓመታት ውስጥ የፍሳሽ ውሃው መረብና የቤተ-አፍኣው (ማለት የመፀዳጃ ተቋማቱ) ይዘት ከ፵፱ በመቶ ወደ ፶፰ በመቶ ሊሻሻል በቅቷል፤ ግን በሚደረጁት ሀገሮች ውስጥ በተፋፈጉት ከተሞችና በገጠሩ አካባቢ የሚገኙት ድሆቹ ነዋሪዎች ከዚያው ከዓለም-አቀፉ እመርታ ያገኙት ድርሻ ኢምንት ነው። የመሻሻሉ ሂደት ከአካባቢ ወዳካባቢም ነው እየቅሉ የሆነው።

ለምሳሌ በንፁሕ ውሃ ኣቅርቦት ረገድ ትልቁ እመርታ የተገኘው እስያ ውስጥ መሆኑን ዘገባው ያመለክታል። በደቡባዊውም የአፍሪቃ ከፊል በንፁሕ ውሃ አቅርቦት ረገድ ጥቂት እመርታ ቢታይም፣ በዚያው አካባቢ ካሉት ነዋሪዎች መካከል ፵፪ በመቶው አሁንም ቢሆን ውሃ የሚቀዱት ከለላ ከማይደረግላቸው ጉድጓዶች፣ ከክፍት ቦዮች ወይም በቀጥታ ከወንዞች ነው። በአፍሪቃው አህጉር ብቻ ውሃ ለመቅዳት በያመቱ የሚፈጅጀው ጊዜ ፵ ሚሊያርድ የሥራ ሰዓታት እንደሚሆን ነው የሚገመተው።

ከአምስት ዓመታት በፊት፣ ፩፻፹፱ መንግሥታት ኒው ዮርክ ውስጥ በተባ መ ድ ዘንድ በገቡት ቃል መሠረት፥ እጎአ እስከ ፪ሺ፲፭ ድረስ--ከእንግዲህ ወዲያ በአሥር ዓመታት ውስጥ ማለት ነው--የንፁሕ ውሃ እና የጽዳት ተቋማት አቅርቦት የሌላቸው ድሆች አሃዝ በግማሽ የሚቀነስ ይሆናል። ግን፣ የተባ መ የሕፃናት መርጃ ድርጅት/ኡኒሴፍና የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት አሁን አጥብቀው እንደሚያስገነዝቡት፣ ይህንኑ ግብ ለመጨበጥ ይቻል ዘንድ፣ በሚመጡት ዓመታት ውስጥ አንድ ሚሊያርድ የሚደርስ ሕዝብ ነው ከጉስቁልናው ኑሮ እየተላቀቀ የንፁሕ ውሃውንና የንጽሕና ተቋማትን አቅርቦት ማግኘት ያለበት።