1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለማችን  ከፍተኛ የታሪክ ሽልማት ያገኙት ጀርመናዊት ተመራማሪ

ሐሙስ፣ መጋቢት 8 2014

የታሪክ ተመራመሪዋ በኢትዮጵያ ላይ ያካሄዱት ጥናት በዋናነት የሚያተኩረው በ15ኛውና በ16ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ በነገሥታቱ ሥርዓትና በቤተ-መንግሥቶቻቸው ባህል (ሥርዓት) ልይ የሚያተኩር ነው። ጀርመናዊትዋ ተመራማሪ በኢትዮጵያ  የነበረውን የሰሎሞናዊ  ሥርወ-መንግሥት ባሕላዊ ታሪክ፤ የሥልጣን ከፍታ አዲስና ሕያው ሥዕል ሥለውልናል ተብሎአል።

https://p.dw.com/p/48ZbP
Verena Krebs erhält den Dan David Prize
ምስል Verena B. Krebs

የዓለማችን  ከፍተኛ የታሪክ ሽልማት ያገኙት ጀርመናዊት ተመራማሪ

በምዕራብ ጀርመን ቦሁም ከተማ በሚገኘዉ ዩንቨርስቲ የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ጀርመናዊት ፕሮፌሰር ቬሬና ክሬብስ በክርስቲያኒያዊቷ ኢትዮጵያ ላይ ላደረጉት የታሪክ ምርምር ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኘውን ከፍትኛ ተቀባይነት እና ክብር ያለው የዳን ዴቪድ የታሪክ ምርምር ከፍተኛ ሽልማት አሸናፊ ሆኑ ይላል በዓለም ሚዲያ ከሁለት ሳምንት በፊት ይፋ የሆነዉ ዘገባ። የቦኹም ዩንቨርስቲ የታሪክ ተቋም ተመራማሪ ፕሮፌሰር ቬሬና ክሬብስ የእዚህ ዓመቱ የዳን-ዴቪድ ሽልማት አሸናፊ ከሆኑት ዘጠኝ ሰዎች መካከል አንዷ እና የመጀመርያዋ ጀርመናዊት የታሪክ ተመራማሪ ናቸው። ዘጠኙ የዘንድሮ ተሸላሚዎች እያንዳንዳቸዉ 300 ሺህ ዶላር አግኝተዋል። የሽልማቱ ዳኞች እንደገለፁት፤ የታሪክ ተመራማሪዋ ወጣትዋ ጀርመናዊት ለመሸለም የበቁት „በጥንት ጊዜ በአውሮጳና በአፍሪቃ መካከል የነበረውን የባህል ልውውጥ አስመልክተው  በምዕራባውያንና በአፍሪቃውያን የታሪክ ምንጮች ላይ ድንቅ ጥናት በማድረግ አዲስና የሚያጓጓ ዕይታን እንድናይ ስላደረጉ ነው“  ሲሉ ገልፀዋል።  ፕሮፌሰር ዶ/ር ቬሬና ክሬብስ የአውሮጳና-የአፍሪቃን ግንኙነት አስመልክቶ አዉሮጳዉያን ሚሲዮኖች በመጀመርያ ወደ አፍሪቃ መጡ የተባለዉን የተለመደውን ዕይታ ቀይረውታል፤ ተብሎአል። 

Verena Krebs erhält den Dan David Prize
ምስል Verena B. Krebs
Verena Krebs erhält den Dan David Prize
ምስል Verena B. Krebs

ፕሮፌሰር ዶ/ር ቬሬና ክሬብስ በኢትዮጵያ ላይ ያካሄዱት ጥናት በዋናነት የሚያተኩረው በ15ኛውና በ16ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያን ታሪክ  ኢትዮጵያ ማለትም በነገሥታቱ ሥርዓትና በቤተ-መንግሥቶቻቸው ባህል (ሥርዓት) ልይ የሚያተኩር ነው። ጀርመናዊትዋ ተመራማሪ የአውሮጳና-የአፍሪቃን ግንኙነት አስመልክቶ ይነገር የነበረውን የተለመደ አመለካከት በመቀየር  እና ቀድሞ በኢትዮጵያ  የነበረውን የሰሎሞናዊ  ሥርወ-መንግሥት ባሕላዊ ታሪክ፤ የሥልጣን ከፍታ አዲስና ሕያው ሥዕል ሥለውልናል ተብሎአል። ጀርመናዊትዋ የታሪክ ምርምር ተሸላሚ የአፍሪቃና የአዉሮጳ ክርስቲያኖች በአንድ የታሪክ ዘመን ምን አይነት ግንኙነት እንደነበራቸዉ፣ እስከዛሬ በአውሮጳውያን አሰሳና ምርምር መነፅር ብቻ ሲታይ በነበረበት ዕይታ ላይ ጥናት በማድረግ አዲስ እይታን ማምጣታቸዉ ተነግሮአል። ይኸዉም ከአዉሮጳ መልክተኞች ቀድሞ የአፍሪቃ ማለትም የኢትዮጵያ ንጉሣዊ አስተዳደር መልክተኞች ወደ አዉሮጳ ተልከዉ ይመጡ እንደነበር በጥናታቸዉ አሳይተዋል። ክሬብስ የመካከለኛው ዘመን የታሪክ ምሁር እና የእደ ጥበብ ታሪክ አዋቂም በመሆናቸዉ በኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ፤ ባህላዊ ቅርሶችንና የቅዱሳን  ሥዕሎችንን ብሎም የአካባቢውን የባህል ታሪክ ለመረዳት መንፈሳዊ ብራናዎች በጥናታቸዉ ተጠቅመዋል።

Verena Krebs erhält den Dan David Prize
ምስል Verena B. Krebs

የዝግጅት ክፍላችን ሰሞኑን በስራና በጋዜጠኞች ቃለ-መጠይቅ የጊዜ እጥረት የገጠማቸዉን ፕሮፌሰር ቬሬና ክሬብስን በስልክ እንኳን ለዓለማችን ከፍተኛዉ የታሪክ ሽልማት አበቃዎት ሲል ለቃለምልልስ አግኝቶዋቸዉ ነበር።  

ቬሬና ክሬብስ፤ «እዉነት ነዉ። ሽልማቱ ለታሪክ ጥናት ምርምር የሚሰጥ በዓለማችን ከፍተኛ የሚባለዉ ሽልማት ነዉ። እናም ይህን በማግኘቴ ትንሽ ቃላት ሁሉ አጥሮኛል ፤ አመሰግናለሁ»   

ዶቼ ቬለ፤ የሽልማቱ አሸናፊ መሆኖትን ሲያዉቁ ምን አሉ ?

«ይገርማል። ሽልማቱን ማሸነፌን የሰማሁት እንደድንገት ነዉ። ምሽት ላይ ቤት ዉስጥ ከባለቤቴ ጋር እራት እየበላን ነበር ። የእጅ ስልኬ ላይ ተደወለ። ስልኬን ማዕድ ቤት ዉስጥ ነበር። የስልክ ጥሪዉን ሳይ መጀመርያ የመሰለኝ የተሳሳተ የስልክ ጥሪ ነዉ ብዬ ነበር። የተሳሳተ የስልክ ጥሪ ነዉ ብዬ ስላሰብኩ ቆየት ብዬ ነዉ ያነሳሁት። እንኳን ደስ ያሎት ቬሬና ክሬብስ የዳን ዴቬድ ሽልማትን አሸንፈዋል የሚል ድምፅ ተሰማኝ። ማመን አልቻልኩም። ደንገጥኩ። በደስታ ተንቀጠቀጥኩ።»   

Verena Krebs erhält den Dan David Prize
ምስል Verena B. Krebs

ዶቼ ቬለ፤ የእዚህ ሽልማት አሸናፊ እንደሆኑ ቀደም ብለዉ አልሰሙም ነበር?

ቬሬና ክሬብስ፤ «አይ ለሽልማቱ መታጨቴን አዉቅ ነበር።  መታጨቴን የሰማሁት ከአንድ ኢትዮጵያዊ እንዲሁም ከአንድ ኤርትራዊ ጓደኞቼ ነዉ የሰማሁት። ግን ለሽልማቱ ብዙ ታዋቂ የታሪክ ተመራማሪዎች በእጩነት የቀረቡበት በመሆኑ በእዉነቱ እኔ ለሽልማት እመረጣለሁ የሚል እምነት አልነበረኝም። አልጠበኩምም። »

ዶቼ ቬለ፤ ከብዙ ጊዜ ልምድ እንደምናዉቀዉ እንዲህ አይነት ሽልማት የሚያገኙ በተለይ ደግሞ የታሪክ ተመራማሪዎች በዕድሜ ገፋ ያሉ ናቸዉ። እርሶ ደግሞ ሲታዬ በጣም ወጣት ኖት። የመጀመርያዋ ከፍተኛ ሽልማትን ያገኙ ወጣት የታሪክ ተመራማሪ ሆነዋል። ይህ አይገርምም?   

ቬሬና ክሬብስ፤ «እዉነት ነዉ። 37 ዓመቴ ነዉ። ከሌሎቹ የታሪክ ምሁራን እና የታሪክ ተመራማሪዎች ጋር ስተያይ እኔ በጣም ወጣት ነኝ። ከዚህ ቀደም ሽልማቱ የሚሰጠዉ በጣም ብዙ ምርምር ላደረጉ ታዋቂ እና አዛዉንት የታሪክ ምሁራን ነበር ። የሽልማት ሰጭዉ ኮሚቴ ሽልማቱን በህይወታቸዉ ለሰሩት የታሪክ ምርምር ልክ እንደኖቤል ሽልማት ነበር የሚያበረክተዉ። እንደኔ እምነት የሽልማት ሰጭዉ ኮሚቴ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ወጣት የታሪክ ባለሞያዎች እና ተመራማሪዎች ወደፊት ጥናታቸዉን አጠናክረዉ እንዲቀጥሉ እና እዚያ ላይ ወጫቸዉን እንዲያደጉ ለወጣት የታሪክ ተመራማሪዎች ሽልማቱን መስጠት ጀምሮአል ወይም ወስኖአል ብዬ አምናለሁ።»   

ዶቼ ቬለ፤ ጥናት ያደረጉበት የኢትዮጵያ ነገሥታት ታሪክ በተለይም ወደ አዉሮጳ ይመጡ የነበሩ ሚሲዮኖች ጉዳይ ለእርሶ ዕድሜ እጅግ ጥንታዊ ነዉ ። እርሶ ደግሞ ወጣት ኖት ። ምርምሩ ስንት ጊዜ ወሰደቦት። እንዴትስ የኢትዮጵያን ታሪክ ለማጥናት ወሰኑ?    

Verena Krebs erhält den Dan David Prize
ምስል Verena B. Krebs

ቬሬና ክሬብስ፤ «የታሪክ ጥናቴን የጀመርኩት ከረጅም ዓመት በፊት ነዉ። በጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር 2008 እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር ማለትም ከ 14 ዓመታት በፊት ነዉ።  የማስተር ዲግሪ ጥናቴን እና ትምህርቴን ጀርመን ውስጥ ነበር የጀመርኩት።  የማስተርስ ዲግሪዬን በመስራት ላይ ሳለሁ ቤተ-መንግሥትና ቤተ- ክህነት በኢትዮጵያ (Church and State in Ethiopia 1270-1527 የተባለዉን በኢትዮጵያዊዉ የታሪክ ተመራማሪ በታደሰ ታምራት የተዘጋጀዉን መፅሐፍ አነበብኩ።  በዚህ መፅጽሐፍ ዉስጥ በተለይም አንድ ምዕራፍ ላይ የተፃፈዉ ይኸዉም  በ15ኛው ክፍለ ዘመን ከኢትዮጵያ ወደ አውሮጳ ይላኩ ስለነበሩ የመንግሥት መልክተኞች እና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጉዳይ ቀልቤን ሳበዉ፤ ነገሩ አስደነገጠኝም። ምክንያቱም እስከዛ ጊዜ ድረስ ታሪክን ስማር በ 15ኛዉ ክፍለ ዘመን ከኢትዮጵያ ንጉሣዉያን አስተዳደር ወደ አዉሮጳ መልክተኛ ይመጣ እንደነበር ምንም ሰምቼ አላዉቅም ስለነበር ነዉ። ይህ ጊዜ አዉሮጳ ሚሲዮኖችን ማለትም መልክተኞችን ወደ አዉሮጳ መላክ ከመጀመሩ በጣም ብዙ ጊዜ ቀደም ብሎ የሆነ ነዉ። በዚህም ምክንያት እጅግ ቀልቤን ስለሳበዉ የማስተር ምርምር ሥራዬን በዚህ ላይ አደርጋለሁ ብዬ ወሰንኩ። በመቀጠልም የዶክተር መመርቅያ ሥራዩንም በዚሁ ላይ አደረኩ። ከስድስት ዓመት በፊት በ15ኛዉ እና 16ኛዉ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ እና በአዉሮጳ መካከል ያለዉን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ላይ ጥናት መጽሐፍ ጻፍኩ። በአጠቃላይ በዚሁ ርእስ ላይ ጥናት ሳደርግ ቢያንስ 10 ዓመት ሆኖኛል። »  

ዶቼ ቬለ፤ ቤተ-መንግሥትና ቤተ- ክህነት በኢትዮጵያ የተባለዉን መጽሐፍ የጻፉትን ኢትዮጵያዊዉን የታሪክ ተመራማሪ ታደሰ ታምራትን አግኝተዋቸዋል?   

ቬሬና ክሬብስ፤ «እሳቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በተጓዝኩበት ወቅትም በጣም አዛዉንት ነበሩ። እንዳለመታደል ሆኖ ግን ሳላገኛቸዉ ነዉ ያለፉት። የማስትሬት ማዕረግ ትምህርቴን ጨርሼ የዶክትሬት ማዕረግ ትምህርቴን መከታተል እንደጀመርኩ እኔን ከ መጀመርያ ጀምሮ ልጥናቴ ያጓጉኝ ጥናቶችን ያጠኑ እና የጻፉ ታዋቂ የታሪክ ምሁራን፣ በኋላ ፕሮፈሰር ታደስ ታምራትን ጨምሮ ብዙ ታዋቂ የታሪክ ባለሞያዎች ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ነበር። በዝያን ጊዜ ለብዙ ጊዜ ተመላልሼ ያገኘዃቸዉ ታዋቂዉን የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ ሪቻርድ ፓንክረስት ብቻ ነበር።»    

ዶቼ ቬለ፤ ዶ/ር ቬሬና ክሬብስ፤ «በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ነገሥታት፣ የእጅ ጥበብና ከላቲን አውሮጳ  ጋር የነበረዉ የዲፕሎማሲ ግንኙነት» በሚል ለአንባብያን ያቀረቡት መጽሐፍ በጣም ዉድ ነዉ። አንድ መጽሐፍ ከመቶ ዶላር በላይ ነዉ የሚያወጣዉ። መጽሐፉ ለምን እንዲህ ዉድ ሆነ? 

Verena Krebs erhält den Dan David Prize | Buchcover

ቬሬና ክሬብስ፤ «እዉነት ነዉ በሚያሳዝን ሁኔታ መጽሐፉ በጣም ዉድ ነዉ። ግን አሁን መጽሐፉን በቅናሽ ለማግኘት እንዲቻል ኢትዮጵያ ዉስጥ ለማሳተም አሁን ወደ በአማርኛ ለመተርጎም እየሰራን ነዉ። ይህን መጽሐፍ በትግርኛም ይተረጎማል። እዉነት ነዉ መጽሐፉ ዉድ ነዉ ። የመጽሐፍ አቅራቢ ተመራማሪዎች ወይም የታሪክ ፀሐፊዎች በዋጋ ዉሳኔ ላይ ምንም አይነት ዉሳኔን አይሰጡም። አሳታሚዎች ያለዉን ወጬ አይተዉ እነሱ ናቸዉ በዋጋዉ ላይ ዉሳኔን የሚያሳርፉት። በዚህም ምክንያት አሁን የሚተረጉም እና በኢትዮጵያ በተመጣጣኝ ዋጋ ማሳተም የምችልበትን መንገድ ባገኝ ጥሩ ነዉ። በኢትዮጵያም ጥሩ ጥሩ አሳታሚ ድርጅቶች እንዳሉ አዉቃለሁ። ይህን መጽሐፊን ለማሳተም ከአምስት ዓመት በፊት አሳታሚ ድርጅቶችን ስጠይቅ ሊቀበሉኝ አልፈለጉም ነበር። ምክንያቱም፤ በዚያን ጊዜ የመካከለኛን ዘመን ታሪክም ሆነ የአፍሪቃን ታሪክ የሚፈልግ ስላልነበረ ነዉ። የተለያዩ አሳታሚ ድርጅቶችን ጠይቄ ብዙዎች አሁን ይህ ርዕስ ከኛ ፕሮግራም ጋር የሚሄድ አይደለም እያሉ የእንቢታ መልስን ብቻ ነበር የሰጡኝ።  በመጨረሻ መጽሐፉን ያተመለኝ አሳታሚ ድርጅት ብዙ ብር ጠየቆኝ ነዉ ሊታተምልኝ የበቃዉ። ለዚህ ነዉ።»  

ዶቼ ቬለ፤ ቬሬና መቼ ነበር ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የሄዱት? 

ቬሬና ክሬብስ፤ «ለመጀመርያ ወደ ኢትዮጵያ የሄድኩት በጎርጎረሳዉያኑ እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር 2011 ነዉ። መጀመርያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ወደሚገኘዉ ወደ ኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ነዉ የሄድኩት ። በተቋሙ ለረጅም ወራቶች ጥናት አካሂጃለሁ። በዚህ ወቅት በጣም በጣም ጥሩ ቤተሰቦች ተዋዉቄ የምኖረዉ እነሱ ጋር ነበር።  ከዝያ በኋላ በዝያዉ ዓመት ማለትም እንደ ጎርጎረሳዉያኑ  አቆጣጠር 2011 እንዲሁም 2012 በሰሜናዊ ኢትዮጵያ መቀሌ ዩኒቨርስቲ ነበርኩ።»   

Verena Krebs erhält den Dan David Prize
ምስል Verena B. Krebs

ዶቼ ቬለ፤ እናም ለታሪክ ጥናት የሚሆኖትን መረጃዎች ያገኙት በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ነዉ ማለት ነዉ?  

ቬሬና ክሬብስ፤ « በጣም የሚገርመዉ ብዙዎቹ (80%) የኔ ዋቢ ፁሁፎች በአውሮፓያን ላቲንኛ እና ጣልያንኛ  ቋንቋዎች ነው። ለምሳሌ የጥንት የኢትዮጵያ ነገስታት በመልክተኞቻቸዉ በኩል ይልኳቸዉ የነበሩ ደብዳቤዎች ሁሉ ልመልሶቻችው አውሮፓ ብ ቨኒስ ይገኛሉ። ክዚ በመንሳት ለምሳሌ ከኢትዮጵያ የጥንት የኢትዮጵያ ነገስታት የተፃፉትደብዳቤዎች ምግምት ይቻላል።  ከኢትዮጵያ የጥንት ነገስታት የተላኩት ዲፕሎማት መልክተኛ ይዘዋቸዉ ከመጡት ንዋየ ቅዱሳን መካከል አራት የቁም ነብር (እንስሣት) ይገኙባቸዋል ፤ እኚህ መልክተኛ ስለመጡ ደስ ብሎናል፤ እኛም ይህን እና ይህን ስጦታ መስጠት እንፈልጋለን፤ የሚል ፁሁፎች ይገኛሉ።  በጥንት ጊዜ ኢትዮጵያ ከአዉሮጳ ጋር የነበራትን  ግንኙነት  በተመለከተ ብዙ ታሪካዊ ነገሮች የሚገኘዉ በእዉነትም ከሆነ አዉሮጳ ዉስጥ ነዉ። በኢትዮጵያ ጥናት ሳደርግ በተለይ ትክክለኛ የሆኑ  ታሪካዊ እና ጥንታዊ ንዋየ ቅዱሳን በዓይኔ በማየት ጥናቴን ሰርቻለሁ። የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርስ እና የእጅ ጥበብ ስራዎች በክርስትያን ኢትዮጵያ እና አዉሮጳ መካከል አስገራሚ አይነት ግንኙነት አለዉ። ይህን በተመለከተ በመቀሌ ብሎም ደግሞ በአዲስ አበባ በሚገኙ ጥንታዊ የእጅ ጥበብ ስራ ስብስቦችን ብሎም ሌሎች ጥንታዊ ታሪካዊ ነገሮች በመኖራቸዉ እና በማግኘቴ ጥናቴን መስራት ችያለሁ።»    

Verena Krebs erhält den Dan David Prize
ምስል Verena B. Krebs

ዶቼ ቬለ፤  በአዉሮጳ የሚገኙት የኢትዮጵያ ነገስታት ደብዳቤዎች የተፃፉት በአማርኛ ነዉ? 

ቬሬና ክሬብስ፤ አይድሉም « 10 በመቶዉ የሚሆኑትን ታሪካዊ ጽሑፎቹ የተፃፉት በአረብኛ ሲሁን ቀሪዎቹ 10 በመቶዉ የሚሆኑትን ደግሞ የተፃፉት በግዕዝ ቋንቋ ነው። ቀሪዎቹ 80 በመቶዉ ደግሞ የተፃፉት በአዉሮጳ ቋንቋዎች ታሪካዊ  አብያት መዛግብት የጽሑፎችጡ ናችዉ። በዚህም ምክንያት ለኔ ነገሩን ለመረዳት ቀላል ነበር ። ምክንያቱም እኛ ጀርመን ትምህርት ቤት  ዉስጥ የላቲን የፈንሳይኛ እና  ሌሎች የአዉሮጳ ቋንቋን ስለምንማር  ነገሩን አቅሎልኛል። »  ከኢትዮጵያ የጥንት የኢትዮጵያ ነገስታት ግን አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ጥንታዊ እና ታሪካዊ የፅጽሑፎች የተቀመጠ ነዉ።

ዶቼ ቬለ፤ ፕሮፊሰር ቬሬና ክሬብስ ሰሞኑን ኢትዮጵያዉያንን ያስቆጣዉ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርስ በኢቤ ድረገፅ ሽያጭ መደርደርያ ላይ መቀመጡን ሰምተዋል? 

ቬሬና ክሬብስ፤ « ተሰርቀዉ በኢቤ ላይ ለሽያጭ ቀረቡ ስለተባለዉ የኢትዮጵያ ቅርሶች ጉዳይ በዶቼ ቬለ ዘገባ ተፅፎ አይቻለሁ። ጥሩ ዘገባ ነዉ። የኢትዮጵያ ቅርሶች ኢቤ ላይ ቀረቡ እየተባለ ሲነገር ከአስር ወይም ከ 15 ዓመት በፊት በቅርብ ጊዜ ከ አምስት ዓመት በፊትም ሰምቻለሁ።  ይህን አይነቱን ቅርሶች ይዘዉ የሚመጡት ቱሪስቶች ከቄሶች ላይ እየገዙ ነዉ ። በእዉነቱ ከሆነ ይህ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት  ሕገወጥ ነዉ። በቅርቡ ኢቤላይ ወጡ የተባሉትን ጥንታዊ ቅርሶችን ድረገፅ ላይ አይቼያቸዋለሁ ፤ እና የእዉነት ጥንታዊ ናቸዉ ብዬ ለመናገር ይከብደኛል። ሻጪዎች ሁሌም ቢሆን የመካከለኛዉ ክፍለዘመን ቅርሶች እያሉ ነዉ የሚሸጡት። ይህን እኔ አላምንም። አብዛኞቹ  በ18ኛዉ በ 19ኛዉ  ወይም በ 20ኛዉ ክፍለዘመን የተሰሩ ናቸዉ። እንደዚ አይነት ቅርስ ላይ የሚያትኩሩ የተሳሳቱ ዘግባዎች እና አሉባልታ በኋላ የእውንትኛ ቅርሶች ገበያ ላይ ሲመጡ ልምናሰማው ድምጽ ታአማኒነት እንዳእእሰጋሎ እሰጋሎህ።

Verena Krebs erhält den Dan David Prize
ምስል Verena B. Krebs

ዶቼ ቬለ፤ ስለኢትዮጵያ ታሪክ አጥንተዋል፤ በኢትዮጵያም ነበሩ ፤ ኢትዮጵያን እንዴት አገኝዋት? 

ቬሬና ክሬብስ፤ « ኢትዮጵያን እንዴት አገኘኳት? ኢትዮጵያ በጣም ናፍቃኛለች። በኮሮና ምክንያት ለረጅም ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ አልተጓዝኩም።  ለመጨረሻ ጊዜ ኢትዮጵያ የነበርኩት በጎርጎረሳዉያኑ 2019 እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ። በዝያን ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዝኩት  ከተማሪዎቼ ጋር ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ነበር። ብዙ ታሪካዊ የኢትዮጵያን ከተሞች ጎብኝተናል። ያ ሁሉ ናፍቆኛል። ኢትዮጵያ በጣም ዉብ ሃገር ነች። ብቻ ቃላት ያጥረኛል ለመግለፅ። ለምሳሌ በትግራይ እና በአማራ ክልል ገዳማት ዉስጥ የሚገኙ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ንዋየ ቅዱሳትን  ለማየት እና ለማጥናት ፈልገን ወደ ገዳማት ሄደናል። እነዚህ ገዳማት ቦታ ላይ ለመድረስ ግን እጅግ ፈታኝ ነበር። ብዙ እግር መንገድ ብዙ ዉጣ ውረድ ነበረዉ። እዝያም ከደረስን በኋላ የፈለግነዉን አይተናል። በገዳማቱ ዉስጥ ካሉ አባቶች ጋርም ጠላ ጠጥተናል። እና ገዳማቱ ዉስጥ ያገኘናቸዉ ጥንታዊ የብራና ላይ ጽሑፎች መጻህፍት እንዲሁም ከአባቶች የተደረገልን ገለፃ ይህን በአንድ ጊዜ ማግኘት እና ሁሉን ነገር ማየት ያለዉን ስሜት በቃላት መግለፅ በእዉነቱ ያስቸግራል። » 

በተረፈ በአዲስአበባ ቦሌ ርዋንዳ የኖርኩበት ቤት ጋርድን «የአትክልቱ ስፍራ» እና እንደ ቤተሰብ የኖርኩባቸዉ ዶክተር ተሰማ መንገሻ እና ወ/ሮ አስቴር ናፍቀዉኛል ሲሉ ቬራና ክሬብስ ተናግረዋል።  ዶክተር ተሰማ መንገሻ የምሥራቅ አፍሪቃ የበረሃ አንበጣ ቁጥጥር ድርጅት ዋና ኃላፊ ነበሩ ። ዶክተር ተሰማ እና ወሮ አስቴር ወደ ኢትዮጵያ ጨርሰዉ ከመመለሳቸዉ በፊት በአሜሪካ እና በኬንያ ለረጅም ዓመታት የኖሩ መሆናቸዉን እንደ እናት ከሆኑኝ ወ/ሮ አስቴር ጋር በአፍሪቃ እና በምዕራቡ ዓለም ያለዉን ሃይማኖታዊ፤ ታሪካዊ እና የኑሮ እና ህይወት ጉዳዮች ላይ ለረጅም ጊዜያቶች ውይይት እናደርግ  ነበር፤ ሲሉ ቬሬና ተናግረዋል። 

Verena Krebs erhält den Dan David Prize
ምስል Verena B. Krebs

ዶቼ ቬለ፤ ከተማሪዎቾ ጋር የትኞቹን የኢትዮጵያ ከተሞች ጎበኛችሁ? 

ቬሬና ክሬብስ፤ «ከተማሪዎቼ ጋር መጀመርያ ላሊበላ ነበርን፤ ከዝያ ባህርዳር፤ ከዝያ ጎንደር፤ ከዝያ አክሱም፤ አድዋ፤  አቡነ ገብረ ሚካኤል (ፍልፍል ገዳም) ገርዓልታ  እንዲሁም መቀሌ ዩንቨርስቲ ነበርን። መቀሌ ዩንቨርስቲ ከኛ ጋር የሚሰራ ዩንቨርስቲ በመሆኑ እና እኔም ግማሹን የዶክትሬት ጥናቴን  የሠራሁት እዝያ በመሆኑ ፤ መቀሌ ዩንቨርሲቲ መገኘታችን በጣም አስፈላጊ ነበር።»  

ዶቼ ቬለ፤ በኢትዮጵያ በተለይ ሰሜናዊ ኢትዮጵያ ጦርነት ዉስጥ ነዉ ። ምን ተሰማዎት

Verena Krebs erhält den Dan David Prize
ምስል Verena B. Krebs

ቬሬና ክሬብስ፤ « ልቤን ሰብሮታል። አዎ ልቤን በጣም ሰብሮታል። ምክንያቱም ጦርነቱ በትግራይ፣ ደሴ፣ ላሊበላ እና  በሌሎች ከተሞች የሚገኙ አብዛኞቹን የኔን ጓደኞች እና የሥራ ባልደረቦቼን በመጎዳታቸዉ ነዉ።  ልቤ ተሰብሮአል።» 

ዶቼ ቬለ፤ ፕሮፌሰር ቬሬና ክሬብስ ይን በተመለከተ መናገር የሚፈልጉት መልዕክት አለ? 

ቬሬና ክሬብስ፤ «ከባድ ጥያቄ ነው። እኔ የታሪክ ተመራማሪ እንደመሆኔ መጠን ሥራዬ እና ትኩረቴ ከረጅም ጊዜ በፊት ብሆነ ታሪካዊ ኩነት ላይ ነው። ስለዚህም በአሁኑን ጊዜ ምን መደረግ እንዳለበት የሚረዳ የመፍትሄ መላ የለኝም። ሆኖም ግን ሰላምን እመኛለሁ። እንደኔ እምነት በአሁኑ ወቅት ሁሉም ሰው ሰላምን ይመኛል፤ ይህን  በርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። በአሁኑ ጊዜ ሰላምን የማይመኝ አንድ ሰው እንኳ አለ ብዬ አላምንም። እንደዚሁም ባደረግሁት ምርምር እንደተመለከትኩት ከሆነ፤ ለምሳሌ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጲያ የሰለሞናዊው ሥርወ- መንግሥት በነበረበት ጊዜ እስከዛሬ ከምናስበው በጣም በተለየ መልኩ ብዙና የተወሳሰበ ጊዜ ነበር። በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ ንጉሥ የነበረው ዘረ-ያዕቆብ ወደ ሮም ወደ ጳጳሱ የላካቸው አምባሳደሮች (መልእክተኞች) አንድ ጣሊያናዊ፣ አንድ ኢትዮጵያዊ መነኩሴና አንድ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ነበሩ። ይህ ዛሬ ምሳሌ ሆኖ ለእኛ የሚያሳየን ነገር፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ቀድሞም (ድሮም) በጣም በተለያዩ ባለድርሻ አካሎች መካከል ዓይነተ-ብዙ ትብብሮች በስኬት ይከናወኑ እንደነበረ ነው። አሁን በኢትዮጵያ ስላለው ነባራዊ-ሁኔታ ግን መፍትሔ ሊሆን የሚችል ምንም የሚረባ ነገር መናገር አልችልም፣ ምክንያቱም ፖለቲካን የሚረዱ (የሚያውቁ) ሌሎች የተሻሉ ሰዎች በመኖራቸዉ ነዉ።»  

Verena Krebs erhält den Dan David Prize
ምስል Verena B. Krebs

የዳን-ዴቪድ ሽልማት በዓለማችን ከፍተኛ እና ለታሪክ ምርምር ትልቅ አስተዋጾኦን ላደረጉ ሰዎች የሚበረከት ከፍተኛ ሽልማት ሲሆን ሽልማቱም የሚሰጠው በእስራኤል ቴላቪቭ ከተማ የሚገኘው የዳን-ኤቪድ- ተቋም እና በቴላቪቭ ዩንቨርስቲ አማካኝነት ነዉ። ፕሮፌሰር ዶ/ር ቬሬና ክሬብስ የዘንድሮዉን ስልማት የተቀበሉ የመጀመርያዋ ጀርመናዊት የታሪክ ተመራማሪ ናቸዉ። 

ፕሮፌሰር ቬሬና ክሬብስ ለሰጡን ቃለ ምልልስ እያመሰገንን ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።  

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ