የውጭ ጣልቃ ገብነት የበዛበት የሶርያ ጦርነት | ዓለም | DW | 12.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የውጭ ጣልቃ ገብነት የበዛበት የሶርያ ጦርነት

ሩሲያ በሶርያ እና በኢራቅ «እስላማዊ መንግስት» መሰረትኩ ባለው ጽንፈኛ የ«አይ.ኤስ.» ቡድን ላይ ጥቃት ከጀመረች የሩሲያን እርምጃ የሶርያው ፕሬዝዳንት በሽር አል-አሳድ በደስታ ቢቀበሉትም ከአውሮጳ ህብረትና ዩናይትድ ስቴትስ ግን ትችት በርትቶበታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:38

የሶርያ ጦርነት

ሩሲያ በዓለም ፖለቲካ ያላትን ተደማጭነት በአዲስ መልክ ለመገንባት ጥረት ጀምራለች። የሶርያ ጦርነትን እጣ ፈንታ የምትወስነው ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ ልዕለ ኃያልነትን ለብቻዋ የተቆጣጠረች የምትመስለው ዩኤስ አሜሪካ አይደለችም የሚል መልዕክት ማስተላለፍ የፈለገችም ይመስላል። ለማንኛውም ሩሲያ በሶርያ እና ኢራቅ «እስላማዊ መንግስት መስርቻለሁ» በሚለው ጽንፈኛ የ«አይ.ኤስ.»ቡድን ላይ ከ12 ቀናት በፊት የአየር ጥቃት የጀመረችው በምዕራባዊ ሶርያ ነበር። ጥቃቱ ጥቂት ቆየት ብሎ ከካስፒያን ባህር ላይ ካሉ የጦር መርከቦች የሚምዘገዘጉ ክሩዝ ሚሳዔሎችንም ጨምሮዋል። የሩሲያ ጦር አዛዦች ጥቃቱን የጀመሩት ሃሳቡን ለፓርላማ አቅርበው ተቀባይነት ባገኘ በሰዓታት ውስጥ ነበር። «አይ.ኤስ.» እየተባለ የሚጠራውን ጽንፈኛ ቡድን ይዞታዎች፤ የጦር መጋዘኖች ዒላማ ያደረገውና መነሻውን ከላታኪያ ያደረገው ጥቃት በሶርያ ፕሬዝዳንት በሽር አል-አሳድ ጥያቄ የተንቀሳቀሰ መሆኑን የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናግረዋል።
«የሩሲያ የጥቃት እርምጃ የተጀመረው ከፕሬዝዳንት በሺር አል አሳድ በቀረበልን ጥሪ መሰረት ነው። እርምጃችንም ከዓለም አቀፍ ህግጋት ጋር የሚጣረስ አይደለም።»


«ሩሲያ እግረኛ ወታደሮችን ወደ ሶርያ የማዝመት እቅድ የላትም» ሲሉ የነበሩት ፕሬዝዳንት ፑቲን በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ለሃገራቸው ስጋት እንደሆነም አስታውቀው ነበር። ሪቻርድ ቤሬት የጸረ-ሽብርተኝነት ተንታኝ ናቸው።
«ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዓላማቸው የሶርያ ጦር በአይ.ኤስ ታጣቂዎች ላይ በእግረኛ ወታደሮች ጥቃት መፈጸም እንዲችል ማጠናከር መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህም በመጀመሪያ ራሳቸው የአየር ድብደባ መፈጸምን መርጠዋል።»
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጽንፈኛ ቡድኑ በሶርያ ውጤታማ ከሆነ ለተመሳሳይ ዓላማ ወደ ሩሲያ ሊዘልቅ እንደሚችልም ነው የገለጹት። ፕሬዝዳንት ፑቲን ሃገራቸው በሶርያ የምታካሂደው ጥቃት ዋነኛ ዓላማ የአገራቸውን ብሄራዊ ጸጥታ ማስጠበቅ ነው ይበሉ እንጂ እንደ ሪቻርድ ቤሬት ከሆነ የክሬምሊን ባለስልጣናት ከፍ ያለ ስሌት ነው የያዙት።
«ወደ ሶርያ ሄደው ከጽንፈኛው አይ.ኤስ ጎን የሚዋጉ ሩሲያውያን ቁጥር 2400 መሆኑን መንግስት አስታውቋል። ትክክለኛው ቁጥር ግን ከዚያ ሊበልጥ ይችላል። አይ.ኤስ. በሰሜናዊ ካውከሰስ የራሱን ግዛት መስርቻለሁ ብሏል። እናም ውስን የሽብር ስጋት አለባቸው። ነገር ግን የፕሬዝዳንቱ ፍላጎት ከዛ የሰፋ ነው። ሩሲያ እስካሁን እጇን ያስገባችው በሶርያ ብቻ ነው። እናም በአሜሪካ የበላይነት በሚታይበት በመካከለኛው ምስራቅ ፕሬዝዳንቱ ያላቸውን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ማሳደግ ይፈልጋሉ።»
በእርግጥ ራሱን አይ.ኤስ ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድን በሰሜናዊ ሩሲያ ግዛት መስርቻለሁ ማለቱ እውነትነት አለው። ከሶርያና ኢራቅ ውጪ በዘጠኝ የተለያዩ አገራት ግዛቶች መስርቻለሁ ባዩ ጽንፈኛ ቡድን የእስልምና እምነት ተከታዮች ከሚበዙበት ከካውካሰስ ግዛት የቀረበለትን ጥሪ የተቀበለው በሰኔ ወር አካባቢ ነበር። ይህ ብቸኛው ገፊ ምክንያት ለመሆኑ የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተቺዎች ጥርጣሬ አላቸው።
የምዕራቡ ጎራ ልዕለ ኃያላን በአሜሪካ እየተመሩ የሶርያ ትርምስ አዛዥ የመሆን እቅዳቸው ፈተና ሲገጥመው ሩሲያን ለመተቸት መሽቀዳደም ያዙ። አሜሪካ በሰው አልባ አውሮፕላኖች የጽንፈኛው ታጣቂ ቡድን ይዞታዎችን፤ማሰልጠኛ ጣቢያዎችንና የጦር መሳሪያ ማከማቻዎችን ስትደበድብ ከርማለች። ታላቋ ብሪታኒያ፤ፈረንሳይና ቱርክም ተመሳሳይ እርምጃዎች ወስደዋል። የፕሬዝዳንት በሽር አል-አሳድ መንግስትን መውደቅ የምትናፍቀው አሜሪካ ነጻ ሶርያ ጦር (Free Syria Army) ተብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድን በስልጠናና የጦር መሳሪያ በማስታጠቅ ስትደግፍ ቆይታለች። በአንጻሩ ሩሲያ አፈሙዞቿን እንደ ምዕራባውያኑ ሁሉ በጽንፈኛው ቡድን ላይ አነጣጠርኩ ስትል ተቃውሞ በረታባት። የዩኤስ አሜሪካ መከላከያ ሚንስትር አሽተን ካርተር የሩስያን ጥቃት የተሳሰተ ነበር ያሉት፤
« የ«አይስል» ያልሆኑ ዒላማዎችን መደብደባቸውን ቀጥለዋል። ይህ መሰረታዊ ስህተት ነው ብለን እናምናለን። ሩስያውያኑ የፈለጉትን ቢሉ፣ የተሳሰተ ስልት በመከተል እነዚህን ዒላማዎች መምታታቸውን እስከቀጠሉ ድረስ፣ እኛ ከነርሱ ጋር ለመተባበር አልተስማማንም። »
በስልጣናቸው ተቃውሞ የበረታባቸው የሶርያ ፕሬዝዳንት በሽር አል-አሳድ ከኢራን፤ሩሲያ እና የሊባኖሱ ሒዝቦላህ ድጋፍ አላቸው። በሌላ ወገን የቆሙት ዩናይትድ ስቴትስ፤ቱርክና የገልፍ ባህረ-ሰላጤ አገራትና ምዕራባውያን አጋሮቻቸው የፕሬዝዳንት አል-አሳድን መቆየት አይፈልጉም። በዚህ መካከል ሁሉም አጥብቀው የሚጠሉት የአይ.ኤስ ጽንፈኛ ቡድን አለ። ሁለቱም ጎራዎች ቢያንስ ጽንፈኛውን ታጣቂ ቡድን ለመዋጋት በአንድ ጎራ የተሰለፉ ቢመስልም ቅሉ የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፉክክራቸውና ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚያደርጉት እሽቅድድም እርስ በርስ አፋጧቸዋል።
ከአራት አመታት በላይ በቀጠለው የሶርያ የርስበርስ ጦርነት ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማና ቭላድሚር ፑቲን መግባባት ተስኗቸው የጎሪጥ እንደተያዩ እዚህ ደርሰዋል። ሩሲያ «አይ.ኤስ.» ላይ ከምትወስደው እርምጃ ጎን ለጎን ፕሬዝዳንት በሽር አል-አሳድን ለመጣል ነፍጥ ያነሱትን ታጣቂዎች ዒላማ አድርጋለች የሚል ስሞታ ይሰማል። እነዚህ ታጣቂ ቡድኖች የኢራን ተቀናቃኝ በሆኑት የገልፍ ባህረ-ሰላጤ አገራት በተለይም ሳዑዲ አረቢያና ኳታር የሚደገፉ ናቸው። ቱርክ ፕሬዝዳንት በሺር አል-አሳድ ስልጣናቸውን እንዲለቁ የምትፈልግ ቢሆንም በቀጥታ ጥቃት አልጀመረችም። የአይ.ኤስ. ጽንፈኛ ታጣቂዎችን የሚደበድቡት የጦር ጀቶቿ ግን እግረ መንገዳቸው በኩርድ ተቃዋሚዎቻቸው ላይ እሳት ማዝነባቸው አልቀረም። እንዲህ በተወሳሰበውና ከዓመት ዓመት አስከፊ እየሆነ በመጣው የሶርያ ምስቅልቅል እጃቸውን ያስገቡት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከባላንጣቸው የዩኤስ አሜሪካ ጦር ጋር የመተባበር እቅድ ፈጽሞ የላቸውም።


« አሜሪካውያኑ ፣ ምንም እንኳን ሕገ ወጥ ቢሆንም፣ በሶርያ ያየር ጥቃት ከጀመሩ ከአንድ ዓመት በላይ በመሆኑ፣ በዚያ ስላለው ሁኔታ የተሻለ እውቀት አለን ካሉ፣ ዒላማዎቹን ይስጡን፣ እናጠቃቸዋል።»

አፍጋኒስታን ዳግም?

በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. 84 ቢሊዮን ዶላር በመከላከያ በጀታቸው ወጪ መድበው የነበሩት ቭላድሚር ፑቲን ግማሽ ያህሉን በ2015 ዓ.ም. የመጀመሪያ ሶስት ወራት ብቻ ወጪ ማድረጋቸውን የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ጥናት ተቋም ያወጣው ጥናት ይጠቁማል።
ሩሲያን ከነበረችበት ማንቀላፋት ቀስቅሰዋል የሚባልላቸው ፑቲን 28 ተዋጊ የጦር ጀቶችን ከኤም 24 ተዋጊ ሔሊኮፕተሮች ጋር ወደ ሶርያ ማዝመታቸውን በቅርብ የወጡ የደህንነት ዘገባዎች ይጠቁማሉ። ይህ ግን ለሁሉም ሩሲያውያን መልካም ዜና ላይሆን ይችላል። የሙጃህዲን ታጣቂዎችን ለመዋጋት አፍጋኒስታን ዘምታ የነበረችው የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ሽንፈት እንዲሁ የሚረሳ አይመስልም። ሶቭየት ህብረት በአፍጋኒስታን ካዘመተቻቸው ወታደሮቿ መካከል 14,000 ያህሉ በህይወት አልተመለሱም።
በዓለም አቀፍ ማዕቀብ ስር ያለችውና የመገበያያ ገንዘቧ የሩብል የመግዛት አቅም መዳከም ያሳሰባት ሩሲያ ለዚህ ጦርነት የምታወጣው ገንዘብ እጅጉን አላስፈላጊ ተብሏል። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አገሪቱ ለጦርነት ወጪ እያደረገች ያለውን የገንዘብ መጠን ከመጪው የአገሪቱ አቅም የሚቀነስ ይሉታል።
የሩሲያ ጉዳይ የአውሮጳ ህብረትንም እጅጉን ያሳሰበ ይመስላል። የሩስያ ተዋጊ አይሮፕላኖች የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ኪዳን -ኔቶ አባል የሆነችውን ቱርክ አየር ክልል ጥሰዋል ሲል ኪዳኑ በተደጋጋሚ ክስ አሰምቷል። የአውሮጳ ህብረት አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጉዳዩ ላይ ሊመክሩ በሉክዘምበርግ ተሰብስበዋል። የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ፌዴሬካ ሞግሄሪኒ ሩሲያ በሶርያ ያደረገችው ጣልቃ ገብነት ብዙ ነገሮችን መቀየሩን ተናግረዋል። አሳሳቢ ጉዳዮች አሉት ያሉት ፌዴሬካ ሞግሄሪኒ «ማስተባበር ካልተቻለ ከፖለቲካ አንጻር ብቻ ሳይሆን በጦር በኩልም በጣም አደገኛ አደጋ ነው የሚሆነው።» ብለዋል።
የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ኪዳን -ኔቶ ዋና ጸሐፊ የንስ ስቶልትንቤርግ ሩሲያን ከምዕራቡ ጋር ያፋጠጠው የሶርያ ጦርነት የፖለቲካ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
«ሩሲያ በሶርያ የምታደርገው የጦር እንቅስቃሴ መጨመሩን ታዝበናል። ይህ ደግሞ አሳሳቢ መሆኑን የአውሮጳ ህብረት ሚኒስትሮች ተስማምተዋል። ሩሲያ ከ«አይስል» ጋር በሚደረገው ትግል ገንቢ ሚና እንድትጫወት ጥሪ አቀርባለሁ። ነገር ግን የሩሲያ ድርጊትና ለመንግስቱ የምታደርገው ድጋፍ ጠቃሚ አይደሉም። የቱርክ የአየር ክልል መጣሱም ተቀባይነት ያለው አይደለም። ኔቶ ጉዳዩን በቅርበት መከታተሉን የሚቀጥል ሲሆን ከቱር ጎን በወንድማማችነት እንቆማለን። በሶርያ ላለው ቀውስ ከምንጊዜውም በበለጠ ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚፈፈለግበት ጊዜ አሁን ነው።በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ኔቶ ይደግፋል።»የሩሲያው ፕሬዝዳንት በበኩላቸው የሳምንቱን መጨረሻ እሁድ ከሳዑዲ አረቢያው የመከላከያ ሚኒስትር ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ጋር ሲመክሩ አሳልፈዋል። በደቡባዊ ሩሲያ በምትገኘው የሶቺ ከተማ ከተካሄደው ምክር በኋላ ልዑል ሳልማን ሩሲያ በሶርያ ባደረገችው ጣልቃ ገብነት አገራቸው ደስተኛ አለመሆኗን ተናግረዋል። ልዑሉ ሩሲያ ከኢራን ጋር አጋርነት ልትመሰርት ትችላለች የሚል ስጋትም እንዳላቸው አልሸሸጉም። የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው «ሁለቱ ወገኖች በሶርያ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አላማ አላቸው። ከሁሉም በላይ አገሪቱ በ«እስላማዊ መንግሥት» እጅ ስር እንዳትወድቅ ማድረግ ነው።» ሲሉ ተናግረዋል። ልዑሉ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ካደረጉት ውይይት በኋላ በሽር አል አሳድ ከስልጣናቸው እንዲለቁ አገራቸው እንደምትፈልግ አልሸሸጉም።
የበሽር አል አሳድን መንግስት ትደግፋለች የሚል ክስ የሚቀርብባት ሩሲያና የሶርያውን ፕሬዝዳንት ውድቀት ለማፋጠን ሌት ተቀን ጉድጓድ የምትምሰው ሳዑዲ አረቢያ ስለ መስማማታቸው ማረጋገጫ መጠበቅ የዋህነት ይመስላል። የሁለቱ ወገኖች እጅጉን የተራራቁ ፍላጎቶች የሚታረቁበት መንገድ ስለመኖሩ ምልክት አልታየም።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ከሩሲያ አቻዎቻቸው ጋር የአየር ጥቃት የሚፈጽሙበትን አግባብ መወያየታቸው አስታውቀዋል። ውይይቱ የሶርያውን ምስቅልቅል ባይመለከትም የሁለቱ አገሮች የጦር አውሮፕላኖች በአየር ድብደባ ወቅት ሊወስዷቸው በሚገቡ ጥንቃቄዎች ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑን ፔንታገን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ሩሲያና የበሽር አል-አሳድ ታማኞች የ«እስላማዊ መንግስት» ይዞታ ባሏቸው አካባቢዎች የሚፈጽሙትን ጥቃት ማጠናከራቸውን የአገሪቱ የመንግስት ቴሌቭዥን ጣቢያ ዘግቧል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሁማን ራይትስ ዎች ሩሲያ የክላስተር የጦር መሳሪያዎችን በሶርያ እየተጠቀመች ነው ሲል ክስ አቅርቧል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሩሲያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከለከለውን የጦር መሳሪያ ለመጠቀሟ የፎቶግራፍ ማስረጃዎች አግኝቻለሁ ብሏል። ሩሲያ የክላስተር ቦምብን ከመጠቀም አልፋ ለበሽር አል-አሳድ ታማኞች ሰጥታለችም ብሏል። ለጊዜው ሩሲያም ሆነች ፕሬዝዳንቷ ቭላድሚር ፑቲን እርምጃቸውን ከማድነቅ ውጪ ያሉት ነገር የለም።


ሶርያ ግን ለዜጎቿ የሐዘን ምድር ሆናለች። የአሜሪካ፤ቱርክ፤ታላቋ ብሪታኒያ፤ፈረንሳይ እና ሩሲያ ጥቃት ከሰማይ የበሽር አል-አሳድ መንግስት፤ «እስላማዊ መንግስት» ተብዬውና ሌሎች ታጣቂዎች ከምድር ነፍጥ አንግበው አንዱ በሌላው ላይ ይተኩሳሉ። ሴቶችና ህጻናት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ይሸሻሉ። መሸሽ ያልሆነላቸው በሰቀቀን ሞትን በፍርሃት ውስጥ ይጠባበቃሉ።

እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic