የውጭ ዝርያ ያላቸው የጀርመን ፓርላማ አባላት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 15.10.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የውጭ ዝርያ ያላቸው የጀርመን ፓርላማ አባላት

ዘንድሮ በተካሄደው የጀርመን ምክር ቤት አባላት ምርጫ ከሻነፉት ተወዳዳሪዎች መካከል አንድ አፍሪቃዊ ጀርመናዊ ይገኙበታል ። በዘንድሮው ምርጫ የምክር ቤት መቀመጫ ለማግኘት የበቁትን አፍሪቃዊ ጀርመናዊ የህዝብ እንደራሴን ጨምሮ የውጭ ዝርያ ያላቸው የጀርመን ምክር ቤት አባላት ቁጥር ከፍ እያለ ነው ።

« ስለ እኔ ና ስለ መጪው የጀርመን ምርጫ የሚያወሳውን በራሪ ፅሁፍ ልስጣችሁ ? »

በትውልድ ሴኔጋላዊው የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ በጀርመንኛው ምህፃር SPD አባል ዶክተር ካራምባ ድያቢ ሃለ በተባለችው ከተማ የምርጫ ዘመቻ ባካሄዱበት ወቅት ለሃላፊ አግዳሚው የሚያቀርቡት ጥያቄ ነበር ። ዶክተር ድያቢ ያኔ ወጪ ወራጁን በመጨበጥ ከሰዎች ጋር አጭር ውይይት በማድረግ ብቻ ሳይሆን ቤት ለቤት በመዘዋወወርም ጭምር ነበር የምርጡኝ ዘመቻቸውን ያካሄዱት ። መስከረም 12 2006 ዓም በተካሄደው የጀርመን ምክር ቤት አባላት ምርጫ ዲያቢ እንደተጠበቀው በጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መቀመጫ በማሸነፍ የመጀመሪያው አፍሪቃዊ ጀርመናዊ ለመሆን በቅተዋል ። ዶክተር ድያቢ የሚወክሏት ሃለ በምሥራቅ ጀርመኑ የዛክሰን አንሃልት ፌደራዊ ክፍለ ግዛት የምትገኝ በምጣኔ ሃብትና የትምህርት ማዕከልነት የምትታወቅ ከተማ ናት ። ከጀርመን ዩኒቨርስቲዎች አንጋፋዎቹ ሃለ ነው የሚገኙት ። ድያቢ እጎአ በ1986 ነበር ሃለ የመጡት ።« እርግጥ ነው ያኔ ጀርመንኛ አልናገርም ነበር ። BMW ና ቡንደስሊጋ ከሚሉት ቃላት በስተቀር ሌላ ቃል አላውቅም ነበር ። እነዚህ ደግሞ በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን ማንም ሊሰማቸው የሚፈልጋቸው ቃላት አልነበሩም ። ከዚህ በተጨማሪም አጠቃላዩ የሶሻሊዝም ዘመን አኗኗር ከሴኔጋል የተለየ ነበር ። እነዚህ ለኔ በጣም ያልተለመዱ ነበሩ ። »

SPD-Landesparteitages Sachsen-Anhalts in Magdeburg Dr. Karamba Diaby

ዶክተር ካራምባ ድያቢ

የነፃ ትምህርት እድል አግኝተው በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን በሃለ ዩኒቨርስቲ ኬሚስትሪ አጠኑ ።በ1980ቹ በሃገራቸው የተማሪዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ይሳተፉ የነበሩት ድያቤ በሃለ ዩኒቨርስቲም የዓለም ዓቀፍ ተማሪዎች ኮሚቴ መሪ ነበሩ ። ያኔ በዩኒቨርስቲው አሉ የሚሏቸውን አድሎዎች ታግለዋል ። የበርሊኑ ግንብ ከፈረሰ በኋላ እንደ ማንኛውም ምሩቅ ሥራ ማግኘት አዳጋች የሆነባቸው ዲያቢ የPHD ትምህርታቸውን ቀጠሉ ። ለመመረቂያ ያካሄዱት ጥናትና ምርምር ሳይንሱንና ተሟጋችነቱን አብሮ ለማስኬድ ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረላቸው ። ይኽው የዶክተር ድያቢ ጥናት አንድ የቤት ገንቢና ሻጭ ድርጅት ከሃለ ወጣ ብሎ የሚገኝ መናፈሻን ለማውደም መናፈሻው ተበክሏል ሲል ያቀረበውን የሃሰት ፈጠራ ውድቅ አድርጓል ። ወጣቱ ኬሚስት በሽግግሩ ወቅት ከተረፉት የከተማዋ መለያዎች አንዱ የሆነውን መናፈሻ ለማዳን በመብቃታቸው ለህዝቡ እንደ ባለውለታ ነው የሚታዩት። ድያቢ ከዚያ በኋላም በጀርመናውያንና በውጭ ዜጎች መካከል የባህል ግንኙነትና መግባባት ለማስፈን በሚያስችሉ ሃላፊነቶችም ሰርተዋል ። በተለይ ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ ያደረጉት ድያቢ በ2009 ዓም ነበር የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ አባል የሆኑት ። ከአንድ ዓመት በፊት ደግሞ እጎአ በጥቅምት 2012 ከተማቸውን ሃለን ባካተተው የምርጫ ወረዳ SPDን ወክለው ለምክር ቤት እንደራሴነት ለመወዳደር ተመረጡ ። ከ11 ወራት በኋላም የተካሄደውን ምርጫ አሸንፈው የጀርመን ፌደራል ምክር ቤት አባል ሆኑ ። ድያቢ በአሁኑ ጊዜ ህዝቡ ችግሮችን ከመጋፈጥና ለመፍትሄውም ከመጣር ይልቅ አንዳንድ የምሥራቅ ጀርመን አካባቢዎችን እየጣለ በመሄዱ አይስማሙም ።

Deutschland Bundestag Charles M. Huber MdB CDU

ቻርልስ ሁበር

«በዚህ ጉዳይ ላይ ሰዎች ሊያስቡበት የሚገባ ይመስለኛል ። ሁሌ መተቸት ብቻ ሳይሆን

ዜጎች ለውጥ ለማምጣት እኔም አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ ማለት መቻል አለባቸው ።»

ድያቢ የተወከሉላት ሃለ የውጭ ዜጎችን እጇን ዘርግታ የምትቀበል ከተማ አለመሆኗና በርካታ የቀኝ መስመር ተከታይ ፓርቲዎች ደጋፊዎች እንደሚገኙባት ይነገራል ። እርሳቸው ግን ለዚህ ቦታ አይሰጡም ። አደገኛ በሚባሉ የከተማዋ አካባቢዎች እንኳን በምሽት ሲዘዋወሩ ጥበቃ ያስፈልጋቸው እንደሆን ሲጠየቁ አይቀበሉም ። ዲያቢ የሃለ ስም በክፉ እንዲነሳ አይፈልጉም ። ሆኖም በከተማይቱ በጀርመናውያንና በውጭ ዜጎች መካከል ችግሮች እንዳሉ ያውቃሉ ። ራሳቸውም ቢሆኑ የዘረኛ ጥቃት ሰለባ መሆናቸው አልቀረም ። ይህ ግን ድያቤን ይሄ ብዙ አያስጨንቃቸውም ። በርሳቸው እምነት የውጭ ዜጎችን ጥላቻና ዘረኝነትን የሚቃወሙ ብዙ ሰዎች አሉ ። ደቡብ ምዕራብ ሴኔጋል በምትገኝ ማራሳስ በተባለች ትንሽ ከተማ የተወለዱት ካራምባ ዲያቢ ለወላጆቻቸው የመጨረሻ ልጅ ናቸው ። ወላጆቻቸው በ 7 ዓመታቸው በመሞታቸው ታላቅ እህታቸው ጋ ነው ያደጉት የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ሴኔጋል ሲሆን ። ከፍተኛ ትምህርታቸ እዚያው ሴኔጋል ከጀመሩ በኋላ ነበር ጀርመን መጥተው ያጠናቀቁት ። በአሁኑ ሰዓት በጀርመን ምክር ቤት እንደ ዶክተር ድያቢ ሁሉ የውጭ ዝርያ ያላቸው ተወካዮች ቁጥር ጨምሯል ። በ2009 21 የነበረው የውጭ ዝርያ ያላቸው የህዝብ እንደራሴዎች ቁጥር በዘንድሮው ምርጫ 35 ደርሷል ። ቻርልስ በአሁኑ ምርጫ የምክር ቤት መቀመጫ ያሸነፉ አፍሪቃዊ ጀርመናዊ የክርስቲያን ዲሞክራት ፓርቲ አባል ናቸው ። በሙያቸው ተዋናይ የሆኑት ሁበር የተወለዱት በደቡብ ጀርመንዋ ሙኒክ ከተማ ሲሆን አባታቸው ሴኔጋላዊ ዲፕሎማት እናታቸው ደግሞ ጀርመናዊ ናቸው ። በጀርመን ፓርላማ የውጭ ዝርያ ያላቸው ተወካዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሊሄድ የቻለበትን ምክንያት ከትምህርት ጋር ነው የሚያያይዙት ።

Charles Muhamed Huber Schauspieler CDU-Bundestagsabgeordneter

ሁበር

«እንደሚመስለኝ «የውጭ ዝርያ ያላቸው» የሚል መጠሪያ የተሰጣቸው ወጣቶች የትምህርት ደረጃ ተሻሽሏል ። ቀደም ባሉት ጊዜያት ወደ ጀርመን ለመጡም ይሁን ወደ ሌሎች ሃገራት ለሄዱ የመጀመሪያዎቹ ትውልዶች ምክር ቤት ውስጥ መግባት የሚቻል ነገር አልነበረም ። በመላው ዓለም በርካታ የውጭ ዝርያ ያላቸው ሰዎች ወይም ስደተኞች ይገኛሉ ። ሆኖም ብዙ የውጭ ዝርያ ያላቸው ሰዎች በሚገኙባቸው ሃገራት እንኳን ሳይቀር የተለየ የቆዳ ቀለምም ሆነ የውጭ ዝርያ ያለው የምክር ቤት አባል በጣም በጥቂቱ ነው የሚገኘው »

በጀርመን ምክር ቤት ውስጥ የውጭ ዝርያ ያላቸው ተወካዮች ቁጥር ከሌሎች እንደ ፈረንሳይ ብሪታኒያ ወይም ኖርዌይን ከመሳሰሉ የአውሮፓ ሃገራት ጋር ሲነፃጸር ግን ዝቅተኛ ነው ። በዚህ ረገድ ጀርመን ወደ ኋላ የቀረችበትን ምክንያት ሁበር የተማሩ የውጭ ዜጎች በብዛት ካለመኖራቸው ጋር ያያይዙታል ።

« ለዚህ ምክንያት አለው ፈረንሳይና ብሪታኒያ ከረዥም ጊዜያት አንስቶ ከውጭ ዜጎች ጋር የተያያዘ ታሪክ አላቸው ። የዚህም ምክንያቱ እነዚህ ሃገራት በአፍሪቃ ና በእስያ ቅኝ ቅኝ ገዥዎች ነበሩ ። ጀርመን ግን የነርሱን ያህል የቅኝ ገዥነት ልምድ የላትም ። የውጭ ዜጎች ወደ ጀርመን መምጣት የጀመሩት በ1960 ዎቹ ነው ። የመጡትም እውቀት በሚያስፈልጋቸው ሞያዎች ለመሥራት ሳይሆን በግንባታ ፣ በአነስተኛ ንግዶችና በመሳሰሉት ለመሰማራት ነበር ። እንደሚመስለኝ መጪው ትውልድ ራሱን በከፍተኛ ትምህርት ሊያሳድግ ይገባል ። »

Tür zu Tür Wahlkampf mit Karamba Diaby

ድያቢ

ያ ማለት ግን በጀርመን የተማሩ የውጭ ዜጎች የሉም ማለት አይደለም /

« በርግጥ የተማሩ የውጭ ዜጎች ጀርመን ውስጥ አሉ ። በተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት ከቀድሞዎቹ ቅኝ ግዛቶች የመጡ ላቅ ያለ የትምህርት ደረጃ ያላቸው አፍሪቃውያን አሉ ። መጀመሪያ ላይ ግን የምክር ቤት አባል ወይም ሳይንቲስት የመሆን እድል አላገኙም ። ጀርመንን ልንወቅስ የሚገባ አይመስለኝም ። »

በሁበር አስተያየት በጀርመን ያሉትን እድሎች መጠቀም ና ውጤት ላይ ለመድረስ መሞከር የእያንዳንዱ የውጭ ዜጋ የግል ጥረት መሆን ይገባዋል

ሰዎች ለሚያደርጉት ነገር ሁሉ ተነሳሽነቱ ከራሳቸው መምጣት አለበት ይህ ደግሞ የቆዳ ቀለም ጉዳይ አይደለም ። የአንድ ሰው ስኬት መንግስት የሚያደርገውን ግፊት መሰረት ያደረገ መሆን የለበትም ። መሆን የምትፈልገውን መወሰን ያለብህ ራስህ ነህ ። ከህንድ የመጡ የኮምፕዩተር ባለሞያዎች በBMW እንዲሁም በመርሰዲስ ቤንዝ ኩባንያዎችና በሌሎችም ቦታዎች የሚሰሩ አፍሪቃውያን አሉ ። እንደሚመስለኝ እዚህ ሁሉም እድል አለው ። ይህም እኔ በደረስኩበት ደረጃ ይገለፃል »

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic