የውጭ ንግድ ዘርፍ የብድር አቅም  | ኤኮኖሚ | DW | 20.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የውጭ ንግድ ዘርፍ የብድር አቅም 

የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እድገት እያሳየ እንዳልሆነ እና በሚፈለገው ደረጃ ያልተራመደ፤ ከችግር አዙሪት ያልወጣ ነውም ይላሉ በውጭ ንግዱ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች። ዘርፉ ካለበት ችግር ብለው ከሚጠቃቅሱት አንዱም የብድር አገልግሎት አሰጣጥ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:48

የውጭ ንግድ ዘርፍ ችግሮች አንዱ የብድር አቅርቦት ነው

ኢትዮጵያ የውጭ ንግድ በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከፍ እንዲል እየተሰራ መሆኑ ይነገራል። የገቢ ንግድ እንዲጨምር የሀገር ውስጥ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪን ለማስተካከል ጥረት ይጠይቃል። በውጭ ንግድ ዘርፍ መሰራቱ ለሀገር ጠቃሚ መሆኑ አያጠያይቅም፤ ብዙዎችም የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። ይህም ለማካሳት ደግሞ የዘርፉን ችግሮች መቅረፍ አሌ የማይባል ይሆናል ይላሉ። በዚህም በርካታ አሉበት የተባለው የዘርፉ ችግሮች በግብርና ምርቶች፣ በማዕድን፣ በኢንዱስትሪ በሌላውም ሊተኮርበት የሚገባ መሆኑ ይጠቀሳል። የውጭ ንግድ በዘርፉ አሉበት ከሚባሉት ችግሮች አንዱ የብድር አቅርቦት ነው። ለበርካታ ባለኃብቶች የብድር አገልግሎቱ ችግር በመንግስትም ሆነ በግል ባንኮች ላይ እንደሚስተዋል ቅሬታቸውን ያሰማሉ።

ብድር የሚሰጠው የገንዘብ መጠንና ብድሩ በወቅቱ ሊደርስላቸው አለመቻሉ ለወራት ዘግይቶ እንደሚደርሳቸውም አንዳንድ በስራው የተሰማሩ ይገልጻሉ። የብድር አገልግሎቱ ሂደቱ ረጅም ቀናትን የሚፈጅ መሆኑንና በሚፈልጉት ወቅት አለመገኘቱንም አቶ ቢኒያም ብርሃኔ የቡና ላኪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ያረጋግጣሉ። በዚህም ስራቸውን ለማከናወን እንደሚቸገሩ ይናገራሉ። “ባንኮች ብድር ለመስጠት ረጅም ጊዜ ይፈጅባቸዋል። የብድር አሰጣጡ ችግር አለው። ነጋዴው በሚፈልገው ወቅት አግኝቶ የሚያስፈልገውን ሥራ የሚሰራበት ሁኔታ አይደለም።” ለ11 ዓመታት ቁም እንስሳት ላኪነት ስራ ተሰማርተዋል፤ አቶ ዲና ገዛሀኝ።  

በቁም እንስሳት ንግድ ዘርፍ ባለው የኮንትሮባንድ ችግር ምክንያት ባንኮች ብድር ለመስጠት ስጋት አለባቸው ይላሉ። “በቁም እንስሳት ንግድ ዘርፍ ላይ የኮንትሮባንድ ንግድ አስቸጋሪ ነው። ባንኮች በዚህ የኮንትሮባንድ ንግድ ምክንያት የዘርፉ አዋጭነት ጥርጣሬ ስላላቸው ለብድር ድጋፍ አያደርጉም።

Somalia Hafen Djibouti Dschibuti

በዘርፉ ላይ ውጤታማነት አለማመን ነው መልስ የሚሰጡት።” ጋስኮ ትሬዲንግ ሃ/የተ/የግ/ማ ጥራጥሬ ፣ ሰሊጥ፣ የቁም እንስሳት እና ስጋ ምርቶችን ወደ ውጭ የሚልክ ድርጅት ነው። 24 ዓመታትን በዘርፉ የውጭ ንግድ የተሰማራው ጋስኮ ትሬዲንግ ብድር ማግኘቱ አስቸጋሪ ነው ብለው እንደማያስቡ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ኃይሉ መለሰ ጠቅሰው። ዋናው ነገር የሚያስፈልገውን መስፈርት አሟልቶ መገኘት ነው ሲሉም ይናገራሉ። ሆኖም እንደችግር የሚያነሱት ብድር ጠይቀው ሁለት ወር እና ሶስት ወር መጠበቅ እንደሚገደዱ በዚህም ለንግዱ ስራ አስቸጋሪነቱን ይገልጻሉ። “የውጭ ንግድ ገበያው በተለያዩ ችግሮች እየቀነሰ ነው። የውጭ ንግድ በአጠቃላይ ከባድ ነው። ባንኮች ብድርን ይሰጣሉ። በርግጥ ዋስትና ማስያዣ ይጠይቃሉ። የግልም የመንግሥትም ባንኮች በውጭ ንግድ ላይ ብድር ማግኘት አስቸጋሪ ነው ብዬ አላስብም። ሆኖም ግን አንድ ወርና ሁለት ወር ብድሩን ለማግኘት የሚወስድበት ጊዜ ግን አለ።” ኢትዮጵያ በቁም እንስሳት ንግድ ዘርፍ የሚፈለገውን ያህል ተጠቅማለች ለማለት እንደማይቻል ጠቅሰው፤ ለቁም እንስሳት ውጭ ገበያ ንግዱ የሚሰጠው ብድር የሚፈለገው ያህል እንዳልሆነ አቶ አንተነህ አለሜ የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ነጋዴዎች ማህበር ስራ አስኪያጅ ይገልጻሉ። “ስራውን ለመስራት ትልቅ ወጭ የሚጠይቅ ነው። የገንዘብም፤ የቦታም ጭምር የሚያስፈልግ ቢሆንም በከፍተኛ ሁኔታ ይሄ ባለመሟላቱ ምክንያት ማግኘት ያለብንን እያገኘን አይደለም። የብድር አገልግሎቱ የሚያረካ አይደለም። የቁም እንስሳት ንግድ በባህሪው የገንዘብ መጠንን የሚጠይቅ ነው። ባንኮች ለውጭ ላኪ ባለሀብቶች በሚያስፈልገው መጠን ብድር እየሰጡ ነው የሚል እምነት የለኝም።” በተደጋጋሚ የሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሀላፊ ልናገኛቸው እና ምላሽ ልናገኝም አልቻልንም። የውጭ ንግድ ዘርፉ ላይ የምርት ጥራት ያነጋግራል ቢባልም፤ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ይታመናል። የኮንትሮባንድ ንግድ ሰለባ የሆነው የሀገሪቱ የቁም እንስሳት ችግርም ቆም ብለን ልናስብ፤ መፍትሄም ሊበጅለት የሚገባው ጉዳይ ሲሉ በዘርፉ ያሉ ስጋታቸውን አሁንም ይገልጻሉ።

ነጃት ኢብራሂም

አዜብ ታደሰ    
 

Audios and videos on the topic