የዋጋ ግሽበት የተጫነው የኢትዮጵያ በጀት | ኤኮኖሚ | DW | 07.07.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የዋጋ ግሽበት የተጫነው የኢትዮጵያ በጀት

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በመጨረሻ ስብሰባቸው ለ2014 ዓ.ም. ያጸደቁት በጀት ካለፈው አመት ጋር ሲወዳደር በብር 18 በመቶ ቢጨምርም በዶላር ግን ቀንሷል። ያለፈው አመት የኢትዮጵያ መንግሥት በጀት በብር 476 ቢሊዮን፤ በዶላር ደግሞ 13.7 ቢሊዮን ገደማ ነበር። የዘንድሮው በብር ወደ 561.7 ከፍ ቢልም በዶላር 12.9 ቢሊዮን ሆኗል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:23

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የዋጋ ግሽበት የተጫነው የኢትዮጵያ በጀት

ከትናንት በስቲያ ሰኞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በ2014 ዓመታዊ በጀት ላይ ለመወያየት በተሰበሰቡበት ወቅት ያቀረቧቸው ጥያቄዎች አብዛኞቹ በዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት ሳቢያ ሥጋት የተጫናቸው ነበሩ። ወይዘሮ ሐዋ አሊ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል "የዋጋ ንረቱ በአርብቶ አደሩ እና በሀገሪቷ ወሰን አካባቢዎች በሚኖሩ በተለይም አቅመ ደካሞች እና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ እጅግ ከፍተኛ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል። አቶ ታደሰ መሰሉ የተባሉ ሌላ የምክር ቤቱ አባል "የዋጋ ግሽበት ወይም የዋጋ ንረትን በተፈለገው መንገድ መቆጣጠር ባለመቻሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ እና በደሞዝ የሚተዳደሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል። በዚህ ምክንያት የዕለት ኑሯቸውን ለመግፋት ተቸግረው ይገኛሉ" በማለት እንደ ወይዘሮ ሐዋ ሁሉ ጥያቄ ከማቅረባቸው በፊት ጠጠር ያለ አስተያየት ሰጥተዋል።

ሥልጣኑ ለተጨማሪ አንድ አመት ተራዝሞ ስድስት አመታት ያገለለው ምክር ቤት አባላት የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠር ረገድ እንዳልተሳካለት ፊት ለፊት ከመናገር አላፈገፈጉም። ወይዘሮ ቱፋኒ ቱራ "መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት እየተባባሰ የመጣውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር ልዩ ልዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ የቆየ ቢሆንም የዋጋ ግሽበቱ የመጨመር እንጂ የመቀነስ አዝማሚያ የለውም" ሲሉ ተደምጠዋል። ወይዘሮ ሰናይት ደስታ ደግሞ "የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ በርካታ ተዛማጅ የማሻሻያ ሥራዎች ተግባራዊ ቢሆኑም በተጨባጭ ግን የዋጋ ንረቱን ማስተካከል እና በነጠላ አሃዝ መገደብ አልተቻለም" በማለት ችግሩን ለመቅረፍ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደተሳነው የሚጠቁም አስተያየት አቅርበዋል።

ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ "በኤኮኖሚው ያመጣናቸውን ለውጦች ልናመጣ ያልቻልንበት አንዱ ዘርፍ ግሽበት ነው" በማለት መንግሥታቸው በእርግጥም በመቆጣጠር ረገድ እንዳልተሳካለት ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።  ጠቅላይ ምኒስትሩ በማብራሪያቸው ላለፉት አመታት ሲንከባለል የቆየ የዋጋ ግሽበት፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ነዳጅ እና ማዳበሪያን በመሳሰሉ ሸቀጦች ላይ የታየ የዋጋ ጭማሪ አስተዋፅዖ ማበርከታቸውን ጠቅሰው "እሱ ላይ እንዳናተኩር ደግሞ ግራ እና ቀኝ የያዙን በጣም በርካታ ጉዳዮች አሉ። በእነዚህ ምክንያቶች የዋጋ ግሽበቱ በሚፈለገው ልክ አልተስተካከለም" ብለዋል።

Äthiopien l Premierminister Ahmed Abiy

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ "በሚቀጥለው አመት ዋና ዋና ሸቀጦችን ገዝተን ግሽበት እንዳያመጣ ብናደርግ የኑሮ ውድነትን አይቀርፈውም፤ በአንድ አመት በምንሰራው ሥራ መቅረፍ አይቻልም" ሲሉ ተደምጠዋል።

ዐቢይ "በሚቀጥለው አመት ዋና ዋና ሸቀጦችን ገዝተን ግሽበት እንዳያመጣ ብናደርግ የኑሮ ውድነትን አይቀርፈውም፤ በአንድ አመት በምንሰራው ሥራ መቅረፍ አይቻልም" ሲሉ ተደምጠዋል። "ላለፉት አስራ ስድስት አመታት በየአመቱ ባለሁለት አሃዝ የዋጋ ግሽበት ነበር። ይኸ አንደኛው በሌላው ላይ እየተደመረ እየተደመረ የመጣ የዋጋ ግሽበት ሸማቾች እናንተ ባነሳችሁት ልክ ወይም ከዚያ በላይ ሸምተው ማደር በጣም ፈታኝ ሆኗል" ብለው በእርግጥም በኢትዮጵያ ዜጎች ላይ ያሳደረውን ጫና ገልጸውታል።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዋጋ ግሽበቱን መቀነስ ባይችልም መንግሥታቸው ጥረት ማድረጉን እንዳላቆመ ሥጋት ለበረታባቸው የምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል። ለዚህም ባለፉት ሶስት አመታት "ከውጭ በምንገዛው መጠን ከሸጥን የኑሮ ውድነት ያባብሳል" በሚል አመክንዮ መንግሥት ነዳጅ ከገዛበት ዋጋ በታች እየሸጠ 47 ቢሊዮን ብር መክሰሩን በማሳያነት ጠቅሰዋል። ውኃ እና የቤት ኪራይ የመሳሰሉ አገልግሎቶች ክፍያ እንዳይጨምር ሙከራ መደረጉን፣ በአዲስ አበባ የዳቦ ማምረቻ በማስገንባት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት መደረጉን ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እየጠቀሱ መንግሥታቸው መፍትሔ ፍለጋ የሰራቸውን ዘርዝረዋል።  

Somalia Äthiopien Viehzucht-Nomaden

ወይዘሮ ሐዋ አሊ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል "የዋጋ ንረቱ በአርብቶ አደሩ እና በሀገሪቷ ወሰን አካባቢዎች በሚኖሩ በተለይም አቅመ ደካሞች እና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ እጅግ ከፍተኛ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል

"እስካሁን መንግሥት አንደኛ ምግብ ነክ ምርቶች በርከት ብለው እንዲገቡ ጥረት አድርጓል። ብዙ ቢሊዮን ብር መድበን ለማስገባት ሞክረናል። ሁለተኛው ለሕብረት ሥራ ማህበራት ግማሽ ቢሊዮን ብር ገደማ ተጨማሪ ብድር እንዲያገኙ እና ሸቀጦች ማከፋፈል እንዲችሉ ለማድረግ ተሞክሯል። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የሚጠቀሙበት አንዱ ቦታ ስለሆነ። ሶስተኛ የአቅርቦት ሰንሰለቱ ሳንካ አስቸጋሪ በመሆኑ የገበያ ማዕከላት አዲስ አበባም በተለያየ ቦታ በስፋት ለመገንባት ጥረት ተደርጓል። አራተኛ የግሉ ዘርፍ በፍራንኮ ቫሉታ ተጨማሪ ታክስ ሳይከፍል ስንዴ፣ ስኳር፣ ዘይት፣ ሩዝ፣ የሕፃናት ዱቄት እንዲያስገባ ተፈቅዷል። በፍራንኮ ቫሉታ የፈቀድንው በቂ ስላልሆነ መንግሥት በተለይ ስንዴ፣ ዘይት እና ስኳር ተጨማሪ ሐብት መድቦ እያስገባ ይገኛል" ያሉት ዐቢይ የመንግሥት ሙከራዎች በተፈለገው መጠን ግሽበቱን ባይቀንሱም በተወሰነ ደረጃ ማገዛቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚለው ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይም "ሕገ-ወጥ" ያሏቸውን ነጋዴዎች ለግሽበቱ አስተዋጽዖ ማበርከታቸውን ጠቅሰው ተጠያቂ አድርገዋል። ዐቢይ መደብሮቻቸው "የታሸጉባቸው" ፈቃዶቻቸው "የተሰረዙባቸው" ግፋ ሲልም "በክስ ሒደት ላይ" የሚገኙ መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሠረት የዋጋ ግሽበት በሰኔ ወር ወደ 24.5 በመቶ ከፍ ብሏል። የምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ ከ23.7 በመቶ ወደ 28.7 በመቶ ሲያድግ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ከ14.8 በመቶ ወደ 19 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ሥራ አጥነት፣ የኤኮኖሚ መቀዛቀዝ እና የብድር ጫናን የመሳሰሉ ብርቱ ምጣኔ ሐብታዊ ችግሮች ቢኖሩም የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ የዋጋ ግሽበትን ቀዳሚ ያደርጉታል። አቶ አብዱልመናን የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ባለፉት አስር አመታት እየተንከባለለ ዛሬ ካለበት በመድረሱ ይስማማሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ በሚበደረው የገንዘብ መጠን ላይ ገደብ የሚጥለውን የባንኩን አዋጅ በማሻሻል ከተወሰደው እርምጃ በኋላ የበረታው የዋጋ ግሽበት "ባለፉት ሶስት አመታት ግን በጣም ብሶበታል" ሲሉ ያስረዳሉ።

"ምን አልባት የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ኤኮኖሚው ላይ በጣም የወደቀበት ዘርፍ ቢኖር የዋጋ ግሽበት ላይ ነው። ከዚያ በፊት ከነበረው በጣም ብሶበታል። በቅርብ ጊዜያት ደግሞ በጣም ብሶበታል" የሚሉት አቶ አብዱልመናን መሐመድ በተለይ በቅርብ ጊዜ እንዲበረታ አድርገዋል ያሉባቸውን ምክንያቶች ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

Äthiopien | Traditioneller Markt in Debre Markos

አቶ ታደሰ መሰሉ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል "የዋጋ ግሽበት ወይም የዋጋ ንረትን በተፈለገው መንገድ መቆጣጠር ባለመቻሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ እና በደሞዝ የሚተዳደሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል። በዚህ ምክንያት የዕለት ኑሯቸውን ለመግፋት ተቸግረው ይገኛሉ" በማለት ጥያቄ ከማቅረባቸው በፊት ጠጠር ያለ አስተያየት ሰጥተዋል።

"አንደኛ የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም አቀፍ ተቋማት ጫና ምክንያት ብርን እያዳከመ ነው። በአንድ አመት ውስጥ ብር ከሌሎች መገበያያዎች አኳያ ወደ 18 በመቶ ነው እየደከመ ያለው። ይኸ ትልቅ ተፅዕኖ አለው። የኢትዮጵያ መንግሥት ፍጹም መቀበል ያልነበረበትን ነገር በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ተፅዕኖ ተቀብሎ ነዳጅም ሆነ ከውጭ አገር የሚመጣ ማንኛውም ነገር ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል። በዚህ ላይ የፖለቲካ አለመረጋጋቱ አለ፤ የብር ህትመቱ አለ" ይላሉ አቶ አብዱልመናን መሐመድ።

በምክር ቤቱ አባላት የዋጋ ግሽበቱን በሚቀጥለው አመት ለመቆጣጠር መንግሥትዎ ምን አቅዷል? ተብለው የተጠየቁት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ዋናው ጉዳይ የገንዘብ እና ፊስካል ፖሊሲ ቁጥጥራችንን ማጠናከር ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። "የሚያስፈልጉ የምግብ ሸቀጦች በማምረት፤ የማንችላቸውን በማስገባት ለማስተካከል ጥረት ይደረጋል" ብለዋል። ከአመት አመት እየተንከባለለ ግፋ ሲልም እየተከመረ ለመጣው የዋጋ ግሽበት መፍትሔ ለማበጀት ዐቢይ እንዳሉት "መሬት ጦም ማደር የለበትም።" የበጋ ስንዴ ምርትን እና ኩታ ገጠም እርሻን ማጠናከር ዐቢይ እና መንግሥታቸው ተስፋ የሰነቁባቸው አማራጮች ናቸው።

"በሁሉም ክልሎች ባይሆንም በተወሰኑ ክልሎች የበጋ ስንዴ ውጤት በጣም ከፍተኛ ነው። በዚህ አመት አምና የሰራንውን 60፣ 70 እና 80 በመቶ ማሳደግ ብንችል 20 እና ከዚያ በላይ ሚሊዮን ኩንታል እናመርታለን። ይኸ በእጅጉ ያግዛል። ሶስተኛው ኩታ ገጠም [እርሻን ማስፋፋት] ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የተሸነሸነ መሬት ራስን በምግብ ለመቻል አያስችልም የሚሉ ንግግሮች ነበሩ። እኛ የተሸነሸነ መሬት የለም። የተሸነሸነው ጭንቅላት ነው፤ መሬቱን ሰብሰብ አድርገን፤ አርሶ አደሩን ሰብሰብ አድርገን በቴክኖሎጂ ብናግዝ ኮሜርሺያል እርሻን ማረጋገጥ ይቻላል የሚል ሐሳብ ጀምረን በጣም ሰፊ ርቀት ተኪዷል። ነገር ግን ዘንድሮ ቢያንስ በእጥፍ ማደግ አለበት" ብለዋል ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ።

ዐቢይ "በጥቂት ሰዎች" የተያዘ ያሉትን እና "ሲፈልጉ ያዝ ሲፈልጉ ለቀቅ" እንደሚያደርጉት የተገለጸውን የሥርጭት ሰንሰለት መቆጣጠር ሌላው የጠቀሱት ጉዳይ ነው። መንግሥታቸው ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረውን ገንዘብ እንደሚቀንስም ተናግረዋል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ ግን "ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ ይኸ ብር የማዳከሙን ጉዳይ ቢተዉት ነው የሚሻለው። ምንም የሚያኬድ አይደለም። በዚህ ሁኔታ የቀጠለ እንደሆነ በጣም እየከፋ ሊመጣ ይችላል" እያሉ ያስጠነቅቃሉ።  

"በብሔራዊ ባንክ ገንዘብ የማተሙ ጉዳይ በቅርብ ጊዜ የመቀነስ ነገር ታይቷል። ገንዘብ ከማተም የግምዣ ቤት ሰነድ በመሸጥ የበጀት ጉድለቱን የመሙላት አካሔድ አለ። ይኸ ጥሩ እርምጃ ነው። በመካከለኛ ጊዜ መታሰብ ያለበት ነፃ የሆነ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋም እና ገለልተኛ የሆነ የገንዘብ ፖሊሲ እንዲያወጣ ማሰብ ነው። ከዚያ ባሻገር የአገሪቱን የፖለቲካ ችግር መፍታት ነው። አገሪቱ የተረጋጋች እንደሆነ ገበሬውም ተረጋግቶ ያርሳል። ከብር ማዳከም በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱም በጣም አስከፊ ደረጃ ደርሷል። እሱም አባብሶታል" ብለዋል። 

የምክር ቤቱ አባላት በመጨረሻ ስብሰባቸው ለ2014 ዓ.ም. 561.7 ቢሊዮን ብር በጀት አጽድቀዋል። ይኸ በጀት ካለፈው አመት ጋር ሲወዳደር በብር 18 በመቶ ቢጨምርም በዶላር ግን  ቀንሷል። ያለፈው አመት የኢትዮጵያ መንግሥት በጀት በብር 476 ቢሊዮን በዶላር ደግሞ 13.7 ቢሊዮን ገደማ ነበር። የዘንድሮው በብር ወደ 561.7 ከፍ ቢልም በዶላር 12.9 ቢሊዮን ሆኗል።

Äthiopien Tigray-Krise

በትግራይ የተቀሰቀሰው ውጊያ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ ሌሎች ምክንያቶች ባስከተሉት ወጪ ሳቢያ ለፌድራል መንግሥቱ ለ2013 ዓ.ም የተበጀተው ገንዘብ በማለቁ የምኒስትሮች ምክር ቤት 26 ቢሊዮን ብር ገደማ ተጨማሪ በጀት በዚህ አመት አጽድቋል።

በትግራይ የተቀሰቀሰው ውጊያ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ ሌሎች ምክንያቶች ባስከተሉት ወጪ ሳቢያ ለፌድራል መንግሥቱ ለ2013 ዓ.ም የተበጀተው ገንዘብ በማለቁ የምኒስትሮች ምክር ቤት 26 ቢሊዮን ብር ገደማ ተጨማሪ በጀት በዚህ አመት አጽድቋል። አቶ አብዱልመናን ይኸ ተጨማሪ በጀት የመጠየቅ ጉዳይ በሚቀጥለው አመት መደገሙ እንደማይቀር ይናገራሉ።

አቶ አብዱልመናን መሐመድ "የኑሮ ውድነቱ በዚህ የቀጠለ እንደሆነ ገንዘቡ ስለማይበቃ መንግሥት ተጨማሪ በጀት መጠየቁ አይቀርም። በጀቱ ሲዘጋጅ አሁን ባለው የዋጋ ሁኔታ ነው የተዘጋጀው። በጀቱን ወደ ማስፈጸም በሚገባበት ጊዜ፤ ዕቃ እየተወደደ በሚመጣበት ሰዓት ገንዘቡ አይበቃም" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

ዐቢይ የኢትዮጵያን የኤኮኖሚ ይዞታ ያሳያሉ ያሏቸውን ቁጥሮች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አቅርበዋል። የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ1,000 ዶላር በላይ "ዘሏል" ያሉት ዐቢይ የኢትዮጵያ አጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን (GDP) ወደ 4.2 ትሪሊዮን ብር ወይም ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። በጠቅላይ ምኒስትሩ አባባል ከአንድ ትሪሊዮን በላይ ብር በባንክ ይዘዋወራል፤ የባንኮቹ ጥሪት ጥሬ ገንዘብን ጨምሮ ወደ 1.9 ትሪሊዮን ብር ደርሷል። በገቢ እና ወጪ ንግድ መካከል ያለው ልዩነት በ2011 ዓ.ም. ከነበረበት 14.6 ወደ 9.3 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቅሰው "ይበል የሚያሰኝ" ብለውታል። ኢትዮጵያ በዐቢይ ማብራሪያ መሠረት 3.5 ቢሊዮን ዶላር ለውጭ ገበያ ካቀረበቻቸው ሸቀጦች አግኝታለች።

ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ አመታዊ የምርት መጠን ወደ 37 በመቶ ገደማ የነበረው የአገሪቱ የውጭ ዕዳ ወደ 26 በመቶ እንደቀነሰ ተናግረዋል። ከውጭ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የገባው መዋዕለ ንዋይ በ20 በመቶ ማደጉን የተናገሩት ጠቅላይ ምኒስትሩ "2.7 ቢሊዮን ዶላር በአይነት እና በመጠን ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል" ሲሉ ተደምጠዋል። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሊገባበድ ጥቂት ወራት በቀሩት አመት የተሠሩ አበይት ኤኮኖሚያዊ ክንዋኔዎችን ጠቅሰው "ከ2012 በጣም የተሻለ ለ2011 የቀረበ ዕድገት ዘንድሮ ይጠበቃል" ብለዋል።

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic