የዋሽንቱ ንጉስ ዮሐንስ አፈወርቅ | ባህል | DW | 03.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የዋሽንቱ ንጉስ ዮሐንስ አፈወርቅ

"ያገሬን ልጅ አልኩኝ እሱን ባለ ዋሽንቱን፣ የወንዜን ልጅ አልኩኝ እሱን ሰምቼ ድምፁን " እጅጋየሁ ሽባባዉ ለባለዋሽንቱ ያዜመችዉ ነዉ። ባለዋሽንቱ በዋሽንቱ በሃገሩ ፍቅር እስከ መቃብርን በሕዝብ በልቦና አትሞ በዓለም አቀፍ መድረክ ከሕዝብ ለሕዝብን ጨምሮ በተለያዩ መድረኮች በአምባሳደርነት ሰርቶአል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:49

ዕውቀቱን የሚያስተላልፍበት ተቋም ሊናቋቁምለት ይገባን ነበር

የእዚያን ጊዜዉ አፍላ ወጣት በእጁ የሰራትን ዋሽንት ይዞ ከጎጃም ክፍለ ሀገር ከአገው ምድር አውራጃ ባንጃ ወረዳ ግሽ አባይን በእግሩ አቆራርጦ አዲስ አበባ ገብቶ ፤ በረኝነት የተማራትን የቤተሰቡን የቀየዉን የባልንጀራ ጨዋታን የሚያስታዉስበትን የዋሽንት ጨዋታ፤ አዲስ አበባ አስገብቶ እና አዘምኖ ፤ በፍቅር እስከ መቃብር በማኅበረሰቡ ልቦና ጽኑ ፍቅርን አትሞ፤ በሕዝብ ለሕዝብ ዓለምአቀፋዊ መድረክ የሃገሩ የባህል አምባሳደር ሆኖ ጠቆር ባለች ቦርሳዉ የያዛቸዉን በጣት የሚቆጠሩ ዋሽንቶችን ይዞ ፓሪስ ፤ ለንደን፤ ሞስኮ፤ በርሊን፤ ሮማ፤ ቶክዮ ለሙዚቃ አፍቃሪዎች የዋሽንቱን ቅላፄ አንቆርቁርቁሯል። የዋሽንቱ ንጉስ ዮሐንስ አፈወርቅ! ባለቅኔና ፀሐፊ ተዉኔት አያልነህ ሙላቱ ፤ የዋሽንቱን ንጉስ ዩሐንስ አፈወርቅን በቅርበት ያቀዋል። 

«ዮኃንስ አፈወርቅ ማለት ለኔ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ በተለይ ደግሞ ከአንድ ከገጠር የመጣ ከገጠር የወጣች ዋሽንትን ይዞ ፤ ከጎጃም ከግሽ አባይ አዲስ አበባ በግሩ ገብቶ ፤ በረኝነት የተማለረዉን የዋሽንት ጨዋታ አዲስ አበባ አስገብቶ አዘምኖ ለዓለም አቀፍ ያበቃት ነዉ።»  የዋሽንቱ ንጉስ ዩሐንስ አፈወርቅ በሕዝብ ለሕዝብ የሙዚቃ ቡድን ላይ በመድረክ ያቀረበዉን ሙዚቃ ነበር የተከታተልነዉ። ባለቅኔና ፀሐፊ ተዉኔት አያልነህ ሙላቱ እንደሚለዉ ዩሐንስ አፈወርቅ ጋር ማኅበር አቋቁሞ ነበር።

እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ ያለውን የባህል ሙዚቃ መሣሪያ ዕውቀቱን የሚያስተላልፍበት ተቋም ሊናቋቁምለት ይገባን ነበር። የብዙዎች አስተያየት ነዉ። ሙዚቃ የሚያቀርብበትም መድረክ ከመዝናኛና ከመማርያ ባሻገር የጥበብ መድረኩ የቱሪስት መስዕብ ሆኖ በተጎበኘም ነበር።  የአምስት ልጆች አባቱ የዋሽንቱ ንጉስ ዩሐንስ አፈወርቅ የካቲት 18፤ 2011 ዓም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ለዋሽንት የተሰሩት የዩሐንስ ከንፈርና ጣቶች ዛሬ ዝም የሰራቸዉ ሥራዎች ለዘላለም ሃዉልት ሆነዉ ሲያስታዉሱት  ይኖራሉ። «DW» ለቤተሰብ እና ለወዳጅ ዘመድ መጽናናትን ይመኛል።

 

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic