የዊኪሊክስ መስራች ታሰረ | ዓለም | DW | 11.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የዊኪሊክስ መስራች ታሰረ

የብሪታንያ ፖሊስ በኤኳዶር ኤምባሲ ሎንደን ውስጥ ተጠልሎ የከረመውን የዊኪሊክስ መሥራች ጁሊያን አሳንጅን ማሠሩ ተቃውሞም ድጋፍም አስከተለ። ምሥጢራዊ መረጃዎችን አደባባይ በማውጣት የሚታወቀው ዊኪሊክስ ባለቤት ላለፉት ሰባት ዓመታት ገደማ ሎንዶን በሚገኘው የኤኳዶር ኤምባሲ ጥገኝነት ጠይቆ ተቀመጦ ነበር።

 

የብሪታንያ ፖሊስ በኤኳዶር ኤምባሲ ሎንደን ውስጥ ተጠልሎ የከረመውን የዊኪሊክስ መሥራች ጁሊያን አሳንጅን ማሠሩ ተቃውሞም ድጋፍም አስከተለ። ምሥጢራዊ መረጃዎችን አደባባይ በማውጣት የሚታወቀው ዊኪሊክስ ባለቤት ላለፉት ሰባት ዓመታት ገደማ ሎንዶን በሚገኘው የኤኳዶር ኤምባሲ ጥገኝነት ጠይቆ ተቀመጦ ነበር። ዊኪሊክስ ኢኳዶር ሕገወጥ በሆነ መንገድ ለአሳንጅ የሰጠችውን ከለላ ድንገት በማቋረጧ ዓለም አቀፍ ሕግን ጥሳለች ሲል ከሷል። የኤኳዶር ፕሬዝደንት ሌኒን ሞሬኖ ግን ክሱን አስተባብለዋል፤

«ሚስተር አሳንጅ ምንም እንኳን ተገቢውን ደንብ እንዲያከብር በተለያየ አጋጣሚ ቢጠየቅም፤ በተደጋጋሚ ከሃቫና እና ካራካስ የዲፕሎማሲ ጥገኝነት አሰጣጥ ሥርዓትን የሚቃረን ተደጋጋሚ ጥሰት ፈጽሟል። በተለይም በሌሎች ሃገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ደንብን የሚጻረረውን ደንብ ጥሷል።»

አክለውም ለሌላ ሀገራት ተላልፎ እንዳይሰጥ ከብሪታንያ የመተማመኛ ቃል እንደተገባላቸውም አመልክተዋል። የብሪታኒያ ፖሊስ በበኩሉ ዩናይትድ ስቴትስ ተላልፎ እንዲሰጣት በመጠየቋ ዛሬ ረፋዱ ላይ አሳንጅን በቁጥጥር ሥር እንዳዋለው አስታውቋል። አሳንጅ ስዊድን ውስጥ በወሲብ ጥቃት ክስ ተመስርቶበት ቆይቷል።  ደጋፊዎቹ መታሰሩን ፕረስ ነፃነት ላይ የተወሰደ አሉታዊ ርምጃ ነው በሚል ሲያወግዙ፤ ተቃዋሚዎቹ በአንፃሩ ለፍትህ መከበር የተደረገ ነው እያሉ ነው። የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ የአሳንጅ መያዝ ማንም ከሕግ በላይ እንዳልሆነ አመላካች ነው ብለውታል። የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በበኩላቸው የዴሞክራሲ እጅ ነፃነትን እያነቀ ነው ማለታቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል። ጁሊያን አሳንጅ በዌስት ሚንስቴር ማጅስትሬት ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

 

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ